በሊጉ የአምስተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ በቀዳሚነት በተደረገው ጨዋታ ሲዳማ ቡና በእንዳለ ከበደ ብቸኛ ግብ ወልቂጤ ከተማን ረቷል ።
ወልቂጤ ከተማዎች በአራተኛው ሳምንት በሀዋሳ ከተማ በተረቱበት ጨዋታ ላይ በነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አራት ለውጦችን በማድረግ በቴዎድሮስ ሀሙ ፤ ኤፍሬም ዘካሪያስ ፤ አቤል ነጋሽ እና ጌታነህ ከበደ ምትክ ብርሀኑ ቦጋለ ፤ ፋሲል አበባየሁ ፤ ተመስገን በጅሮንድ እና አቡበከር ሳኒን ሲያስገቡ በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ በሳምንቱ በኢትዮጵያ ቡና በተሸነፉበት ጨዋታ በነበረው ምርጥ አስራ አንድ ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ጨዋታውን ጀምረዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ወልቂጤ ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ ለመጫወት ጥረቶችን ሲያርጉ በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ በተለይም ከመስመር ወደ መሀል በሚቀነሱ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ።
- ማሰታውቂያ -
ምንም እንኳን ሁለቱም ክለቦች በየራሳቸው መንገድ የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጥረቶች ቢያደርጉም ግብ ጠባቂዎችን የፈተኑ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረው ቆይተዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ብዙአየሁ ተስፉ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ሆኖ ወደ ግብ የመታው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።
በአጋማሹ ግልፅ የጠራ ዕድል በ18ኛው ደቂቃ ላይ የተመለከትን ሲሆን ይገዙ ቦጋለ በሳጥን ውስጥ ሆኖ በረጅም የደረሰውን ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ኳሱን ከግቡ አናት በላይ ሰዶታል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይም ሌላ ጠንካራ የግብ ሙከራ ሳንመለከት አጋማሹ ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡና ጫን ብሎ ጨዋታውን የጀመረ ሲሆን በተለይም በመስመሮች በኩል የተጠናከረ የማጥቃት እንቅስቃሴ አድርገዋል ።
በ47ኛው ደቂቃ ላይ መሃሪ መና በግራ መስመር አቅጣጫ ይዞ የገባውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ሮበርት ኦዶንካራ መልሶታል ። ሮበርት ኦዶንካራ ኳሱን በሚመልስበት ወቅት በቡልቻ ሹራ ጣቱ ላይ በተሰራበት ጥፋት ጨዋታውን መቀጠል ባለመቻሉ በጀማል ጣሰው ተቀይሮ ወጥቷል ።
ወልቂጤ ከተማ የተሻሉ በነበሩቀች ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ወደ ፊት ለማድረስ ጥረቶችን ማድረግ ችለዋል ። ነገር ግን ከመሀል የሜዳው ክፍል አልፈው የግብ ዕድል ለመፍጠር በእጅጉ ተቸግረው ነበር ።
በሲዳማ ቡና በኩል ከመሀሪ መና ሙከራ በኋላ ይህ ነው ሊባል የሚችል የግብ ዕድል መፍጠር ያልቻሉ ሲሆን ሶስተኛው የማጥቃት ዞን ላይ ሲገቡ የነበራቸው አፈፃፀም ድክመት ለዚህ መንስኤ ሆኗል ።
በ76ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች ያገኙትን የቅጣት ምት ያኩቡ መሀመድ ከግቡ ትይዩ በቀጥታ አክርሮ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ጀማል ጣሰው መልሶታል ።
በ79ኛው ደቂቃ ላይም ፍሬው ሰለሞን ከሳጥን ውጨሐ ያደረገው ሙከራ በግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው ተመልሷል ።
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን ጎድዊን ኦባጆ ከሙሉቀን አዲሱ በረጅም የተላከለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ነፃ ለነበረው እንዳለ ከበደ የቀነሰለትን ኳስ እንዳለ ከመረብ አሳርፎታል ።
ጌታነህ ከበደን ቀይረው በማስገባት ግብ ለማስቆጠር ጥረቶችን ሲያደርጉ በነበረበት ወቅት ግብ ያስተናገዱት ወልቂጤ ከተማዎች በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ተጭነው ለመጫወት ፍላጎት ቢታይባቸውም አቮኖን የፈተነ የግብ ሙከራ ለማድረግ አልቻሉም ነበር ።
በሲዳማ ቡና በኩል ጨዋታውን በመቆጣጠር ያስቆጠሩትን ግብ አስጠብቀው ለመውጣት ያደረጉት ጥረት ውጤታማ ሆኖ ከጨዋታው ሶስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ችለዋል ።
በስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች (ድሬዳዋ ስታድየም) በመጪው ጥቅምት 26(ቅዳሜ) 12:00 ላይ ወልቂጤ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚጫወቱ ሲሆን ጥቅምት 28(ሰኞ) በ9:00 ላይ ሲዳማ ቡና ከአዳማ ከተማ ይጫወታሉ ።