በ2022 የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ማጣርያ አራተኛ ዙር የመልስ ጨዋታ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአበበ ብቂላ ስታዲየም የታንዛንያ ብሔራዊ ቡድንን 2ለ0 አሸንፈዋል።
አስቀድሞ ከሁለት ሳምንታት በፊት ዳሬሰላም ላይ በታንዛኒያ ብሔራዊ ቡድን 1ለ0 ተሸንፈው የነበሩት የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን በዛሬው ዕለት በመልሱ ጨዋታ ተጋጣሚያቸውን የታንዛኒያ ብሔራዊ ቡድን በረድኤት አስረሳኸኝ ሁለት ጎሎች አሸንፈዉ ወደ አምስተኛው እና ወደ መጨረሻው ዙር ተሸጋግረዋል።
ለተከታታይ አስራ አንድ ጨዋታዎች ያህል ያለሽንፈት ተጉዞ የነበረዉ የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከሳምንታት በፊት ካጋጠመዉ ሽንፈት በማገገም በዛሬው ዕለት ወደ አሸናፊነት የተመለሱበትን ድልም ነዉ ያስመዘገቡት።
በቀጣይ በመጨረሻዉ የማጣሪያ ጨዋታ የጋናን እና ኡጋንዳ ብሔራዊ ቡድንን አሸናፊ የሚገጥሙ ሲሆን የደርሶ መልሱን ጨዋታ በድል የሚወጡም ከሆን ኮስታሪካ በምታዘጋጀው የ2022 የአለም ከ20 አመት በታች የሴቶች ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ይሆናል።
አስተያየት ይስጡ