በአምስተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ፋሲል ከነማ የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፏል።
ተመጣጣኝ የሚባል የጨዋታ እንቅስቃሴ በተመለከትንበት የጨዋታው የመጀመሪያ አስር ያህል ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች የሜዳዉን የመሀል ክፍል ተቆጣጥረው ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ለመድረስ ሲጥሩ ሲስተዋል ፤ በዚህ ረገድ ግን በንፅፅረ አፄዎቹ የተሻሉ ነበሩ ማለት ይቻላል።
በዚህም በ7ኛዉ ደቂቃ ላይ አማካዩ ይሁን እንዳሻው ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተገኘዉን ቅጣት ምት የቀኝ መስመር ተጫዋቹ ሱለይማን ሀሚድ ሲያሻማዉ ቸርነት ጉግሳ በጭንቅላቱ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ የግቡን አግዳሚ ታካ ወደ ዉጭ ወጥታለች። ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ በ8ኛዉ ደቂቃ ላይ የአፄዎቹ የመስመር ተጫዋች ሽመክት ጉግሳ ከፍሪምፖንግ ጋር ታግሎ ያገኛትን ኳስ ወደ ግብ ሲሞክር የግቡ ቋሚ በሚመልስበት ሰዓት በአቅራቢያው ይገኝ የነበረዉ ታፈሰ ሰለሞን በድጋሚ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ተከላካዩ ምኞት ደበበ አዉጥቶታል።
- ማሰታውቂያ -
በ18ኛዉ ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር በኩል የተገኘዉን ኳስ ኢስማኤል ሲያሻማዉ ጥሩ አቋቋም ላይ ይገኝ የነበረዉ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ምክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ኢላማዋን ሳትጠብቅ ወደ ዉጭ ወጥታለች። በድጋሚ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ፈረሰኞቹ አደገኛ ሙከራ ማድረግ ችለዋል በዚህም ተከላካዩ ረመዳን የሱፍ ያሻማዉን ኳስ አጥቂው ኢስማኤል ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ለጥቂት ወጥታበታለች።
በ30ኛዉ ደቂቃ ላይ የቀኝ መስመር ተከላካዩ አለምብርሀን ይግዛው ቀጥታ ወደ ግብ የላካት ኳስ ለጥቂት ወደ ዉጭ ወጥታበታለች።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ ጥቂት ደቂቃዎች በቀሩበት ሰዓት ግን አፄዎቹ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች የሰሩትን የቅብብል ስህተት ተከትሎ የተገኘዉን ኳስ ሽመክት ለታፈሰ ሰለሞን አቀብሎት አማካዩ ከሳጥኑ ዉጭ ቀጥታ ወደ ግብ በመላክ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከዕረፍት መልስ ግለቱ ጨምሮ በተመለሰዉ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ የአቻነቷን ግብ ለማስቆጠር ቶሎ ቶሎ ወደ አፄዎቹ የሜዳ ክፍል መግባት ቢችሉም ለግብ የቀረበ ሙከራን በማድረግ ረገድ ግን ያን ያህል ስል ነበሩ ማለት አይቻልም። በተቃራኒው ፋሲል ከነማ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ሲችል በግብ ጠባቂዉ ቻርልስ ሉክዋጎ ድንቅ ብቃት ሲከሽፉ ተስተውሏል።
በተደጋጋሚ ከጨዋታው በዘለለ በነበሩ ፍትጊያዎች ምክንያት ቶሎ ቶሎ የዳኛ ፊሽካ ሲሰማበት በነበረዉ ጨዋታ በሁለተኛዉ አጋማሽ ምንም እንኳን ጠንከራ ጠንካራ የሚባል አደገኛ ሙከራን ያን ያህል ተመልክተናል ባይባልም በአንፃሩ በ75ኛዉ ደቂቃ ላይ ግን የፋሲል ከነማዉ የመሐል ተከላካይ ከድር ኩልባሊ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ላይ የሰራዉን ጥፋት ተከትሎ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።
በዚህም በቁጥር ጎዶሎ የነበሩት አፄዎቹ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ቀይረው በማስወጣት ተከላካይ በማስገባት በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ይቃጡባቸዉ የነበሩ ሙከራዎችን ሲመክቱ ተስተውሏል። በተለይ የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ቀመጣ ቁጥር ፈረሰኞቹ የማጥቃት ሀይላቸዉን በይበልጥ አጠናክረዉ የአቻነት ግብ ለማግኘት ሲጥሩ በተቃራኒው አፄዎቹ ዉጤቱን አስጠብቀዉ ለመዉጣት ቀሪ ደቂቃዎችን በመከላከያ ላይ ተጠምደዉ ቆይተዋል። በዚህም አፄዎቹ የሊጉን መሪ አንድ ለዜሮ በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።