ዋልያዎቹ የ33ኛ የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ ጨዋታቸውን በ1 ለ 1 ውጤት አጠናቀዋል ። ምሽት አንድ ሰዓት ጀምሮ በባፎሳም ኩዌኮንግ ስታድየም በተደረገው ጨዋታ ቡርኪናፋሶዎች ከእረፍት በፊት ባስቆጠሩት ግብ ሲመሩ ቢቆዩም ከእረፍት መልስ 49ኛ ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠረው ግብ ሁለቱም ሀገራት አንድ አንድ ነጥብ ይዘው ወጥተዋል ።
በኬፕቨርዴው ጨዋታ እና በካሜሩን የሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታ ባሳዩት አቋም ብዙ ትችች ያስተናገዱት ዋልያዎቹ በዛሬው ጨዋታ የፎርሜሽን ለውጥ አድረገው ነበር የገቡት ። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከዚህ ቀደም የሚጠቀሙበትን የ4-3-3 አሰላለፍ በመቀየር በ4-2-3-1 አሰላለፍ ነበር ጨዋታውን የጀመሩት ። በካሜሩን ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ የሶሰት ተጫዋቾችን ቅያሪ ያደረጉ ሲሆን ያሬድ ባየህን በምኞት ደበበ ፤ አስራት ቱንጆን በሱሌማን ሀሚድ ፤ ይሁን እንደሻውን በመስዑድ መሀመድ እንዲሁም ጌታነህ ከበደን በአማኑኤል ገብረሚካኤል ቀይረው ገብተዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት ለመንቀሳቀስ የቻሉት ዋልያዎቹ ከኋላ መስርተው በመሄድ ከፊት መስመር በሚገኙ ተጫዋቾች ጫና ለማሳደር ጥረቶችን አድርዋል ። በአንፃሩ ቡርኪናፋሶዎች በረጃጅም ኳሶች እና በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ።
በጨዋታ የመጀመሪያው ኢላማውን የግብ ሙከራ የተደረገው በ9ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ። አምበሉ ጌታነህ ከበደ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ከአቡበከር ናስር የደረሰውን ኳስ ወደ በግራ እግሩ ወደ ግብ ሞክሮት በግብ ጠባቂው ተመልሶበታል ። በ23ኛ ደቂቃ ላይም በካሜሩን ጨዋታ ግብ ያስቆጠረው ዳዋ ሆቴሳ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በቀላሉ በግብ ጠባቂው ተይዟል ።
በ25ኛው ደቂቃ ላይ ግን ቡርኪናፋሶ ቀዳሚ የምታደርጋቸውን ግብ አገኙ ። አማካዩ አዳማ ጉይራ ከመሀል ያሻገረው ኳስ የደረሰው ባያላ የግብ ጠባቂውን የተክለማርያም ሻንቆን መውጣት ተመልክቶ ኳሱን ከመረብ ማገናኘት ችሏል ። ከግቡ በኋላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተረጋጋ ሁኔታ ጨዋታውን መቀጠል የቻለ ቢሆንም ተጫዋቾቸለ ወደ ግብ ሲደርሱ የነበረው አለመናበብ ኳሶች በቀላሉ እንዲበላሹባቸው አድርጎ ነበር ።
በ35ኛ ደቂቃ ላይ በዳዋ ሆቴሳ ጥረት ጌታነህ ከበደ ያገኘውን ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ በግብ ጠባቂው ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በቡርኪናፋሶ መሪነት ተጠናቀቀ ።
የሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ በኋላ ዋልያዎቹ ግብ ለማስቆጠር የፈጀባቸው ሰባት ያህል ደቂቃዎች ብቻ ነበሩ ። ሱራፌል ዳኛቸው ከግራ መስመር አካባቢ የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ግብ ሲያሻማው የቡርኪናፋሶው ተጫዋች ስቲቭ ያጎ በሳጥጅ ውስጥ በእጅ መነካቱን ተከትሎ የዕለቱ ዳኛ ሁነቱን በቫር ከተመለከቱ በኋላ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል ። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ጌታነህ ከበደ 52ኛ ደቂቃ ላይ አስቆጥሮ የጨዋታውን ውጤት ወደ 1 ለ 1 ቀየሮታል ።
ከዚህ በኋላ የነበረው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በአመዛኙ በተመጣጣኝ አንቅስቃሴ የተደረገ ነበር ። በሁለቱም በኩል በፈጣን ወደ ግብ ለመድረስ የሚደረጉ ጥረቶች በሶስተኛው የማጥቃት ክልል በሚደርሱበት ጊዜ በቀላሉ ይበላሹ ነበር ። በቡርኪናፋሶ በኩል በተለይም በመሰመር ለማጥቃት የነበራቸው ፍላጎት ከፊት መስመር ባሉ ተጫዋቾቻው አለመናበብ ይከሽፍባቸው ነበር ።
በሁለቱም ብሄራዊ ቡድኖች በኩል ሶስት ነጥቡብን ይዞ ለመውጣት የተለያዩ ቅያሪዎች የተደረጉ ቢሆንም ውጠፈጤት ቀያሪ ግን መሆን አልቻሉም ። ጨዋታውም በአንድ አቻ ውጤት ተፈፀመ ።
በተመሳሳይ ሰዓት የተደረገው የካሜሩን እና የኬፕቨርዴ ጨዋታ እንደ ኢትዮጵያ እና ቡርኪናፋሶ ጨዋታ በአንድ አቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ምድቡን አዘጋጇ ካሜሩን በ7 ነጥብ መሪ ሆና ስታጠናቀቅ ኢትዮጵያ በ1 ነጥብ ከምድቡ ተሰናባች ሀገር ሆናለች ።