የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ተጀምረዋል ።
በቀዳሚነት ከቀን 10:00 ጀምሮ የተደረገው የኢትዮጵያ መድኅን እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል ።
በጨዋታው በኢትዮጵያ መድኅን በኩል የነበረው የመጀመሪያ ምርጥ 11 ይህን ይመስላል ። አቡበከር ኑራ ፣ አብዱልከሪም መሀመድ ፣ ተካልኝ ደጀኔ ፣ ሐቢብ መሀመድ ፣ አስጨናቂ ፀጋዬ ፣ አሚር ሙደሲር ፣ ሀብታሙ ሸዋለም ፣ ባሲሩ ኡመር ፣ ሐቢብ ከማል ፣ ኪቲካ ጀማ እና ሲሞን ፒተር ።
በአዳማ ከተማ በኩል የነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍም እንደሚከተለው ነው ። ሰይድ ሀብታሙ ፣ ጀሚል ያዕቆብ ፣ ሚሊዮን ሰለሞን ፣ አዲስ ተስፋዬ ፣ ደስታ ዮሀንስ ፣ አማኑኤል ጎበና ፣ መስዑድ መሀመድ ፣ ዳንኤል ደምሴ ፣ አብዲሳ ጀማል ፣ አሜ መሀመድ እና ቦና አሊ ናቸው ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሁለተኛ ላይ የተቀመጠው ኢትዮጵያ መድኅን ወደ መሪነቱ ለመመለስ ጨዋታውን ያደረገ ሲሆን ገና በ10ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ መሆን ችሏል ።
ሲሞን ፒተር ከሳጥን ውጪ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ ሲተፋው በቅርብ የነበረው ሐቢብ ከማል ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ።
አዳማ ከተማዎች በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የተሻለ ለመንቀሳቀስ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስም ችለዋል ።
በ36ኛው ደቂቃ ላይ አዳማ ከተማ ወደ አቻነነት ተመልሷል ። አሜ መሀመድ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ቦና አሊ አግኝቶ በፍፁም መረጋጋት ኳሱን ከመረብ ላይ አሳርፏል ።
በቀሪዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ላይ ኢትዮጵያ መድኅኖች በተወሰኑ አጋጣሚዎች ዳግም ወደ መሪነት ለመመለስ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በአዳማ ከተማ በኩል ግን እጅግ ያለቀላቸው ኳሶችን አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ።
በ37ኛው ደቂቃ ላይ ኪቲካ ጀመረ በቀኝ የሳጥኑ አቅጣጫ ከአዲስ ተስፋዬ ጋር ታግሎ ይዞ የገባውን ኳስ ለመቀነስ ጥረት ቢያደርግም የደረሰበት ተጫዋች አልነበረም ። ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ግብ አስቆጣው ሐቢብ ከማል በረጅም የደረሰውን ኳስ ለመጠቀም ሲሞክር የአዳማ ከተማው ግብ ጠባቂ ሰይድ ሀብታሙ ከግቡ ወጥቶ እንዳይጠቀምበት አድርጓል ።
ከአንድ ደቂቃ በኋላ ቦና አሊ የደረሰውን ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ የዕለቱ ኮከብ የነበረው አቡበከር ኑራ መልሶበታል ። የአቡበከር ድንቅ ብቃት ዳግም በታየበት ሌላ የግብ ሙከራ ምልሰት አብዲሳ ከማል በግሩም ሁኔታ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ግቡ ላይ እንዳይቆጠር ማድረግ ችሏል ።
በ44ኛው ደቂቃ ላይ ዳግም አብዲሳ ጀማል እና አቡበከር ኑራ በተገናኙበት የግብ ሙከራ አዳማ ከተማ መሪ ሆነ ተብሎ ቢጠበቅም አቡበከር ግቡን ለሁለተኛ ጊዜ ሳያስደፍር የመጀመሪያው አጋማሽ እንዲጠናቀቅ አድርጓል ።
የሁለተኛው አጋማሽ ቀዳሚ ደቂቃዎች ላይ የአሰልጣኝ ይታገሱ ቡድን ወደ ግብ በተሻለ የመድረስ አዝማሚያ ቢያሳይም በ51ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግብ አስተናግዷል ።
ሐቢብ ከማል በረጅም የተላከለትን ኳስ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ለማስቆጠር ጥረት በሚያደርግበት ወቅት በሚሊዮን ሰለሞን ጥፋቶ ተሰርቶበት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ሐቢብ ከመረብ አሳርፏል ። ጥፋቱን የሰራው ሚሊዮን ሰለሞን በበኩሉ በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ።
በጨዋታው ሁለተኛ ግብ ያስቆጠረው ሐቢብ ከማል በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛቶች ሰባት አድርሷል ።
ከግቡ በኋላ የአሰልጣኝ ፀጋዬ ገብረመድህን ቡድን ኳሱን ተቆጣጥሮ ለመጫወት የቻለ ሲሆን ወደ አዳማ ከተማ ግብ ቀርቦ የግብ ሙከራ ከማድረግ አንፃር ግን ያን ያህል ነበሩ ።
በአንፃሩ የቁጥር ብልጫ የተወሰደባቸው አዳማ ከተማዎች በጥቂት አጋጣሚዎች የተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል ለመፈትሽ ሞክረዋል ።
በ69ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጣሪው ቦና አሊ ከመስዑድ መሀመድ የደረሰውን ኳስ ከሳጥን ውስጥ ሆኖ ወደ ግብ መሞከር ቢችልም ግብ ጠባቂው በቀላሉ አድኖበታል ።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ ስምንት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት አዳማ ከተማዎች ዳግም ወደ አቻነት የተመለሱበትን ግብ አስቆጥረዋል ።ተቀይሮ የገባው አድናን ረሻድ ኳስ እና መረብን ያገናኘው ተጫዋች ነው ።
ቀሪዎቹ የመጨረሻ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ከጨዋታው ሶስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት ጥረቶች የተደረጉበት ሲሆን በተለይም በ90+3 ላይ ቢንያም አይተን ከሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ አክርሮ ወደ ግብ የመታው እና በአቡበከር ቸየመለሰው ኳስ ተጠቃሽ ነው ።
በመጨረሻም ጨዋታው 2 – 2 ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ መድኅን በ27 ነጥቦች ዳግም ወደ ሊጉ መሪነት ሲመለስ አዳማ ከተማ በበኩሉ በ15 ነጥቦች በነበረበት 12ኛ ደረጃ ለመቆየት ተገዷል ።
ከጨዋታዉ በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ በጨዋታው የነበራቸው እንቅስቃሴ ጥሩ አለመሆኑን በመግለፅ በርካታ ኳሶችን ያዳነውን ግብ ጠባቂውን አቡበከር ኑራን አድንቀዋል ። በአንፃሩ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የመከኑት ኳሶች ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተናግረዋል ።
በጨዋታው የነበሩ ቁጥራዊ መረጃዎች
ኢትዮጵያ መድኅን 2 – 2 አዳማ ከተማ
10 የግብ ሙከራ 15
6 ኢላማቸውን የጠበቁ 9
10 ጥፋት 16
0 ቢጫ ካርድ 4
0 ቀይ ካርድ 1
4 የማዕዝን ምት 9
52% የኳስ ቁጥጥር 42%
ቀጣይ የ15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች
ሐሙስ የካቲት 16 (ምሸት 1:00)
አዳማ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ
አርብ የካቲት 17 (ቀን 10:00)
ሀድያ ሆሳዕና ከ ኢትዮጵያ መድኅን