የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አ.ማ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን እንዲሁም በተናጥል ለስፖርቱ ባለሙያዎች የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ሲሰጥ መቆየቱ ይታወቃል። ባለፉት ወቅቶች ለአሰልጣኞች፣ ዳኞች፣ የክለብ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች እና ሌሎችም ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱም ይታወሳል።
በተመሳሳይም በዛሬዉ ዕለት መስከረም 28 በባህር ዳር ከተማ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አ.ማ በአሜሪካ የልብ ማህበር በኢትዮጵያ አማካኝነት ለህክምና ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቷል። ለአስራ ስድስቱ የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች የህክምና ባለሙያ እና ወጌሻዎች ለአንድ ቀን በተሰጠው ስልጠና ባለሙያዎቹ ለውድድር በሚገኙበት ከተማ በእግር ኳስ ጨዋታዎች ላይ የሚከሰቱ የልብና ተያያዥ ድንገተኛ አደጋዎችን መለየትና ማከም ላይ ያተኮረ የስራ ላይ ስልጠና ነው።
በአጠቃላይም መርሃ ግብሩ በሙያው እውቀትና ልምዱ ባላቸው ባለሙያዎች በንድፈ ሃሳብና በተግባር ልምምድ ሲደገፍ ከአሜሪካ የልብ ማህበር በኢትዮጵያ የስልጠና ማዕከል ዶ/ር ሃወኒስ አሰፋ እና አቶ ብሩክ ድባቡ አሰልጥነዋል። በስተመጨረሻም ሰልጣኞች የተግባር ፈተና የተፈተኑ ሲሆን የስልጠና ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት(ላይሰንስ) ከሚመለከተው ማሰልጠኛ ማዕከል በሁለት ቀን ውስጥ እንደሚላክ ተመላክቷል።
- ማሰታውቂያ -
©Escl