በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ በአዳማ ከተማ እና መቻል መካከል ተደርጎ ዳዋ ሆጤሳ እና አሜ መሀመድ ባስቆጠሯቸው ግቦች አዳማ ከተማ 2 ለ 0 አሸንፏል ።
በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመሩት አዳማ ከተማዎች በአንደኛው ሳምንት በፋሲል ከነማ በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሁለት ለውጦችን በማድረግ በሰይድ ሀብታሙ እና ዊሊያም ሰለሞን ምትክ ኩዋሜ ባህን እና ፍሬድሪክ ሀንሰን ሲያሰልፉ በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት መቻሎች በሳምንቱ ሀድያ ሆሳዕናን በረቱበት ጨዋታ ላይ የነበረውን ምርጥ አስራ አንድ ሙሉ ለሙሉ ተጠቅመዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ መቻሎች በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የጀመሩ ሲሆን በተደጋጋሚም የተጋጣሚያቸውን የአዳማ ከተማን የኋላ ክፍል ለመፈተን ችለው ነበር ። በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች በመከላከል ላይ ጠንካራ በመሆን እና የመቻልን የማጥቃት ሂደት በማቋረጥ የሚገኙ ኳሶችን በፈጣን ወደ ፊት በማድረስ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ችለዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ የግብ ሙከራ ምንይሉ ወንድሙ በሁለተኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ከተነሳ ኳስ በግንባር ገጭቶ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት በግብ ጠባቂው ግብ ከመሆን ድኗል ።
- ማሰታውቂያ -
አዳማ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የቻሉ ቢሆንም ኢላማውን የጠበቁ ሙከራዎች ግን ማድረግ አልቻሉም ነበር ። ጨዋታው 19ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል ።
አሜ መሀመድ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ለመጠቀም በሚጥርበት ጊዜ በአህመድ ረሺድ በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ዳዋ ሆጤሳ ከመረብ አሳርፎታል ።
ቀጣዮቸለ የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታው ደቂቃዎች ጠንካራ ፉክክር የተደረገባቸው ነበር ። መቻሎች ቶሎ ቶሎ ወደ አዳማ ከተማ የግብ ክልል ኳሶችን በማድረስ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የጨዋታውን መሪነት የጨበጡት አዳማ ከተማዎች ለተጋጣሚ የፊት መስመር ተጫዋቾች ክፍተቶችን ባለ መስጠት ግብ እንዳይቆጠርባቸው አድርገዋል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በአዳማ ከተማ የ1 ለ 0 መሪነት ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ የቀድሞ ክለቡን በሚገጥመው ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት መቻሎች በመጀመሪያው አጋማሽ እንደነበረው ወደ ፊት በመድረስ ብልጫውን በመውሰድ የተጫወቱ ሲሆን የተለያዩ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ቀይረውም በማስገባት የአቻነቱን ግብ ፍለጋ ሲኳትኑ ቆይተዋል ።
በ63ኛው ደቂቃ ላይ የአጋማሹ ቀዳሚው የግብ ሙከራ ሲደረግ የቀድሞው የፋሲል ከነማ ተጫዋች በረከት ደስታ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ወደ ግብ የመታውን ኳስ በግብ ጠባቂው ኩዋሜ ባህ ተቆጣጥሮታል ።
በአሰልጣኝ ይተገሱ እንዳለ የሚመሩት አዳማ ከተማዎች የአጋማሹን አብዛኛውን ክፍለ ጊዜ ከኳስ ጀርባ በማሳለፍ ውጤቱን ለማስጠበቅ እና ቀደም ብሎ እንደነበረው በተወሰኑ አጋጣሚዎች ወደ መቻል የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ሲያደርጉ ተስተውሏል ።
በ71ኛው ደቂቃ ላይም ዳዋ ሆጤሳ ከደስታ ዮሀንስ የተሻገረለትን ኳስ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ለጥቂት ሳይሳካ ቀርቷል ። ጨዋታው በአዳማ ከተማ የ1 ለ 0 መሪነት ዘጠና ደቂቃው ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ ከመቻል ተጫዋቾች በተነጠቀ ኳስ በአሜ መሀመድ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ በተመታ ኳስ ሁለተኛ ግባቸውን ማስቆጠር ችለዋል ።
በመጨረሻም ጨዋታው በአዳማ ከተማ የ2 ለ 0 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል ።
በሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ጥቅምት 2(ረቡዕ) መቻል ከአርባምንጭ በ10:00 የሚጫወት ሲሆን አዳማ ከተማ በበኩሉ ጥቅምት 4(አርብ) 10:00 ላይ ከአዳማ ከተማ ይጫወታሉ ።