በሊጉ የ21ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን መርሀግብር ቀዳሚ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አስከ መጀመሪያው አጋማሽ በሁለት ግብ ልዩነት ሲመራ ቢቆይም በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ግቦች አንድ ነጥብ ይዞ ወጥቷል ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ20ኛው ሳምንት ጨዋታ በአዳማ ከተማ ሲረቱ ከተጠቀሙት ምርጥ አስራ አንድ አራት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን ካክፖ ቼሪፊዳይን ፣ ያሬድ የማነ ፣ ነፃነት ገብረመድህን እና ጎሜዝ ፓውል አለንን በዘሪሁን ታደለ አንዳርጋቸው ይላቅ ፣ ሙሴ ከበላ እና ስንታየሁ ወለጬ ተክተው ገብተዋል ።
በወልቂጤ ከተማ በኩል በሳምንቱ ሲዳማ ቡና ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ በማቲያስ ወልደአረጋይ ምትክ ብዙአየሁ ሰይፉን አሰልፈዋል ።
- ማሰታውቂያ -
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜን በውድድር አመቱ ለሁለተኛ ጊዜ የአሰልጣኝ ለውጥ አድርገው ወደዚህ ጨዋታ የመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ያሳዩበት ነበር ።
በጨዋታው የመጀመሪያ የግብ ዕድል በስድስተኛው ደቂቃ ላይ የተመዘገበ ሲሆን አብዱራህማን ሙባረክ ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ የመስመር ተከላካዩ ታፈሰ ሰርካ በግንባር ገጭቶ በግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው ተመልሷል ።
ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ግን በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚመሩት ወልቂጤ ከተማዎች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል ።
በአስረኛው ደቂቃ ላይ አቤል ነጋሽ ከጌታነህ ከበደ የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ግብ አስቆጥሯል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ግብ የተቆጠረባቸው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ተጭነው በመጫወት የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገዋል ።
ነገር ግን ለረጅም ደቂቃዎች የወልቂጤ ከተማውን የግብ ዘብ ጀማል ጣሰውን የፈተነ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረው ነበር ። ምናልባትም በአጋማሹ ሊጠቀስ የሚችል ሁለተኛ የግብ ሙከራ በ37ኛው ደቂቃ በስንታየሁ ወለጬ አማካኝነት ማድረግ ቢችሉም ጀማል ኳሱን ተቆጣጥሮታል ።
አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ወቅት የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሳሙኤልን አስፈሪ ያሻገረውን ኳስ ዘሪሁን ታደለ ጨርፎት ያገኘው ጌታነህ ከበደ የወልቂጤ ከተማን መሪነት ወደ 2 – 0 ከፍ አድርጓል ።
በዚህም ጌታህ ከበደ በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛቶች 14 ማድረስ ችሏል ።
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ቶለ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የጣሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በ53ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጨዋታው የተመለሱበትን ግብ አስቆጥረዋል ።
ከስንታየሁ ወለጬ የተነሳው ኳስ በአብዱራህማን ሙባረክ በኩል አልፎ አማካዩ አብነት ደምሴ ከመረብ አሳርፎታል ።
ከ16 ደቂቃዎች በኋላም ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከ2 – 0 መመራት ወደ ሁለት አቻ የመጡበትን ግብ አግኝተዋል ።
አማረ በቀለ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ አብዱራህማን ሙባረክ አግኝቶ የወልቂጤ ከተማ ተጫዋቾች ባልጠበቁት መልኩ ወደ ግብ የመታው ኳስ በጀማል ጣሰው መረብ ላይ አርፏል ።
በአጋማሹ ተቀዛቅዘወ የታዩት ወልቂጤ ከተማዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ በሁነኛ አጥቂያቸው ጌታነህ ከበደ በሚመራው የፊት መስመራቸው ግብ ለማግኝት ቢጥሩም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል ።
በመጨረሻም ጨዋታው 2 – 2 ፍፃሜውን አግኝቷል ።
በ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰኞ ሚያዝያ 23 በ9:00 ወላይታ ድቻ ከለገጣፎ ለገዳዲ ሲጫወቱ ረቡዕ ሚያዝያ 25 በ9:00 መቻል ድሬዳዋ ከተማን ይገጥማል ።