በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለተኛ ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕናን ከወላይታ ድቻ አገናኝቶ ሳይሸናነፉ 2 – 2 በሆነ ውጤት ጨዋታቸውን አጠናቀዋል ።
ሀድያ ሆሳዕናዎች በ28ኛው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን ነጥብ ባስጣሉበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ስድስት ለውጦችን በማድረግ ሶሆሆ ሜንሳህ ፤ ኤልያስ አታሮ ፤ ፀጋዬ ብርሀኑ ኤፍሬም ዘካርያስ ፤ ራምኬል ሎክ እና ኡመድ ኡክሪን በመሳይ አያኖ ፤ ሄኖክ አርፊቹ ፤ እያሱ ታምሩ ፤ ሳምሶን ጥላሁን ፤ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን እና ባዬ ገዛኸኝ ምትክ ሲያሰልፉ በወላይታ ድቻ በኩል ደግሞ በሳምንቱ ጅማ አባጅፋርን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ ቢንያም ፍቅሬን በስንታየሁ መንግስቱ ተክተው ገብተዋል ።
በሊጉ የደረጃ ወገብ ላይ የሚገኘቱን እና በተረጋጋ ጉዞ ላይ ያሉትን ሁለቱን የደቡብ ክለቦች ያገናኘው ጨዋታ ለዕይታ መልካም የሆነ እንቅስቃሴ የታየበት እና በሁለቱም በኩል ተጋጣሚያቸውን አሸንፈው ለመውጣት ብርቱ ትግል ያደረጉበት ጨዋታ ነበር ።
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ወላይታ ድቻዎች ተጭነው ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን በነዚህ ደቂቃዎች ላይ በሀድያ ሆሳዕና በኩል ኳሶችን በፈጣን ወደ ፊት በማድረስ ( በተለይም ኡመድ ኡክሪን ኢላማ ያደረጉ ኳሶች ) የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የቻሉ ሲሆን በዚህም በ16ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል ።

ኡመድ ኡክሪ በተከላካዮች መካከል ከአበባየሁ ዮሀንስ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ እየገፋ ይዞ በመሄድ የሀድያ ሆሳዕናን የመጀመሪያ ግብ ማስቆጠር ችሏል ።

ከግቡ በኋላ ሀድያ ሆሳዕናዎች ኳሱን ይዘው በመጫወት ጠንካራውን የወላይታ ድቻ የኋላ ክፍል ለማስከፈት ጥረቶችን አድርገዋል ። በ19ኛው ደቂቃ ላይም ኤልያስ አታሮ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ኡመድ ኡክሪ አግኝቶ ሊወጣበት የነበረውን ኳስ አክርሮ ወደ ግብ ሞክሮ በሶስት ደቂቃ ልዩነት ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት በግቡ ቋሚ ተመልሶ ሳይሳካ ቀርቷል ።
ቀጣዩ የግብ ሙከራ 33ኛው ደቂቃ ላይ ሲመዘገብ ራምኬል ሎክ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የመታው ኳስ በግብ ዘቡ ቢንያም ገመቱ ተመልሷል ።
ከሀድያ ሆሳዕና የግብ ክልል የራቁት በፀጋዬ ኪዳነማርያም የሚመሩት የጦና ንቦቹ በ36ኛው ደቂቃ ላይ አቻ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል ። መልካሙ ቦጋለ በረጅም የመታውን ኳስ ቢንያም ፍቅሬ ተቆጣጥሮ ለአናጋው ባደግ ያደረሰው ሲሆን አናጋው ኳሱን አረጋግቶ ከርቀት አክርሮ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ሶሆሆ ሜንሳህን አልፎ ከመረብ ላይ አርፏል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በ1 – 1 ውጤት ተጠናቀቀ ።
ተመጣጣኝ ሊባል በሚችል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተጀመረው የሁለተኛው አጋማሽ ላይ የጦና ንቦቹ በተሻለ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመድረስ ያሳለፉት ነበር ።
በአጋማሹ ቀዳሚ የግብ ሙከራም 54ኛው ደቂቃ ላይ ቃልኪዳን ዘላለም የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች ስህተትን ተጠቅሞ ያገኘውን ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መምታት ቢችልም ሶሆሆ ሜንሳን ማለፍ የቻለ አልነበረም ። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ተቀይሮ የገባው እንድሪስ ሰይድ ከግራ መስመር አቅጣጫ ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ ቢንየም ፍቅሬ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
የጨዋታው ደቂቃ መቁጠሪያ 61ላይ ባመላከተበት ጊዜ ሀድያ ሆሳዕናዎች ዳግም መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አግኝተዋል ። የወላይታ ድቻ ተጫዋቾችን ስህትት ተከትሎ ኳሱን ያገኘው ፀጋዬ ብርሀኑ ከቀኝ መስመር ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ የመጀመሪያው ግብ አስቆጣሪ ኡመድ ኡክሪ ለቡድኑም ሆነ ለራሱ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል ።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ከተጋጣሚያቸው ወላይታ ዲቻ በረጃጅም ወደ ግብ ክልላቸው የሚደርሱ ኳሶች ግን የተከላካይ መስመራቸውን የፈተኑ ነበሩ።
ቃልኪዳን ዘላለምን ቀይሮ የገባው ዘላለም አባቴ በ70ኛው ደቂቃ ላይ በረጅም የተላከለትን ኳስ ተቆጣጥሮ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተከትሎ ኳሱን ከፍ አድርጎ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ከግቡ አናት በላይ በመውጣቱ ሳይሳካለት ቀርቷል ።
በ75ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም ፍቅሬ በረጅም የደረሰውን ኳስ ለዘላለም አባቴ አቀብሎት ዘላለም ከግብ ጠባቂው ፊት ለፊት ያገኘውን ኳስ ለማመን በሚከብድ መልኩ ከግቡ አናት በላይ ልከታል ። ከአንድ ደቂቃ በኋላም የሁለቱ ተጫዋቾች ጥምረት ዳግም በታየበት የግብ ዕድል ቢንያም ፍቅሬ በግንባር ገጭቶ ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል ።
የጦና ንቦቹ ሁለተኛውን ግብ የመፈለግ ጥረት ዳግም ቀጥሎ በ80ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችለዋል ። ዮናታን ኤልያስ ከግራ መስመር ወደ መሀል ያሻገረውን ኳስ የሀድያ ሆሳዕናው የመሀል ተከላካይ ፍሬዘር ካሳ ኳሱን ለማውጣት ሲሞክር በራሱ መረብ ላይ አሳርፎታል ።

በመጨረሻም ጨዋታው ሌላ ግብ ሳይታከልበት 2 – 2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ ነጥቡን 42 አድርሶ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሀድያ ሆሳዕና በ36 ነጥብ በነበረበት 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።

በሊጉ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሰኔ 23 ( ሀሙስ ) ረፋድ 4:00 ላይ ወላይታ ድቻ ወልቂጤ ከተማን ሲገጥም በዕለቱ 10:00 ላይ ሀድያ ሆሳዕና ከሲዳማ ቡና የሚጫወቱ ይሆናል ።
አስተያየት ይስጡ