በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 29ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ አስቀድሞ መዉረዱን ያረጋገጠዉን ጅማ አባጅፋርን በሆነ ዉጤት በማሸነፍ ራሱን ከመዉረድ አጣብቂኝ አዉጥቷል።
ረፋድ 4:00 ሲል የጀመረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ተመጣጣኝ የሚባል ፋክክርን ያስመለከተን ነበር በተለይ በወልቂጤ ከተማዎች በኩል ከሶስት ጨዋታዎች ቅጣት በኋላ ወደ ጨዋታ በተመለሰላቸዉ አጥቂያቸው ጌታነህ ከበደ አማካኝነት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዉ ነበር። በዚህም በተለይ ጨዋታዉ በጀመረ ገና በ5ኛዉ ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር በኩል ከረመዳን የሱፍ የተሻገረለትን ኳስ ጌታነህ ከበደ ቀጥታ በጭንቅላቱ ወደ ግብ ቢሞክራትም የግቡን አግዳሚ ታካ ወደ ዉጭ ወጥታለች።
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ አጥቂዉ በድጋሚ ከግብ አቅራቢያ የተገኘዉን ቅጣት ምት ወደ ግብ ምክሮ የነበረ ቢሆንም ኢላማዉን ሳይጠብቅ ወደ ዉጭ ወጥቷል።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታዉ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዉ የነበሩት ክትፎዎቹ በተለይ ከዉሀ ዕረፍት መልስ ለግብ የቀረበ አደገኛ ሙከራን በአጥቂው ጌታነህ አማካኝነት ማድረግ ችለዉ የነበረ ቢሆንም በጅማዉ ግብ ጠባቂ አልዓዛር አማካኝነት ከሽፏል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ትለዉ የነበሩት ክትፎዎቹ በ32ኛዉ ደቂቃ ላይ ግን መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። በተጠቀሰዉ ሰዓት በቀኝ መስመር በኩል የተገኘዉን ቅጣት ምት ሀብታሙ ሸዋለም ሲያሻማ ጥሩ አቋቋም ላይ የገኝ የነበረዉ ተከላካዩ ዉሀብ አዳምስ ወደ ግብነት ቀይሮ ክትፎዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል።
በተደጋጋሚ የጅማዎችን የግብ ክልል ሲያንኳኩ የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች ጨዋታዉ ሊገባደድ ሁለት ደቂቃዎች ያክል ሲቀሩት ደግሞ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ያደረጉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በ43ኛዉ ደቂቃ ላይ አጥቂዉ ጌታነህ አክርሮ ወደ ግብ የላካት ኳስ የግቡን አግዳሚ ነክታ ስትመለስ በአቅራቢያው የነበረዉ ሀብታሙ ሸዋለም በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሮ የመጀመሪዉ አጋማሽ በወልቂጤ ከተማዎች 2ለ0 መሪነት እንዲጠናቀቅ አስችሏል።
በመጀመሪያ አጋማሽ ምንም እንኳን ጥሩ የጨዋታ ምንገድ ቢኖራቸዉም ይህ ነዉ የሚባል አደገኛ ሙከራን ማድረግ ያልቻሉት ጅማ አባጅፋሮች ከአጋማሹ መልስ ወደ ጨዋታዉ መመለስ የሚችሉበትን እድል ማግኘት ችለዉ ነበር። በ51ኛዉ ደቂቃ ላይ በሀይሉ ተሻገር ሱራፌል አወል ላይ የሰራዉን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ሱራፌል ቢመታም የግብ ዘቡ ሮበርት ኦዶንካራ አድኖበታል።
በተቃራኒው ከዕረፍት መልስ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በማድረግ ወደ ጨዋታዉ ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋሉት ጅማዎች በ55ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ድጋሚ ለግብ የቀረበ ሙከራን ማድረግ ችለዉ ነበር፤ የመስመር አጥቂዉ ዱላ ሙላቱ ከሮባ ወርቁ የተቀበለዉን ኳስ በአስገራሚ ሁኔታ ያመከናት ኳስ እጅግ አስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።
እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ከዕረፍት መልስ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ተስኗቸዉ የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች ግን የጨዋታው መጠናቀቂያ አካባቢ በ86ኛዉ ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን ወደ ሶስት ከፍ ያደረጉበትን ግብ ማሰሰቆጠር ችለዋል። በዙሁ ደቂቃ ላይም አክሊሉ ዋለልኝ ከግራ መስመር በከል አመቻችቶ ያቀበለዉን ኳስ ጫላ ተሽታ አስቆጥሮ ጨዋታዉ በወልቂጤ ከተማዎች ሶስት ለዜሮ አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ተወጥቷል።
ዉጤቱን ተከቶሎ ወልቂጤ ከተማ በ35 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በአንፃሩ ጅማ አባጅፋር በ23 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።