በአስራ ሶስት ነጥቦች እና በስምንት ደረጃዎች ተበላልጠዉ ሶስተኛ እና አስራ አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ዲቻ ያገናኘዉ የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ሁለት አቻ በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።
ባሳለፍነዉ ሳምንት የሊጉ መርሐግብር ለገጣፎ ለገዳዲን 7ለ1 በሆነ ዉጤት አሸንፎ የነበረዉ ኢትዮጵያ መድን እና በተቃራኒው ከኢትዮ ኤሌትሪክ ጋር አንድ አቻ በሆነ ዉጤት ተለያይቶ በነበረዉ የአሰልጣኝ ፀጋየ ኪዳነማርያም ቡድን ወላይታ ዲቻ መካከል በተደረገው የሁለቱ ክለቦች ፍልሚያም ገና ጨዋታው በተጀመረው አንድ ደቂቃ ወላይታ ዲቻዎች ቀዳሚ ለመሆን ተቃርበዉ ነበር በዚህም የመድን ተከላካዮች የሰሩትን ስህተተ ተጠቅሞ ዘላለም አባተ የሞከራትን ኳስ አቡበከር ኑሪ እንደምንም ኳሷን አዉጥቷታል።
ከዚች ሙከራ በኋላ በቶሎ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሞከሩት መድኖች ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በባሲሩ አማካኝነት ጥሩ ሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራን ማድረግ ሲችሉ ከደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ወላይታ ዲቻዎች ብሩክ ሙሉጌታ ላይ የሰሩትን ስህተት ተከትሎ የተሰጠዉን ፍፁም ቅጣት ምት ሀብታሙ ሸዋለም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
- ማሰታውቂያ -
በጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም በ21ኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ተስተናግዶበታል ፤ በዚህም የወላታ ዲቻዉ የመስመር አጥቂ ቃልኪዳን ዘላለም ከአበባየሁ ዮሐንስ የተሻገረለትን ኳስ ከርቀት ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ለማግኘት ሲጥሩ የነበሩት መድኖች ውጥናቸዉ ሰምሮ በ43ተኛዉ ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም ከመድን የቀኝ ማጥቃት በኩል የተሻገረዉን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ በጭንቅላቱ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሎ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ተነቃቅተዉ የተመለሱት የሚመስሉት መድኖች በቶሎ በ51ኛዉ ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም ብሩክ ሙሉጌታ ከወገኔ የተሻገረለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን መሪ አድርጓል።
ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በድጋሚ ቶሎ ቶሎ ወደ ወላይታ ዲቻ የግብ ክልል በመድረስ ማጥቃታቸዉን የቀጠሉት መድኖች በሲሞን ፒተር ፣ ኪቲካ ጀማ እና ብሩክ ሙሉጌታ አማካኝነት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጥር ሲጥሩ ተስተውሏል። በተቃራኒው የማጥቃት ባህሪ ያላቸዉን በርከት ያሉ ተጫዋቾች ቀይረዉ በማስገባት የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የነበሩት ዲቻዎች ዉጥናቸዉ ሰምሮ በ68ተኛዉ ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት የተገኘዉን ኳስ ዮናታን ኤልያስ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። በዚህም የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ዉጤት ተገባዷል።
ዉጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ መድን በ37 ነጥቦች ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በተቃራኒው ወላይታ ዲቻ ደግሞ በ24 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።