በዕለተ ፋሲካ በተደረገዉ የአስራ ዘጠነኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ የመጨረሻ መርሐግብር የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድን ፋሲል ከተማ መቻልን 1ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ የሚገኘዉን ፋሲል ከነማ እንዲሁም በወራጅ ቀጠናዉ ዞን ላይ የሚገኘዉን የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ቡድን መቻል ባገናኘዉ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ዉጤቱን አጥብቀው እንደመፈለጋቸዉ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ለመንቀሳቀስ ሲጥሩ የተስተዋለ ሲሆን ፤ በ8ተኛዉ ደቂቃ ላይም መቻሎች ቀዳሚ መሆን የሚችሉበትን አጋጣሚ በሀይሉ ሀይለማርያም አማካኝነት መሞከር ቢችሉም ኳሷን የግቡ አግዳሚ አውጥቶባቸዋል።
- ማሰታውቂያ -
ከዚች ለግብ የቀረበች ሙከራ በኋላም አፄዎቹ ወደ ጨዋታው በመግባት በ16ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም መቻሎች ሳጥን ዉስጥ ኳስ በእጅ መንካታቸዉን ተከትሎ የተገኘዉን ፍፁም ቅጣት ምት ሽመክት ጉግሳ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። ከዚች ግብ መቆጠር በኋላ በተደጋጋሚ በተለይ የሜዳውን የመሐል ክፍል እና የመስመር ላይ እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ወደ ተጋጣሚ ቡድን የመጨረሻው የግብ ክልል ለመድረስ ሲጥሩ የተስተዋለ ሲሆን ፤ በተቃራኒው አፄዎቹ የፊት አጥቂያቸዉን ኦሴ ማውሊ ማዕከል ያደረጉ ረጃጅም ኳሶችን በመጣል ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የተስተዋለ ቢሆንም ሁለቱም ክለቦች ዉጥናቸዉ ሰምሮ ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጠር አጋማሹ በአፄዎቹ 1ለ0 መሪነት ተገባዷል።
ከዕረፍት መልስ የተቀዛቀዘ በነበረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ አፄዎቹ በአንፃራዊነት ተሽለዉ ለመንቀሳቀስ ሲጥሩ የተስተዋለ ሲሆን በዚህም በ61ኛዉ ደቂቃ ላይ በታፈሰ ሰለሞን አማካኝነት ድንቅ የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል።
በተቃራኒው የተወሰኑ ተጫዋቾችን ቀይረዉ ወደ ሜዳ በማስገባት የአቻነት ግብ ለማግኘት ሲጥሩ የነበሩት መቻሎች በከንዓን ማርክነህ እና እስራኤል እሸቱ አማካኝነት ጥሩ ጥሩ የሚባሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ግን ቀላል ሊሆኝላቸዉ አልቻለም። በተቃራኒው ያገቧትን ጎል አስጠብቀዉ ለመዉጣት ወደ ራሳቸዉ የግብ ክልል አፈግፍገዉ በመጫወት ላይ የነበሩት አፄዎቹ ጨዋታዉን 1ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችለዋል።
ዉጤቱን ተከትሎም ፋሲል ከነማ በ27 ነጥቦች ስድስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በተቃራኒው መቻል ደግሞ በ23 ነጥቦች አስራ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።