ሳምንታዊዋ ባለቀለም የስፖርት ጋዜጣ ሀትሪክ ስፖርት በመብራት መቆራረጥና በማተሚያ ቤት ችግር ምክንያት በዕለተ ቀኗ ማክሰኞ ለንባብ አለመብቃቷ የሚታወስ ነው፡፡ ይህንንም ለተወደዳችሁ አንባቢዎቻችን መግለፃችን የሚታወስ ነው፡፡ይሁንና ተፈጥሮ የነበረው ችግር በመቀረፉ መረጃዎቹን ሙለ ለሙሉ በመቀየር በነገው ዕለት (ቅዳሜ መስከረም 6/2010 ዓ.ም) ለንባብ እንበቃለን፡፡ ለመሆኑ በዚህኛውስ ዕትም ምን ምን ጉዳዮችን ይዛ ይሆን?
– ከለንደን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መልስ ከኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ውጪ ቃለ-ምልልስ ሰጥቶ የማያውቀው የ10 ሺህ ሜትር የወቅቱ የዓለም ንጉስ ሙክታር ኢድሪስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ ጋር ቃለ-ምልልስ አድርጓል፡፡ ከጋዜጣዋ ማኔጂንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ጋር በነበረው ቆይታ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ያሳለፈውን ውጣ ውረድና አሳዛኝ ታሪኩን በግልፅነት አጫውቶታል፡፡ በባዶ እግር ከመሮጥ ተነስቶ የዓለም ሻምፒዮን እስከመሆን ደረጃ ያደረሰውን ገድል፣ ተስፋ ከቆረጠ በኋላ ዳግም እንዴት ወደ ስልጠናው ተመልሶ ለጀግንነት እንደበቃና ሌሎችንም ለማመን የሚከብዱ የህይወት ውጣ ውረዶቹን ይናገራል፡፡ እጅግ አስገራሚና ለሌሎችም ትልቅ ትምህርት የሚሆን ነው፤ በእርግጠኛነት ይወዱታል፡፡
– በአዲሱ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ካርሎስ ማኑዌል ቫዝ ፒንቶ ዙሪያ አዳዲስና ያልተሰሙ መረጃዎችንም ይዛለች፡፡
– ከባህር ማዶ አሌክስ ኦክስሌድ ቻምበርሌይን አርሰናልን ለቅቆ ሊቨርፑልን ከተቀላቀለ በኋላ የሠጠው የመጀመሪያ ቃለ-ምልልሱ፣ የቼልሲው ኮከብ ሴስክ ፋብሪጋስ እሁድ የቀድሞ ክለቡን አርሰናልን በተቃራኒ መግጠሙን አስመልክቶ የሠጠው መግለጫ፤ በማን.ዩናይትድ እንደ አዲስ የተወለደው ማሩዋን ፌላይኒን የተመለከተ መረጃ፣ አሌግዛነደር ላካዜቴ በአርሰናል ሊያሳካው ስለሚፈልገው ጉዳይ እና ሌሎችንም በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን አካትታለች፤ በእርግጠኛነት ትመችዎታለች፡፡ በመሆኑም ነገ ቅዳሜ መስከረም 6/2010 ዓ.ም ለንባብ የምትበቃዋን ሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ በማለዳው እንዲኮመኩሟት ስንጋብዝዎ በታላቅ አክብሮት ነው፡፡
- ማሰታውቂያ -
– ከነገው ዕትም በተጨማሪ እንደተለመደው ዘወትር ማክሰኞ ቀኗን ጠብቃ የምትወጣ ሲሆን በዚህም መሰረት የፊታችን ማክሰኞ ዳግም በሌላ ጥንቅር እንደምንገናኝ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡
– ተጨማሪ ትኩስ ስፖርታዊ መረጃዎችን ከጋዜጣዋ በተጨማሪ በድረ-ገፃችን www.hatricksport.com ላይ ማግኘት ይችላሉ፡፡
– -ነገ ለንባብ የምትበቃው ሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ የፊት ለፊት ገፅ ይህንን ይመስላል፡፡ መልካም ቅዳሜ!