ዛሬ ከሀገራችን አልፎ በመላው ዓለም ስሙን በወርቅ ቀለም ከማፃፉ በፊት በበርካታ
መሰናክሎችና ውጣ ውረዶች ተፈትኗል፤ በአካባቢው ማህበረሰብ ሲሰነዘርበት ከነበረው
“እብድ ነው፤ ጤነኛ አይደለም” ከሚለው አደናቃፊ አስተያየት ጀምሮ የልምምድ መስሪያ
- ማሰታውቂያ -
ጫማ ችግር፣ በቂ የላብ መተኪያ አለማግኝት፤ ወደአሰበበት የውጤት ማማ የመውጣት ውጣ
ውረዶች የዚህን ሰው የአትሌቲክስ ሕይወት በፈተና የተሟላ አድርገውታል፡፡
ዛሬ ግን ይሄ ታሪክ ተቀይሯል፤ እነዛ አላፈናፍን ብለው ያስቸገሩትን የሕይወት ውጣ
ውረዶችንና የመሰናክሎችን ምሽግ በፅናትና በጥንካሬው ደርምሶ በመጣል ዓለም በትናንት
ማንነቱ ሳይሆን በስኬታማነቱ ስሙን ከፍ አድርጋ የምትጠራው አትሌት ለመሆን በቅቷል።
የዛሬው እንግዳችን አትሌት ሙክታር እድሪስ፡፡
በለንደኑ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፕዮና አልሸነፍ ብሎ ያስቸገረውን ሞ ፋራህን በማሸነፍ
የኢትዮጵያውያንን ቁጭት ያበሰው አትሌት ሙክታር እድሪስ ዘመንና ዕድሜን በምታሸጋግረው
የጳጉሜን ወር ድልድይ ላይ ከጋዜጠኛ ይስሃቅ በላይ ጋር አነጋጋሪ ቆይታ አድርጓል፡፡
የአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ እንግዳ የሆነው አትሌት ሙክታር እድሪስ ስለ ትዳር አጋሩ
ማንነት፣ ስለ አዲስዋ ልጃቸው፣ በሞ ፋራህ ላይ ስለተቀዳጀው ድል፣ “እብድ ነው” ስለመባሉና
በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለጋዜጠኛ ይስሐቅ በላይ ሳይሰስት አውርቶታል፡፡
አትሌት ሙክታር እድሪስ በለንደኑ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ ባለቤት
በመሆኑ የትውልድ ከተማው የስልጤ ዞን የ200ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት፤የኢ.ፊ.ድ.ሪ
መንግስት በበኩሉ በአ.አ ከተማ ለቤት መስሪያ የሚውል 400ካ.ሜ የመሬት ስጦታ በክቡር
ጠ/ሚ አማካይነት ተበርክቶለታል።
ሀትሪክ፡- እንኳን አደረሰህ…?
ሙክታር፡- እንኳን አብሮ አደረሰን፤ በዚህ
አጋጣሚ መላው የኢትዮጵያ ህዝብን እናንተም
ለአዲሱ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ መልካም
አዲስ ዓመት ይሁንላችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …እናመሰግናለን… በዓል
እንዴት ነበር…?
ሙክታር፡- …ዕድል ገጥሞኝ አዲሱን
አመት በደስታ እያከበርኩ ነው፤ በበርካታ
ድሎቻችና አዳዲስ ነገሮች ወደ አዲሱ ዓመት
በመሸጋገሬ በዓሉ ከሌላ ጊዜ በተለየ ደመቅ
ብሎ ነበር ያለፈው፡፡
ሀትሪክ፡- ከትናንት በስቲያ ጀምሮ አሮጌው
ዓመት ብለን መጥራት የጀመርነው 2009
ዓ.ም ለሙክታር የተለየ ዓመት ነው ብል
ተሳስቼ ይሆን…?
ሙክታር፡- ምንም አልተሳሳትክም…!
ያለፈው ዓመት (2009) ለእኔ በጣም የተለየና
በርካታ ስኬቶችን ያገኘሁበት ዓመት ሆኖ ነው
ያለፈው፤ በለንደኑ የአለም ሻምፒዮና ለራሴም
ለአገሬም ታሪካዊ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቻለሁ፡
፡ ከዚህ ሌላ በእኔ ስም (በአባትነት) የምትጠራ
አዲስ ህፃንም ይህችን አለም በመቀላቀልዋ
ከፍተኛ ደስታ ያገኘሁበት ልዩ ዓመትም ሆኖ
ነው ያለፈው፡፡
ሀትሪክ፡- ሙክታር ማስቀደም የሚገባኝን
ትልቁን ነገር ዘንግቼው፤ ከለንደኑ የአለም
ሻምፒዮና ድልህ በኋላ የሴት ልጅ አባት
ሆነሃል፡፡ የቤተሰብህም ቁጥር ከሁለት ወደ
ሶስት ከፍ ያለበት አጋጣሚ ተፈጥሮልናል
የልጅ አባት በመሆንህ እንኳን ደስ ያለህ
ማለት እፈልጋለሁ?
ሙክታር፡- እንኳን አብሮ ደስ አለን…
የሴት ልጅ አባት ለመሆን በመብቃቴ በጣም
ተደስቻለሁ፤ አላህ(ፈጣሪ) ለዚህ ማዕረግ
ስላበቃኝ ከልቤ አመሰግናለዋለሁ፡፡ በለንደኑ
ድሌ ተደስቼ ሳለባራ የሴት ልጅ አባት
የመሆን ክብር ስላገኘሁ ደስታዬ ፍፁም ልዩ
ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ልጅ የአላህ (የፈጣሪ)
ስጦታ እንደሆነ ባውቅም እንዲህ በደስታ
የተፈነቀነከው የአሰብከውን በፆታ በኩል
የተመኘኸውን አግኝተህ ነው?
ሙክታር፡- አዎን በጣም…! በእርግጥ
አላህ(ፈጣሪ) የፈቀደልኝን ለመቀበል ዝግጁ
ብሆንም ሴት ልጅ ብትሆንልኝ ብዩ ተመኝቼ
ነበር፤ አላህ(ፈጣሪም) የምኞቴን የልቤን
መሻት አይቶ ሴት ልጅ ስለሰጠኝ በማያባራ
ደስታ ውስጥ ነኝ፤ በባህላችን ሴት ልጅ ገዳም
ናት ይባላል ገና ይህችን ምድር ሳትቀላቀል
ነው የእሷ ገድ መታየት የጀመረው(ሣቅ)
በጣም በጣም ተደስቻለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- እንዲህ የተደሰትክባትን
ልጃችሁን ማን አላችኋት…? ዳቦ ቆርሳችሁስ
ስም አወጣችሁላት…?
ሙክታር፡- …አዎን አውጥተንላታል…፤
ሞፈሪያት ሙክታር እድሪስ የሚለው መጠሪያ
ስምዋ እንዲሆን ቤተሰብ አፅድቆላታል፡፡
ሀትሪክ፡- የልጃችሁን ስም ሞፈርያት
ሙክታር ብለህ የሰየምክበት የተለየ ምክንየት
አለህ?
ሙክታር፡- ስያሜውን ያወጣንላት
በሁለት ምክንያቶች ነው፤ አንደኛው
ሞፈርያት ማለት አሪፍ፤ ምርጥ እንደማለት
ስለሆነ የልጃችንን አሪፍነት ምርጥነት
ለመግለፅ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እሷ
የተወለደችው አልሸነፍ ብሉ ያስቸገረንን
ሞ ፋራህን ባሸነፍኩበት ሳምንታት ውስጥ
በመሆኑ ያንን ድልም በእስዋ ስም ሁሌም
ለመዘከርና ለማስታወስ ብሎም ታሪካዊ
እንዲሆን በማሰብሞ ፋራህንም ለማስታወስ
ነው ሞፈርያት ብለን ስም ያወጣንላት፡፡
ሀትሪክ፡- ሴት ልጅ አምጥታ
ያስታቀፈችህ፤ የልጅ አባት ያደረገችህ
ባለቤትህን አስተዋውቀን እስኪ…? …
ከሙክታር በስተጀርባ… ያለችው ሴት ማን…
ናት…? …እንዴትስ ተዋወቃችሁ…?
ሙክታር፡- …ትውውቃችን… ትንሽ
ቆየት ያለ ነው…፤…ለመጀመሪያ ጊዜ
የተዋወቅነው…ሁለታችንም ወረዳችንን
ወክለን ለዞን ለመወዳደር ስንሄድ ዞን ላይ ነው
የተዋወቅነው…፡፡
ሀትሪክ፡- …እንዴ…! …ባለቤትህም…
እንደ አንተ… አትሌት ናት ማለት ነው…?
ሙክታር፡- …ከዛሬ ስምንትና አስር
ዓመት በፊት አካባቢ… በወረዳና በዞን ደረጃ
400 እና 800 ሜትር ሩጫ ትሞካክር
ነበር…፤ ሁለታችንም ወረዳችንን ወክለን
ለዞን ለመወዳደር ስንመጣ… በዚያ አጋጣሚ
ተወዋቅን… ግን ብዙም አልቆየንም…
በትውውቃችን መሃል እሷ ወደ ሳውዲ አረቢያ
ሄደች…፡፡
ሀትሪክ፡- …በወቅቱ…
የፍቅር
ግንኙነት…
ነበራችሁ ማለት ነው…?
ሙክታር፡- …ከትውውቅ… የዘለለ
ነገር… ብዙም አልነበረንም…፤ …
ግን…ግንኙነታችን አጭር ቢሆንም…
አቀራረባችን… ወደ ፍቅር…ከፍ እያለ…
ሊሄድ እንደሚችል ያስታወቅ ነበር…፡፡ ከላይ
እንዳልኩህ ብዙም በትውውቃችን ሳንገፋ እሷ
በመሃል ወደ ውጪ በመሄድዋ ሁሉም ነገር
በወቅቱ ባለበት ቆመ፤ ለስምንት ዓመት ያህል
አካባቢ ሳንገናኝና ሳንደዋወል ቆየን፡፡ አሁን
ከረጅም ገዜ በኋላ እንደ አዲስ ታድሶ ነው
በአንድ ጣሪያ ስር መኖር የጀመርነው፡፡
ሀትሪክ፡- ግን እኮ ስምንት ዓመት
ረጅም ጊዜና ሰፊ ክፍተት የሚፈጥር ዓመት
ይመስለኛል፤ ሳትገናኙ ሳትደዋወሉ መቆየትና
እንደገና ፍቅሩን ማደስ ከባድ አይሆንም?
እስቲ እውነቱን ንገረኝ ሙክታር…?
ሙክታር፡- …ምንድነው
የምትጎረጉረው…? (ሳቅ) እውነት ነው ረጅም
ጊዜ ነው፤ ረዘም ላለ ጊዜ ስላልተገናኘንና
ስለተጠፋፋን በመሃል ከሌላ ሴት ጋር
ተዋውቄ ነበር፡፡ እንደውም እሷ ይሄኔ ዝም
ብላ አትቀመጥም የራስዋ ህይወት ሊኖራት
ይችላል፤ እኔም ዝም ብዬ መቀመጥ የለብኝም
በሚል ስሜት ከሌላ ሰው ጋር የመቀራረብ
ከዛ ከፍ ሲልም ወደ ትዳር የመተሳሰብ ሁኔታ
ውስጥ የመግባት ሃሳቦች በውስጤ ነበሩ፡፡
በመሃል ግን እሷ ስልኬን ከጎረቤት፣ ከወንድምቼ
ጋር አፈላልጋ ደወለችልኝ፤አወራችኝ፡፡ በአፍላ
የልጅነት ስሜት የተጀመረው ፍቅራችን
መቀጠል እንዳለበትና ከእኔ ጋር በፍቅር መኖር
እንደምትፈልግ ራስዋ ጥያቄ አቀረበችልኝ፡፡
ሀትሪክ፡- …ታዲያ አንተ በወቅቱ ምን
ምላሽ ሰጠሃት…ቀደም ሲል የጀመርከውስ…?
ሙክታር፡- እንዳልኩህ ስልኬን
አፈላልጋ የ “አብረን እንኑር፤ የእንጋባ”
ጥያቄ ያቀረበችልኝ እሷው ናት፤ “በለጋ
እድሜ የተጠነሰሰው ፍቅር ለፍሬ መብቃት
አለበት” በሚል አቋሟን ገለፀችልኝ፤ በመሃል
ከተዋወኳት ጋር አንዳንድ ያልተመቹኝ የባህሪ
ችግሮች ነበሩ፤ ከአንድ ሰው ፍላጎት ይልቅ
የሁለት ሰው ፍላጎት ያለው ይሻላል ብዬ
ላቀረበችልኝ “የእንጋባ፤ አብረን በአንድ ጣሪያ
ስር እንኑር” ጥያቄ እሺ በደስታ ነው የሚል
ምላሽ ሰጠኋት። ከእኔ ጋር አብራ ለመኖር
ከነበረችበች ሳውዲ አረቢያ በቀጥታ መጣች፤
በቃ ተጋባን ይሄው ነው ታሪኩ፡፡
ሀትሪክ፡- ሰርጋችሁ እንዴት ነበር…? …
ድል ባለሰርግ ነው ኒካ ያሰራችሁት?
ሙክታር፡- …(እየሳቀ)…አይ አንተ
ቀልደኛ ሰው ነህ… የምን ሰርግ አመጣህ…
እኛ በሰርግ አልተጋባንም፤ በአገራችን ባህልና
ወግ መሰረት እሷ ውጭ እያለች ቤተሰቦቿ
ጋር ሽማግሌ ላኩኝ፤ ቤተሰቦቿም በስርዓቱ
መሰረት ፈቀዱልኝ፤ ስትመጣ በቃ በአንድ
ላይ መኖር ጀመርን፡፡ ያኔ በለጋ እድሜ
የተጀመረው ግንኙንት አድጎ አሁን በአንድ
ጣሪያ ስር ከመኖር አልፈን ልጅ ለማፍራትም
በቃን ማለት ነው፡፡
ሀትሪክ፡
– አላህ(ፈጣሪ)
ምን አይነት
የትዳር ጓደኛ ነው
የሰጠህ…? …
እስቲ ባለቤትህን
በአንደበትህ
ግለፃት…?
ሙክታር፡
– …ግለፃት…
ስትል…?
ሀትሪክ፡- …
ቁንጅናዋን…
ባህሪዋንና…
ስለእሷ ያለህን
አመለካከት
ግለፅልኝ ለማለት
ነው?
ሙክታር ፡
– …አይ ቁንጅና…!
ግን ቁንጅና ምንድነው…? …
አላህ የፈጠረው… የሰው ዘር በሙሉ ለራሱ
ቆንጆ ነው፡፡ ከሚታየው ቁንጅና በላይ ውስጣዊ
ውበት፣ ባህሪ፣ ስነ-ምግባር ነው ትልቁ
ቁምነገር፤ ባለቤቴ ዛየን አብዱራዛቅ በጣም
መልካም ባህሪና ስብዕና ያላት ናት፡፡ በዚህ ላይ
ደግሞ ለስፖርቱ ቅርበትና ፍቅር ያላት መሆኑ
የበለጠ በጣም ለእኔ አስፈላጊ ሴት እንድትሆን
አድርጓታል፡፡ ለእኔ ለሙያዬ ሁሌም ቅድሚያ
የምትሰጥ ብቻ ሳትሆን የምታግዘኝ ሴት ናት፡
፡ በሙያዬ ውጤታማ እንድሆን በእንዲህ
መልኩ የተቀረፀች ሰው መኖርዋ በጣም
አግዞኛል፡፡ የአሁኑን የቅርቡን ብታይ እንኳን
በለንደን የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ
ላገኘሁት ድል የእሷ እገዛ በጣም ከፍተኛ ነበር፡
፡ በቂ ዝግጅት በቂ እረፍት እንዳገኝ ትኩረቴን
ሁሉ ውድድር ላይ እንዳደርግ ለራሴና
ለአገሬ አንድ ቁም ነገር ያለው ስራ እንድሰራ
ታበረታታኛለች፡፡ ከልምምድና ከውደድር
መልሰ በቂ የላብ መተኪያ በማዘጋጀት ከጎኔ
የቆመች፤ ለእኔ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነች
ሰውን ነው አላህ(ፈጣሪ) የሰጠኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ሙክታር የተወለድከው በስልጤ
ዞን ነው…?
ሙክታር፡- …ምነው…?…አዎን በስልጤ
ዞን የተወለድኩት፡፡
ሀትሪክ፡- የስልጤ ምድር ያፈራችው
በርካታ ታላላቅ ሰዎች በተለያዩ የኃላፊነት
ስራ ላይ እንዲሁም አንቱ የተባሉ ነጋዴዎች
እንዳሉ አውቃለሁ፤ የሰልጤ ዞን በአትሌቲክስ
ወይም በውጤታማ አትሌት ስምዋ ሲጠራ
ግን ሰምቼ አላውቅም… አንተስ ይሄንን
ታዝበሃል…?
ሙክታር፡- …የምትለው እውነትነት
አለው… በተለይ በንግዱ ላይ ብዙ አሉ፤
ግን እንዳይመስልህ የስልጤ ምድር
ስላልተሰራበት፤ ብዙ ትኩረትና ድጋፍ
ስለሌለው እንጂ በርካታ አገርን የሚያስጠሩ
አትሌቶችን ማፍራት ይቻላል፡፡ አላህ(ፈጣሪ)
ቢረዳኝ በቀጣይ በአትሌቲክሱ ላይ በስፋት
ገብቼ በርካታ አትሌቶች እንዲወጡ በርትቼ
እሰራለሁ፡፡ ስልጤ ዞን የአትሌቶች ደሀ
አለመሆንዋን ሰርቼ አሳያለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- የሚታወቅ አትሌት ሳይሆን
አትሌቲክስ በብዛት በማይዘወተርበት አገር
አንተ ውጤታማ አትሌት እሆናለሁ ብለህ
ነው ወደ ሩጫው የገባኸው?
ሙክታር፡- አረ በፍፁም…! እኔ
እንደዚህ እንደአሁኑ አትሌቲክሱን ሙያዬ
ኑሮዬ ይሆናል እታወቅበታለሁ፤ አልፎ
ተርፎም አገር አስጠራበታለሁ ብዬ አይደለም
የገባሁበት፤ በትምህርት ቤት ደረጃ መሮጥ
ጀምሬ ነው ሳላስበው የገባሁበት እንጂ ሯጭ
ለመሆን አስቤም ተመኝቼም አላውቅም፡
፡ የትምህርት ቤት ውድድር ነው ለዛሬው
ማንነቴ ምክንያት የሆነው፤ ባልተለመደበት
ባልታወቀበት መንገድ ሄጄ ነው የዛሬው
ሙክታር የተገኘው፡፡ በትምህርት ቤት
እንደቀልድ እሮጣለሁ ብዬ ገባሁ፤ ከዚያ
ዞን ለመወከል በቃሁ እንደዛ እያልኩ ነው
ያደኩት፡፡ በጣም የሚገርምህ እንኳን አትሌት
ሊኖር የሚሮጥ ሰው “ጤነኛ ሰው፤ አይደለም
እብድ ነው” እየተባለ በሚታሰብበት መንደር
ሯጭ መሆንን ማሰብ የህልም ያህል ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ይሄንን ነገር እንኳን
አስታወስከኝ፤አንተ በምትሮጥበት፣ ልምምድ
በምትሰራበት ሰአት “እብድ ነው፤ ጤነኛ ሠው
አይደለም” በሚል የአካባቢው ሰው ይናገር
ነበር የሚባለው እውነት ነው?
ሙክታር፡- እውነት ነው…!…ሁሌም
ልምምድ ስሰራ፤ ስሮጥ የተመለከቱ ሰዎች
ለምሰራው ስራ ክብር ከመስጠት ይልቅ ልብሴን
አውልቄ በቁምጣ መሮጤን ከእብድትና ጤነኛ
ካለመሆን ጋር አያይዘው ይናገሩ ነበር፡፡
በተለይ ልምምድ ስሰራ ሁሌም የሚመለከቱኝ
ሰዎች “ይሄ ልጅ አበደ እንዴ…?…ጤነኛ
አይደለም… መሰለኝ…” በማለት እርስ
በርሳቸው ያወሩ ነበር፡፡ አንዳንዶች ደግሞ እኔ
ስሮጥ ሲያዩ “የሞተ ሰው ቢኖር ነው፤ ለቅሶ
ሊነግር ነው የሚሮጠው” የሚሉበት ሁኔታ
ነው የነበረው፤ እንደዚህ አይነቱ አመለካከት
ባለበት ማህበረሰብ ውስጥ የስኬትን ጫፍ
መበጨበጥ ከባድ ቢሆን እኔ ምን ቸገረኝ
የፈለጉትን ይበሉ እኔ እነሱ እንዳሉት እብድ
አይደለሁም ጤነኛ ነኝ ደግሞም የምሮጠው
በራሴ እግር በራሴ ሰውነት ነው እነሱ ያውሩ
እኔ ስራዬን እሰራለሁ በማለት አካባቢያዊ
ጫናዎችን ተቋቁሜ ነው እዚህ የደረስኩት፡፡
ሀትሪክ፡- መቼም ይሄ የምትለው
አመለካከት ሞ ፋራህን በማሸነፍ የአለም
ሻምፒዮን፣ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት፣ የአገር
ጀግና ከሆንክ በኋላ የተቀየረ የተለወጠ
ይመስለኛል?
ሙክታር፡- ወረዳ፤ ከተማው አካባቢ ነው
እንጂ ወደ ውስጥ ገባ ስትል ይሄ አመለካከት
ከዚህ ሁሉ ድል በኋላም አልተለወጠም፡፡
ቴሌቭዥን፣ ሬድዮ ያለበት አካባቢ ስለ እኔ
ብቻ ሳይሆን ስለ አትሌቲክስ ስለ ስፖርት
ግንዛቤው አለ፤ ግን ሚዲያ የማይደርስበት
ትንሽ ገባ ያሉ ቦታዎች ስትሄድ ያ
አመለካከት እንዳልተቀየረ ትረዳለህ፤ መረጃው
ብዙም ስለሌላቸው አትፈርድባቸውም፡፡
አሁንም የአለም ሻምፒዮና የጀግና አቀባበል
የተደረገልኝ ሰው ሆኜም ነገ ስሮጥ ቢያዩኝ
“ይሄ ልጅ እብድ ነው” ማለታቸው የማይቀር
ነው፤የዚህ ሁሉ ችግር ምክንያቱ የመረጃ
እጥረትና የግንዛቤ ማነስ ነው።
ሀትሪክ፡- ሙክታር የሚለው ስም
ዛሬ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው
አለም በውጤታማነት በጀግንነት በስፋት
ይታወቃል፤አሁን ያገኘኸውን ክብርና እውቅና
ለማግኘት ግን ብዙ መሰናክሎች ፈተናዎችን
እንዳለፍክ ነው የሰማሁት፡፡ ለብዙዎች
ትምህርት ይሰጣል የሚል እምነት ስላለኝ
ለዛሬ እውቅና ከመብቃትህ በፊት ያለፈውን
ውጣ ውረድ አጫውተኝ እስቲ?
ሙክታር፡- እኔ ያሳለፍኩትን
የተሸከምኩትን መከራ በዚህች ደቂቃ
አውርተን አንጨርሰውም፤ በምድር ላይ
እንደ እኔ የተፈተነ በውጣ ውረዶች ውስጥ
እንደወርቅ በእሳት ተፈትኖ የወጣ ሰው አለ
ለማለት ይቸግረኛል፡፡ ስትሮጥ “እብድ ነው”
የሚል ስያሜ ከሚሰጥህ ማህበረሰብ ጀምሮ
የአቅም ችግር ተዳምሮበት በውጣ ውረድ
ውስጥ እንዳልፍ አድርገውኛል፡፡ ልምምድ
በባዶ እግሬ፣ በካልሲ ብቻና ከዚያ ከፍ ሲልም
በተቀዳደደ ጫማ በመስራት ብዙ ፈተናዎችን
አስተናግጄ ነው ያለፍኩት፤ ብታምንም
ባታምንም አንድ ጫማን እየሰፋሁ፤እየጠገንኩ
ከአንድ ዓመት በላይ እንደተጠቀምኩበት
ታውቃለህ…?
ሀትሪክ፡- ስለ እሷ ጫማ የሰማሁት ነገር
አለ፤ ስትሰፋት፣ ስትጠግናት ጫማዋ በአንተ
እየተማረረች ሳለ ውሻ ወስዶ ነው የገላገላት
ይባላል… እስቲ እሷን ታሪካዊ ጫማ መለስ
ብለህ አስታውሰኝ?
ሙክታር፡- (በጣም ሣቀ) …ምን
መሰለህ… በባዶ እግር፣ ትንሽ ቆርቆር
ሲያደርገኝ ደግሞ በካልሲ ከፈተናና ከውጣ
ውረዶች ጋር እየታገልኩ ስሮጥ ያየኝ አቶ —
—- የሚባል ሰው ነው ከችግሩ ልገ
ላግለው ብሉ ገዝቶ የሰጠኝ፤ ይህችን
ጫማ ለዝነጣም ለልምምድም ያለእረፍት
ስጠቀምባት ነገሮች ሁሉ ከአቅሟ በላይ
ይሆኑባትና ትቀዳደዳለች፡፡ ከተቀደደች በኋላ
መጣልና መገላገል ሲገባት እየጠጋገንኩ
እንደገና ስትቀደድ ደግሞ እየሰፋሁ አለቅ
አልኳት፡፡ አንድ ቀን ሆድ ብሷት ነው መሰል
የመበተን ያህል ስትቀደድ ቆዳ አምጥቼ ሰፍቼ
እንደገና እሰራባት ጀመር፡፡ በዚሀ መሃል
ልምምድ ሰርቼ መጥቼ በጣም የደከመች
ስለሆነ ቤት ከምትገባ ብዬ ውጪ ሳስቀምጣት
ሽታ አመጣች መሰለኝ ውሻ ጠርታ ውሻው
ይዛት ጠፋ… (በጣም ሳቅ) ይህችን ጫማ
ብታምንም ባታምንም እየተጠጋገነች ከአንድ
አመት ከስድስት ወር በላይ ተጠቅሜባታለሁ፤
በእኔ ተሰቃይታ ቆይታ ነበር በመጨረሻ ሽታ
የጠራው ውሻ ነፃ አወጣት፡፡ በአጠቃላይ እኔ
አሁን ለምገኝበት ደረጃ የበቃሁት ነገሮች
አልጋ በአልጋ ሆነውልኝ አይደለም፤ ብዙ
ፈተናዎችን መሰናክሉችን አይቼ ተፈትኜ ነው
እዚህ የደረስኩት፡፡
ሀትሪክ፡- እነዚህ ሁሉ ፈተናዎችና
መሰናክሎች ለተስፋ መቁረጥ እጅ እንድትሰጥ
አላደረጉህም?
ሙክታር፡- የነገሮች መደራረብና
፣ፈተናዎች ከመሻሻል ይልቅ እየባሱ
መምጣታቸው እንዲሁም የቤተሰቦቼ “አረፈህ
ተማር” ቁጣና ምክር ተረባርበው ለተስፋ
መቁረጥ እጅ እንድሰጥ ሊያደርጉኝ ሲሉ አንድ
ሰው በድንገት መጥቶ ነው አወጣኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ማነው ነፃ ያወጣህ…?
ሙክታር፡- ኢብራሂም ጄይላን ነዋ…!
ሀትሪክ፡- ኢብራሂም ጄይላን አትሌቱ…?
ሙክታር፡- አዎን አትሌቱ…! በወቅቱ እኔ
እኮ ገና ከስልጤ አልወጣሁም፤ በፈተናዎች
በመከራዎች መብዛት በነገሮች አለመሳካት
በጣም በተበሳጨሁበትና ለተስፋ መቁረጥ እጄን
ለመስጠት በተቃረብኩበት ሰአት የአላህ(ፈጣሪ)
መልዕክተኛ ሆኖ ነፃ ያወጣኝ አትሌት
ኢብራሂም ጄይላን ነው፡፡ አሁን እንደዚህ
ሳወራህ ቀላል ነገር ይመስልሃል፤ በወቅቱ
ግን ለእኔ የተላከ ነፃ አውጪ ነው የሆነልኝ፤
በጣም በተስፋ መቁረጥ በተከበብኩበት ወቅት
“ኢብራሂም ጄይላን የሚባል አዲስ ሰው
ሞ ፋራህን አሸነፈ”፤ የሚል ዜና ስሰማና
የእሱ ድል ሲወራ ሳዳምጥ የሆነች አንዳች
የመቃቃትና የመነሳሳት መንፈስ በውስጤ
ተፈጠረ፤ “ውስጤ አንተም እንደ እሱ አንድ
ቀን አሸናፊ ትሆናለህ” አለኝ፡፡ ብቻ ምን
ልበልህ የእሱ የአሸናፊነት መንፈስ በውስጤ
ከፍተኛ የመነሳሳትና የመነቃቃት መንፈስ
ዘራብኝ፡፡ ሊያንበረክከኝ የነበረውን ተስፋ
መቁረጥ እኔው ራሴ መልሼ አንበረከኩት፡
፡ ከዚያ በኋላ ለፈተናዎችና ለመሰናክሎች
ሳልሸነፍ ፊት ሳልሰጥ ጠንክሬ መስራት
እንዳለብኝ የኢብራሂም ጄይላን ድል ትልቅ
መልዕክት አስተላልፎልኝ ለዚህ በቅቻለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ወደ ሩጫው አለም እንድትገባ
ተፅዕኖ የፈጠሩብህ ሰዎች እነማን ነበሩ?
ሙክታር፡- ሃይል ገብረስላሴ የመጀመያው
ሰው ነው፤ለእኔ ሃይሌ ድሮም አሁንም ትልቅ
ተምሳሌቴ ነው፡፡ ወደ ሩጫው እንድሳብ ብቻ
ሳይሆን እንዳሸንፍም ጭምር ትልቅ ተፅዕኖን
የፈጠረብኝ ሰው ነው፡፡ ከእሱ በተጨማሪ
00እነ ቀነኒሳ በቀለ፣ ኢማና መርጊያ እና አሊ
አብዶሽም በእኔ የሩጫ ህይወት ላይ ያሳረፉት
ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ወደ ሩጫው ተጎትቼ
እንድገባ ተምሳሌት የሆኑኝ እነሱ ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- ከሞ ፋራህ ጋር ለንደን ላይ
ከመገናኘታችሁና አንተ ከማሸነፍህ በፊት
በተደጋጋሚ የትራክ የበላይቱን ይዞ ሲያሸንፍህ
ምን ይሰማህ ነበር?
ሙክታር፡- ሁሉንም አትሌትና
ኢትዮጵያዊ እንደሚያበሳጭ ሁሉ እኔም
በጣም ነበር የምበሳጨው፤በዓለም ሻምፒዮና
ደጋግሞ ሲያሸንፍ ሳይ ያመኝ ነበር፡፡ እንዴት
ይሄንን ሰውዬ በቃህ ማለት አቃተን? ብዬ
በጣም እቆጭ ነበር፤ዘንድሮም ወደ ለንደን
የተጓዝኩት በዚህ የቁጭት ስሜት ውስጥ
ሆኜ ነው፤ እንደውም ከቁጭት የተነሳ
ዘንድሮ ይሄንን ሰውዬ አሸንፈን ቁጭታችንን
ካልተወጣን እያልኩኝ ስዝት ነበር፡፡ እኔ
እንደውም ዘንድሮ ካላሸነፍኩት ከትራክ ወጥቼ
ወደ አስፋልትና ማራቶን እገባለሁ በማለት
ከማናጀሬ ጋር ጭምር በዚህ ጉዳይ እስከ
መነጋገር ደርሼ ነበር፡፡ ከትራክ እወጣለሁ
ያልኩት ወደ አስፋልት መግቢያ ጊዜ ላይ ሆኜ
ሳይሆን ከመበሳጨቴ የተነሳ ነው፤ ግን አላህ
ረድቶኝ አይሸነፍም የተባለን ሰው በመጨረሻ
በሽንፈት እንዲሰናበት አድርጌዋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ለንደን ላይ ከሞ ፋራህ
ሽንፈት በኋላ ፕሬስ ኮንፈረንስ ላይ አግኝቼህ
“እሱን በማሸነፍህ ራስህን እንደ ልዩ ጀግና
ትቆጥራለህ ወይ?” ብዬ ጠይቄህ ነበር፡፡ ዛሬም
የምደግመው ይሄንኑ ጥያቄ ነው፤ ሙክታር
አልሸነፍ ያለውን ሞ ፋራህን በማሸነፉ ራሱን
እንደ ልዩ ጀግና ይቆጥራል?
ሙክታር፡- እውነት ለመናገር ሞ ፋራህ
አልሸነፍ እያለ የትራክ ንጉስነታችንን ነጥቆ
ሲያበሳጨን እንደ ነበር መካድ አይቻልም፡፡
ከዚህ መነሻነት አልሸነፍ ያለ ጀግናን ማሸነፍ
ጀግንነት መሆኑን የምናገረው በኩራት ነው፤
ይሄ ድልም በእኔ ላይ ብቻ ሳይሆን ከህዝባችን
አልፎ ተርፎም በተቀናቃኞቻችን በኬንያና
በኡጋንዳ ሳይቀር “ሞ ፋራህ እንኳን ተሸነፈ”
በሚል የተለየ የደስታ ስሜት መፈጠሩን
ስታይ ድሉ ትልቅ ድል እንደሆነ ትረዳለህ፡፡
በተገኘው ድል ያልተደሰተ ያልቦረቀ ሰው ፈልጎ
ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ሞ ፋራህ የአለማችን
ምርጡና ትልቅ አትሌት መሆኑን በውጤቱ
ያስመሰከረ በመሆኑ ይሄን መካድ አይቻልም፡፡
ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ወርቅና ብሩን እየነጠቀን
የኖረን ሰው በአገሩና በደጋፊው ፊት ማሸነፍ
በቀላል የሚገለፅ ድል ባይሆንም ከእኔ ውጪ
ጀግና ሰው የለም ብሎ የሚያስፎክር ነው
ግን አልልም፡፡ ምክንያቱም በአገራችን ከእኔ
በላይ የሰሩ፣ በጣም ብዙ ውጤት ያስመዘገቡ
ጀግኖች እያሉ እኔ ራሴን ጀግና ነኝ ብል
ብዙዎች ይታዘቡኛል ብቻ ሳይሆን የብዙ
ጀግኖች ክብርንም መንካት ነው፡፡ እኔ ገና ለገና
አንድ የአለም ዋንጫ አሸንፌ እራሴን እንደ
ልዩ ጀግና ከቆጠርኩ አለቀልኝ በቃ ጠፋሁ
ማለት ነው፡፡ ደጋግመህ ሳታሸንፍ ሪከርዶችን
ሳትሰባብር አንድ ወርቅ ስላገኘህ ብቻ ራስን
ጀግና ብሎ መጥራት መታበይ ነው፡፡ ጀግና
ለመባል ሌሎች ጀግኖች የሰሩትን መስራት
ያስፈልጋል፡፡ ያ በሌለበት ጀግንነት ከባድ ነው፡
፡ ይሄን ስልህ ግን በሞ ፋራህ ላይ ያገኘሁት
ድል ቀላል ነው እያልኩህ አይደለም፡፡
ሀትሪክ፡- በለንደኑ የአለም ሻምፒዮና በሞ
ፋራህ ላይ የተቀዳጀኸው ድል ለህይወትህ ምን
አዲስ ነገር ይዞ መጥቷል?
ሙክታር፡- በጣም ብዙ ነገሮችን ይዞልኝ
መጥቷል፤ ሁሉንም እንደ አዲስ ቀይሯል
ብል ይቀለኛል፡፡ ሙክታር የሚለው ስም ዛሬ
በመላው አለም የቤተሰብ ያህል እንዲታወቅ
በአሽናፊነት እንዲነሳ አድርጓል፡፡ ከተለያዩ
አገሮች በአለም ሻምፒዮናነት በክብር ግብዣ
እንዲመጣልኝ ተፈላጊነቴም እንዲጨምር
ምክንያት ሆኗል፡፡ ከእነዚህ ሁሉ በላይ
ለራሴም ለአገሬም በታሪክ ሲታወስ የሚኖር
ትልቅ ክብርን ይዞልኝ መጥቷል፡፡ ብዙዎች
በታሪክ ሰሪነት በአኮራኸን አይነት ስሜት
እንዲመለከቱኝ እንዲሸልሙኝ እና እውቅና
እንዲሰጡኝ የለንደኑ ድል የራሱን ተፅዕኖ
ፈጥሯል፡፡ ከዚህ በፊት የምታውቅበት ሁኔታ
ቢኖርም ከሞ ፋራህ ድል በኋላ ብዙ ሰው
ሙክታር የሚለውን ስም ጠንቅቆ አውቆታል፤
የለንደኑ ድል ይሄንን ሁሉ ትርፍ ነው ይዞልኝ
የመጣው፡፡
ሀትሪክ፡- ግን እኮ በሞ ፋራህ ላይ
በተቀዳጀኸው ድል የተፈጠረው ደስታ ሳያበራ
ዙሪክ ላይ በዳይመንድ ሊግ መልሶ ሞ
ፋራህ አሸነፈህ፤ ሁለቱን ውጤቶች እንዴት
አስተናገድካቸው? በሳምንቱ መሸነፍህስ
አላበሳጨህም?
ሙክታር፡- እውነት ልንገርህ
አልተበሳጨሁም፤ ይሄንን ስልህ መሸነፍን
ወድጄው አይደለም፤ እንደውም በወቅቱ
ከነበረው ሁኔታ መጀመሪያ ሶስተኛ ተብዬ
ተሰርዞ ነው ሁለተኛ የተባልኩት እንጂ
ሶስተኛም ብሆን ለእኔ ውጤቱ ትልቅ ነው፤
በጣምም ነበር የምደሰተው፡፡
ሀትሪክ፡- እንዴ ሙክታር ምን ማለትህ
ነው? የአለም ሻምፒዮንነት ደስታህ ሳያበራ
ባሸነፍከው፤ በተበቀልከው ሰው መልሰህ
መሸነፍህ ያስደስታል?
ሙክታር፡- እንደዚህ ያልኩበት የራሴ
የሆነ ምክንያት አለኝ፤ በወቅቱ እንደ ነበረው
ሁኔታ ከሆነ ሶስተኛና ሁለተኛ መውጣት
አይደለም ለውድድር መቅረቤ በራሱ ከባድ
ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- እንዴት…?
ሙክታር፡- ለንደን ላይ ሞ ፋራህን
ለማሸነፍ፤ ለአገሬ ወርቅ ለማምጣት ያለኝን
ሁሉ አሟጥጬ ተጠቅሜያለሁ፤ ጉልበቴን
ጨርሻለሁ፤ በጉዞ ተንገላትቻለሁ፡፡ ከዚህ
ሌላ ደግሞ ባለቤቴ ልጅ ለመገላገል ተቃርባ
ስለነበር እሷን ወደ ሆስፒታል በማመላለስና
በመንከባከብ ነበር ቀኑንም ሌሊቱንም
ሳሳልፍ የነበረው፤ በዚህ ላይ በተገኘው ድል
በተፈጠረው የደስታ ስሜት በርካታ ሰዎች
“እንኳን ደስ ያለህ!” ለማለት በየጊዜው በብዛት
ወደ ቤት በመምጣታቸው ምክንያት እንቅልፍ
አጥቼ በደስታ ተዳክሜ አንድ ቀን ብቻ
ልምምድ ሰርቼ የመጣው ይመጣ ብዬ ነው
ወደ ውድድር የገባሁት፡፡ በቂ እረፍት ሳላገኝ፣
ለውድድሩ ትኩረት ሳልሰጥ፣ በደስታና በጉዞ
ተዳክሜ በአንድ ቀን ልምምድ ተወዳድሬ
ሁለተኛ መውጣት አይደለም ውድድሩን
መጨረሴ በራሱ ለእኔ ትልቅ ውጤት ነው፡፡
በዋናው ውድድር የአገርን ስም በሚያስጠራው
ስራ ላይ ማድረግ የሚገባኝን አድርጌያለሁ፡፡
ዙሪክ ላይ ግን በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ሆኜ
ሳላቋርጥ ሁለተኛ መውጣቴ ለእኔ ከማሸነፍም
በላይ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በዙሪክ የዳይመንድ ሊግ
ውድድር ላይ የነበረው የ5ሺህ ሜትር ሩጫ
ትንቅንቅ በጣም አስገራሚ ነበር፤ በነገራችን
ላይ በዚህ ውድድር ላይ ተጠልፋችሁ
ባትወድቁ ኖሮ ውጤቱ አሁን ከተመዘገበው
በተለይ ሊቀየር ይችል ነበር ትላለህ?
ሙክታር፡- አዎን የሚቀየር ይመስለኛል፤
ውድድሩን በደንብ ተከታትለኸው ከሆነ
መጨረሻው መስመር ላይ እኔ ቀድሜ
እጄን አስገብቼ ነበር፤ ውጤቱ የተሰረዘበት
በትውልድ ኬኒያዊ ሆኖ ለአሜሪካ የሚሮጠው
አትሌት ጠልፎ ባይጥለኝ ኖሮ ውጤቱ
ሊቀየር ይችል ነበር የሚል እምነቱ ነው
ያለኝ። ምክንያቱም እጆቼን አስገብቼ ነበር፤
ባልወድቅ ኖሮ በጣም በተጣበበ ሁኔታ
ማሸነፍ የምችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችል
እንደነበር አስባለሁ፡፡ ውድድር ውስጥ ስትኖር
ማሸነፍም መሸነፍም፤ መቅደምም መቀደምም
ያለና የሚኖር በመሆኑ ውጤቱን በፀጋ ነው
የምቀበለው፡፡
ሀትሪክ፡- የስልጤ ዞን 200ሺህ ብር
የገንዘብ ሽልማት “ከእኛ ምድር ወጥተህ
አኮራኸን” በሚል ስሜት ሽልመውሃል
ጠብቀኸው ነበር?
ሙክታር፡- እውነት ለመናገር
አልጠበኩም፤ እንዳልከውም የገንዘብ ሽልማት
ሸልመውኛል እኔ ከገንዘቡ በላይ ክብሩንና
እውቅናውን ነው ትልቅ ቦታ የምሰጠው፡
፡ ዞኑ እኔን በዚህ መልኩ መሸለሙ የበለጠ
እንድሰራ ከማነሳሳቱም በላይ ለሌሎች
ወጣቶች የማያስተላልፈው መልዕክት ትልቅ
ነው፤ አንድ ያለው እውነት ግን ለሽልማት
ሲጠሩኝ የጠበኩት ሌላ ነገር ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- ምን ነበር የጠበቅከው?
ሙክታር፡- እውነት ለመናገር ገንዘብ
አልጠበቅኩም፤ ለውጤቴም ለእኔም መጠሪያ
የሚሆን መሬት ይሰጡኛል የሚል ግምቱ
ነበረኝ፡፡ በእርግጥ የስጦታ ትንሽ እንደሌለው
አውቃለሁ፤ በተሰጠኝ ስጦታም ደስተኛ ነኝ፡፡
ገንዘብ ጠፊ በመሆኑ ለስሜ መጠሪያ የሚሆን
መሬት ቢሰጡኝና ለትውልድ አገሬ ህዝብ
የሚሆን ትልቅ የገበያ ማዕከል ወይም እንግዶች
ወደ ከተማችን ሲመጡ የሚያርፉበትን
ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል የምገነባበት መሬት
ቢሆን ደግሞ የበለጠ እደሰት ነበር ብቻ
ሳይሆን ሁላችንም ይጠቅማል የሚል እምነቱ
ነበረኝ፡፡ እነሱ ያሰቡትን አድርገዋል፤ በዚህ
በጣም አመሰግናቸዋለሁ፡፡