በርካታ ክስተቶች የተስተዋሉበት የባህርዳር ከተማ እና የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል ።
ባህርዳር ከተማዎች በሁለተኛው ሳምንት በወልቂጤ ከተማ በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ስደስት ለውጦችን በማድረግ ያሬድ ባየህ ፤ ፈቱዲን ጀማል ፤ በረከት ጥጋቡ ፤ ፉአድ ፈረጃ ፤ አደም አባስ እና ሀብታሙ ታደሰን በቋሚ አሰላለፍ በማካተት ተስፋዬ ታምራት ፤ ዳዊት ወርቁ ፤ ያብስራ ተስፋዬ ፤ አለለኝ አዘነ ፤ ፍፁም ጥላሁን እና ኦሴ ማውሊን በተጠባባቂ ወንበር ላይ በማድረግ ጨዋታቸውን ጀምረዋል ። በድሬዳዋ ከተማ በኩል በሳምንቱ በሀድያ ሆሳዕና በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ ብረክ ቃልቦሬን በመሀመድ አብዱለጢፍ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል ።
ጨዋታው ከዚህ ቀደም ከነበሩት ጨዋታዎች በርካታ ቁጥር ያለው ደጋፊ በተገኘበት እና በሜዳ ላይ እንቅስቃሴም በርካታ ሁነቶችን ያስተናገደ ነበር ። ባህርዳር ከተማዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ በኳስ ቁጥጥሩ አንፃራዊ ብልጫን በመውሰድ የተጫወቱ ቢሆንም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር አንፃር ግን ደከም ብለው ታይተዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በአሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ የሚመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በተፈጠረባቸው ጫና የመልሶ ማጥቃት ኳሶችን በመጠቀም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገዋል ።
አንድነበረው የጨዋታ ሂደት በግብ ሙከራዎች ያልታጀበው ጨዋታ በ26ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግዷል ።
በአጋጣሚው የድሬዳዋ ከተማው ቢንያም ጌታቸው በረጅም የደረሰውን ኳስ ለመጠቀም በሚጥርበት ወቅት በቀድሞ የፋሲል ከነማ ተጫዋች ያሬድ ባየህ በተሰራበት ጥፋ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል ። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ያሬድ ታደሰ በማስቆጠር ብርቱካናዎቹን መሪ አድርጓል ።
ከግቡ በኋላም ባህርዳር ከተማዎች ቀደም ብሎ እንደነበረው ጫና ማሳደረቻውን የቀጠሉ ቢሆንም የድሬዳዋ ከተማን የኋላ መስመር አልፈው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ግን በድጋሚ ተቸግረው ቆይተዋል ።
በአጋማሹ 36ኛ ደቂቃ ላይ የባህር ዳር ከተማው አደም አባስ በድሬዳዋ ከተማው የመስመር ተከላካይ እንየው ካሳሁን በተሰራበት ከባድ ጥፋት በቀጥታ ወደ ሆስፒታል ለማምራት ተገዷል ። በጥፋቱ እና በዕለቱ የመሀል ዳኛ የካርድ ውሳኔ ያልተደሰቱን የጣና ሞገዶቹ ደጋፊዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውሞቸውን አሰምተዋል ።
ጨዋታው ቀጥሎ በ44ኛው ደቂቃ ላይ ፉአድ ፈረጃ ከርቀት ያደረገውን ድንቅ የቅጣት ምት ሙከራ የድሬዳዋ ከተማው ግብ ጠባቂ ፍሬው ጌታሁን በድንቅ ብቃት ግብ ከመሆን አድኖታል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በድሬዳዋ ከተማ የ1 ለ 0 መሪነት ተጠናቋል ።
የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወደ አንድ አቅጣጫ ያደላ የጨዋታ እንቅስቃሴ የተስተናገደበት ሲሆን በመመራት ላይ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫን በመውሰድ በተጋጣሚያቸው ላይ ከፍተኛ ጫናን በማሳደር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረዋል ።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል በመከላከሉ ላይ ትኩረት በማድረግ ባህርዳር ከተማዎች ክፍተቶችን እንዳያገኙ ጥረቶችን ሲያደርጉ የግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ብቃት ተደምሮበት ግባቸውን ሳያስደፍሩ ለበርካታ ደቂቃዎች መቆየት ችለዋል ።
በአሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው የሚመሩት የጣና ሞገዶቹ የአጋማሹ የመጀመሪያ የግብ ዕድላቸውን በ55ኛው ደቂቃ ላይ ማድረግ የቻሉ ሲሆን ያገኙትን የቅጣት ምት በፍጥነት በማስጀመር ዱሬሳ ሹቢሳ ፍሬው ጌታሁንን በማለፍ ጭምር አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ተከላካዩ አሳንቴ ጎድፍሬድ ደርሶ አድኖታል ።
በመጀመሪያው አጋማሽ በአደም አባስ ላይ በሰራው ጥፋት የማስጠንቀቂያ የቢጫ ካርድ ተመልክቶ የነበረው እንየው ካሳሁን በ60ኛው ደቂቃ ላይ በዱሬሳ ሹቢሳ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ።
የቁጥር ብልጫውን የወሰዱት ባህርዳር ከተማዎች የአቻነቱን ግብ ፍለጋ ጥረታቸውን ሲቀጥሉ በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች መሪነታቸውን ለማስጠበቅ ሳጥናቸው አጥረው ቆይተዋል ።
በዚህ መሀል የተወሰኑ የግብ ዕድሎችን የፈጠሩት የጣና ሞገዶቹ በ69 እና 74ኛ ደቂቃዎች ላይ በዱሬሳ ሹቢሳ እና ፉዓድ ፈረጃ አማካኝነት ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች በፍሬው ጌታሁን ተመልሰዋል ።
በ77ኛው ደቂቃ ላይ ግን የቀድሞው የሰበታ ከተማ ተጫዋች ዱሬሳ ሹቢሳ ከበረከት ጥጋቡ የደረሰውን ኳስ ከመረብ በማሳረፍ ቡድኑን አቻ አድርጓል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ በበርካታ ደጋፊዎቻቸው ታጅበው በመጫወት ላይ ያሉት ባህርዳር ከተማዎች የማሸነፊያውን ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ማድረግ ቢችሉም ሁለተኛውን ግብ የሚያስቆጥርላቸው ተጫዋች ሳያገኙ ጨዋታው ተጠናቋል ።
በአምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ጥቅምት 14(ሰኞ) 7:00 ድሬዳዋ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ ሲጫወት ጥቅምት 16(ረቡዕ) 7:00 ላይ ደግሞ ባህርዳር ከተማ ለገጣፎ ለገዳዲን የሚገጥም ይሆናል ።