የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ከተማ መካከል ተደርጎ ሁለት አቻ ተጠናቋል ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአራተኛው ሳምንት ለገጣፎ ለገዳዲን በረቱበት ጨዋታ ላይ የነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ላይ ለውጥ ሳያደርጉ የገቡ ሲሆን በአዳማ ከተማ በኩል ደግሞ በሳምንቱ በቅዱስ ጊዮርጊስ በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ አስራአንድ ሶስት ቅያሪዎችን በማድረግ ታዬ ጋሻው ፤ ዳንኤል ደምሴ እና ዊልያም ሰለሞንን በሚሊዮን ሰለሞን ፤ አዲስ ተስፋዬ እና አሜ መሀመድ ምትክ ወደ ሜዳ አስገብተዋል ።
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ የፉክክር መንፈስ የታየበት እና በሁለቱም በኩል ከጨዋታው ውጤት ይዘው ለመውጣት ጥረቶች የተደረጉበት ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
ገና በአንደኛው ደቂቃ ላይ በአዳማ ከተማ በኩል ጠንካራ የግብ ሙከራ የተደረገ ሲሆን ዳዋ ሆቴሳ ከርቀት በቀጥታ ወደ ግብ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ መልሶታል ።
በሁለቱም በኩል የሚደረጉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች እምብዛም የተጋጣሚን ተከላካዮች አልፈው የሚደረጉ የግብ ሙከራዎች ሳይታዩ ቢቆዩም በ31ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያው ግብ ተቆጥሯል ።
ምንያህል ተሾም ለፀጋ ደርቤ ከርቀት የላከለትን ኳስ የአዳማ ከተማው ግብ ጠባቂ ኩዋሜ ባህ ወጥቶ ለመያዝ በሚጥርበት ወቅት የሰራውን ስህተት ተከትሎ ሄኖክ አየለ ከፀጋ ደርቤ ተቀብሎ ከመረብ አሳርፏል ።
ቀድመው ግብ ያስተናገዱት አዳማ ከተማዎች ለተቆጠረባቸው ግብ መልስ ለመስጠት ሶስት ያህል ደቂቃዎች ብቻ ነበር የፈጀባቸው ። አንጋፋው ተጫዋች መስዑድ መሀመድ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የመታው ኳስ በዘሪሁን ታደለ መረብ ላይ አርፏል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ የአዳማ ከተማ ብልጫ አይሎ የታየበት ሲሆን በተለይም የቡድኑን ቁልፍ ተጫዋች ዳዋ ሆቴሳ ተጎድቶ ቢወጣም ቡድኑ በማጥቃቱ መልካም ጊዜን ማሳለፍ ችሏል ።
በአጋማሹ ቀዳሚ የግብ ሙከራ በ59ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ አማኑኤል ጎበና ከሳጥን ውጪ ያደረገውን አስደናቂ የግብ ሙከራ ዘሪሁን ታደለ በድንቅ ብቃት ግብ ከመሆን አድኖታል ።
ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ግን አዳማ ከተማዎች መሪ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል ። አብዲሳ ጀማል ከአብነት ደምሴ የነጠቀውን ኳስ ለአሜ መሀመድ አቀብሎ ከተከላዮች ጀርባ በመግባት ዳግም የደረሰውን ኳስ በግሩም አጨራረስ ከመረብ ቀላቅሎታል ።
ከግቡ በኋላ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ጫና ፈጥረው ይጫወታሉ ተብሎ ቢጠበቅም አዳማ ከተማዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ችለዋል ።
ወደ መጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ግን የተሻለ ወደ ፊት መድረስ የቻሉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በመጨረሻም ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘው መውጣት የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል ።
በ84ኛው ደቂቃ ላይ እንዳርጋቸው ይላቅ ከቅጣት ምት ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ አብነት ደምሴ በኩዋሜ ባህ መረብ ላይ አሳርፎታል ።
በመጨረሻም ጨዋታው ልክ እንደ ዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ሁለት ለሁለት ተጠናቋል ።
በስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች(ድሬዳዋ ስታድየም) በመጪው ጥቅምት 26(ቅዳሜ) 12:00 ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወልቂጤ ከተማ ሲጫወት ሰኞ ጥቅምት 28(ሰኞ) 9:00 ላይ አዳማ ከተማ ከሲዳማ ቡና የሚጫወቱ ይሆናል ።