ካለፋት አራት የሊጉ ጨዋታዎች ሶስቱን በአቻ ዉጤት ያጠናቀቀው የዮርዳኖስ አባዩ ድሬዳዋ ከተማ እና በተመሳሳይ ካለፉት አራት ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በሁለቱ ሽንፈትን ያስተናገደዉ ሀዋሳ ከተማ ባደረጉት የአምስተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ሁለት አቻ በሆነ ዉጤት ጨዋታቸዉን አጠናቀዋል።
ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በተስተዋለበት የጨዋታው የመጀመሪያ አስራ አምስት ያህል ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች በመሀል ሜዳዉ ላይ ኳስ ተቆጣጥረው ለመጫወት ሲጥሩ የነበረ ሲሆን በሙከራ ረገድ ተጠቃሽ የነበረቸዉ በ3ኛዉ ደቂቃ በሀዋሳ ከተማ በኩል የተደረገዉ ነበር። በዚህም የድሬዳዋ ከተማ ተከላካዮች መዘናጋትን ተከትሎ የተገኘዉን ኳስ ኤርትራዊው አጥቂ በግራ መስመር በኩል ገፎቶ ወደ ሳጥን መግባት ችሎ የነበረ ቢሆንም መጠቀም ሳይችልበት ቀርቷል።
- ማሰታውቂያ -
በ20ኛዉ ደቂቃ ደግሞ የሀዋሳ ከተማ ተከታዮች የሰሩትን የቅብብል ስህተት ተከትሎ የተገኘዉን ኳስ የፊት መስመር አጥቂዉ ቻርልስ ለቢኒያም ጌታቸዉ አቀብሎት ተጫዋቹ ከርቀት አክርሮ በመምታት ግብ ማስቆጠር ችሏል። በዚህም ብርቱካናማዎቹ ገና በጊዜ ጨዋታዉን አንድ ለዜሮ በሆነ ዉጤት መምራት ጀምረዋል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ለማግኘት ተጭነዉ መጫወት የጀመሩት ሀይቆቹ ወጥናቸዉ ሰምሮ በ30ኛዉ ደቂቃ ላይ አቻ መሆን ችለዋል። በዚህም ከቀኝ መስመር በኩል የተሻማዉን የቅጣት ምት ኳስ ተጋናዊዉ ተከላካይ ላዉረንስ ላርቴ በጭንቅላቱ በመግጨት ወደ ግብነት ቀንሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።
በ45ኛዉ ደቂቃ ላይ ከአማካዩ ኤልያስ አህመድ የተሻገረለትን ሷስ አጥቂዉ ቢኒያም ጌታቸዉ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ወደ ግብነት በመቀየር ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛው ግብ ማስቆጠር ችሏል። በዚህም የመጀመሪያው አጋማሽ በብርቱካናማዎቹ ሁለት ለአንድ መሪነት ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ሀይቆቹ የአቻነት ግብ ለማግኘት ቶሎ ቶሎ ወደ ድሬዳዋ ከተማ የግብ ክልል መድረስ ሲችሉ በተቃራኒው ብርቱካናማዎቹ ድሬዳዋ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት እና በመስመር በኩል በሚጣሉ ኳሶች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሲሞክሩ ተስተውሏል።
በዚህም በ46ኛዉ ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር በኩል የተሻገረዉን ኳስ አሊ ሱለይማን ሲያሻማ በቅርቡ የነበረዉ ሙጅብ ቀጥታ ወደ ግብ ሲሞክር ግብ ጠባቂዉ ፍሬዉ ጌታሁን ሲመልስ በድጋሚ ሀዋሳዎች ምክረዉ የድሬዳዋ ከተማ ተከላካዮች እንደምንም ኳሷን አዉጥተዋታል።
በሁለተኛዉ አጋማሽ በሂደት የጨዋታው እንቅስቃሴ እየቀዘቀዘ ሲሄድ በተመሳሳይ እንደ መጀመሪያዉ አጋማሽ በሙከራ ረገድ ያን ያህል ተጠቃሽ ሙከራም ሳያስመለክተን ሲቀጥል ፤ ነገር ግን ጨዋታዉ ለመገባደድ ሁለት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት ሀይቆቹ አቻ መሆን የቻሉበትን ግብ አግኝተዋል። በዚህም የመስመር ተጫዋቹ እዮብ አለማየሁ ያቀበለዉን ኳስ ኤርትራዊው አጥቂ አሊ ሱለይማን ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል። ምንም እንኳን በሙከራ ረገድ እምብዛም አመርቂ ባይሆንም ጨዋታዉ ጥሩ ሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ተስተዉሎበት ሁለት አቻ በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።