ከአንድ ቤተሰብ ውስጥ እኔም ሆንኩ ወንድሜ ግብ ጠባቂ ሆነን መምጣታችን ብቸኞቹ ተጨዋቾች ሳያደርገን አይቀርም”ዳንኤል ተሾመ /አዳማ ከተማ/

“አዳማ ከተማ ሁለት የውጪ ሀገር ግብ ጠባቂዎችን አስፈርሞ ስለነበር እኔ የመጫወት እድሉን አላገኘሁም ነበር፤” በአሁን ሰዓት ላይ ደግሞ ክለቡ ዜጋ ግብ ጠባቂ ስለሌለው ለቡድኑ ጉዳትን ከማስተናገዴ በፊት የመጫወት እድሉን ላገኝ ችያለው የሚለው የአዳማ ከተማው ግብ ጠባቂ ዳንኤል ተሾመ ነው።

የአዳማ ከተማ ክለብን ከመቀላቀሉ በፊት በግብ ጠባቂነት ለወሊሶ ከተማ እና ለአዲስ አበባ ከተማ ለመጫወት የቻለው እና በሐዋሳ ዩንቨርስቲም ትምህርቱን ሊማር የቻለው ዳንኤል ተሾመ ስለ ግብ ጠባቂነቱ፣ ስለ ቡድናቸው እና በሌሎች ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ለሀትሪክ ስፖርት ድረ-ገፅ አስተያየቱን ሰጥቷል።

ስለ ኳስ ጅማሬው

“መጀመሪያ በፕሮጀክት ደረጃ ነው በተወለድኩበት ወሊሶ ከተማ ውስጥ መጫወት የጀመርኩት። አጥቂ ሆኜም ነው ስጫወት የነበረው። አንድ ጊዜ ታዲያ ግብ ጠባቂያችን በቀይ ሲወጣ አሰልጣኛችን ታሪኩ ደንድር እኔን አስገባኝና ጥሩ ስሆን ከዛን ሰዓት አንስቶ ግብ ጠባቂ ሆኜ መጫወት ጀመርኩ”።

በቤተሰቡ ውስጥ ስንት ወንድምና እህት እንዳለው እና ሌላ ስፖርተኛ እንዳለ

“በቤተሳባችን ውስጥ ከእኔ ውጪ አንድ ወንድምና አንድ እህት ነው ያለኝ፤ አንዱ ወንድሜ ኢብራሂም አብደላም እንደ እኔ ሁሉ ግብ ጠባቂ ነው። ለወሊሶ ከተማም እየተጫወተ ነው። የእሱን ግብ ጠባቂነት መሆን ስመለከትም በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሁለት ግብ ጠባቂዎች መውጣታቸው የእኛን ቤተሰብ ብቸኛ ሳያደርገን የቀረ አይመስለኝም”።

በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸው ክለባቸው ስላለው ወቅታዊ አቋም

“ባለፉት በርካታ ጨዋታዎቻችን ብዙ ነጥብ ልንጥል ብንችልም በችግሮቻችን ዙሪያ ከአሰልጣኛችን ጋር ስለተነጋገርን አሁን ወደ ማሸነፉ ልንመጣ እና በአቋም ደረጃም ልንሻሻል ችለናል”።
ለአዳማ ከተማ በሰሞኑ ጨዋታዎች እየተሰለፈ አለመሆኑ
“ልክ ነህ፤ የማልሰለፈው በልምምድ ወቅት ጉዳትን አስተናግጄ ስለነበር ነው። አሁን ግን ከህመሜ የዳንኩኝ ስለሆንክ ለቡድኔ የሚቀጥሉት ጨዋታዎች ላይ የምደርስለት ነው የሚሆነው”።

ስለ ቡድናቸው ጠንካራ እና ደካማ ጎን

“በብዙ ጨዋታዎች ላይ ያለንን ጠንካራ ጎን እንደተመለከትኩት በመስመር ላይ እንቅስቃሴ በእነ ታፈሰ ሰርካ እዮብ ማቲያስ በበላይ እና በአካሉ አጥቅተን ስንጫወት ነው። በክፍተት ደረጃ ደግሞ ያለን ደካማ ጎን ብዙ ጊዜ ወደ ኋላ ሸሽተን ስንጫወት ጎሎችን የምናስተናግድ መሆኑና ጎሎች የሚቆጠሩብን ደግሞ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ስለሆነም ቶሎ ለማንሰራራት አለመቻላችን ነው፤ አሁን ግን ይሄን ችግር እያረምነው ይገኛል”።
በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የቡድናቸውን ውጤት አስመልክቶ
“እንደ አዳማ ከተማ ትልቅ ቡድንነት እስካሁን ባሰብነው መልኩ ጥሩ የሚባል ውጤትን እያስመዘገብን አይደለንም፤ ለዚህ ልንዳረግ የቻልነውም አዲስ ቡድን ስለገነባንና በቂ የሚባል የዝግጅት ጊዜ ልምምድንም ስላልሰራን ነው። በዛ ላይ የወዳጅነት ጨዋታን ሳናደርግ እና የ15 ቀን ምርጫም በፈጀ የዝግጅት ጊዜ ልምምድ ወደ ውድድር ውስጥ ስለገባን ይሄ ለውጤት ማጣታችን ምክንያት ሆኗል”።

በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸው በቀጣይ ጊዜ የት ድረስ እንደሚጓዙ

“ሐዋሳ ከተማን ያሸነፍንበት ጨዋታ ለእኛ ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኖናል። ከዚህ በኋላም ይሄ ድል ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ይቀጥላል። በተለይ ደግሞ በሁለተኛው ዙር ላይ በጣም ጥሩ የሚባለውን ቡድንና በስኬታማነቱ የሚታወቀውን ክለብ ዳግም የምናስመለክት ይሆናል”።

ስለ ቀጣይ ጊዜ እቅዱ

“በአዳማ ከተማ ክለብ ቆይታዬ ቡድኑ የውጪ ሀገር ዜጎችን ብቻ ይጠቀም ስለነበር በእነሱ በመሸፈኔ ለቡድኔ ብዙም ግልጋሎት ሳልሰጥ ቀርቻለሁ። ስቀመጥም የሚሰማኝ ነገር ነበር። አሁን ላይ ግን ለቡድኑ የምጫወትበትን እድል ስላገኘው እኔነቴን በማሳየት ቡድኑን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስና እስከ ብሄራዊ ቡድን ደረጃም ተመርጬ ለመጫወት በርትቼ እሰራለሁ”።

ኢትዮጵያ ውስጥ ግብ ጠባቂ የለም ስለመባሉ

“ይሄን ስሰማ ያመኛል፤ ጥሩ ጥሩ ግብ ጠባቂዎች አሉን ብዬም ነው የማስበው። እንዴት ነው ለሀገር ውስጥ ተጨዋቾች ብዙ የመጫወት እድል ሳይሰጥ ግብ ጠባቂ የለም የሚባለው። በእዚህ አባባል ዙሪያ እኔ አልስማማም። ከዛ ይልቅ ከተጠባባቂነት በመምጣት ጭምር ለብሄራዊ ቡድን በመጫወታቸው ለእነሱ ከፍ ያለ አድናቆት ነው ያለኝ”።

በመጨረሻ

“አዳማ ለአገራችን እግር ኳስ ጥሩ ነገርን ያበረከተ ቡድን ሆኖ በአሁን ሰዓት ላይ እያስመዘገበ ያለው ውጤት የሚገባው አይደለም። በሁለተኛው ዙር ጥሩ ውጤት የምናስመዘግብ ይመስለኛል። በተረፈ በእስካሁኑ የኳስ ቆይታዬ እኔን በማሰልጠን ለዛሬ ደረጃ እንድደርስ ያደረጉኝን ታሪኩ ደንድርን በአዲስ አበባ ከተማ የመጫወት እድልን የሰጠኝን አስራት አባተንና ስዩም ከበደን ፤ የአዳማ ከተማ አሰልጣኝ አስቻለው ሀ/ሚካኤል እንደዚሁም ቤተሰቦቼን አመሰግናለሁ”።

Hatricksport website editor

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Hatricksport website editor