የውድድር አመቱ መጨረሻ በሆነዉ የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ30ኛ ሳምንት ጨዋታ የመጀመሪያ ዕለት ጨዋታ ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ቀን ዘጠኝ ሰዓት ላይ ያደረጉትን ጨዋታ ያለ ግብ 0ለ0 በሆነ አቻ ዉጤት አጠናቀዋል።
አስቀድሞ ለአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እና ረዳታቸው የማስታወሻ ፎቶ ግራፍ ስጦታ በማበርከት በጀመረዉ የዕለቱ ጨዋታ ፋሲል ከነማ በፈጣን የመስመር ማጥቃት እና ፊት መስመር ላይ የሚገኙት ተጫዋቾች ኢላማ ያደረጉ ረጃድም ኳሶችን ከኋላ መስመር በመጣል አደጋ ለመፍጠር ሲጥሩ የተስተዋለ ሲሆን ነገር በመጀመሪያዎቹ ሀያ አምስት ያህል ደቂቃዎች አደገኛ የሚባል ተጠቃሽ ለግብ የቀረበ ሙከራ ለማድረግ ሲሞክሩ እምብዛም መመልከት አልተቻለም ነበር ። በዚህ ሂደት የቀጠለዉ ጨዋታ በ26ተኛ ደቂቃ ላይ ከፍጥነት ጋር ማጥቃት የቀጠሉት አፄዎቹ በአማካዩ ሱራፌል ዳኛቸው አማካኝነት የመጀመሪያ ተጠቃሽ ሙከራ ማድረግ ችለዋል።
በተመሳሳይ የጨዋታውን የመሐል ክፍል በመቆጣጠር እና በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ አፄዎቹ የሜዳ ክፍል ለመግባት እንዲሁም ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የነበሩት ቡናማዎቹ ደግሞ የጨዋታዉ ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጥር ምንም እንኳን በአፄዎቹ ብልጫ ቢወሰድባቸዉም ነገር ግን ግብ ሳያስተናግዱ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል ማምራት ችለዋል።
- ማሰታውቂያ -
ከዕረፍት መልስ የመጀመሪያውን አይነት የጨዋታ መንገድ ሲከተሉ በነበሩት ሁለቱም ክለቦች ቡናዎቹ በ50ኛዉ ደቂቃ ላይ ድንቅ ሙከራን በወጣቱ ተጫዋች ማኑኤል አማካኝነት ማድረግ ሲችሉ ነገር ግን ኳስና መረብን ለማገናኘት እጅግ በጣም ሲቸገሩ ተስተውሏል። ከደቂቃዎች በኋላ ደግሞ አጥቂዉ ብሩክ በየነ ከቆመ ኳስ አስደናቂ ሙከራን ማድረግ ችሎ የነበረ ቢሆንም የግብ ዘቡ ሳማኪ ሚካኤል ግን በአስገራሚ ብቃት መልሶበታል።
በተቃራኒዉ ከዕረፍት መልስም በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸዉን አይነት የጨዋታ መንገድ ይዘዉ የቀጠሉት አፄዎቹ ምንም እንኳን በሁለተኛዉ አጋማሽ የመጀመሪያ ሀያ ያህል ደቂቃዎች ተጠቃሽ ሙከራን ማድረግ ተቸግረዉ በቡናማዎቹ በመጠኑም ቢሆን ብልጫ የተወሰደባቸው ፋሲሎች በእነዚህ ደቂቃዎች ውስጥ ግን በፊት መስመር ተጫዋቾቹ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ ፣ ዱላ ሙላቱ እና ሱራፌል አማካኝነት ሙከራዎችን ማድረግ ችለዉ ነበር ፤ በጨዋታው መገባደጃ ወቅት በ81ኛዉ ደቂቃ ላይ ግን አፄዎቹ ጥሩ የግብ ዕድል መፍጠር ችለዉ ነበር ፤ በዚህም የመስመር ተጫዋቹ ዱላ ሙላቱ ያሻገረለትን ኳስ ኦሴ ማዉሊ በግቡ ቋሚ አስታኮ ወደ ዉጭ ልኳታል። በዚህ ሂደት የቀጠለዉ የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታም ግን ሳይስተናገድበት 0ለ0 በሆነ አቻ ዉጤት ተገባዷል።