የ2015 ዓ/ም የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ የ30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመደረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን ዛሬም ከፕሪሚየር ሊጉ ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚወርደዉ ሶስተኛዉ ክለብ የሚለይበት ወሳኝ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰአት ይደረጋሉ።
ከዚህ በፊት ቀሪ ጨዋታዎች እያሏቸው በጊዜ ከሊጉ ለገጣፎ ለገዳዲ እና ኢትዮ ኤሌትሪክ የተሰናበቱ ሲሆን እነሱን ተከትሎ ከሊጉ ላለመዉረድ በርካታ ክለቦች ትንቅንቅ ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን በስተመጨረሻም ላለመዉረድ የሚደረገዉ ትንቅንቅ ዉስጥ ወልቂጤ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ቀርተዋል።
በሊጉ ዉስጥ ቀሪ አንድ አንድ ጨዋታ ብቻ እየቀራቸዉ ወልቂጤ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ በ34 ነጥብ እና በ33 ነጥብ የደረጃዉ ሰንጠረዥ ግርጌ 13ኛ ደረጃ ላይ እና 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
- ማሰታውቂያ -
ከሁለቱ ክለብ አንዱ ወደ ከፍተኛ ሊግ ወራጅ የሚሆን ሲሆን ጨዋታቸውን ዛሬ በተመሳሳይ ሰአት የሚያደርጉ ይሆናል።
በዚህም መሰረት ዛሬ ከቀኑ 9:00 ሰአት አርባምንጭ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ ጋር በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩንቨርስቲ ስታዲየም ጨዋታዉን የሚያደርግ ሲሆን እንዲሁም በእዛው ሰአት ወልቂጤ ከተማ ከ አዳማ ከተማ ጋር በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታዉን የሚያደርጉ ይሆናል።
የዛሬዉን ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች የሚያሸንፉ ከሆነ ወልቂጤ ከተማ በ37 ነጥብ ሊጉ ዉስጥ መቆየቱን የሚያረጋግጥ ሲሆን አርባምንጭ ከነማ በበኩሉ በ1 ነጥብ አንሶ በ36 ነጥብ ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚወርድ ይሆናል።
ይህ ለሁለቱም ክለቦች ወሳኝ የሆነዉ የመጨረሻው ጨዋታ ዛሬ ከቀኑ 9:00 ሰአት ላይ የሚደረግ ይሆናል።