በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ሲደረጉ በአዳማ አበበ ቢቂላ እና በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታድየም የተደረጉት የተመሳሳይ ሰአት ጨዋታዎች ሶስተኛውን ወራጅ ክለብ አሳውቀዋል ።
በአበበ ቢቂላ ስታድየም የተደረገው የወልቂጤ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ 1 – 1 ሲጠናቀቅ
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታድየም የተደረገው የአርባምንጭ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ በተመሳሳይ 1 – 1 መጠናቀቁን ተከትሎ አርባምንጭ ከተማ ወደ ከፍተኛው ሊግ መውረዱግን አረጋግጧል ።
በጨዋታው በሀዋሳ ከተማ በኩል በ29ኛው ሳምንት በባህርዳር ከተማ በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሶስት ለውጦችን በማድረግ በበረከት ሳሙኤል ፣ ኤፍሬም አሻሞ እና ተባረክ ሄፋሞ ምትክ ፀጋአብ ዮሐንስ ፣ ዳንኤል ደርቤ እና እዮብ አለማየሁ ወደ ጨዋታው ሲገቡ በሳምንቱ በድሬዳዋ ከተማ የተረቱት አርባምንጭ ከተማዎች በጨዋታው ከተጠቀሙት አሰላለፍ በተመሳሳይ ሶስት ለውጦች በማድረግ በመሪሁን መስቀለ ፣ አሸናፊ ኤልያስ እና ኤሪክ ካፓይቶ ምትክ አቡበከር ሻሚል ፣ በላይ ገዛኸኝ እና ተመስገን ደረሰን አሰልፈዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ አርባምንጭ ከተማዎች ተጭነው በመጫወት የጀመሩ ሲሆን ቀድመው ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን ለመቆጣጠር ጥረቶችን ያደረጉበት ነበር ።
ጨዋታው ገና አንድ ደቂቃ እንኳን ሳይሞላው አህመድ ሁሴን ከቀኝ አቅጣጫ ወደ ግብ ክልል ያሻገረው ኳስ በአላዛር ማርቆስ ተይዟል ። ከሰኮንዶች ቆይታ በኋላ የአርባምንጭ ከተማን የፊት መስመር ከሚመሩት ሶስት ተጫዋቾች አንዱ የሆነው በላይ ገዛኸኝ ከተመስገን ደረሰ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ መሞከር ቢችልም በግብ ጠባቂው ግብ ከመሆን ድኖበታል ።
በሀዋሳ ከተማ በኩልም በስድስተኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ደርቤ የመኮንን መርዶክዮስን መውጣት ተመልክቶ ከቀኝ መስመር ወደ ግብ የላከው ኳስ ግብ ጠባቂው ግብ ከመሆን አድኖታል ።
ጨዋታው 12ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን አዞዎቹ ግብ አስቆጥረዋል ። በውድድር አመቱ ከዚህ ጨዋታ በፊት 8 ግቦችን አስቆጥሮ የነበረው አህመድ ሁሴን ከተመስገን ደረሰ ከቀኝ አቅጣጨ የደረሰውን ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ በመምታት ክለቡን መሪ ያደረገ ግብ አስቆጥሯል ።
በአርባምንጭ ከተማ በኩል በተለይም በቀኝ መስመር የሚደረጉ የማጥቃት ሂደቶች አደገኛ አጋጣሚዎች መፍጠር የቻሉ ነበሩ ። በአመዛኙ ከግራ መስመር የሚነሱት የአዞዎቹ እንቅስቃሴዎች በሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች ሲመለሱ ቆይተዋል ።
በሀዋሳ ከተማ በኩል በብዛት በራሳቸው የሜዳ ክፍል ላይ ይቆዩ የነበረ ሲሆን በተወሰኑ አጋጣሚዎች በረጅም በሚጣሉ ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገዋል ።
በ23ኛው ደቂቃ ላይም ሀይቆቹ የሆኑበትን ግብ ከመረብ አሳርፈዋል ። ሙጂብ ቃሲም ከመስመር ያሻገረውን ኳስ እዮብ አለማየሁ የበርናንድ ኦቼንጌን መዘናጋት ተጠቀሞ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ።
በ25ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ደረሰ በረጅም የደረሰውን ኳስ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ሳይቆጣጠረው በቀረበት ወቅት ፀጋአብ ዮሐንሽ በዕጁ ቢነካም የመሀል ዳኛውን ኢንተርናሽናል አርቢትር ባምላክ ተሰማን የፍፁም ቅጣት ምት ለመስጠት ሳያሳምን ቀርቷል ።
በ28ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳ ከተማዎች ዳግም መሪ መሆን የሚችሉበትን አጋጣሚ በአሊ ሱሌማን አማካኝነት ማግኘት ቢችሉም የአሊ ሱሌማን ኳስ ከግቡ አናት በላይ ወጥቷል ።
በቀጣዮቹ የመጀመሪያ አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ አዞዎቹ በሁለቱም መስመሮች ወደ ሀዋሳ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን አድርገዋል ።
በ41ኛው ደቂቃ ላይ ወርቅይታደስ አበበ በቀኝ መስመር በኩል በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ግቡ ይዞ የቀረበውን ኳስ ለተመስገን ደረሰ አቀብሎት የነበረ ቢሆንም የተመስገን ደረሰ ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።
የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታው ፍሰት በአንድ አቅጣጫ ብቻ ተወስኖ የታየበት ፤ አርባምንጭ ከተማዎች ሙሉ ለመሉ በማጥቃት ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በመከላከል ያሳለፉበት ነበር ።
በተለይም በሊጉ ለመቆየት በጨዋታው አሸንፈው የወልቂጤ ከተማን ነጥብ መጣል ይጠብቁ የነበሩት አዞዎቹ በርካታ የግብ ዕድሎች መፍጠር ቢችሉም አንዱንም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ።
በአጋማሹ ቀዳሚ የግብ ሙከራ በ54ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ በመልሶ ማጥቃት ይዘው የገቡትን ኳስ በአህመድ ሀሴን እና መላኩ ኤልያስ በኩል አልፎ ተመስገን ደረሰ ማግኘት ችሎ የነበረ ቢሆንም የተመስገን ደረሰ ኳስ በአላዛር ማርቆስ ተመልሷል ።
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም አህመድ ሁሴን ከሳጥን ውስጥ ሆኖ ያደረገው የግብ ሙከራ በድጋሚ በግብ ጠባቂው አላዛር ተመልሷል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይም አዞዎቹ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን በማጠናከር በተደጋጋሚ የሀዋሳ ከተማን የኋላ ክፍል እና ግብ ጠባቂው አላዛርን መፈተን ችለዋል ።
በአቡበከር ሻሚል ፣ አህመድ ሁሴን እና ተመስገን ደረሰ አማካኝነትም ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር ።
በ72ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ሻሚል ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ተመልሷል ።
በ74ኛው ደቂቃ ላይም አህመድ ሁሴን በቀኝ አቅጣጫ ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ፀጋአብን በማለፍ በድጋሚ ግብ ጠባቂውን ለማለፍ ሲጥር የተመለሰበት ሲሆን ቡታቃ ሸመና አግኝቶ ወደ ግብ የመታው ኳስ በሰይድ ሀሰን ግብ ከመሆን ድኗል ።
በሀዋሳ ከተማ በኩል በቁጥር በርከት ብለው በመከላከል ላይ ሲያተኩሩ በተወሰኑ አጋጣሚዎች የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች አድርገዋል ።
ነገር ግን ፊት ላይ የነበረው የአህመድ ሁሴን ፣ የተመስገን ደረሰ እንዲሁም ተቀይሮ የገባው የኤሪክ ካፓይቶ የማጥቃት እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ወደ ሳጥን መግባት ቢችልም ኳስ እና መረብን ማገናኘት ሳይችሉ ቀርተዋል ።
በመጨረሻም የተጨመሩት አራት ደቂቃዎች ተጠናቀው የመሀል ዳኛ የኢንተርናሽናል አርቢትር ባምላክ ተሰማ የጨዋታ መጠናቀቂያ የፊሽካ ድምፅ የአርባምንጭ ከተማን ከሊጉ መሰናበት ያረጋገጠ ሆኗል ።