ወሳኝ በነበረዉ እና ሶስተኛዉን የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወራጅ ቡድን የሚለየዉ አንደኛዉ መርሐግብር በነበረዉ የቀን ዘጠኝ ሰዓት የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም የ30ኛ ሳምንት ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ 1ለ1 በሆነ ዉጤት አቻ መርሐግብራቸዉን አጠናቀዋል።
በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ መሪነት የተጀመረዉ ወሳኙ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም በጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር ሲጀምር ገና በመባቸዉ በ2ተኛዉ ደቂቃ ላይም ተመስገን ደረሰ ያቀበለዉን ኳስ በላይ ገዛኸኝ ወደ ግብ ሞክሮ የበነበረ ቢሆንም የግብ ዘቡ አልዓዛር መልሶበታል።
- ማሰታውቂያ -
ከጨዋታዉ መጀመሪያ አንስቶ በሙከራ ረገድ የተሻሉ የነበሩት እና የጨዋታዉን ዉጤት አብዝተዉ ይፈልጉት የነበሩት አዞዎቹ በ13ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር ችለዋል ፤ በዚህም የመስመር ተጫዋቹ ተመስገን ያቀበለዉን ኳስ አጥቂዉ አህመድ ሁሴን በድንቅ ብቃት ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
በጨዋታዉ እንቅስቃሴም ሆነ በሙከራ ረገድ ብልጫ የተወሰደባቸዉ ሀይቆቹ ከኋላ ወደ አጥቂዎቹ በሚጣሉ ረጃጅም ኳሶች አልፎ አልፎ ግብ ለማስቆጠር ሲያደርጉት የነበረዉ ጥረት ተሳክቶላቸዉ በ23ተኛዉ ደቂቃ ላይ አቻ መሆን ችለዋል ፤ በዚህም አጥቂዉ ሙጅብ ቃሲም ያሻገረለትን ኳስ እዮብ አለማየሁ ወደ ግብ በመቀየር ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታም አርባምጭ ከተማ በመስመር ተጫዋቾቹ ተመስገን ደረሰ ፣ አህመድ እና በላይ ገዛኸኝ በመሳሰሉ ተጫዋቾች ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም በመጀመሪያው አጋማሽ ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በተመሳሳይ ሀዋሳ ከተማም በተከታታይ በአሊ ሱለይማን እና ሙጅብ አማካኝነት ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ሁለቱም ክለቦች ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ በተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ በቀጠሉት በሁለቱ ክለቦች ጨዋታም በ51ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ አቡበከር ሻሚል ከመላኩ ኤልያስ የተቀበለዉን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ በግቡ አናት ላይ ወደ ዉጭ ወጥታለች።
ከደቂቃዎች በኋላ በ54ተኛዉ ደቂቃ ላይ በድጋሚ አጥቂዉ አህመድ ሁሴን ከመሐል ሜዳ እየገፋ ሳጥን ዉስጥ ከገባ በኋላ አጥቂዉ ኳሷን ለመላኩ ሲያቀብለዉ እርሱ ደግሞ ለተመስገን ደረሰ በጥሩ አመቻችቶለት የነበረ ቢሆንም ተጫዋቹ በቀጥታ ኳሷን ወደ ግብ ሲሞክር ግብ ጠባቂዉ አልዓዛር ማርቆስ እንደምንም ኳሷን መልሷታል።
በ74ተኛዉ ደቂቃ አጥቂዉ አህመድ ሁሴን ተከላካዮችን አታሎ ሳጥን ዉስጥ ከደረሰ በኋላ ወደ ግብ የሞከረዉን ኳስ በዕለቱ ድንቅ የነበረዉ የግብ ዘቡ አልዓዛር ሲመልሰዉ ኳሷ ሌላኛዉን አጥቂ ተመስገን ደረሰ ጨርፋ ለጥቂት ወደ ዉጭ ወጥታለች። የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በመጣ ቁጥር አዞዎቹ ጫናቸዉን አበርትተዉ ሲቀጥሉ ፤ በተቃራኒው ሀይቆቹ በፊት መስመር ተጫዋቾቻቸው ኢላማቸዉን ያልጠበቁ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ሁለቱም ክለቦች የማሸነፊያ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ መደበኛዉ 90 ደቂቃ 1ለ1 በሆነ አቻ ዉጤት ተገባዷል። ዉጤቱን ተከትሎም አርባምንጭ ከተማ ከሊጉ የወረደ ሶስተኛዉ ክለብ ሆኗል።