የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአንደኛ ዙር የመጨረሻ ወይንም የ15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት መደረግ ሲጀምሩ በቀዳሚነት የተደረገው የፋሲል ከተማ እና የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በፋሲል ከተማ የ4 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
በ14ኛው ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አቻ የተለያዩት ፋሲል ከተማዎች በጨዋታ ተጠቅመውት ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን ሚካኤል ሳማኪ ፣ ከድር ኩሊባሊ ፣ ሱራፌል ዳኛቸውን አና ፍቃዱ አለሙን በይድነቃቸው ኪዳኔ ፣ አስቻለው ታመነ ፣ ሀብታሙ ተከስተ እና ኦኪኪ አፎላሏቢ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል ። በሳምንቱ በአዳማ ከተማ የ3 ለ 1 ሽንፈት ያስተናገዱ ድሬዳዋ ከተማዎች አምሰት ለውጦችን በማድረግ በፍሬው ጌታሁን ፣ ዓወት ገብረሚካኤል ፣ አብዱራህማን ሙባረክ ፣ ሙኽዲን ሙሳ እና ማማዱ ሲዲቤ ምትክ ደረጄ አለሙ ፣ አውዱ ናፊዩ ፣ እንየው ካሳሁን ፣ ሄኖክ አየለ እና ሳሙኤል ዘሪሁንን አሰልፈዋል ።
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን ቀስ በቀስ ግን አፄዎቹ ኳሱን ይዘው በመጫወት ወደ ፊት ለመሄድ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በድሬዳዋ ከተማ በኩል ደግሞ በተለይም ሁለቱን የፊት አጥቂዎች ኢላማ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶች ይደርሱ ነበር ።
በጨዋታው የነበረው የመጀመሪያው የግብ ዕድል 4ኛ ደቂቃ ላይ የታየ ሲሆን በድሬዳዋ ከተማ በኩል ሄኖክ አየለ ለሳሙኤል ዘሪህን የሰነጠቀለትን ኳስ ሳሙኤል በሁለት የፋሲል ከተማ ተከላካዮች መሀል አልፎ ፊት ለፊት ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኘቶ ኳሱን በአግባቡ መምታት ሳይችል ቀርቷል ።
በፋሲል ከተማ በኩል በረከት ደስታ 15ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ የሞከረው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደ ውጪ የወጣ ሲሆን በ18ኛው ደቂቃ በኋላ ደግሞ ሽመክት ጉግሳ በተመሳሳይ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የላከው ኳስ በግብ ጠባቂው ተይዟል ። በተከታታይ ደቂቃዎች ላይ ወደ ድሬዳዋ ከተማ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ ለመድረስ የቻሉት አፄዎቹ 20ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል ። ከበረከት ደስታ ወደ ሳጥን ውስጥ የተላከለትን ኳስ በፍጥነት ገብቶ ያገኘው ሽመክት ጉግሳ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ችሏል ። ይህም ሽመክት በውድድር አመቱ ያስቆጠረው የመጀመሪያ ግቡ ሆኖ ተመዝግቧል ።
ከግቡ መቆጠር አራት ደቂቃዎች በኋላ ኦኪኪ አፎላቢ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ሆኖ ከሽመክት የደረሰውን ኳስ ከግቡ ትይዩ ነፃ ለነበረው በረከት ደስታ አቀብሎት የነበረ ቢሆንም የበረከት ኳስ በግብ ጠባቂው ደረጄ አለሙ ተይዟል ።
ከውሀ እረፍት መልስ ድሬዳዋ ከተማዎች በተወሰነ ጥሩ ለመንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን ወደ ፋሲል ከተማዎች ሳጥን ገብተው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ግን ተቸግረው ነበር ። የመጀመሪያ አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ መሀመድ አብዱለጢፍ ከቅጣት ምት ያሻገረው ኳስ በሄኖክ አየለ በኩል አልፎ ሳሙኤል ዘሪሁን በጭንቅላት ገጭቶ ወደ ግብ ቢሞክረውም ለጥቂት ከግቡ አግዳሚ በላይ ወጥቷል ። የመጀመሪያ አጋማሽም በፋሲል ከተማ መሪነት ተጠናቋል ።
ሁለተኛው የጨዋታው አጋማሽ ፈጣን እንቅስቃሴ የታየበት እና በግቦችም የታጀበ ነበር ። ምንም እንኳን ድሬዳዋ ከተማዎች በአጋማሹ መጀመሪያ ላይ የፊት መስመራቸውን ለማጠናከር አብዱራህማን ሙባረክን እና ጋዲሳ መብራቴን ቀይረው ወደ ሜዳ ቢገቡም በተጋጣሚያቸው ከፍተኛ ብልጫ ተወስዶባቸው ነበር ። አፄዎቹ በፈጣን እንቅስቃሴዎች የድሬዳዋ ተከላካይ መስመርን በደንብ መፈትን የቻሉ ሲሆን በተለይም ከሁለቱ ክንፎች በሚነሱ ኳሶች ግቦችን ለማግኘት የሚያደርጓቸው ጥረቶች ውጤታማ አድርጓቸው ወጥተዋል ።
በ56ኛው ደቂቃ ላይ አምሳሉ ጥላሁን በረጅም የላከለትን ኳስ ያገኘው አጥቂው ኦኪኪ አፎላቢ የግብ ጠባቂውን ደረጄ አለሙን ስህተትም ተጠቅሞ ያስቆጠረው ግብ የአፄዎቹን መሪነት ወደ 2 ለ 0 ከፍ አድርጓል ። በፈጣን እንቅስቃሴያቸው የቀጠሉት ፋሲል ከተማዎች ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ሌላ ግብ አግኝተዋል ።
ሽመክት ጉግሳ በፍጥነት ወደ ሳጥን እየገባ ለነበረው አለምብርሀን ይግዛው ያቀበለው ኳስ መልሶ ሲደርሰው በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት 60ኛ ደቂቃ ላይ ለክለቡ 3ኛ ለራሱ ደግሞ 2ኛ ግብ አስቆጥሯል ።
ከአብዱራህማን እና ጋዲሳ በተጨማሪ የፊት መስመር ተጫዋቻቸውን ሙኽዲን ሙሳን ቀይረው ያስገቡት ድሬዳዋ ከተማዎች ለደቂቃዎች ያን ያህል የፋሲል ከተማን ተከላካዮች የፈተነ እንቅስቃሴ ለማድረግ ተቸግረው ቆይተው የነበረ ሲሆን 64ኛ ደቂቃ ላይ በአብዱራህማን ሙባረክ አማካኝነት ወደ ግብ ተመቶ በይድነቃቸው ኪዳኔ የተመለሰው ኳስ በአጋማሹ የመጀመሪያ ሙከራቸው ነበር ።
በ74ኛው ደቂቃ ላይ ከድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች የተነጠቀውን ኳስ ያገኘው በረከት ደስታ በቀኝ የሳጥኑ አቅጣጫ በኩል በመግባት አክርሮ የመታው ኳስ ከመረብ ላይ አርፏል ።
ድሬዳዋ ከተማዎች በ84ኛ ደቂቃ ላይ ጋዲሳ መብራቴ ባሻገረው የቅጣት ምት ኳስ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር ። የተሻገረውን የቅጣት ምት አብዱራህማን ሙባረክ ወደ ግብ ልኮት በይድነቃቸው ሲመለስ በድጋሚ አግኝቶ በግንባር ወደ ግብ ሞክሮት የነበረ ቢሆንም ኳሱ ግብ መሆን ሳይችል ቀርቷል ።
መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ አለሙ በቀኝ የሳጥኑ አቅጣጫ ወደ ግብ ክልል ይዞት የሄደውን ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ግብ ጠባቂው ደረጄ አለሙ አምክኖበታል ። በመጨረሻም ፋሲል ከተማ 4 ድሬዳዋ ከተማ 0 ሆኖ ጨዋታው ተጠናቋል ።

ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከተማ ነጥቡን 26 በማድረስ በጊዜያዊነት ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ድሬዳዋ ከተማ በነጥቡም ሆነ በደረጃው ላይ ለውጥ ሳያደርግ በ16 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።
በ16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ( አዳማ ከተማ ) ፋሲል ከተማ ሀድያ ሆሳዕናን ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ወላይታ ድቻን የሚገጥሙ ይሆናል ።
አስተያየት ይስጡ