በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የመጀመሪያ ቀን ውሎ ምሽት 1 ሰዓት ጀምሮ የተደረገው የአዳማ ከተማ እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ምንም ግብ ሳያስተናግድ 0 ለ 0 ተጠናቋል ።በ14ኛው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን 3 ለ 1 የረቱት አዳማ ከተማዎች በጨዋታው ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ በዮሴፍ ዮሐንስ ታደለ መንገሻ ተክተው የገቡ ሲሆን በሳምንቱ መከላከያን 3 ለ 2 ያሸነፉት ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በቋሚ አሰላለፉ ላይ በተመሳሳይ አንድ ለውጥ ብቻ ያደረጉ ሲሆን አብዱልባሲጥ ከማል በቃሉ ገነን ተክቶ በጨዋታው ላይ አንዲሰለፍ አድርገዋል ።በፈጣን እንቅስቃሴ የተጀመረው ጨዋታ በሁለቱም በኩል በፈጣን ወደ ግብ ለመድረስ ወይም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ፍላጎቶች የታዩበት ነበር ። በሀዋሳ ከተማ በኩል ኳሱን ይዘው በመጫወት እና ከፊት መስመር ለሚገኙት ተጫዋቾች በማድረስ የግብ አማራጮችን ለመፈለግ ጥረቶች የተደረጉ ሲሆን በአዳማ ከተማ በኩል ደግሞ በተለይም በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ላይ ረጃጅም ኳሶችችን በመጠቀም የሀዋሳ ከተማን የተከላካይ ክፍል ለመፈተን ጥረዋል ።
በጨዋታው የነበረው የመጀመሪያ ሙከራ በሀዋሳ ከተማ በኩል የተደረገ ሲሆን መስፍን ታፈሰ 6ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ በጀማል ጣሰው ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። በ21ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ በረጅም የደረሰውን ኳስ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ለማለፍ ሲሞክር ከሳጥን ውጪ ኳሱን ሊያስጥለው የወጣው ግብ ጠባቂው መሀመድ ሙንታሪ ኳሱን በእጁ በመንካቱ በቀጥታ የቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ። በተመሳሳይ ባሳለፍነው ሳምንት አዳማ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ ላይ ዳዋ ሆቴሳ በተመሳሳይ መልኩ ያገኘውን ኳስ ለማለፍ ሲሞክር የድሬዳዋ ከተማው ግብ ጠባቂ ፍሬው ጌታሁን በእጁ ነክቶ በቀይ ካርድ ከሜዳ መሰናበቱ ይታወሳል ።ከቀይ ካርዱ በኋላ ሀዋሳ ከተማዎች አብዱልባሲጥ ከማልን በማስወጣት ዳግም ተፈራን በግብ ጠባቂ ቦታ ላይ አስገብተዋል ። በ10 ተጫዋቾች ለመጫወት የተገደዱት ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ኋላ አፈግፍገው ለመጫወት የተገደዱ ሲሆን አዳማ ከተማዎች ደግሞ ኳሱን ይዘው በመጫወት የሀዋሳ ከተማን የኋላ መስመር ለማስከፈት ጥረቶችን አድርገዋል ።
መደበኛው የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት የፋሲል ተካልኝ ቡድን ቁልፉ ተጫዋች እና የቡድኑ አምበል ዳዋ ሆቴሳ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ የወጣ ሲሆን በምትኩም አቡበከር ወንድሙ ገብቷል ። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ምንም ግብ ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ አዳማ ከተማዎች ይበልጥ ጫና በማሳደር የጀመሩት ሲሆን ቶሎ ቶሎ ወደ ሀዋሳ ከተማ የግብ ክልል በመድረስ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል ።
- ማሰታውቂያ -
52ኛ ደቂቃ ላይ በአዳማ ከተማ በኩል ዘካርያስ ከበደ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ የቀረ ሲሆን ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ አብዲሳ ጀማል በተመሳሳይ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የላከው ኳስ በቀላሉ በዳግም ተፈራ ተይዟል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ሀዋሳ ከተማዎች በተለይም በፈጣን መልሶ ማጥቃቶች ወደ ፊት ሄደው የግብ ሙከራዎችን ለማግኘት የሚያደርጓቸው ጥረቶች ውጤታማ ያልነበሩ ሲሆን ተባረክ ሄፌሞ በ78ኛ ደቂቃ ላይ ካደረገው የግብ ሙከራ ውጪ ሌላ ሙከራ ማምረግ አልቻሉም ። በመጨረሻም የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 27 በማድረስ ለጥቂት ሰዓታት ተነጥቆ የነበረውን የሁለተኛ ደረጃን መልሶ ሲያገኝ አዳማ ከተማ ደግሞ ነጥቡን 21 ቢያደርስም የደረጃ ለውጥ ሳያደርግ 6ኛ ላይ ተቀምጧል ።
በ16ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ( አዳማ ከተማ ) አዳማ ከተማ ወልቂጤ ከተማን ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ጅማ አባጅፋርን የሚገጥሙ ይሆናል ።