“የየትኛውም ስታዲየም ግንባታና ባለቤትነት የፌዴራልና የክልል መንግስታት እንጂ እኔን አይመለከተኝም”
ሲል የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሃፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን እንደተናገሩት
” የየትኛውም ስታዲየም ባለቤት የክልልና የፌዴራል መንግስት እንጂ የፌዴሬሽኑ አይደለም በባለቤትነትም አልያዘም በዋናነት የፌዴራል መንግስቱ ሆኖ ክልልሎችን እያገዘ የስታዲየም ግንባታውን ያከናውናል” ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል።
በማህበራዊ ድረ ገጾች የሚተላለፉትን ትችቶች እንዳዩት የገለጹት ዋና ጸሃፊው “ተገቢና ትክክለኛውን መስመር የያዘ አይደለም የአፍሪካ ዋንጫውን የማጣሪያ ጨዋታ በአገራችን ማስተናገድ ባለመቻላችን እናዝናለን ካፍን ለማስፈቀድ የምንችለውን ሁሉ አድርገናል የፌዴሬሽናችን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ተወክለው ከመጡት ባለሙያ ጋር ሆነው የሚችሉትን የማሳመን ጥረት አድርገዋል የአማራ ክልላዊ መንግስት የካፍን መመዘኛ በተወሰነ መንገድ ለማሟላት ያደረገውን ጥረት በማየት ፌዴሬሽኑ የገምጋሚውን ባለሙያ የትራንስፖርት የሆቴልና የቀን አበል ሙሉ ወጪ በመቻል ፍቃድ ለማግኘት የሚችለውን አድርጓል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
እንደ ሀገር ሲታይ ከካፍ መመዘኛ አንጻር የስታዲየሞች ግንባታ ምን ሊያሟላ ይገባል የሚለውን ታሳቢ ሳይደረግ የሚገነቡ ስታዲየሞች መሆናቸው ከካፍ መስራች አገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በሜዳዋ ጨዋታውን እንዳታካሂድ መገደዷ እንደ ሀገር ትልቅ ሀዘን መሆኑን በመግለጽ የስፖርት ቤተሰቡ ቅሬታውን እያሰማ ነው።
ካፍ በሰጠው ማሳሰቢያ ኢትዮጵያ ተለዋጭ ሜዳዋን እስከ ነገ ግንቦት 4/2014 ድረስ እንድታሳውቅ ቀነ ገደብም መስጠቱ ታውቋል።
አስተያየት ይስጡ