በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ውሎ ሁለተኛ ጨዋታ ሰበታ ከተማን ከጅማ አባጅፋር አገናኝቶ ሰበታ ከተማ ከመመራት ተነስቶ 2 – 1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል ።
ሰበታ ከተማዎች በ22ኛው ሳምንት ጨዋታ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ሲጋሩ ከተጠቀሙት ምርጥ 11 አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ ዱሬሳ ሹቢሳን በቢስማርክ አፒያ ምትክ ወደ አሰላለፍ ሲመልሱ በጅማ አባጅፋር በኩል በሳምንቱ አርባምንጭ ከተማን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አራት ለውጦችን በማድረግ ወንድማገኝ ማርቆስ ፤ ሙሴ ከበላ ፤ ዳዊት እስጢፋኖስን እና መሀመድኑር ናስርን በያብስራ ሙሉጌታ ፤ አስጨናቂ ፀጋዬ ፤ እዮብ አለማየሁ እና ዳዊት ፍቃዱ ምትክ ጨዋታውን እንዲጀምሩ ማድረግ ችለዋል ።

ሁለቱ በወራጅ ቀጠናው ውስጥ የሚገኙ እና ለረጅም ሳምንታት በዚህ ቦታ የተቀመጡትን ክለቦች ያገናኘው ጨዋታ ከጅምሩ ፈጥን ያለ እንቅስቃሴ ያስመለከተን ሲሆን ገና በ7ኛው ደቂቃ ላይ በተቆጠረ ግብ ጅማ አባጅፋሮች መሪ መሆን ችለዋል ። ሙሀመድኑር ናስር ከሽመልስ ተገኝ የተላከለትን ኳስ በሁለት ተከላካዮች መሀል አምልጦ በመግባት ወደ ግብ የመታው ኳስ በለአለም ብርሀኑ መረብ ላይ አርፏል ።

ከግቡ በኋላ ሰበታ ከተማዎች ለፊት መስመር አጥቂዎቻቸው በሚጣሉ ኳሶች የጅማ አባጅፋርን የኋላ መስመር አልፈው የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል የመድረስ አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻለለ ሲሆን 20ኛው ደቂቃ ላይም አቻ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል ። በቅድሚያ ከግራ መስመር አቅጣጫ ላይ ከዱሬሳ ሹቢሳ የደረሰውን ኳስ ሳይጠቀም የቀረው ዴሪክ ንስባምቢ በድጋሚ ከተቃራኒ አቅጣጫ ከጌቱ ሀይለማርያም የተሻገረለትን ኳስ በግንባር በመግጨት የጅማ አባጅፋር መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል ።

ሰበታ ከተማዎች ጫናቸውን አጠናክረው በመቀጠል በተለይም ከመስመር በሚነሱ ኳሶች የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረቶችን ማድረግ ችለው ነበር ።
በጨዋታው 34ኛ ደቂቃ ላይ የሰበታ ከተማው ሳሙኤል ሳሊሶ ባጋጠመው ጉዳት ምክነያት በዘካርያስ ፍቅሬ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል ።

በ36ኛው ደቂቃ ላይ ንስባምቢ በቀኝ አቅጣጫ የተሰነጠቀለትን ኳስ አክርሮ ወደ ግብ መሞከር ቢችልም ኳሱ ለጥቂት ከግቡ አግዳሚ በላይ ወጥቷል ። በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ጅማ አባጅፋሮች በተወሰነ ወደ ፊት ለመድረስ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ችለው ነበር ።
ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሰበታ ከተማዎች በመጀመሪያ አጋማሽ ያሳዩትን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማስቀጠል የጀመሩት ሲሆን በአንፃሩ ጅማ አባጅፋሮች ወደ ኋላ አፈግፍገው በመጫወት አልፍ አልፎ በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ወደ ሰበታ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ ሲጥሩ ቆይተዋል ።
በ46ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ዘካርያስ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ይዞ የገባውን ኳስ በውሳኔ መዘግየች ምክንያት መጠቀም ሳይችል ሲቀር ኳሱን ያገኘው ጌቱ ሀይለማርያም ጠንከር አድርጎ ወደ ግብ የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል ።

በ52ኛው ደቂቃ ላይ መሀመድኑር ናስር ከአድናን ረሻድ ጋር ያደረጉት ድንቅ ቅብብል ሳጥን ውስጥ ገብቶ በመሀመድኑር ናስር ወደ ግብ ቢሞከርም ለአለም ብርሃኑ ወጥቶ ኳሱን አድኖታል ።
በ60ኛው ደቂቃ ላይ ሰበታ ከተማዎች መሪ የሆኑበትን ግብ ማግኘት ችለዋል ። ሽመልስ ተገኝ በዱሬሳ ሹቢሳ ላይ ሳጥን ውስጥ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ በማስቆጠር የጨዋታውን ውጤት ወደ 2 – 1 መቀየር ችሏል ።

ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ዴሪክ ንስባምቢ ከጌቱ ሀይለማርያም በረጅም የደረሰውን ኳስ ተቆጣጥሮ ለአብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ያመቻቸለትን ኳስ ሁለተኛውን ግብ ያስቆጠረው አብዱልሀፊዝ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ አድኖበታል ።

በቀጣዩቹ ደቂቃዎች ላይ ጅማ አባጅፋሮች ቀደም ብሎ ከነበራቸው እንቅስቃሴ በተሻለ ወደ ሰበታ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ያደረጉ ቢሆንም ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታውን አጠናቀዋል ።
ውጤቱን ተከትሎም ሰበታ ከተማ ነጥቡን 17 በማድረስ በነበረበት 16ኛ ደረጃ ሲቀጥል ጅማ አባጅፋርም በ19 ነጥብ በ15ኛ ደረጃ ላይ የሚቆይ ይሆናል ።

በ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 8 ( ሰኞ ) ጅማ አባጅፋር 10:00 ላይ የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲገጥም ከሁለት ቀናት በኋላ ግንቦት 8 ( ረቡዕ ) ረፋድ 4:00 ላይ ሰበታ ከተማ ወልቂጤ ከተማን የሚገጥም ይሆናል ።
አስተያየት ይስጡ