በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት 5 ጨዋታዎች በአ/አ እና በክልል ዛሬ(እሁድ) ተደርገዋል። በአ/አ ስታዲየም በተካሄደ 1 ጨዋታ መከላከያ ከ ፋሲል ከተማ ተጫውተው በእንግዳው ቡድን ፋሲል ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሜዳው ውጪ ድንቅ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው ፋሲል ከተማ ዛሬ ድል ማድረጉን ተከትሎ አሁንም ባለመሸነፍ ግስጋሴው ቀጥሏል። መከላከያ በበኩሉ አጀማመሩ ጥሩ ባይሆንም ያለፉትን 4ጨዋታዎች አለመሸነፉን ተከትሎ ወደ ቀድሞ አቋሙ የተመለሰ ቢመስልም ዛሬ ሽንፈት አጋጥሞታል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያውን ሙከራ ለማስተናገድ የፈጀበት 3ደቂቃዎች ብቻ ነበር። 3ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከተማው ኤርሚያስ ሀይሉ ከበረኛ ጋር ተገናኘቶ የሞከረው ኳስ ወደ ውጭ ወጥቶበታል። 14ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው መስፍን ኪዳኔ የሞከራት ኳስ ለግብ እጅግ የቀረበች ነበረች። 19ኛው እና 20ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከተማዎቹ አብዱረህማን ሙባሪክ እና ዳዊት እስጢፋኖስ ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው የነበረ ሲሆን ከነዚህ ሙከራዎች 1ደቂቃ በኋላ ከቀኝ መስመር ኤርሚያስ ሀይሉ ያሻገረለትን ኳስ የቀድሞው የቅ/ጊዮርጊስ ተጫዋች ራምኬል ሎክ ከመረብ በማሳረፍ ፋሲል ከተማዎችን (አፄዎችን) ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኋላ መከላከያዎች ውጤቱን ለመቀልበስ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ከመሸነፍ ማምለጥ አልቻሉም። 34ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው አማካይ በሀይሉ ግርማ ከርቀት የሞከራት ኳስ በግቡ አናት ላይ ወጥታለች፡፡ በጨዋታው በተደጋጋሚ ወደ ጎል በመድረሱ ና በኳስ ቀጥጥሩ ረገድ ፋሲሎች ጥሩ ነበሩ፡፡

ከመጀመሪያው ግማሽ ጋር ሲነፃፀር በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ በተስተዋለበት በዚህ ጨዋታ ፋሲል ከተማ ከሜዳው ውጪ እንደመጫወቱ ውጤቱን ለማስጠበቅ ጥንቃቄን የተላበሰ ጨዋታ ሲጫወት ተስተውሏል፡፡ በጨዋታው የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና አማካይ ዳዊት እስጢፋኖስ ጥሩ መንቀሳቀስ ሲችል
በ72ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከተማው አብድራህማን ሙባሪክ (ግሪዳው) ተቀይሮ የገባውን የመከላከያው አማካይ ማራኪ ወርቁን በመማታቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል፡፡ የአብድራህማን መውጣት ተከትሎ የቁጥር በብልጫውን የያዙት መከላከያዎች የአጥቂ ቁጥራቸውን ተጫዋች በመቀይር ለመጨመር ጥረት ቢያደርጉም ግብ ማስቆጠር አልቻሉም፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት መከላከያዎች ያገኙዋትን ቅጣት ምት አማካዩ ቴዎድሮስ ሞክሮ ሊጠቀምባት ሳይችል ጨዋታው በአፄዎቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ውጤቱንም ተከትሎ 1ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ፋሲል ከተማ ከመሪው ደደቢት በ7 ነጥቦች ርቆ 15ነጥቦችን ሰብስቦ 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችል መከላከያ በበኩሉ ከወራጅ ቀጠና በ2 ነጥቦች ብቻ ርቆ በ10 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ምንያምር ፀጋዬ ~መከላከያ
“በጨዋታው የአጥቂ ችግር እንዳለብን አሰተውለናል፡፡ በቁጥር ብልጫ ይዘንም ጎል ማስቆጠር አልቻልንም፡፡ የፋሲሉ ተጫዋች በቀይ ከወጣ በኃላ የቁጥር ብልጫችንን ተጠቅመን አጥቂ ብናስገባም ግብ ማስቆጠር አልቻልንም፡፡ በአንፃሩ ፋሲሎች በጎዶሎ አየተጫወቱ ተጠናክረው ነው ጨዋታውን የጨረሱት፡፡ በሁለተኛው ዙር የአጥቂ ችግራችንን ለመቅረፍ ተጫዋች አናስፈርማለን”
አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ~ፋሲል ከተማ
“በመጀመሪያው አጋማሽ በጨዋታው የተሻልን ነበር፡፡ ያገኘናቸውን የግብ ማግባት አጋጣሚዎች አልተጠቀምንም ሆኖም ባስቆጠርናት አንድ ጎል አሸነፈናል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ግሪዳው ከወጣ በኃላ የቁጥር ብልጫ ቢወሰድብንም ውጤቱን አስጠብቀን ወጥተናል፡፡ በውጤቱም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡”


አስተያየት ይስጡ