መነሻ ገጽ Oldies but Goodies  “ጊዮርጊስም ሆነ ሌላ ክለብ ለመግባት ብዬ የለበስኩትን ማልያ አልሸጥኩም፤ ክብር የሰጠኝን የቡና ደጋፊንም በዚህ መልኩ የማሳዝን ሰው አይደለሁም” “የካሳዬ ስብስብ በቡና የምስረታ ታሪክ ዳግም ተፈጥሯል ብዬ ለመናገር ይቸግረኛል” ሳዳት ጀማል (የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡናና የብ/ቡድንተጫዋች)
Oldies but Goodies ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣ

“ጊዮርጊስም ሆነ ሌላ ክለብ ለመግባት ብዬ የለበስኩትን ማልያ አልሸጥኩም፤ ክብር የሰጠኝን የቡና ደጋፊንም በዚህ መልኩ የማሳዝን ሰው አይደለሁም” “የካሳዬ ስብስብ በቡና የምስረታ ታሪክ ዳግም ተፈጥሯል ብዬ ለመናገር ይቸግረኛል” ሳዳት ጀማል (የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡናና የብ/ቡድንተጫዋች)

አጋራ
አጋራ


ትውልድ ሠፈሩ፦ ተወልጄ ያደኩት
ተክለኃይማኖት አካባቢ የሚገኘውና በተለምዶ
“ከረዩ” የሚባለው አካባቢ ነው፤የተወለድኩበት
ሰፈር የጠነከረ ማህበራዊ ግንኙነት ያለበት
መፈቃቀርና መከባበር ብሎም መተሳሰብ
ያለበት ሰፈር ነው፡፡ አልፎ አልፎ በተለይ
ቀደም ባሉት አመታት በወጣትነት እድሜ
ከሚፈጠር ባህሪ በቡድን ፀብ ስሙ ቢነሣም
ታላቅ ታናሽን የሚያከበርበት በፍቅር ለመጡ
ፍቅር በሆነችው ሠፈር ተክለኃይማኖት
ውስጥ ነው የተወለድኩት፡፡
ከመነሻው ግብ ጠባቂ ሆኖ ጀምሮ
ነው ግብ ጠባቂ ሆኖ ጫማውን የሰቀለው፡-
በእርግጥ በልጅነቴ ጥሩ እግር ኳስ ተጫዋችም
ነበርኩ፡፡ እንደውም አጠንክሬ ብይዘውና
ብገፋበት ከበርረኝነቱም በተጫዋችነቱም
ብዙ ርቀት መጓዝ እችል ነበር፡፡ ነገር ግን
በወቅቱ ከታላላቆቼ ጋር እጫወት ስለነበር
የሚጫወት እድሉን ስለማይሰጡኝና በረኛ
እንድንገባ ይፈልጉ ስለነበር በአብዛኛው ወደ
ግብ ጠባቂነቱ እያዘነበልኩ መጣሁ ከፍ ሲል
በረኝነቱንም ወደድኩት እንደገናም በዚህ
ገፋሁበት እድሉ ሰፊ ነው በማለት በግብ
ጠባቂነት ተስቤ ቀረሁ፤ በግብ ጠባቂነትም
ጫማዬን ሰቀልኩ፡፡

ግብ ጠባቂ እንዲሆን ከፍተኛ ተፅዕኖ
ስላሳደሩበት እንደ ሞዴል ስለሚያያቸው
ተጨዋቾች፡- ወደ አራት የሚጠጉ ተጨዋቾች
በተለያየ ጊዜ አሻራቸውንና ተፅዕኖአቸውን
አሳርፈውብኛል፤ ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስ፣ በለጠ
ወዳጄ፣ ታዲዮስ ጌታቸውና ፀጋአብ አሰገዶም
ተፅዕኖ ፈጥረውብኝ ግብ ጠባቂነትን እንድወድ
ያደረጉኝ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ ለእኔ በግብ
ጠባቂነት ሙያ ለማደግ የእነሱ አሻራ ከፍተኛ
ነው፡፡ እነዚህ ግብ ጠባቂዎች ከሞዴልነት
ባለፈ ለዚህች ሀገር የማይዘነጋ ትልቅ ውለታን
ጥለው ያለፉ የማከብራቸውም ናቸው፡፡

በሰው ስም አጭበርብሮ ስለገባበትና
በአንድ ኳስ እይታ ብቻ የመመረጥ እድል
ስላገኘበት መብራት ኃይል፡- ለመጀመሪያ ጊዜ
በክለብ ደረጃ የተያዝኩት መብራት ኃይል ሲ
ቡድን ውስጥ ነው፤ መብራት ሲ ለመግባት
ነገሮች እንደ አሁኑ ቀላል አልነበሩም፡፡
እድሉን ለማግኘት የሚመዘገበው ተጨዋች
ከአንድ ሺህ ሁለት መቶና ሶስት መቶ የበለጠ
ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 50ው ግብ ጠባቂ ነው፡፡
ለአንድና ሁለት በረኛ ከዚህ ሁሉ ሰው መካከል
ነው እንደ ወርቅ በእሳት ነጥረህ የምትወጣው፡
፡ ለእኔ በግብ ጠባቂነት ትልቅ ደረጃ መድረስ
የላቅ አስተዋፅኦ ካላቸው ባለውለተኛው ቻቻ
እንዲሁም ጎላ ሚካኤል እያለሁ ሽመልስ
(ሽሜ) አሁንም አሰልጣኝ ነው) በዋናነት
ይጠቀሳሉ፡፡ መብራት የተጨዋች ምርጫ
ሲያደርግ ቻቻ ይዞኝ ሄደ፤ ሌሎች ተጨዋቾችና
ተመዝግበዋል ፡፡ ሳየው መመረጥ እችላለሁ፤
ግን አልተመዘግብኩም፤ በዚህም ተቆጨሁ፡
፡ ወዲያው ግን አንድ ሃሣብ መጣልኝ፤
ተመዝግቦ በቀረ ተጨዋች ስም ለምን አቤት
ብዬ አልሞክርም የመጣው ይምጣ አልኩ፤
አሁን ስሙን ረሳሁት የአንድ ተጨዋች ስም
ሲጠራ “አቤት” የሚል ተጨዋች ሲጠፋ
እንደደነገጠና እንዳልሰማ ሰው አቤት አልኩ፤
እውነተኛው ተጨዋች መስያቸው ግባ ተባልኩ፡
፡ በወቅቱ ምርጫውን የሚያደርገው (ነፍሱን
ይማረውና) የመብራት ኃይል ባለውለተኛ
የሆነው አሰልጣኝ ቢረጋ ነበር፡፡ ቢረጋ እኔን
የመረጠኝ በአንድ ኳስ ነው፤አንድ ያጠረ ኳስን
አውጥቼ ሳድን አይቶ “በቃ አንተ ትችላለህ፤
ውጣ፤ እንደውም ምርጫው ሲያልቅ ተመለስ”
አለኝ፤ አላመንኩም፡፡ ምርጫው ከሳምንት
በላይ ስለወሰደ ቁርጤን ለማየት ወደ መብራት
ኃይል ስሄድ ስሜ ያውም በአንደኝነት ቦርድ
ላይ ተለጥፎ እየሁት፣ በጣም ተደሰትኩ፡፡
ብዙዎች በጣም ስለሚያደንቁትና

ከመብራት ስኬት ጋር ስሙ ተያይዞ
ስለሚነሳው አሰልጣኝ ቢረጋ፡- ከመብራት
ኃይል ስኬታማነትና ተከታታይ ድል

አሰልጣኝ ቢረጋ የላቀ አስተዋፅኦ አለው፡፡
ቢረጋ የመብራት ኃይል ምሶሶ የውጤታማነት
የጀርባ አጥንትም የነበረ ሰው ነው፡፡ የእሱ
መሞት አሁን የሚታየው በተተኪ ድርቅ
የተጠቃው መብራት ኃይል ለመፈጠሩ
ምክንያት ነው የሚል የግል እምነት አለኝ፡
፡ መብራት ኃይል ውስጥ የነበረው የቢረጋ
በተተኪዎች የማመን ህልም በመቀጨቱ
መብራት ከውጤት ጋር የከረረ ፀብ ውስጥ
እንዲወድቅ አድርጎታል የሚል እምነት አለኝ፡
፡ ቢረጋ በታዳጊ ቡድን ደረጃ የሚመለምላቸው
ተጨዋቾች ለክለቡ ብቻ ሣይሆን ለሌሎች
ክለቦችና ለሀገር ጭምር ትልቅ ውለታን የዋሉ
ናቸው፡፡ በቢረጋ ያልሰለጠነ ለስኬት ያልበቃ
ተጨዋች ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው፤ እነ
ኤልያስ ጁኸር፣ ያሬድ ከበደ፣ ጌታቸው ካሳ
(ቡቡ) ዘላለም ምስክር (ማንዴላ)፣ ዳንኤልና
አንዋር ሲራጅ (ትንሿ) የመሳሰሉ በአንድ
ወቅት እግር ኳሱ ላይ የፈነዱ ተጨዋቾችን
የመለመለው ቢረጋ ነው፡፡ ቢረጋ መሰረት
ያለው ሥራ የሠራ ግን ብዙም ያልተወራለት
እሱም ሲሞት የመብራት የተተኪዎችን
ማፍሪያ ማሽንም አብሮ የሞተበት ሁኔታ
ነው ያለው፡፡
ከመብራት ሲ ወደ ዋናው ቡድን ስላደገበት

አጋጣሚ፡- መብራት ሲ በአንድ ጨዋታ
ከተመረጥኩ በኋላ የቆየሆት ለአንድ አመት
ከግማሽ ያህል ነው፤ ወዲያውኑ ወደ ቢ እና
ወደ ዋናው ቡድን ነው ያደኩት፡፡ አንድ ጊዜ
የቢ ቡድን ግብ ጠባቂ ይጎዳል ቤንች ያለው
ላይ እምነት አልተጣለበትም መሰለኝ በወቅቱ
የቢ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት አቶ ታደለ
(ነፍስ ይማር) እኔን ከሲ ቡድን አስጠርተው
ለቢ ቡድን ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታ
ላይ ያሰልለፉኛል፡፡ ይህ ጨዋታ የእኔን ቀጣይ
ህይወት በር የከፈተ አጋጣሚ ነበር፡፡ ይሄንን
ጨዋታ ሲከታተል የነበረው የዋናው ቡድን
አሰልጣኝ ተስፋዬ ቱታ “ይሄንን ልጅ ወደ
ዋናው ቡድን አስመጡልኝ” ይላል፤ በዚህ
መሠረት ወደ ዋናው ቡድን አደኩ፡፡ በቢ
ቡድን ተይዤ ብዙ ሳልጫወት ነው ወደ
ዋናው ቡድን ያደኩት ከሲ በቀጥታ አደኩ
ማለቱ ይቀለኛል፡፡
ዋናው ቡድን ካደገ በኋላ ስለተፈጠረበት
የተለየ ስሜት፡– እንደ ሞዴል ስታያቸው፣
ስታደንቃቸው ከነበሩት ተጨዋች ጋር አብረህ
የምትጫወትበት እድል ማግኘት ምን አይነት
ስሜት እንደሚፈጥር መግለፅ ይከብደኛል፡
፡ እንደ ሞዴል የማያቸውና በማደንቃቸው
ከእነ በለጠ ወዳጆ፣ ቅጣው ሙሉ ጎን መቆም
ለእኔ ለማመን የሚከብድ የህልም ያህል ነበር
በወቅቱ፤ ለዚህ መብቃት ትልቅ ኩራትም
ክብርም ነው ለእነሱ ካለኝ ክብር፤ በሙሉ
አይንህ እንኳን የምታያቸው ተጨዋቾች
አይደለም፤ በወቅቱ ተጨዋች ለተጨዋች
የነበረው ክብር በጣም ልዩ ነበር፡፡ አሁን
በተጨዋቹ መካከል ካለው የአለመከባበር ችግር
ከምትሰማው አንፃር በጣም ታዝናለህ፡፡ በእኛ
ጊዜ ግን ሁሉም ሲኒዬሮችን እናከብራለን፡፡
የነበረው መከባበር በጣም ልዩ ነበር፡፡ ሲነዬር
ተጨዋቾች ሰርቪስ ውስጥ ሣይገቡ ወይም
ምግብ መመገቢያ ክፍል ውስጥ እነሱ ገብተው
ሳይቀመጡ እኛ ገብተን አንቀመጥም፤ እዛ
ድረስ ነው መከባበራችን ነው፡፡ ይሄን ያህል
መከባበር ባለበት ቡድን ውሰጥ ከታላላቅ
ተጨዋቾች ጋር አብረህ የምትጫወትበት
እድል ማግኘት ለእኔ የህልም ያህል እንጂ
እውነት አለመሰለኝም፤ እነ ኤልያስ ጁህር፣
ተስፋቲ፣ ሲሳይ ተሰማ፣ መስፍን (ፒስ)፣
ኤርሚያስ ተፈሪ አዋር ያሲን፣ አንዋር
ሲራጅ (ትንሿ) እነዚህን የመሳሰሉ የወቅቱ
ከዋክብትን ያሰባሰበ ቡድን አባል ስሆን ተልቅ
ኩራት ነው የተሰማኝ፡፡
በዚህ ደረጃ ያሞካሸው ክለብ ውሰጥ
መቆየት ሣይችል ቀርቶ ወደ ደብረብርሃን
ብርድልብስ ስለማምራቱ፡- ወደ መብራት
ዋናው ቡድን ማደጌና ከላይ በስም ከጠራኋቸው
ተጨዋቾች ጋር መካተቴ ቢያስደስተኝም
በክለቡ ቆይታዬ ልጋፋው የማልችለው ፈተና
ከፊቴ በመጋረጡ በክለቡ ውስጥ የፍላጎቴን
ያህል አልቆየሁም፡፡ በተለይ በግብ ጠባቂነት
ቦታ በለጠ ወዳጆን ቅጣው ሙሉን የመሳሰሉ
ተጨዋቾች መኖራቸ የመሰለፍ ጭላንጭል
ተስፋ እንኳን እንዳይኖረኝ አድርጓል፣ ከሁለቱ
ግብ ጠባቂዎች በተጨማሪ ፀጋዘአብ አስገዶም
ወደ ክለቡ መምጣቱ ነገሮችን የበለጠ
አከበደው፡፡ እነ በለጠ ወዳጆ ቅጣውና ፀጋዘአብ
ተአምር ካልተፈጠረ በስተቀር ቦታቸውን
በብቃታቸው አያስነኩም፡፡ እነሱን አስቀምጬ
መሰለፍ ስለማልችል በጊዜ ቦታዬን መፈለግና
መጫወት ራሴን ማሳየት ወደምችልበት ክለብ
መሄድ አለብኝ ብዬ መብራት ኃይልን ለቅቄ
ወደ ደብረብርሃን ብርድ ልብስ አመራሁ፡፡
እንዳሰብኩትም የደብረብርሃን ቆይታዬ ሌላ
ያልታሰበ እድል ይዞልኝ መጣ፡፡ በደብረብርሃን
የተዋጣለት ብቃት በማሳሣየቴ አሁን የልደታ
ክፍለ ከተማ አሰልጣኝ የሆነው ጋሻው አረዳ
መልምሎኝ አሁን አዳማን በሚያሰለጥነው
አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ ስር ጥሩ የሚባል
የጨዋታ ጊዜን አሳልፌያለሁ፡፡

ከአዲስ አበባ ፖሊስ ወደ ኒያላ ሲዘዋወር
“አሁን ገና ከሲኦል ወደ ገነት ገባሁ”
ስለማለቱ፦ እንዳልኩህ ለደብረብርሃን ስጫወት
አይተው አዲስ አበባ ፖሊሶች ወሰዱኝ፤
በአዲስ አበባ ፖሊስ የታወቁ ስም ያላቸው
ተጨዋች ባይኖሩም መጥፎ የጨዋታ ጊዜን
አላሳለፍኩም፡፡ ከክለቡ ጋር ብዙም ሳልጓዝ
ወደ ኒያላ ነው ያመራሁት፡፡ ኒያላ እንድፈርም
ደግሞ በጣም ያሳመነኝ አብርሃም መብራቱ
ነበር፡፡ በወቅቱ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢት.ቡና
በጣም ይፈልጉኝ ነበር፡፡ በሆነ አጋጣሚ
ቡናዎችን ሜክሲኮ የሚገኘው የክለቡ ጽ/ቤት
ሄጄ ከክለቡ ኃላፊዎች ጋር ተነጋገሬ ስወጣ
በወቅቱ የኒያላ አሰልጣኝ የነበረው አብርሃም
መብራቱ ምክትሉ መርሻ ሚደቅሳ ከደበበ
እንግዳ ወርቅ (ታዋቂ የስፖርት ቤተሰብ) ጋር
ሆነው ከቡናዎች ጋር ተነጋግሬ ስወጣ አገኘኝ፡
፡ ቡናና ጊዮርጊስ እንደጠየቁኝ ከቡናዎች ጋር
እየነጋገርኩ እንደሆነ ሲነግራቸው አብርናም
“ቡና ጊዮርጊስ መግባባትህ ትልቅ ነገር ነው፤
ነገር ግን መሰለፍ እችላለሁ ወይ? የሚለው
አስበሃዋል? ምክንያቱም ቡና አሊ ረዲ፣ ቅዱስ
ጊዮርጊስ ደግሞ ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስ ታዱን
የመሳሰሉ ግብ ጠባቂዎች አሏቸው፤ እነዚህን
አስቀምጠህ እንዴት ነው የምትሰለፈው?
ለምን እኔ ጋ መጥተህ አትጫወትም? ነገ
ትልቅ ደረጃ ትደርሳለህ፤ ስትሰለፍ ደግሞ
ለብ/ቡድን የመመረጥ እድሉንም ታገኛለህ”
ብሎ እዛው አሳመነኝ፤ እኔም ወዲያው እሺ
አልኩት፡፡ 10 ሺህ ብር የፊርማ ገንዘብ ሁሉ
አሰጥቶኝ ለኒያላ ፈረምኩ፤ ወደ ክለቡ ስገባ
አያያዛቸው፣ ምግቡ፣ የምናርፍበት ሆቴልና
ሁሉ ነገሩ ልዩ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር
ለንፅፅር አይቀርብም፡፡ በተለይ አዳማ “ፓላስ”
የሚባል ሆቴል ሲያሳርፉኝ አልጋው አንሶላው
ምግቡ ልዩ ግርምትን ፈጥሮብኝ ገና አሁን
ከሲኦል ወደገነት ገባሁ” ብያለሁ፡፡

ኒያላ እንደገባ በሳምንቱ በፖሊስ ተይዞ
በካቴና ታስሮ ሲወሰድ አሁን ደግሞ” ከገነት
ወደ ሲኦል ተመለስኩ” ስለማለቱ፡- ይሄ
አጋጣሚ በጣም የሚገርም ነው፤ ዝግጅት
ላይ ነበርን፤ ወንጂ ደርሶ መልስ ሮጠን በጣም
ደክሞኛል፡፡ መመገቢያ ክፍል ውሰጥ ዳቦውን
ማርማራታ እየቀባሁ ፓሬጅ ለመብላት
እየጠበኩ ባለበት ሰዓት ሁለት የማውቃቸው
ፖሊሶች በእጃቸው ካቴና ይዘው ሽጉጣቸውን
እያሳዩኝ ፈጠን ፈጠን እያሉ ወደ እኔ መጡ
ከዚያ በጣም ኮስተር ብለውና አፍጥጠውብኝ፡፡
“ተነስ ውጣ ትፈለጋለህ” አሉኝ ከትሬይንግ ነው
የመጣሁት በጣምም ርቦኛል ልብላ ስላቸው
“ቀልድን ትተህ ተነስ ውጣ፤ በህግ ቁጥጥር
ስር ነህ” ብለው ማደናበር ያዙ፡፡ ወዲያው
ከተቀመጥኩበት ጎትተው አንስተውኝ እንደ
ሌባ እጄን በካቴና ጠፍንገው እየገፈተሩ ውጭ
ወዳቆሙት የፖሊሰ መኪና ውስጥ ከተቱኝ፡
፡ በወቅቱ የነበረው ሁኔታ ተጨዋቹን ሁሉ
በጣም ስላስደነገጣቸው ሁሉም ፍጥጥ ብለው
ያዩኛል፡፡ በዚህን ጊዜ እኔም ከሲኦል ወደ ገነት
ገብቼ ነበር አሁን ደግሞ ከገነት ወደ ሲኦል
እየወረድኩ ነው፤ግን አይዟችሁ ወደ ገነት
እመለሳለሁ አልኳቸው፤ እጄን በካቴና ያሰሩት
በመኪና የጫኑኝ ቀደም ሲል የተጫወትኩበት
የአዲስ አበባ ፖሊስ አባሎች ናቸው፤
አንደኛው የፖሊስ የህዝብ ግንኙነት አንደኛው
የፖሊስ ኮሚሽነሩ ረዳት ነበሩ፡፡ ክለቡን ጥዬ
ወደ ኒያላ በመሄዴ በጣም በመበሳጨታቸው
ነው በካቴና አስረው በቀጥታ የወሰዱኝ ወደ
ፖሊስ ኮሚሽነሩ ቢሮ ነበር፡፡ እኔም ኮሚሽነሩ
ጋር እንደገባሁ ኮሚሽነሩን ውለታዬ በካቴና
መታሰር ነው? ስላቸው እሣቸው “አንተ እኮ
ወታደር ነህ” አሉኝ እኔም ወታደር ሳልሆን
እግር ኳስ ተጨዋች ሲቪል ነኝ ስላቸው
“ውሰዱና አስገቡት” አሉ፡፡ እሳቸው ይሄን
ያሉት ክለቡን እንደምጠቅም ስለሚያውቁና
ፈርቼ ሃሳቤን በመቀየር ለክለቡ እንድጫወት
ነበር፡፡ እኔ ግን የመጣው ይምጣ እንጂ ሃሳቤን
አልቀየርም አልኩ፤ ከዛሬ ነገ እፈታለሁ ስል
ሳምንት ያሀል እንደቀልድ ታሰርኩ፡፡ አባቴ
ተሯሩጦ ከእስር ቤት አስፈታኝ በፍርድ
ቤትም ነፃ የወጣሁበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡

ለእግር ኳስ ህይወቱ ትልቅ ውለታን
ስለዋሉለት ቤተሰቦቹ በተለይ ወላጅ አባቱ
ስላደረጉለት ነገር፡- ስለ አባቴ ማውራት
ተደርጎ እንዳይወስድብኝ እንጂ የእኔ አባት
ለእግር ኳስ ያለው ፍቅር ለእግር ኳስ
የከፈለውን በአንደበቴ መግለፅ በጣም ከባድ
ነው፡፡ ምክንያቱም እግር ኳስ ለአባቴ
ከመዝናኛ ባለፈ ህይወቱ ነው፡፡ አባቴ ለእግር
ኳሱ እንዳደረገው ውለታና እንደተመልካችነቱ
በስታዲየም ዙሪያ ያለው ድጋፍ፣ ሰው ለእሱ
ያለው ፍቅር ከፍ ያለ ቢሆንም በኢትዮጵያ
የእግር ኳስ ተመልካችነት ሙሉ እድሜውን
ከመገበሩ አንፃር አባቴ የከፈለው መስዋዕትነት
ያህል ክብር ተሰጥቶታል ማለት አልችልም፡፡
አባቴ ሙሉ ህይወቱን እኔ ከመፈጠሬ በፊት
ጀምሮ ቅ/ጊዮርጊስንና ብ/ቡድኑን ሲደግፍ ነው
የኖረው፡፡

በተለይ የቅዱስ ጊዮርጊስን ቡድን
አስመራ ድረስ ሄዶ በመደገፉ ሁሉ የሚታወቅ
ነው፡፡ ወደ እኔ ስትመጣ እኔ ለደረስኩበት
ደረጃ የአባቴ በአጠቃላይ የወላጆቼ ድጋፍ
በቃላት አይገለፅም፡፡በተለይ አባቴ መብራት
ኃይል ሲ ገብቼ ስታዲየም ስጫወት ካየኝ በኋላ
አመለካከቱ ብቻ ሣይሆን ድጋፉም በከፍተኛ
ሁኔታ ነው የተለወጠው፡፡ አባቴ ጥሩ ስሆን
ማሞገስ ብቻ ሳይሆን ስሳሳትም የሚያርመኝ
ሳጠፋ ከጥፋት የሚመልሰኝ ከአባትነትም
በላይ ከአሰለጠኑኝ አሰልጣኞች እኩል ቦታ
የምሰጠው ነው፡፡ ነፍሷን ይማረውና የምወዳት
እናቴም ወ/ሮ ራህመት ሽኩራ በእግር ኳስ
እድገቴና ለስኬታማነቴ ሚናዋ ትልቅ ነበር፡፡

በአንድ ወቅት አባቱ አቋሙ በወረደበትና
ጥሩ ባልሆነበት ጨዋታ በተቃሪኒው
ተጫዋቾቹን “በረኛ ብቻ ነው ያላቹሁ”
ስለማለታቸው፡- አንድ ጊዜ ኒያላ እያለን ነው
ትዝ ይለኛል ቡድናችን ይሸነፋል፤ ቡድኑ
መሸነፍ ብቻ ሳይሆን እኔ በእለቱ ጨዋታ ጥሩ
አልነበርኩም፡፡ በዚህም ሁሉም ሰው እኔኔ
ይወቅሰኛል፡፡ ጨዋታ ጨርሰን ሰርቪሳችን
ውስጥ ስንገባ አባቴ መጥቶ የተናገረው ነገር
እንኳን ሌላው እኔን ራሴን ንዴቴን አስረስቶ
አስቆኛል፡፡ አባቴ የአኔን ሞራል ከመጠበቅና
የሰውን አመለካከት ለመቀየር ወደ ሰርቪሳችን
ገብቶ ተናግሮ ሲወርድ ሁሉም በግርምት
ነው የሳቀው፡፡ ነገሩን የበለጠ አስቂኝና
አስገራሚ ያደርገው ደግሞ “በረኛ ብቻ ነው
ያላችሁ” ያለው አባቴ መሆኑ ሲታወቅ ነው፡
፡ አባቴ ይሄን ከተናገረ ከስንተኛው ቀን
በኋላ አሰልጣኛችን አብርሃም መብራቱና
ምክትሉ መርሻ ሚደቅሳ ማን እንደነገራቸው
አላውቅም ሰምተው “አንተ ባለፈው በረኛ ብቻ
ነው ያላችሁ ያሉት ለካ አባትህ ናቸው?”
ብለውኝ የሳቅነውን ሳቅ ዛሬም በግርምት
አስታውሰዋለሁ፡፡ አባቴ አማካሪዬ አሰልጣኜ
ብቻ ሣይሆን የስነ ልቦ ባለሞያዬ እንደሆነም
ይሄ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
በካሳዬ አራጌ ተመልምሎ ከኒያላ ወደ
ኢትዮጵያ ቡና ስላደረገው ዝውውር፡- በኒያላ
እግር ኳስ ክለብ ወርቃማ የሚባሉ ሶስት
የውጤት አመታትን ካሳለፍኩ በኋላ በጣም
ወደማደንቀውና ወደምወደው የካሳዬ አራጌው
ኢት.ቡና ነው ያመራሁት፤ በነገራችን ላይ
በኒያላ በየአመቱ ዋንጫ እያገኘሁ ታሪክ
እየሰራን ነው ያለፍነው፡፡

ከኒያላ ወደ ኢትዮጵያ
ቡና የተዘዋወርኩት በካሳዬ አራጌ ቀጥተኛ
ጥያቄነው፤ ካሳዬ አራጌ አብደላ ከሚባለው
የቡና ደጋፊ ጋር ሰፈሬ ድረስ በመምጣት
ለቡና ሊያስፈርመኝ እንደሚፈልግ ገልጾ ነው
ቡና የገባሁት፡፡ በወቅቱ ካሳዬ ሊያስፈርመኝ
እንደሚፈልግ ሲያናግረኝ የእሱ የአጨዋወት
ስታይል አዲስ እንደሆነና ለዚያ ደግሞ አንተ
ኳስ ስለምትችል በጣም ታስፈልገኛለህ ብሎኝ
1995 ዓ.ም ላይ በካሳዬ ጥያቄ ኢትዮጵያ
ቡናን ተቀላቀልኩ፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ኬክ ቆርሶ
ስላደረገለት ደማቅ አቀባበል፡- ወደ ኢትዮጵያ
ቡና ያደረኩት ዝውውር ሁሌም በውስጤ
አለ፤ በጣም የማደንቀው ካሳዬ ሰፈሬ ድረስ
መጥቶ አነጋግሮኝ በመፈረሜ ተደስቼ ሳላባራ
የክለቡ ደጋፊዎች ሶደሬ ግብዣ አድርገው
“የእንኳን ደህና መጣህ” ኬክ ቆርሰው ነው
የተቀበሉኝ፡፡ አለም፣ የትም እና አሁን ሞቷል
መሰለኝ ነፍሱን ይማረውና አዲሱ የሚባል
የጎማ ተራ ልጆች ለቡና ፈርሜ እንደጨረስኩ
በልዩ ዝግጅት ያደረጉልኝ ደማቅ አቀባበል
መቼም የማልዘነጋው ነው፤ በክለቡ በነበረኝ
ቆይታ ደጋፊው ስደክም እያበረታ፣ ስጠነክር
ይበልጥ እያጠነከረኝ ለስኬት እንድበቃ
አድርገውኛል፡፡ የደጋፊው የድጋፍ አሰጣጥ
ዛሬም የምትናፍቀው ነው፡፡ ሁሌም ስለዚህ
ደጋፊ ባሰብኩ ቁጥር በጣም የምቆጨው
ይሄንን ለትልቅ ስኬት ያበቃኝን ደጋፊ
የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ አሸናፊ አድርጌ
ሳልውጣና በድል ሳልክሰው መለያየቴ ነው፡
፡ አንድ ጊዜ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ አግኝተን
ብናስደስተውም የሊጉን ዋንጫ አሳክቼ
ባለመውጣቴ እቆጫለሁ፡፡ ምክንያቱም
ደጋፊው ከልብ ደጋፊ በመሆኑ ሻምፒዮናነት
ይገባዋል፡፡
በወቅቱ ስለነበረው የኢት.ቡና ስብስብ፡
በ2005 የነበረው የኢትዮጵያ ቡና የካሳዬ
ስብስብ በቡና የምስረታ ታሪክ ተፈጥሯል
ብዬ ለመናገር ይቸግረኛል፤እንደዚህም
እንደቀላል የምትገልፀው አይደለም፡፡ በጣም
ልዩና በታሪክ አጋጣሚ አንዴ ብቻ የሚፈጠር
ቡድን ነው ብል ይቀለኛል፡፡ አይተኸው
ከሆነው ቡደኑ ከጫፍ እስከ ጫፍ ኳስ
በሚችሉ ተጨዋቾች የተዋቀረ ነው፡፡ በካሳዬ
አሰልጣኝነት የተገነባውን ቡድን መግለፅ
ይቸግረኛል፡፡ እደግመዋለሁ፤በቡና ታሪክ
ተተክቷል ብሎ መናገር ይከብዳል፤ በጥሩ
ስብስብ ምርጥ 1995ትን አሳልፈናል፡፡
ለካሳዬ አራጌ ስላለው የተለየ ክብር፡
– ካሳዬ አራጌ ከባህሪው ጀምሮ የተለየ ነው
፤የሚሰራቸው ስራዎች በሙሉ ምክንያታዊ
ናቸው፤ ሜዳ ላይ ሊያጋጥሙህ የሚችሉ
ነገሮችን ትሬይኒንግ ላይ ጨርሰህ ነው
የምትመጣው፡፡ ጨዋታ የመቀየር ብቃቱ
ልዩ ነው፡፡ የአልጣኝነት ባህሪው ዲሞክራት
ነው፤ ለአንድ ቡድን የሚመች አሰልጣኝም
ነው፡፡ በተለይ እኔን ሰፈሬ ድረስ መጥቶ
ክብር ሰጥቶ ኢት.ቡና ውሰጥ አቅሜን
አውጥቼ እንድጫወት የፈጠረልኝ ከፍተኛ
በራስ የመተማመን ስሜት የተለየ ነበር፡፡
“እነጠቃለሁ ብለህ ያሰብከውን ከመስራት
ወደ ኋላ አትበል ተነጠቅና ይግባ” በማለት
በራስ የመተማመን አቅሜን አዳብሮ 95ትን
አንድ ስህተት ሣልሰራ ጨርሼ 96 ላይ ግን
ከዚያ ሲስተም ስንወጣ ስህተቶች ተፈጥረው
በእኔ ሥህተት የገቡ ኳሶች አሉ፤ በአጥሩ
ካሳዬ ትልቅ ራዕይ የነበረው ወጣ ያለ ሃሳብና
ምክንያታዊ የሆነ አሰልጣኝ ነበር ለእኔ፡፡
ኢት.ቡና እያለ ቅ/ጊዮርጊስ ለመግባት

ሲል ሆን ብሎ ጎል እንዲገባ አድርጓል
በሚል ስለመወቀሱ፡- ኢት.ቡና እያለሁ ስሜ
በዚህ ደረጃ በመነሣቱ በጣም አዝኛለሁ፤ያለ
ኃጢአቴ ያለ ስሜ ስም የተሰጠኝ ደግሞ 96
ላይ ለኮኮብ ተጨዋችነት ከእነ ደጉ ደበበ
ጋር በታጨሁበት ወቅት መሆኑ ነው፤ ቡና
ሻምፒዮን ቢሆን ትልቅ ክብር ነው የማገኘው፤
ይሄንን ያህል ደጋፊ ይሄንን የሚያህል ታላቅ
ክለብን የሚጎዳ ተግባር በመፈፀም የአዕምሮ
ሠላሜን ማጣት የምፈልግ ሰው አይደለሁም፡
፡(በጣም በስሜት ውስጥ ሆኖ) …ወላሂ…
ደግሜ ወላሂ… ነው… የምልህ… እናቴ
የገባችበት… ጉድጓድ ውስጥ… ልግባ…
ጊዮርጊስ ለመግባት ብዬ የሠራሁት ሥራ
የለም፤ ብዙ ሰዎች እንዲረዱኝ የምፈልገው
ጊዮርጊስም ሆነ ሌላ ክለብ ለመግባት
የለበስኩትን ማልያ አልሸጥም፤ ክብር
የሚሰጠኝን የቡና ደጋፊ በዚህ መልኩም
የማሳዝን ሰው አይደለሁም፡፡ ከወሬው
በፊትም ሆነ በኋላ ጊዮርጊሶች ይፈልጉኝ
ነበር፤ እንደተባለው ጊዮርጊስ ብገባ የተወራው
የፈጠራ ወሬ እውነት ተደርጎ ይወሰዳል
በዚህም የሚያከብረኝ ደጋፊ ያዝንብኛል ብዬ
የጊዮርጊስን ጥያቄዎች ትቼ ወደ መከላከያ
የገባሁት፡፡ ይሄን ያሀል ዋጋ የከፈልኩት
ንፁህ ሰለሆንኩ ደጋፊውን ስለማከብረው ለእኔ
ያላቸው ክብርም እንዳይጠፋ ከመስጋት ነው፤
ከዚህ ውጭ የተወራው እኔን የማይገልፅ ልብ
ወለድ ወሬ ነው፤ ለነገሩ ስሙን መጥራት
የማልፈልገው ተጫዋች ነው ይሄን ድርሰት
ደርሶ ያወራው፡፡ ወሬውን ፈጥሮ በማውራቱ
ከትዝብት ውጪ ያተረፈው ነገር አለ ለማለት
ይቸግረኛል፡፡

ባንኮች የሰጡትን 30 ሺህ ብር መልሶ
በ20 ሺህ ብር መከላከያ ስለገባበት አጋጣሚ፡-

እውነት ነው ከቡና ወጥቼ በ30 ሺህ የፊርማ
ብር ወደ ባንኮች ገብቼ ነበር፤ ባንክ እንድገባ
ደግሞ የቀድሞ የክለቡ ተጨዋችና የሥራ
አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ከጨዋታ ዘመኑ
በኋላ ደግሞ የቀድሞ ተጨዋቾችና ደጋፊዎች
ማህበርን በፕሬዚዳንትነት የሚመራው
ሸዋረጋ ደስታ ትልቅ ሚና ነበረው፡፡ ወደ ባንክ
ሳመራ በሰዓቱ አሰልጣኝ አልቀጠረም ነበር፤
በኋላ ላይ ገ/መድህን ኃይሌ አሰልጣኝ ሆኖ
ተሾመ፡፡ ገ/መድህን ከመጣ በኋላ መግባባት
ስላልቻልንና ትሬይኒንጉ ስላልተመቸኝ
በዚህ ሁኔታ መቀጠል የማይታሰብ ሆነ፡
፡ የሚሰጠን ልምምድ መሸከም ከምችለው
በላይ መሆኑ የባንክ ቆይታዬን አሳጥሮታል፡
፡ አሰልጣኙን በክለቡ ለመቆየት የምችልበት
ሁኔታ የለም በስምምነት ልቀቁኝ አልኩት፡፡
እሱም “የወሰድከውን 30 ሺህ ብር መልሰህ
መሄድ ትችላለህ አለኝ፡፡ በዚህ ምክንያት
አስራት ኃይሌ ወደሚያሰለጥነው መከላከያ
አመራሁ፤ ይሄን ያደረኩት አንደኛ የባንኮችን
ስልጠና መቋቋም ባለመቻሌ ሲሆን ሁለተኛው
ምክንያቴ ደሞ በውጤታማው አሰልጣኝ
አስራት ኃይሌ የመሰልጠን የዘመናት ጉጉቴን
ለማሳካት ስል 10 ሺህ ብር ቀንሼ በ20 ሺህ
ብር መከላከያ ልገባ ችያለሁ፡፡ በወቅቱ 20 ሺህ
ብር የመከላከያ ትልቁ ክፍያ ስለሆነ እንጂ
ከዚያም በላይ ይሰጡኝ ነበር፤ 10 ሺህ ብር
ቀንሼ መግባቴ እንደ ጉዳት ቢታይም ከአስራት
ጋር መስራቴ ግን ከገንዘብ በላይ ነበር ለእኔ፡፡
ሀገሪቱ ውስጥ ባሉት አሰልጣኞች በሙሉ
በመሰልጠን ሪከርድ ይዟል ስለመባሉ?
ያሰለጠኑኝን ዘርዝር ከምትለኝ ያላሰለጠኑኝን
ጥራ ብትለኝ ይቀለኛል፡፡ ምክንያቱም
ሁሉም አሰልጥነውኛል፤ እውቀታቸውን
አፍስሰወብኛል፡፡ ከመብራት ብነሣ ቢረጋ፣
ጋሽ ታደለ፣ ተስፋዬ ቱታ፣ ፍቃደ ሙለታ፣
ጋሽ ሐጎስ፣ የደብረብርሃኑ…..፤ አሰልጣኝ
ተገኔ፣ አብርሃም መብራቱ፣ መርሻ
ሚደቅሳ፣ አብርሃም ተ/ኃይማኖት፣ አስራት
ኃይሌ፣ ንጉሴና በለጠ፣ ጋሽ ከማል፣ በጣም
የማደንቀው ዘላለም (ሞውሪንሆ)፣ በብሔራዊ
ቡድን ደረጃ በአማካሪነት ቢሆንም መንግሥቱ
ወርቁ፣ ገዛኸኝ ማንያዘዋል፣ አበራ ሀብቴ፣
ዳኜ፣ ተስፋዬ ፈጠነ፣ ወርቁ ደርገባ፣ ስዩም
ከበደ፣ ተስፋዬ ገብሩ፣ ከማንም በላይ ትልቅ
ክብር የምሰጠው አሰልጣኝ ስዩም አባተ
ኧረ ምን የቀረ አለ? የስልጠና በረከቱን
እኔ ላይ ያላፈሰሰ አሰልጣኝ የለም፤ ሁሉም
ለእኔ እድገት የራሳቸው ሚና አለና ከልብ
አመሰግናቸዋለሁ፡፡
ከእነዚህ ሁሉ የሳዳት ምርጥ አሰልጣኝ

ማን ይሆን?

ማበላለጥ ከባድ ነው፤ ለሁሉም ክብር
አለኝ፤ የግድ መጥራት አለብህ ካልከኝ ግን
ከጃንሜዳ መርጦ ሀገር የመወከል ኃላፊነት
የሰጠኝን ጋሽ ሰውነት ቢሻውን አስበልጣለሁ፡
፡ ከእሱ ሌላ በዘመኑ ስኬታማ ለነበረው
ስዩም አባተ የተለየ ቦታ አለኝ፡፡ አሁን ደግሞ
በየጊዜው ራሱን እያስተማረ በጨዋነት
ሙያውን አስከብሮ የሚሰራው ሁሌም
በእጅ ላፕቶፑን ይዞ እውቀት በመግበየት
ምሳሌ የሚሆነው ውበቱ አባተን የተለየ ቦታ
ከምሰጣቸው አንዱ ነው፡፡
የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ ጨዋታ ብሎ
የሚጠራው፡- 1995 ላይ ቡና እያለሁ ቅዱስ
ጊዮርጊስን 1ለ0 ያሸነፍንበት የማታ ጨዋታ
የእኔ ምርጡ ጨዋታ ነው፡፡
ግብ ጠባቂ ነው ግብ እንዳይቆጠር
ከመከላከል በዘለለ በስሙ የተመዘገበ ግብ
አስቆጥሮ ይሆን፡- ቡና ገበያ እያለሁ ሁለት
ጎሎችን አስቆጥሬ በስሜ አስመዝግቤያለሁ፡
፡ በጥሎ ማለፍ ሻምፒዮና ከሐዋሳ ከተማ
ጋር ስንጫወት አንድ ፔናሊቲ አድኜ አንድ
አስቆጥሪያለሁ፤ ከዚህ ሌላ ከብርሃንና ሠላም
ጋር ስንጫወት በተመሳሳይ ፔናሊቲ አስቆጥሬ
የሁለት ጎል ባለቤት መሆን ችያለሁ፡፡
የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ ተጨዋች፡- የእኔ
የጨዋታ ዘመኔ ምርጥ ተጨዋች ብዬ አንድ
ሰው መጥራት ይቸግረኛል፤ ምክንያቱም
ብዙ ምርጦች ስለነበሩ። ከእነዚህ ውስጥ ግን
በግንባር ቀደምትነት የምጠራው ዬርዳኖስ
አባይን ሲሆን ከእሱ ሌላ ብዙ ያልተወራለት
ተስፋሁን ጋዲሣ (ኮል)፣ አንዋር ሲራጅ
(ትንሿ) ዳዊት እስጢፋኖስ የሀዋሳው ሙሉጌታ
ምህረት ከምርጦች ተርታ የምመድባቸው
ናቸው፡፡
እነማን በተከላካይነት ከፊቱ ሲቆሙ
ይመቸዋል ወይም ይቀለዋል፡- አንዳርጋቸው
ሰለሞንና ሳሙኤል ደምሴ (ኩኩሻ)፤ እነሱ
በተከላካይነት ከፊቴ ሲቆሙ ከፍተኛ በራስ
የመተማመን ስሜት ይሰማኛል፡፡ እነዚህ
ሁለት ተጨዋቾች ደፋሮች መሆናቸው
ኳሱን መቻላቸው ሁሉንም ነገር ቀላል
ያደርግልኛል፤ ከሁለቱ ሌላ አንድ ሆኖ የብዙ
ያህል የምትቆጥረው ብርሃኑ ፈየራ ሲኖር
ደግሞ የበለጠ ምቾት ይሰማኛል፡፡ ብርሃኑ
ጀግና ተጫዋች ነው፤ እሱ ከፊትህ ካለ
የክሮስ ኳሶችን ለማዳንና ለመሻማት እንኳን
አትወጣም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተከላካዮች
ትልቅ ቦታ የምሰጠው ለብርሃኑ ፈየራ ነው፡፡
አብሮት ባለመጫወቱ የሚቆጨው፡-
ሙሉጌታ ከበደ (ወለዬው) አብሬው ተጫውቼ
ድንቅ ችሎታውን በቅርበት ባይ በጣም እደሰት
ነበር፡፡
ያልታሰቡ ኳሶች ከሩቅ እየመታ ግብ
እያስቆጠረ ያስቸገረው ተጨዋች፡- በዚህ
በኩል ሳላህዲን ሰይድና ለብርሃንና ሠላም
ይጫወት የነበረው ሙለቀን ወልደዮሐንስ
በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ የሣላህዲን ሰይድ ኳሶች
ፈተና ናቸው፤ አይደለም ለእኔ ለአውሮፓ
ግብ ጠባቂዎችም መከራ ናቸው፡፡ ሙሉቀን
ወልደዮሐንስ በእግር ኳሱ ብዙ ያልተወራለት
ግን አቅም የነበረው በማትገምተው ሰዓት
ከሩቅ እየመታ ግብ በማስቆጠር የሚያሰቃይህ
ተጨዋች ነው፡፡
ወደ ስልጠናው አለም ስለመግባት ሃሣቡ፡
ከላይ እንደገለፅኩልህ በእኔ ላይ እውቀቱን፣
ልምድን ያላፈሰሰ አሰልጣኝ ባለመኖሩ
ከትልቅ ትምህርት ቤት የተመረኩ ያህል ነው
የሚሰማኝ፤ ምክንያቱም ከዚህ ሁሉ አሰልጣኝ
ብዙ የስልጠና እውቀት ገብይቻለሁ፡፡ ከዚህ
ውጪ በሀገር ውስጥ የተሰጡትን ስልጠናዎች
ሁሉ ወስጄ ራሴን በእውቀት አሳድጌያለሁ፡
፡ ግን ወደ ስልጠናው ዓለም ለመግባት
በሩ ተከርችሞ ተዘግቷል፡፡ ወደ ስልጠናው
ለመጠጋት የተለየ ስልትን ይጠይቃል፡፡
ልጠጋ ብትል የሚያስጠጋህ የለም፡፡ በሀገሪቱ
የበረኛ እጥረት አለ በውጪ በረኞች ተወረናል፡
፡ በረኞችን የሚያሰለጥኑት እውቀቱም
ልምዱም የሌላቸው ናቸው፡፡ በእነዚህ ሰዎች
እየሰለጠኑ ጥሩ ጥሩ በረኞችን እንመኛለን?
ይሄ ለእኔ ቀልድ ነው፡፡ በረኞችን ለማሰልጠን
የተለየ እውቀትና ልምድ ይጠይቃል፡፡ እኛ
ልምዱንም እውቀቱንም ይዘን አያሰጠጉንም፡፡
ሆሳዕና ላይ ስድስት ወር ሰርቼያለሁ፡፡ በዚህ
አጋጣሚ ዕድሉን የሰጠኝን ግርማ ታደሰ
አመሰግነዋለሁ፡፡ ግርማ ትልቅ ቦታ መድረስ
የሚችል ወጣት አሰልጣኝ ነው፡፡ ተጫውተው
ያለፉ ልምድም ዕውቀትም ላላቸው በሩ
ሲከፈት ወደ ስልጠናው እንመጣለን፡፡
ደካማውን እግር ኳስ ለመምራት ሰዎችን

ለስልጣን ሲሻሙና ምርጫው ይሄን ያህል
ወራት መፍጀቱን በተመለከተ፡-ይሄ በጣም
የሚያሳዝንና የስፖርት ቤተሰቡን ብቻ ሳይሆን
ጉዳዩን የሚታዘቡንም ሁሉ አንገት ያስደፋ
ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ለመምራት ይሄ
ሁሉ ትግል ያስፈልገዋል የሚል እምነት
የለኝም፡፡ እግር ኳሱን በሚጠቅሙ ነገሮች
መድከም የተሻለ ነገር ለመስራትና ከሌሎች
አገሮች እኩል ለመሆን ደፋ ቀና ለማለት
ሲገባን እኛ ገና ከስልጣን ሽሚያ አልወጣንም፡
፡ ይሄ ልብየሚሰብር ነገር ነው፡፡ እግር ኳሱ
ሰዎችን ብቻ በመቀያየር የሚያምን እንጂ
ያሉትን የሚያግዝ ማኅበረሰብ አይደለም
በብዙሪያው ያለው፡፡ እነ አቶ ጁነዲንን
ስራ ይሰራሉ ብለን ስልጣን ሰጥተናቸዋል፡
፡ ልምዱን፣ እውቀቱንና ባህሉን ባወቁበት
ሰዓት ግን እነሱን አውርደን ለሌላ አዲስ
ጀማሪ ለመስጠት ነው ግብግብ የተያያዘው፡
፡ እውነት ለመናገር በእኔ የግል እይታ
አቶ ጁነዲን ብቻውን ሆነ እንጂ ብዙ ሥራ
ሰርቷል፡፡ እግር ኳሱ የሚፈልገው ቅንነት
ያለው ከተንኮል የፀዳ እግር ኳስን ለመጥቀም
የመጣ ሰው ነው፡፡ በሱ የሥልጣን ዘመን ብዙ
ስልጠናዎች ተገኝተዋል፡፡ ብ/ቡድኑን ለረጅም
ጊዜ የሚዘጋጅበትንም እድልም ተፈጥሯል፡
፡ ድክመቶች ቢኖሩም ብዙ ለውጦች እንዳሉ
መካድ አያስፈልግም፡፡ ይሄንን ማስቀጠል
ይገባ ነበር፡፡ የሰው ለውጥ ብቻውን ጥቅሙ
አይታየኝም፡፡ አቶ ጁነዲን በተለይ የቀድሞው
ተጨዋቾችን ውለታ በማስታወስ እንዳሰበ
አውቃለሁ፡፡ እንዳልኩት ችግሮች ቢኖሩም
እንደ አቶ ጁነዲን አይነት ቅን ሰዎችን ነውእግር ኳሱ አጥብቆ የሚፈልገው፡፡
ከውጪ የሚያደንቀው አሰልጣኝ፡- ዚነዲን ዚዳን
ከውጪ ድጋፉን የሚሰጠው ቡድን፡ ሪያል ማድሪድ
ከውጪ የማደንቀው ተጨዋች፡- ካሪም ቤንዜማ
ከውጪ ታዋቂ የእግር ኳስ ሰዎች ባገኘው ብሎ የሚመኘው ፡- ዚነዲን ዚዳን
አሁን በምን ሙያ ላይ ይገኛል፡- እስከ አሁን እንኳን ይሄ ነው የምለው ቋሚ ሥራ ላይ አልነበርኩም፤ አሁን ግን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላላ ምክር ቤት እንደ ዜጋም ለሀገር ውለታ ሠርተህ አልፈሃል ፤ ይሄ ልጅ መቸገር የለበትም በሚል በየአመቱ የሐጂ ጉዞ ላይ ሥራ ያሰሩኛል፡፡

በደቡብ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሥራ እንድሰራ ኃይማኖታዊ ግዴታዬንም እንድወጣ ከፍተኛ እገዛ እያደረጉልኝ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ መሀመድ አሚን ጀማልን፣ ሼህ አልፋይዲን አሊን፣ ሼህ ዑመርን፣ የእስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚዎችና ሠራተኞች እንዲሁም የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ መሀመድ ሸሪፍ፣ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሀጂ ኑር ሁሴን፣ ዋና ፀሐፊው አዲስ አደም ላደረጉልኝ ድጋፍ እና እገዛ በዚህ አጋጣሚ በአላህ ስም አመሰግናቸዋለሁ፡፡
በመጨረሻ ቀረ የምትለው ካለ፡- የጨዋታ ዘመኔ ካለፈ በኋላ ነገሮች ፊታቸውን ባዞሩብኝ በዚያ ፈታኝ ሰዓት ድጋፍ ያደረጉልኝን መዘንጋት አልፈልግም፡፡ ህይወት ጀርባዋን በሰጠችኝ ሰዓት ከጎኔ የቆሙትን ሳልጠቅሳቸው ማለፍ ከማልፈልጋቸው ውስጥ በዋናነት ወላጅ አባቴና እናቴ ፣ የአሚን ጄኔራል ሆስፒታል ባለቤት ዶክተር መሀመድ፣ ሼህ መሀመድ አሚን ጀማል፣ ዶ/ር ሁሴን መሀመድ (ሀዋሳ)፣ ሼህ መሀመድ፣ የወደብ ሆቴል ባለቤት አቶ ክብረት ይግለጡ፣ የተሻለ ህይወት እንዲኖረኝ የሚተጋው አቶ ጌታዘሩ፣ በገንዘብም በሃሳብም በችግሬ ሰዓት አብሮ የቆመው የሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ ውበቱ አባተና ምክትሉ ሙሉጌታ ምህረት ከጨዋታ ዘመኔ ጀምሮ የአማካሪ ያህል የሚያግዘኝ ደበበ እንግዳወርቅ ሁላችሁም በደከምኩ ሰዓት አበርትታችሁኛል፤ ተስፋ በቆረጥኩ ሰዓት ተስፋ ሆናችሁኛልና በአላህ ስም የከበረ ምስጋናዬን ላቀርብላችሁ እፈልጋለሁ፤ አመሰግናለሁ፡፡

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣዜና እረፍትዜናዎች

የጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አጭር የህይወት ታሪክ

ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ከእናቱ ከወ/ሮ ጌጤ ገ/ስላሴ እና ከአባቱ ሀምሳ አለቃ ወልዴ...

ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣ

ሀትሪክ አሁንም ቀጠሮ ማክበር ስልጣኔ ነው በሚለው አቋሟ ጸንታለች

ቅዳሜ ጠዋት በቀጠሮ  ቀናችን  እርስዎ ጋዜጣዋን በእጅዎ ያስገቡ እንጂ አዳዲስና ያልተሰሙ መረጃዎችን...

ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣዜናዎች

ሀትሪክ አሁንም ቀጠሮ ማክበር ስልጣኔ ነው በሚለው አቋሟ ጸንታለች

ቅዳሜ ጠዋት በቀጠሮ  ቀናችን  እርስዎ ጋዜጣዋን በእጅዎ ያስገቡ እንጂ አዳዲስና ያልተሰሙ መረጃዎችን...