በ2010 መደረግ እና መጠናቀቅ እያለበት በተለያዩ ምክንያቶች እየተጎተተ እና እየተንከባለለ ወደ 2011 የተዛወረው የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ዛሬ በሚደረግ 1 የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ የሚቀጥሉ ይሆናል።
በሀዋሳ አርቲፊሻል ስታዲየም በሚደረገው በዚህ ውድድር 5 ቡድኖች የቀሩ ሲሆን ዛሬ በሩብ ፍጻሜው ኢንተርናሽናል አርቢትር ለሚ ንጉሴ በሚመራው ጨዋታ 9:00 ሲል ቅ/ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡና የሚጫወቱ ይሆናል። በተጠናቀቀው የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለቱ ቡድኖች ተገናኝተው በሁለቱም ጨዋታዎች ቅ/ጊዮርጊስ በተመሳሳይ 1-0 በሆነ ውጤት አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል። ቅ/ጊዮርጊስ ከ2006 ዓ.ም በኋላ ከአፍሪካ መድረክ ላለመራቅ እንዲሁም ሲዳማ ቡና ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ መድረክ ለመሳተፍ የዛሬውን ጨዋታ በማሸነፍ ጉዟቸውን ለማሳመር ከባድ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሁለቱ ቡድኖች አሸናፊ ማክሰኞ እለት በግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊውን ጅማ አባጅፋርን የሚገጥም ይሆናል። ጅማ አባጅፋር ለዚህ ግማሽ ፍጻሜ የበቃው ኢትዮ-ኤሌክትሪክን በፎርፌ በማሸነፍ እንደነበር ይታወሳል። በሌላ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ማክሰኞ ኢትዮጵያ ቡና ከመከላከያ የሚጫወቱ ይሆናል። የግማሽ ፍጻሜዎቹ አሸናፊ ሁለት ቡድኖች ደግሞ እሁድ መስከረም 20/2011 ዓ.ም ለፍጻሜ ተጫውተው አሸናፊው ቡድን በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን የሚወክል ይሆናል።
አስተያየት ይስጡ