የጨዋታ ዘገባ| ነብሮቹ በእዮብ በቃታ አስደናቂ የቅጣት ምት ግብ የመጀመሪያውን ዙር በድል አጠናቀዋል

 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር ጨዋታዎች ፍፃሜውን የሚያገኝበት የዚህ ሳምንት ጨዋታ በተጣለበት ቅጣት ጨዋታውን ሀዋሳ ላይ እያደረገ የሚገኘው ሀድያ ሆሳዕና ጅማ አባጅፋርን አስተናግዶ በእዮብ በቃታ ግሩም የቅጣት ምት ግብ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ የመጀመሪያውን ዙር በድል አጠናቋል።

ሀድያ ሆሳዕናዎች ከባለፈው ሳምንት አሰላለፋቸው የምንም ተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ስጊቡ። ጃማ አባጅፋሮች በበኩላቸው የአንድ ተጫዋች ላይ ለውጥ አድርገው ከድር ኬይረዲንን ይዘው ወደ ጨዋታ ገብተዋል።

በአባታቸው ህልፈተ ህይወት ምክንያት ባለፈው ሳምንት ቡድናቸውን ያልመሩት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በዛሬ ጨዋታ ቡድናቸውን እየመሩ ወደ ሜዳ ገብተዋል። ሳቢ ያልነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ ከወትሮው በተለየ ጥቂት ደጋፊዎች ብቻ ጨታውን ተመልክተዋል። ከሚባክኑ ቅብብሎች ውጭ አሰልቺ የነበረው ይህ አጋማሽ ወደ ግብ በመድረስ እና የግብ አጋጣሚዎችን በመፍጠር ሀድያ ሆሳዕናዎች የተሻሉ ነበሩ።18ኛው ደቂቃ ላይ ፒስማክ አፒያ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ያሻማውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ሱራፌል ዳንኤል በግንባሩ ገጭቶ አገባው ሲባል በአግዳሚው ለጥቂት የወጣችበት በሀድያ በኩል አስቆጪ አጋጣሚ ነበረች። በሂደት ብልጫ መውሰድ ባይችሉም ጅማዎች ኳስ ለመቆጣጠር ሲንቀሳቀሱ ይስተዋሉ ነበር። ሁለተኛ ጥቃታቸውን የሰነዘሩት ነብሮቹ 34ኛው ደቂቃ ፒስማክ አፒያ ጥሩ የሚባል ኳስ መሬት ለመሬት ቢመታም ሙንታሪ ይዞታል። ለሀድያ ሆሳዕናዎች በግምት 23ሜትር ርቀት ላይ ፌደራል አርቢትር እያሱ ፈንቴ ጥፋት ተስርቷል በሚል የቅጣት ቢሰጣቸውም። የጅማ አባ ጅፋር አንበል ኤልያስ አታሮ ቅጣት ምቱ ተገቢ አይደለም በሚል የዳኛን ውሳኔ ሲቃወም የቢጫ ካርድ የተመለከተ ሲሆን።

 

ተጫዋቾች እርስ በእርስ በፈጠሯቸው እሰጣ ገባ ጨዋታው ለተወሰኑ ደቂቃዎች ተቋርጦ እንደገና ሲጀምር። ያገኙትን የቅጣት ምት በአግባቡ የተጠቀሙት ሀድያ ሆሳዕናዎች 42ኛው ደቂቃ እዩብ በቃታ የተገኘችውን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ መትቶ ማራኪ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጓል።

 

ከግቧ መቆጠር በኋላ በዳኛ በደል ደርሶብናል በማለት ጅማ አባጅፋሮች በአንበሉ ኤልያስ አታሮ አማካኝነት ክስ አስመዝግበዋል። በዚህ አጋማሽ ብቸኛዋን መከራ ያደረጉት ጅማ አባጅፋሮች ብዙአረው እንደሻው ሳጥን ውስጥ በተረከዝ ወደ ኋላ መልሶለት ኤልያስ አህመድ ሞክሮ ኦቮር ኦቮኖ የተቆጣጠረበት ነበረች። የመጀመሪያው አጋማሽ በሀድያ ሆሳዕናዎች 1-0 መሪነት ለእረፍት ወጥተዋል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ መጠነኛ መነቃቃት ያደረጉት ሁለቱም ቡድኖች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ መድረስ ችለዋል። ነብሮቹ የሚያገኟቸውን ኳሶች ወደ ግራ መስመር በማገዳል ለፒስማክ አፒያለ በመጣል ወደ ተጋጣሚ ግብ ለመድረስ ሲሞክሩ፤ እንግዳዎቹ በኳስ ንክኪ ወደ ተጋጣሚ ግብ በመድረስ የግብ መፈለጊያ አማራጫቸውን አድርገዋል። ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚያቸው ሲደርሱ የነበሩት ሀድያዎች የፒስማክ አፒያ ተደጋጋሚ አጨዋታ ውጭ መሆን የሚላኩለትን ኳሶች ወደ ግብነት ለመቀየር ፈተና ውስጥ ገብተዋል። ኤርሚያስ ሀይሉ ሳጥን ውስጥ መትቶ አቮኖ ቢቆጣጠርበትም።75ኛው ደቂቃ ብዙዓየው እንዳሻው መሬት ለመሬት አክርሮ የምታው ሄኖክ አርፈጮ አወጣለው ሲል በእግሩ ነክቶት ለጥቂት አቮኖ ባይቆጣጠራት ጅማ አባጅፋሮች አቻ ሊሆኑ የሚችልበት አጋጣሚ ነበር።

ሀድያዎች ውጤታቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ወደኋላ በማፈግፈጋቸው ከተጋጣሚያቸው ጫና የበረታባቸው ሀድያዎች መላኩ ወልዴ መሬት ለሬት አክርሮ መትቶት ግብ ጠባቂው አቮኖ መቆጣጠር ሳይችል ቅርቶ ሲተፋው አጠገቡ የነበረው ብዙአየው እንደሻው ወደ ግብ መትቶ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው አግብቶታል ብለው ደስታቸውን ሊገልፁ ሲሉ የግራ ቋሚው መልሶበታል። በዚህ አጋማሽ ነብሮቹ አደረጉት ተብላ ልትጠቀስ የምትችለው የግብ አጋጣሚ በጨዋታው መገባደጃ ከአፈወርቅ የተነሳችው ኳስ አፒያንግ አግንቶ ከግራ ወደ ሳጥን ያቀበለው ኳስ ሱራፌል ጌታቸው አገባው ሲባል በአግባቡ ሳይመታው ቀርቶ ወደ ውጪ ወጥታበታለች። ጨዋታው በሀድያ ሆሳዕናዎች 1-0 ሲጠናቀቅ። ከተካታታይ ስድስት ጨዋታዎች ነጥብ መጣል በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል።

Hatricksport website Editor

Facebook

ሚሊዮን ኃይሌ

Hatricksport website Editor