“የጣና ሞገድ ደጋፊዎች የራሳቸው ቀለም ያላቸዉ ምርጥ ደጋፊዎች ናቸው ፤ {Yellow Wall} የሚል መጠሪያ ካላቸው የዶርቱሞንድ ደጋፊዎች ጋር ይመሳሰሉብኛል” አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ (ባህር ዳር ከነማ) ክፍል-2

ፋሲል፡- …አዎን በጣም ይለያሉ…በጣም የሚገርምህ እኔ እንደ እድል ሆኖ በጣም የተለዩ… ታሪክ ካላቸው…የደጋፊ ሀብታም ከሚባል ክለብ ነው ወደ ባህር ዳር የመጣሁት፤የደጋፊን ወሳኝነት…ጥቅሙንም ጠንቅቄ አውቃለሁ፤ ኖሬበታለሁም፡፡ ወደ ባህር ዳር ከነማ ስመጣ የገጠመኝም ይሄው ነው።የጣና ሞገድ ደጋፊዎችን የተለዩ የሚያደርጋቸው የራሣቸው የሆነ (Color) ቀለም አላቸው፤ክለባቸውን በጣም የሚወዱ…ለክለባቸው የሚሰስቱት ነገር የሌላቸው የእውነት ደጋፊዎች ናቸው፡፡ እኔ እነሱን ደጋፊ ብዬ ከመጥራት ይልቅ ለእኔ የቀኝ እጄን ያህል ለክለቡ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ናቸው ብዬ ነው መጥራት የምፈልገው፡፡ ለዚህም ነው ከስታዲየም ተደስተው እንጂ ተከፍተው እንዳይወጡ እንቅልፍ አጥቼ እየሠራሁ ያለሁት፡፡በተለይ ከጎሉ ጀርባ ያሉት ደጋፊዎች በጣም ያስገርሙኛል…እነሱን ስመለከት ምን እንደሚመጣብኝ ታውቃለህ?ከጎል ጀርባ የሚቀመጡት “Yellow wall’’ በሚል የሚጠሩት የዶርትሙንድ ደጋፊዎች ይመጡብኛል…፤…እነዚህ ደጋፊዎች የእነሱ አይነት የማይበርድ የድጋፍ መልክ ያላቸው ናቸው…፡፡

ሀትሪክ፡- …ባህር ዳር በሜዳው ይበልጥ አይበገሬ እንዲሆነ ያደረጉት እነሱ ናቸው በሚል ለውጤቱ ተጠቃሽ የሚያደርጋቸው በርካቶች ናቸው ፋሲልስ…?

ፋሲል፡- …ትክክል ነው…!ውለታቸው በቃላት የሚገለፅ አይደለም…፤…ግን አንድ ነገር ምን አለ መሰለህ በብዙ ደጋፊ መሃል ታጅበህ መጫወት ሁለት ነገሮች አሉት…አንደኛው በእንቅስቃሴ፣ በጨዋታው የተሻልክ ከሆንክ ወይም እንድትሆን የእነሱ ድጋፍ ትልቅ ጉልበት ይሆንሃል፤ ውጤቱም የጫወታ እንቅስቃሴውም በምትፈልገው መንገድ ካልሄድ ከባድ ጫና ውስጥ ለመውደቅ ትገደዳለህ፡፡ በሜዳችን ብቻ ሣይሆን ተጓዥ ደጋፊዎቻችን ፀሐይ፣ብርድ ሣይሉ አብረው ተጉዘው የሚሰጡን ድጋፍ ከስኬቱ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል…፡፡

ሀትሪክ፡- …ወደ ባህር ዳር ከነማ ስትመጣ ደጋፊው የነበረው አቀባበልና ስለ አንተ የነበራቸው እውቀት እንዴት ነበር…?
ፋሲል፡- …ያው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ከልጅነቴ ጀምሮ በክለብም፣በብሔራዊ ቡድን በተጨዋችነትም በአልጣኝነትም ያሳለፍኩ በመሆኑ ስሜም ታሪኬም እንግዳ አልሆነባቸውም፤ ከበቂ በላይ እውቀቱ እንዳላቸው ነው በተለያየ አጋጣሚ ያረጋገ ጥኩት፡፡ የነበራቸው አመለካከትና በተለይ አቀባበላቸውን በተመለከተ ባህር ዳርን ስረከብ የሰጡኝ ክብር አሀንም ድረስ ሳይሸራረፍ አብሮኝ እንዳለ ነው፡፡ በልምምድ ሜዳ፣ በጨዋታም፣ከጨዋታ ውጪም በአገኘሃቸው አጋጣሚ ለእኔ ክብርም፣ፍቅርም እንዳላቸው እስአከሁን ባለው ነገር ደስተኛ እንደሆኑ ይገልፁልኛል፡፡ ደስታቸውን የሚገልፁልኝን ያህል በቡድኑ ላይ ያላቸውን፣ቢሆን ብለው የሚመኙትን ከመቆርቆር ስሜት በመነጨ…የተሰማቸውን ስሜት ፍፁም ጨዋነትና በሰለጠነ መንገድ ይገልፁልኛልና…በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ እኔም በአፀፋው እነሱን ለማስደሰትና ተገቢውን ክብር ለመስጠት ከመልፋት ቦዝኜ አላውቅም፡፡ ግን እኔ በተፈጥሮዬ በጣም ቁጥብ ነኝ…ብዙ የመቀላቀል ልምዱ የለኝም…ስራዬን ከሰራሁ ወደ ማረፊያዬ ነው የምሄደው፤ይሄ ባይሆን ከዚህ በላይ መግለፅ ይቻል ነበር…፡፡

 

ሀትሪክ፡- …የፕሪሚየር ሊጉ አንደኛው ዙር ተጠናቋል…የደረጃ ሰንጠረዡም በተሻለ ቦታ ላይ እንዳለህ ያወራል…አንተስ በግልህ የእስከ አሁኑ የሙሉ አሰልጣኝነት ጉዞህን እንዴት ነው የመዘንከው…?

ፋሲል፡- …በእርግጥ በአንደኛው ዙር በጣም ብዙ ጠንካራ ጎኖች እንደነበሩን ውጤቱም ሚዲያውም ደጋፊውም የተናገረበት ሁኔታ ነው ያለው፤እኔም በግሌ ለክለቡ እንግዳ…እንደ መጀመሪያ የክለብ ቆይታዬ በአንደኛው ዙር በጣም የተደሰትኩባቸው፣ጥሩ ተስፋ ያየሁባቸው ነገሮችን ታዝቤያለሁ።እኔ ግን በዚህ ላይ ጊዜዬን ከማጥፋት ይልቅ በነበሩብን ደካማ ጎኖች ላይ ማተኮርን ነው የምመርጠው፤በመጀመሪያው ዙር ያየናቸውን ድክመቶች ለማረም ከተጨዋቾቼ ጋር በግልፅ ለመነጋገር ለማውራት ጥረት እያደረኩ ነው፡፡ ከሜዳችን ውጪም በሜዳችንም፣ በተከላካይ ክፍላችን ላይ ያፈጠጡ ድክመቶች እንደነበሩን ተረድቻለሁ…እነዚህን በመፈተሽና እንዴት መታረም ይችላሉ?በሚለው ላይ ነው መጠመድን ያስቀደምኩት።ምክንያቱም ክለቡን የሚጠቅመውም…ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያደርሰውም ይሄ ነው ብዬ ስለማምን በዚህ ላይ አነጣጥሬ እያየሁ ነው…፡፡

ሀትሪክ፡- …አንደኛውን ዙር ወይም 17 ጨዋታዎችን አድርገህ በ27 ነጥብ በ5ኛ ደረጃ ላይ ሆነህ ነው ያጠናቀከው…በተመዘገበው ውጤት እንደአሰልጣኝ ረክተሃል…?

ፋሲል፡- …የእርካታ ጥጉ ላይ ደርሻለሁ ባልልም…በአንደኛው ዙር ያየሁትና የምንገኝበት ደረጀ ብዙም የሚያስከፋኝ ነው ግን አልልህም፤ግን አንዳንዴ በተለይ ከሜዳ ውጪ በጣም ጥሩ አቋም አሳይተን ውጤት ይዘን ልንወጣ ሲገባ ውጤት ያጣንባቸው ጨዋታዎች ያስቆጩኛል፤ እነሱን ብናገኝ ኖሮ አሁን ከምንገኝበት በተሻለ ደረጃ ላይ እንገኝ ነበር ብዬ እንዳስብ ያደረጉኛል፡፡ ግን እንደ አጠቃላይ…ከስኳዴ፣ ከደሞዝ ክፍያ ችግርና…ከነበረብን ጉዳት አንፃር አሁን የምንገኘበት ደረጃ ከበቂ በላይ ነው ብዬ እንዳስብ ያደርገኛል፡፡ አምስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጣችን ብቻ ሳይሆን ከመሪዎቹ በሁለትና በሶስት ነጥብ የአንድ ጨዋታ ርቀት ላይ መቀመጣችን በራሱ ይሄንን እንድል ያደርገኛል፡፡ግን ይሄ የመጨረሻ ግባችን ባለመሆኑ በድክመቶቻችን ላይ ይበልጥ ሰርተን የተሻልን ለመሆን መጣራችንን እንቀጥላለን…፡፡

ሀትሪክ፡- …በተለይ ቡድንህ በሜዳው ያለመሸነፍ ሪከርድ አስመዝግቦ ነው ውድድሩ የተቋረጠው፤የዚህን ምስጢር ምንድነው ማለት ይቻላል?

ፋሲል፡- …የደጋፊው፣ የተጨዋቾቹና የአሰልጣኞች ስብስብ የጋራ ስራ ውጤት ነው መልሴ፤ ይሄ እንዲሳካ የደጋፊው፣የተጨዋቾች፣የአሰልጣኝ ቡድን አባላት የጋራ ርብሮበሽ አሳክቶታል ብዬ ነው የማምነው፡፡ አሠልጣኞች ከተጨዋቾች ጋር የተሻለ ነገር ሣይሠሩ፣ደጋፊው የቀኝ እጅ ያህል ሆኖ የሚታይ ድጋፍ ባይሰጥ ይሄንን ሪከርድ ማሳካት ከባድ ይሆን ነበር ብዬ እንዳምን ያደርገኛል፡፡ የባህር ዳር ከነማ ደጋፊ በሜዳው ሽንፈትን ያልለመደ ደጋፊ በመሆኑ ይሄንን በማስቀጠሌ እኔም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- …ፋሲል ሁለት መልክ ያለው ቡድን ነው የገነባው…አንደኛው በሜዳው የማይሸነፍ… ሁለተኛው የሜዳ ላይ አሸናፊነቱን ከሜዳ ውጭ የማያስቀጥል ቡድን ነው የገነባው…ብለው የሚያወርዱብህን ትችት ትቀበላለህ…?

ፋሲል፡- …ለማንኛውም አስተያየት ክብር አለኝ…ከዚህ አንፃር አስተያየቱን እቀበላለሁ…እግር ኳስ ደግሞ በባህሪው የሚለካው በውጤት ነው፤ሰዎች ለምን ተቹኝ ሣይሆን ከትችቱ ውስጥ መውሰድ ያለብኝን ቁም ነገር መውሰድን ነው የምመርጠው፡፡ እንዳልከው ከሜዳችን ውጪ ያለው ውጤትችን ደካማ በመሆኑ ለዚህ ትችት እንዳደረገን መካድ አልፈልግም፤ ምክንያት ለመደርደር ሳይሆን የእኛ ብቻ ሣይሆን ሌሎች ክለቦችም ከሜዳ ውጭ ያለው ታሪካቸው ከእኛ ብዙም የተለየ አይደለም፡፡ብዙዎቹ ከሜዳ ውጭ ለማሸነፍ ሲቸገሩ ነው የሚታየው፡፡ ብዙ ምክንያቶች መደርደር ቢቻልም እኔ ከሜዳ ውጭ ባለው ደካማ ውጤታችን ላይ ብዙ ስራ መስራትን ነው የማስቀድመው፡፡

ሀትሪክ፡- …ከትምህርቱ በዘለለስ ከሜዳ ውጭ ያለው ውጤትህ ደካማ የሆነበትን ምስጢር ደርስህበታል…?

ፋሲል፡- …ባህር ዳር መሥራት ከመጀመሬ በፊትም ከሜዳ ውጭ ያለው ታሪክ ደካማ የሚባል እንደ ነበር ደጋፊውም ተመልካቹም ያውቃል፤ምናልባት ይሄ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ያሳደረ ይመስለኛል፡፡ ይሄን ተፅዕኖ ከክለቡ በማራቅ በሜዳችን ላይ ያለው የአሸናፊነት ጥንካሬ ወይም መንፈስ ከሜዳችን ውጪም ተግባራዊ እንዲሆን ብዙ መስራት እንዳለብኝ ይሠማኛል፡፡በተለይ በደጋፊውም በተጨዋቾቹም ላይ ያለውን ይሄን ስነ ልቦና በስራ ለመስበር የሚቻለውን አደርጋለሁ፡፡ መጥፎውን በተሻለ ሪከርድ ለመቀየር በአዕምሮ፣በአካል ብቃትና በቴክኒክ ላይ የተሻለ ነገር በመስራት ታሪኩን ለመቀየር መጣሬን እቀጥላለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-ብዙውን ጊዜ በሜዳችሁ ስትጫወቱ በሠፊ ጎል እየመራህ በመጨረሻ ላይ ጎል እየተቆጠረብህ በጥጭንቅ አሸንፈህ የምትወጣበት አጋጣሚም ሌላው የቡድንህ ሰባራ ጎን ተደርጎ ይነሣብሃል፤ ይሄንንስ ልብ ብለሃል?

ፋሲል፡- ሁልጊዜም እንደምለው ደጋፊያችን ወደ ሜዳ የሚመጣው ለመደሰት ነው እንጂ ለጭንቀት አይደለምም፤ቡድኔ 1ለ0 በሆነ ጠባብ ውጤት ደጋፊውን ጭንቀት ውስጥ ከቶ ከሚያሸንፍ ከሁለትና ከሶስት ጎል በላይ አስቆጥሮ ቢያሸንፍ የበለጠ እደስታለሁ፡፡ ግን በተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ ይሄንን ደስታ ያለማስቀጠል ችግሮች ታይተውብናል፤ በቀላሉ ጎሎችን አስቆጥረን ጨዋታዎችንም ተቆጣጥረን ተጨማሪ ማስቆጠር አሊያም በሰፊ ጎል ያለንን ውጤት ማስጠበቅ ሲገባን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጎል እየተቆጠሩብን የመጨነቅ ነገር ታይቶብናል፡፡ የእስከአሁኑ የቡድናችንን ሂደትንም ስንገመግም ጎልተው ከታዩብን ህፀጾች አንደኛው ይሄ ነው፡፡ በዚህ በኩል ያለብንን መዘናጋትና የስነ ልቦና ችግር ለመፍታት ትኩረት ሰጥተን እንሠራለን፡፡ አሸናፊነታችን በአስተማማኝነት እንጂ በጭንቀት የታጀበ እንዳይሆን መስራት ይጠበቅብናል፤የትኛውም ድክመት ቢፈጠር የሚታረመው በስራና በጥረት ነውና በዚህ መልክ ለማረም እንጥራለን፡፡

ሀትሪክ፡-በአንደኛው ዙር በጣም የተበሳጨህበት ወይም ማግኘት የሚገባኝን ያላገኘሁበት ብለህ የምታነሣው ጨዋታ…?

ፋሲል፡- …ሀዲያ ላይ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ስንጫወት እንደነበረን የጨዋታ እንቅስቃሴና ብልጫ አንድ ነጥብ ብቻ አይገባንም ነበር፤ሶስት ነጥብ ይዘን መመለስ ነበረብን ብዬ የምቆጭበት ጨዋታ የመጀመሪያው እሱ ነው። ከፋሲል ከነማ ጋር ተጫውተን በተሸነፍንበት ጨዋታም ቢያንስ ነጥብ መጋራት ይገባን ነበር፡፡ እንደ ነበረን ጨዋታና እንደፈጠርናቸው የግብ እድሎች ቢያንስ ነጥብ መጋራት ይገባን ነበር እላለሁ፤ከጊዮርጊስ ጋርም ተመሳሳይ ስሜት ስሜት ነው ያለኝ፤ በጨዋታው ጥሩ ነበርን ጥሩ የጎል እድል እንደመፍጠራችን ቢያንስ ነጥብ መከፈል ነበረብን፤ ግን ጊዮርጊስ ትልቅ ቡድን ስለሆነ አጋጣሚውን ተጠቁሞ አሸንፎን ወጥቷል፡፡ እነዚህን ነው ባገኘሁት ውጤት ያልረካሁባቸው ጨዋታዎች ናቸው ብዬ በቁጭት የማነሣቸው፡፡

ሀትሪክ፡-የተደሰትኩበት ጨዋታ ነበር ብለህ ከፍ አድርገህ የምታነሣው ጨዋታስ….?

ፋሲል፡- የባህር ዳርን ቡድን በዋና አሰልጣኝነት ይዤ ባህርዳር ላይ ከመቐለ 70 አንደርታ ጋር የመጀመሪያ ጨዋታችንን አድርገን ያሸነፍንበት ጨዋታን ነው የማስበልጠው፡፡ ምክንያቱም ይሄ ጨዋታ በፋሲል የመጀመሪያ ጨዋታዬ ከመሆኑ…ቀጣይ ጉዞዬን የሚያመላክት ሚና ያለው ስለነበር ያንን ጨዋታ በድል በማጠናቀቄ በጣም ያስደስተኝ እሱ ነው፡፡ መቐለ 70 አንደርታ የወቅቱ ሻምፒዮን ከመሆኑ፣የጥሩ አሰልጣኝ፣ ተጨዋቾች ባለቤት ከመሆኑ አንፃር ድሉ የተለየ ትርጉም ሰጥቶኛል፡፡

ሀትሪክ፡-የአንደኛው ዙር የአንተ ምርጡና ጥሩ ቡድን ማን ነበር ብልህ ምን ትመልስልኛለህ…?

ፋሲል፡- የሁሉንም ቡድን ጨዋታዎች እየተዟዟርኩ ስላላየሁ ምላሼ ምን ያህል ሙሉ እንደሚሆን ባለውቅም ከእኔ ጋር ባደረጉት ጨዋታ በመነሣት ስመልስ የስብስቡን ያህል ውጠት አግኝቷል ባልልም አዳማ ከተማ ጠንካራ ነበር፤ ቅድስ ጊዮርጊስም በጣም የተሟላ ቡድን ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ፋሲል ከነማ ደግሞ ካለፈው አመት በተለየ መልኩ ዋንጫዎችን ለመውሰድ እንደተዘጋጀ ምልክት ይታይበታል፡፡ የተጫዋቾቹ የማሸነፍ ፍላጎት…የደጋፊዎች ስሜትም የሚያሳብቀውም ይሄንን ነው፡፡ መቐለ 70 እንደርታም ያለፈው አመት ክብሩን የማስቀጠል አቋሙ አብሮት ያለ ተፎካካሪ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፡፡ የእኔ ቡድንም በራሴ አንደበት እንዳልመሰክር ብዬ ነው እንጂ…(ሣቅ)…

ሀትሪክ፡-ከተጨዋቾችስ ይበልጥ ጎልቶ የወጣ ምርጥ ተጨዋች ነው የምትለውስ…?

ፋሲል፡-… ለእኔ እንደ አንድ አሰልጣኝ ሙጂብ ቃሲም በጣም አስገርሞኛል፤ አንድ አሰልጣኝ ወይም አንድ ክለብ ከአንድ አጥቂ የሚፈልገውን ያለስስት በብቃት እየሰጠ ነው።ቡድኑ በእሱ ጎል እያሸነፈ እየወጣ ነው በስሙ 24 ጎሎችን አስቆጥሯል ከዚህ አንፃር ለእኔ አገራሚው ሰው እሱ ነው። የእኔ ተጨዋች የሆነው ፍፁም ደግሞ እንዲሁ የዘንድሮ ክስተት ነው፡፡ ፍፁም ለአጥቂዎች ለጎል የሚሆን የተመቻቸ ኳስ ከመስጠት ስራው ባለፈ ከመሃል ሜዳ እየተነሣ በስሙ ዘጠኝ ጎል አስቆጥሮ ለግብ አግቢነት እየተፎካከረ ነው፤ይሄ የጥሩነቱ ማሳያ ነው፡፡ የኢት.ቡናው አቡበከር ከጉዳቱ ጋር እየታገለ ለቡድኑ ያለውን ወሳኝነት በብቃቱ እያሳየ ነውና እሱም ከፍ ብለው ከታዩኝ አንዱ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ምናልባት ሊጉ የሚቀጥል ከሆነ በሁለተኛው ዙር ምንድነው ግብህ…?

ፋሲል፡-በህይወቴ ተስፋ የማደረግ ሰው ነኝ…በእርግጠኝነት አምላክ ምህረትን ለአለም አውርዶ ሁሉም ውድድርች ይቀጥላሉ ብዬ ነው ተስፋ የማደርገው፤ አሁን የምንገኝበት ደረጃ በጣም ጥሩ ነው… መሪዎቹን በቅርብ ርቀት እያየናቸው ነው፤ ውድድሩ ሲቀጥል ከሚቀጥሉት 4 ጨዋታዎችም 3ቱን በሜዳችን ነው የምናደርገው፤ በሜዳችን ስንጫወት ጥሩ ሪከርድ አለን፤ከዚህ በመነሣት ዙር በአንደኛው ዙር የነበረውን ይበልጥ የማሳደግ ሃሣቡ ነው ያለን፤ግን ከሁሉም ነገር በፊት ሀገራችን ፣ህዝባችን እንዲሁም አለማችን ሠላምና ጤናማ እንድትሆን አብዝተን መፀለይ አለብን፡፡

ሀትሪክ፡- …ፋሲል አሁን ሙሉ አሰልጣኝ ተብሎ የሚጠራበት ደረጃ ላይ ደርሷል…?

ፋሲል፡ …ሳቅ…እሱን እናንተን የሚዲያ ሰዎችን ነው የሚያስጨንቀው እንጂ እኔን ብዙም አያስጨነቀኝም፤ እኔ ገና እንደሆንኩና ከፊቱ ብዙ ስራ የሚጠብቀው ትንሽ አሰልጣኝ እንደሆንኩ ብቻ ነው የማውቀው። ታላላቆችን ብቻ ሣይሆን ሁሉንም አሰልጣኞች የማከብር፣ ከሁሉም አሰልጣኞች ለመ ማር የተዘጋጀሁ ሰው ነኝ፡፡ አሰልጣኝነት ማለት ኃላፊነት ነው፤ ከሜዳ ላይ ልምምድ ከማሰራት ውጪ የሰዎችን አዕምሮ ለአንድ አላማ አስተባብሮ መምራት ነውና ለዚህ የሚሆን ስንቅ በውስጤ ያለ ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡-… የአለም እግር ኳስ የት ደርሷል…በእድገታቸው በስኬታቸው ዙሪያ ብዙ ሲዘገብ…የእኛ ሀገር ሚዲያ ግን ባለመታደሉ እኛ እየዘገብን ያለነው እከሌ የተባለው ቡድን የ4 ወር…የሶስት ወር የተጨወቾችን ደሞዝ አልከፈለም፤ ተጨዋቾቹ ደሞዝ ስላልተከፈላቸው ልምምድ አቁሙ፤ የ2 ወር ተከፍሏቸው ወይም ቃል ተገብቶላቸው በድርድር ልምምድ ጀመሩ፤ የሚል ዘገባን ከስኬት ይልቅ እንዲዘገብ የተፈረደብን ይመስላል …ይሄን እንደ አሰልጣኝ እንዴት ነው የታዘብከውን…?

ፋሲል፡- መሆን ያለበት እንዳልከውና ብዙውን ጊዜ ተሰጥቶቶና መዘገብ ያለበት ስለዕድገቱ፣ ስለቴክኒክና ታክቲክ፣ ስለ ብቃታቸው እንጂ የደሞዝ አለመክፈል ጉዳይ መሆን አልነበረበትም፤ይሄ እግር ኳሳችን ገና ታች እንዳለ ጠቋሚ ነው፤ ባለፉት ጊዜያት ክለቦች አካባቢ የምትሰማው እንደዚህ አይነት አስደንጋጭ ብቻ ሣይሆን በእቅድና በፕላን እንደማንመራ የሚያሳይ ዜና ነው ስንሰማ የቆየነው፤ይሄ መሆኑ ትልቅ አደጋ አለው። ሁሉም ትኩረት ሰጥቶበት የየአመት እቅድን አውጥቶ የቤት ሥራቸውን ጨርሰው በሚቀጥለው አመት በአዲስ መንፈስ ተዘጋጅተው መምጣት እንዳለባቸው ነው መምከር የምፈልገው፡፡

ሀትሪክ፡-የአንተ ክለብ ባህርዳርም ለተጨዋቾቹ ደሞዝ ባለመክፈል ስማቸው ከተነሱ ክለቦች አንዱ ነው ይሄ ችግር በስራህ፣ በውጤትህ ላይ የሚያመጣው ችግር አለ?

ፋሲል፡- … እንዴት አይኖርም…?…ይኖራል፤ አንተ አንድን ተጨዋች የሚገባውን ሳታደርግለት እንዴት ከእሱ ብዙ ትጠብቃለህ?ደሞዝን ተወውና ሌሎች ማበረታቻ /ኢንሴንቲቮች/ እኮ በሌላው አለም እዚህም የሚሰጠው የተጨዋቹን ሞራል ከፍ ለማድረግ የተሻለ ነገር እንዲያስመዘግብ ለማበረ ታታት ነው፤በዚህን ጊዜ ተጨዋቹ አቅምን አውጥቶ ለመጫወት የሚሰስተው ነገር አይኖርም፡፡ ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒ ማበረታቻውን ተወውና ዋናውን ደሞዝ ሳትሰጠው ስትቀር የተጫዋቹ አዕምሮ ከቴክኒክና ታክቲኩ፣ከጨዋታው ይልቅ “ደሞዝ ይከፈለን ይሆን? አይከፈሉንም?” በሚለው ጥያቄ ጭንቅላቱ እንዲወጠርና በሙሉ አዕምሮው እንዳ ይጫወት እንደሚያደርገው ማድበስበስ አያስፈልግም፡፡ እግር ኳስ ከመዝናኛነት ባለፈ የሀገርን ስምና ባንዲራ ከፍ የሚያደርግ ቢሆንም ከዚህ ከፍ ሲልም መተደደሪያ የራስንም የቤተሰብንም ህይወት የሚመራበት በመሆኑ ትርጉሙ ብዙ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ስለዚህ የአንተ ቡድንም ከዚህ ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ስሙ የተነሣ ክለብ ነውና ይሄ ችግር በውጤትህ በተጨዋቾችህ ስሜት ላይ ችግር ፈጥሯል እያልክ ነው?

ፋሲል፡- የእኔ ተጨዋቾች ከሌላ ፕላኔት የመጡ አይደሉም፤ የሌሎች አዕምሮ እንደሚጎዳው የመ ጫወት ፍላጎት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያደርሰው ሁሉ እነሱም ላይ ይደርሳል፡፡ የእኔ ቡድንም በዚህም ውስጥ ሆኖ ነው አሁን የሚገኝበት ደረጃ ላይ የደረ ሰው፡፡ አንተ በጥያቄህ እንዳነሳኸው ክለባችን ላይ ይሄ ነበር፡፡ የክለባችን የቦርድ ኃላፊዎች ችግሩን ለማ ፋት ጠንካራ የፋይናንስ አቅም ለመፍጠር የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ጥረቶችን እያደረጉ እንደሆነ አው ቃለሁ፤ ሄ መልካም ነገር ነው፡፡ እግር ኳስ የአዕምሮ ውጤት በመሆኑ በእግር ኳሳችን ውስጥ ይሄን መሰል ችግር መወገድ አለበት፤ በዚህ አጋጣሚ ተጨዋቾቼ ችግሮቻቸውን፣ ቅሬታቸውን ወደ ጎን አድርገው ለክለቡ ውጤትና ክብር ቅድሚያ ሰጥተው አሁን የተመዘገበውን ውጤት እንዲመዘገብ ላደረጉት ጥረት ከልብ አመሰግናቸዋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-ጥያቄዬን ጨረስኩ ከመለያየታችን በፊት ከባህርዳር ጋር ያለህ ኮንትራት በዚህ አመት ያልቃል…ከዚያስ…?

ፋሲል፡- እስኪ ጊዜው ይድረስ…ከዚያ በኋላ ከክ ለቡ ጋር የምንነጋገር ነው የሚሆነው፡፡

ክፍል አንድን ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ 👇

https://www.hatricksport.net/የጣና-ሞገድ-ደጋፊዎች-የራሳቸው-ቀለም-ያ/

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.