“የኢትዮጵያ ቡናን ማልያ ለብሼ እንድጫወት ትልቁ ምክንያት የሆነኝ በቃላት የማይገለፀው ደጋፊው ነው”ወንድሜነህ ደረጀ (ኢት.ቡና) ክፍል 1

 

“ኢት.ቡና ካሳዬን ካገኘ በኋላ የሆነ መልክ
እንደያዘ ይሰማኛል”
“ክለቦች የቡናን ጨዋታ ለማበላሸት ሳይሆን በራሳቸው
መንገድ ለማሸነፍ ቢመጡ እግር ኳሱ ይጠቀማል”
ወንድሜነህ ደረጀ (ኢት.ቡና)

የዛሬው እንግዳዬ ፍፁም የተለየ ነው፤ በትናንት ማንነቱ በአስተዳደጉ ከመሸማቀቅ፣ያልሆነው ሆኖ በሚዲያ
ላይ ከመቅረብ ይልቅ ትክክለኛ ማንነቱን በኩራት መናገሩ የበለጠ እንዳከብረው፣ እንዳደንቀው አድርጎኛል፡፡
በተለይ “እናቴ ጠላ ሸጣ መከራ አይታ ነው ያሳደገችኝ” የሚለው ቃል ከአንደበቱ በተደጋጋሚ የሚወጣው በሀፍረት
በመሸማቀቅ ሣይሆን በኩራት መሆኑ የዛሬው እንግዳዬን የኢትዮጵያ ቡና ቁልፍ ተጨዋችና የካሰዬ ፍልስፍና ዋና ቀያሽ
የሆነው ወድሜነህ ደረጀ የችሎታው ያህል በአዕምሮውም እጅግ የበሰለ ተጨዋች ለመሆኑ ከእሱ ጋር በነበረኝ ወደ አንድ ሰዓት የተጠጋ ቃለ ምልልስ በቀላሉ እንድረዳ አድርጎኛል፡፡
የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ የካሳዬ አራጌ የአዲሱ ፍልስፍና ዋነኛው መነሻ ከሆኑት ተጨዋቹ አንዱ የሆነውን ወንድሜነህ ደረጀን በግል ህይወቱ፣ ሁሌም ከአፉ ጠፍተው ስለማያውቁትና በወፍራሙ ስለሚያመሰግቸው እናቱ፣ አሳዛኝ ግን አስተማሪ ስለሆነው አስተዳደጉና የቤተሰቡ ሁኔታ፣ስለ ኢት.ቡና ስብስብና
ካሳዬ ይዞት ስለመጣው ፍልስፍና ተናግሮ አናግሮት ከዚህ በታች ያለውን ምላሽ ሰጥቶታል ተከታተሉን፡፡


ሀትሪክ፡- ውልደትህና እድገትህ መሳለሚያ እህል በረንዳ ልዩ ስሙ አህያ በር የሚባለው አካባቢ ይመስለኛል…ሠፈራችሁ ለምን “አህያ በር” ተባለ የሚለው ጥያቄዬን መንደርደሪያ ባደርገውስ…?

ወንድሜነህ፡- …ሳቅ…በጣም ደስ ይለኛል…እንግዲህ መረጃው ምን ያህል ትክክል ይሁን አይሁን ባለውቅም…በአፈ ታሪክ በወሬ ደረጃ ሲነገር እንደምሰማው ቦታው ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ቦታ ነው…ለንግድ እንቅስቃሴው ማጓጓዣ እንደ ትራንስፖርት የሚጠቀሙት በአብዛኛው አህያ ነው፤የአህያዎቹ ባለቤቶች ስራቸውን ከጨረሱ በኋላ እዛው አካባቢ ባሉ መጠጥ ቤቶች አንድ ሁለት ለማለት አህዮቻቸውን የሚያሰሩት እዛ ስለሆነና በብዛት የሚታዩበት አካባቢ በመሆኑ “አህያ በር” የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ነው በወሬ ደረጃ የሰማሁት(…በጣም…ሳቅ…)፡፡

ሀትሪክ፡- …ከዚህ ሠፈር በትልቅ ደረጃ ወጥተው የተጫወቱ…ስማቸው የሚጠቀስ ተጨዋቾች አሉ…?

ወንድሜነህ፡- …ብዙም የለም…ሰይፈ ውብሸትና የአሁኑ የቡድናችን አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በትልቅ ክለብ ደረጃ የተጫወቱ የሠፈራችን ልጆች ናቸው፡፡

ሀትሪክ፡- …እስቲ ስለቤተሰብህ አውራኝ…ወንድሜነህ ለቤተሰቡ ስንተኛው ልጅ ነው…?

ወንድሜነህ፡- …ሶስተኛና የመጨረሻ ልጅ ነኝ…ከእኔ በላይ ሁለት ወንድሞች ነበሩኝ… ግን እንደአለመታደል ሆኖ ሁለቱም ወንድሞቼ አሁን በህይወት ስለሌሉ ለቤተሰቤ ብቸኛው ልጅ ነኝ…፡፡

ሀትሪክ፡- …ወንድሜነህ ከሞላለት…የተረፈው ከሚባል ቤተሰብ የተገኘ ነው…?

ወንድሜነህ፡- …ኧ…አይደለም…ወንድሜነህ እንደውም አንተ በጥያቄህ ካነሳኸው ፍፁም ተቃራኒ ከሆነ…እጅግ በጣም…ደሃ…ከሚባል ቤተሰብ ነው የተገኘው…፡፡

ሀትሪክ፡- …ብዙውን ጊዜ በቃለ-ምልልስም ላይ ይሁን እንደዚሁ ስታወራ የወላጅ እናትህ ስም ከአፍህ አይጠፋም…፤…ሁሉም እናቱን መውደዱ የሚገርም ባይሆንም አንተ ለእናትህ ያለህ ነገር ግን ፍፁም የተለየ ነው የሚሉ አሉ እውነት ነው…?

ወንድሜነህ፡- …አዎ እውነት ነው…ስለ እናቴ አውርቼ አልጠግብም…የሁሉም እናት ለልጆችዋ እኩል እናት እንደሆነች ባልክድም…የእኔ እናት ግን ከሌሎች እናቶች የተለየች እናት እንደሆነች ነው ውስጤ የሚያምነው…፡፡

 

ሀትሪክ፡- …ማለት…?…ግልፅ አልሆነልኝም…?

ወንድሜነህ፡- …በቃ!…እናቴ ወ/ሮ …. ለእኔ እናቴ ብቻ አይለችም…አባትም፣እህትም፣ ወንድምም፣አጎትም…ሁሉም ነገር ሆና መከራ አይታ ነው ያሳደገችኝ…፤…የሚገርምህ እኔ እድለኛ አይደለሁም…ከላይ እንዳልኩህ…ሁለት ወንድሞቼን በሞት ተነጥቃ…ብቸኛ ልጅዋ ሆኜ ነው ያደኩት፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ ብዙ ልጆች አባት ኖሮአቸው “አባዬ” እያሉ ሲያድጉ እኔ ግን አባቴንም ገና በለጋ እድሜዬ በሞት በመነጠቄ እንደ ሌሎች ልጆች “አባዬ” ለማለት ሳልታደል፣የአባትነት ጣዕም ምን ምን እንደሚል ሳላውቅ ነው እዚህ የደረሰኩት…ግን ምስጋና ለእናቴ ይሁንና እናቴ የስነ-ልቦና ጉዳት እንዳይደርስብኝ አባትም፣እናትም፣አጎትም፣ወንድምም ብቻ ሁሉም ነገር ሆና ነው ያሳደገችኝ፡፡ አባቴ በልጅነቴ ከሞተ በኋላ እኔን የማሳደጉን ኃላፊነቴን የወሰደችው ይህቺው ምስኪንዋ እናቴ ናት፤በዚህ የተነሣ እናቴ እኔን ለማሳደግ ያላየችው መከራ፣ያላሰለፈችው ችግር፣ ያልሸጠችው ነገር የለም፤እናቴ ምን ሸጣ ዛሬ ለምገኝበት ደረጃ እንዳበቃችኝ ታውቃለህ…?

ሀትሪክ፡- …ኧረ አላውቅም…ወንድሜነህ…!…አንተ ካልነገርከኝ በምን አውቃለሁ…?

ወንድሜነህ፡- …አሁን ይሄንን ነገር ስናገር እንባዬ ነው ከፊቴ የሚቀድመኝ…እናቴ ጠላ ሸጣ ነው ያሳደገችኝ…ሙሉውን የእኔን እድሜ ማለት እችላለሁ እናቴ ጠላ ሸጣ በምታገኘው ገንዘብ ነው አሳድጋ አሁን ለምገኝበት ደረጃ ያበቃችኝ፤ዛሬ ሰዎች የደረስኩበትን ደረጃ ሲያዩ ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆነውልኝ ለዚህ የበቃሁ ሊመስላቸው ይችላል…ግን አይደለም…በፈተናዎች ያልተበገረችው፣ብዙ መከራዎችን የተጋፈጠችው እናቴ በከፈለችው መስዋዕትነት ነው እዚህ የደስኩት፡፡ሙሉ ህይወቷን ለራስዎ ሣይሆን ለእኔ ኖራ ያሳደገችኝን እናቴን በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናት እወዳለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- …ብዙዎች በትናንት ማንነታቸውና አስተዳደጋቸው ሲያፍሩ አንተ ግን በኩራት በተለይ ደግሞ የእናትህን ልፋት በዚህ ደረጃ ገልፀህ መናገርህ ለብዙዎች ትምህርት ከመሆን ባለፈ በትናንት ማንነትህ ባለማፈርህ ያስከብርሃል የሚል እምነት አለኝ…፤…በኳስ የተሻለ ደረጃ እንድትደርስ የእናትህ ድጋፍስ እስከምን ድረስ ነበር….?

ወንድሜነህ፡- …በዚህ በኩል እንኳን እናቴ “…ትምህርትህን አርፈህ ተማር፤ኳስ ጋር ድርሽ እንዳትል…” ብለው ከሚከለክሉ እናቶች አንዷ ናት …(ሣቅ).. ኳስ እንዳልጫወት ትከለክለኝ ነበር…የዚህን ምክንያት አሁን ካለፈ በኋላ ስረዳው እናቴ የምታሳድገኝ በብዙ ልፋትና ድካም ከመሆኑ…እንዲሁም ካለብን ችግር አንፃር ኳስ ተጨዋች ሆኖ ያግዘኛል ትልቅ ደረጃ ይደርሳል የሚል እምነት ብዙም ስላልነበራት እንዲሁም ግራ እጄን ምናልባት ልብ ብለህ አይተኸው ከሆነ ስብራት ነገር ስላለው እሱም የደረሰብኝ በኳስ ምክንያት ስለሆነ እናቴ ልጄ ይጎዳብኛል ብላ ወደ ኳስ እንዳልዞር…ከኳስ ይልቅ በትምህርቴ እንድበረታ እንድገፋ ነበር ትልቁ ፍላጎቷ፡፡ በአንድ አጋጣሚ እጄ ተሰብሮ ሐኪም ቤት በሄድኩ ጊዜ ሐኪሙ ድጋሚ ጉዳት እንዳይደርስብኝ ለማስፈራሪያ ብሎ “ኳስ እንዳይጫወት” ስላለ እናቴ ኳስ መጫወቴን አትደግፈውም ነበር፤እንዳልኩህ እናቴ ጠላ ትሸጥ ስለነበር ደንበኞች የሚልኩት እኔን ስለነበር ሱቅ ተልኬ ስሄድ በዚያው ተራግጬ ስለምመጣ እንድጫወት ከመደገፍ ይልቅ መቃወሙን ነበር የምትመርጠው፡፡

ሀትሪክ፡- …አሁንስ…?

ወንድሜነህ፡- …አሁንማ ዋና ደጋፊዋ እሷ ናት…፤…ዛሬ የደረስኩበት ደረጃ የእናቴን የቀድሞ አቋሟን ሳትወድ በግድ እንድትቀይር አስገድዷታል፡፡ በክለብ መታቀፉ፣ስሜ እየተጠራ መምጣት ሲጀምር…በፍላጎቴ፣በስራዬ ጣልቃ መግባቱን ትታ ወደ መደገፉ አዘንብላለች፡፡…አሁን…አሁንማ መቼ ጨዋታ እንዳለን ከእኔ ይልቅ ቀድማ የምታውቀው እሷ ናት…ማለት እችላለሁ፡፡ “ጨዋታ ከእከሌ ጋር አላችሁ አይደል…?…በቴሌቪዥንስ ይተላለፋል…?”…እያለች በጨዋታው ዙሪያ ቀድማ የምታውራኝ እሷው ናት፡፡ በዚህ ብቻ ሣታበቃ የዘወትር ፀሎቷና አምላኳን መለመኗን ተወውና ቤተክርስቲያን ሁሉ ሄዳ ሻማ እስከማብራትና ጥሩ ውጤት እንዲገጥመኝ በሙያዬ የተሻለ ደረጃ እንድደርስ በየጊዜው ስለት ሁሉ ትሳላለች…ዛሬ ካሸነፉ ይሄን አደርጋለሁ…ብላ መሣል…ስለት ማስገባት የዘወትር ልምዷ ነው ብል ይቀለኛል…፡፡…አሁን ሜዳ ውስጥ የምታየው እንቅስቃሴ የእኔ የግል ጥረት ውጤት ብቻ መስሎህ ከሆነ ተሳስተሃል…የእሷ ፀሎት ውጤትና…የአምላክ እርዳታ ድምር ውጤትም ነው…/ሳቅ/…
ሀትሪክ፡- …በጣም እድለኛ ነህ…የጥሩ እናት ባለቤት በመሆንህም ልትኮራ ይገባል…፤… በዚህ ደረጃ ያሳደገሁን…፣…የለፉልህን…አሁንም በፀሎት እየደከሙልህ ያሉትን እናትህን ውለታ መክፈልስ አልጀመርክም… ?

ወንድሜነህ፡- …(ረጅም ዝምታ)…ምን መሠለህ…(አሁንም ረጅም ዝምታ)…የእናትን… ያውም የእንደ እኔ አይነቷን…በብዙ መከራዎችና ፈተናዎች ተከባ ያሳደገችን እናት ውለታ እንዲህ በቀላሉ ከፍለህ የምትጨርሰው ነገር አይደለም…፤…የእሷን ውለታ ውዱንና መተኪያ የሌለውን ህይወቴን ብሰጥ እንኳን ከፍዬ አልጨርሰውም፡፡ እውነታው ይህ ቢሆንም ግን እግዚአብሔር ይመስገን አሁን ለቁም ነገር ደርሼላት በመጠኑም ለመክፈል እየሞከርኩ ነው…ምናልባት ለእናቴ በህይወት ዘመኔ ሠራሁ የምለው ነገር ቢኖር ጠላ በማዘጋጀትና…በመሸጥ እንዳትንገላታብኝ…እንዳትጎሳቆልብኝ ማስቆሜና የቤት እመቤት ሆና ቤተክርስቲያ ሄዳ አምላኳን እያመሰገነች…ማህበራዊ ህይወቷን እንድታሳልፍ ማድረጌ ነው፡፡ ከልጅነቴም ጀምሮ ስመኘው የነበረው እናቴን የመደገፉ፣የማሳረፉ ነገር አሁን በትንሹ ጀምሬያለሁ፡፡ እሷ ተከፍታ…ራሷን አሰቃይታ እኔን አንቀባራ…አስደስታ ያሳደገችኝን ምስኪኗን እናቴን በተረዋ ለማስደሰት እየተፍጨረጨርኩ ነው፤አምላክም የልቤን አይቶ ያግዘኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- …ወንድሜነህን እስቲ አሁን ደግሞ የተለየ ስሜት ውስጥ ከሚከተው የቤተሰብ ጉዳይ እንውጣና ይበልጥ እንዲታወቅም ወደአደረገው በትልቅ ደረጃ ወደሚጠቀሰው የቀድሞ ክለብህ ባህርዳር ከተማ እናውራ እስቲ…?

ወንድሜነህ፡- …ባህርዳር ከተማ እኔን በጣም ያስተዋወቀኝ…በህይወቴ መቼም የማልዘነጋቸው የእግር ኳስ ስኬትን ያገኘሁበት ክለብ ነው፤ከባህር ዳር በፊት ግን ለሱልልታ ከተማ ሁለት አመት ተጫውቻለሁ…የባህር ዳር አገባቤም ሱልልታ እያለሁ እነሱን በሜዳቸው ስንገጥም…ሰዎች አይተውኝ አጩኝ…ስልክ ተለዋወጥን፤በነገራችን ላይ ባህር ዳር ልገባ የነበረው በ2009 ነበር…አንዳንድ ነገሮች ባለማለቃቸው ነገሩ ተጨናገፈ እንጂ ያኔ እገባ ነበር፡፡ በ2010 ጳውሎስ ጌታቸው /ማንጎ/ አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ…እሱ ሲሾም ምርጫ ነበር…ለምርጫ ስም ዝርዝር ሲሰጡት “…ይሄንን ልጅማ አውቀዋለሁ…በጣም እፈልገዋለሁ” አለ፡፡ በ2007 ሱሉልታ ስጫወት ጳውሎስና እዮብ ማለ /አሞካቺ/ ጨዋታችንን መጥተው ያዩ ስለነበር በጣም ያውቁኝ ነበር…በዚህ መንገድ ነው ባህር ዳር የገባሁት…ከላይ እንዳልኩህ በባህር ዳር ያሳለፍኩት ሁለት አመታት በጣም ምርጥና ወርቃማ የሚባል ነበር…ህይወቴን ሁሉ እስከመቀየር የደረሰ ምርጥ ጊዜን ያሳለፍኩበት ክለብ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-…አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው /ማንጎ/ በአንተ ላይ እምነት ቢጥልም የባህር ዳር ከነማ ደጋፊዎች በአንተ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ እምነትም አልነበራቸውም…የሚል ነገር ሰምቻለሁ…እስቲ ሳትደብቅ እውነቱን ንገረኝ… ?

ወንድሜነህ፡- …(ሳቅ)…ምንም የምደብቅህ ነገር የለም…(አሁንም ሳቅ)…ይሄንን ነገር ጳውሎስ ጌታቸው /ማንጎ/ ያነሣዋል፤እኔም ራሴ ስለዚህ ነገር ሳላነሣ ማለፍ አልፈልግም..ምንድነው የሆነው መሰለህ…አሰልጣኝ ማንጎ “እፈልገዋለሁ” ብሎ ለክለቡ ቢያስፈርመኝም…ደጋፊው የሰውነቴን መቅጠን አይቶ “…እንዴ ይሄንን ነው እንዴ እፈልገዋለሁ ብሎ ያስፈረመው…?…” ብለው ጥያቄ ያነሱ ነበር…ሰውነቴ በጣም ቀጭን ነው…ኪሎዬም በጣም ትንሽ…በዚያ ላይ የምጫወተው የተሻለ ሰውነት ነው የሚፈልገው ተብሎ በሚታሰብበት የተከላካይ ቦታ…በዚህ የተነሳ…ደጋፊው እምነት አልጣለብኝም ነበር…የተወሰኑ ማጉረምረሞች ነበሩ፤እኔም ይሄንን አመለካከት መስበርና ማንነቴን ማሳየት አለብኝ አልኩኝ፡፡ ጨዋታ ሲጀምር እነዛ እምነት ያልጣሉብኝ ደጋፊዎች ለመለወጥ ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም…ወዲያው ከተቃውሞ ወደ ድጋፍ መጡ፤መጀመሪያ እንደ ቡድን የጠበቁንን ያህል አልነበረንም…በቀጣይ ግን ቡድኑን ወደ ሊጉ ባስገባንበት ጊዜ የነበረውን ስሜት በቃላት መግለፅ አልችልም፤ፍፁም ልዩ የሚባል የማይዘነጋ ጊዜን ነበር ያሳለፍኩት፡፡

ሀትሪክ፡- …አሁን የኢት.ቡና ንብረት ነህ…ክለቡን በቋሚነት ያውም በብቃት እያገለገሉ ከሚገኙ ተጨዋቾችም አንዱ ነህ…፤…ወደ ኢትዮጵያ ቡና ከመምጣትህ በፊት ለክለቡ የመጫወት ህልሙ ነበረህ…?

ወንድሜነህ፡- …በጣም የሚገርምህ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊም ነበርኩ…ክለቡን ከመውደዴ የተነሣ አንድ ቀን በዚህ ደረጃ የምወደውን ክለብ ማልያ ለብሼ ብጫወት ብዬ እመኝ ነበር…፤…የአብዛኛው የሀገራችን ተጨዋቾች ምኞት ከሁለቱ ኃያላን ክለቦች አይወጣም …

ሀትሪክ፡- …ኢት.ቡና በ2003 የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሣ ወንድሜነህ የት ነበር…?

ወንድሜነህ፡- …አታምነኝም…(ሳቅ)…ቡና ይሄንን ታሪካዊ ድል ሲያስመዘግብ ወንድሜነህ…ሚስማር ተራ ቁጭ ብሎ ጨዋታውን ሲኮሞኩም…በድሉ ሲቦርቆ…በደስታ ሲጨፍር ነበር /ሳቅ/…

ሀትሪክ፡- …በዚህ ደረጃ ስትደግፈው…በድሉ ስትጨፍር አንድ ቀን ለብሼው ብጫወት ብለህ ስትመኘው የነበረውን…የኢትዮ ቡናን ማልያ የመልበስ እድል ስታገኝ፣ህልምህ ወደ እውነትነት ሲቀየር ምን አልክ…?

ወንድሜነህ፡- …ኡ…!….በቃላት መግለፅ የማልችለው…በጣም ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ…፤…በጣም የሚገርምህ…ሲጀመር እኔ በጣም እድለኛ ነኝ…የማስባቸውን… የምመኛቸውን ነገሮች እያገኘሁ፣እያሳካሁ ነው ያደኩት…እግር ኳስ ተጨዋች የመሆን የልጅነት ምኞት ነበረኝ…አሳክቻለሁ…አንድ ቀን የቡናን ማልያ ለብሼ ብጫወት ብዬ ተመኝቼ ነበር እሱንም አሳክቻለሁ…የብ/ቡድን ማልያን ለብሼ ሀገሬን አንድ ቀን ብወክልም ብዬ ተመኝቻለሁ…በቋሚነትም ባይሆን እሱንም በሀ-23 /ኦሎምፒክ ብ/ቡድንና ለቻን ብ/ቡድን ተመርጬ በጅቡቲው የደርሶ መልስ ጨዋታ ተሰልፌ አሳክቻያለሁ…፤…የሆነ ነገር ለማድረግ ስጀመር እንደ እቅድ የማስቀመጣቸው ነገሮች ነበሩ…ከእግዚአብሔር ጋር እያሳካሁ ነው የመጣሁት፡፡ ወደ ተሰማኝ ስሜት ስመለስ ግን የሚያባራ የደስታ ስሜት በውስጤ ነበር፤ልክ የቡና ተጨዋች መሆኔን ያረጋገጥኩበትን ፊርማ ለክለቡ ሳኖር…ከራሴ ጋር አንድ ነገር አወራሁ…ለራሴም ቃል ገባሁ…

ሀትሪክ፡- …ምን ብለህ…?

ወንድሜነህ፡- …ልክ የክለቡ ተጨዋች መሆኔን በፊርማዬ ካረጋገጥኩ በኋላ ከራሴ ጋር ማውራትና ቃል መግባት ነበረብኝ…ትናንት የክለቡ ደጋፊ ነበርኩ…ወይም ደግሞ ክለቡን በጣም ትወደዋለህና የሆነ መስራት የምትፈልገው ነገር አለ…በጣም እላፊ ነገር እንዳለሰብና…ያ ሃሣብ ወይም የበዛ ጭንቀት ጨዋታ ላይ እንዳይመጡብኝ…ደጋፊነቴን ልክ የፈረምኩ እለት እዚህ ጋ አቁሜያለሁ…ከዚህ በኋላ…በቃ ስራ ላይ ነኝ…የክለቡ ተጨዋች ነኝ…ብዬ ለራሴ ራሴው መንገር ነበረብኝ…ነገርኩት…ምክንያቱም የሚጋጩ ነገር ይኖራል ብዬ ስለፈራሁ፤ደጋፊነቴን ትቼ በጣም እንደምወደው፣ወድጄው እንደምጫወት…ለእሱ ያለኝን ለማድረግ እንደማልሳሳ…ውስጤን አሣምኜ ነው መጫወት የጀመርኩት…፡፡

ሀትሪክ፡- …ቡናን እንደትመርጠው…ለክለቡ መጫወትን እንድትመኝ…የሳበህ ምክንያት ምንድነው…?

ወንድሜነህ፡- …ኢት.ቡናን እንድትመርጥ ለክለቡ ለመጫወት ሁለቴ እንዳታስብ የሚያደርጉ ሚሊዮን ምክንያቶች አሉ…የመጀመሪያው ትልቅ ታሪክ ያለው…በጣም የሚያኮራ…ምነው በዚህ ደጋፊ መሀል የመጫወት እድል ባገኝ ብለህ የምትመኘው አይነት ደጋፊ ባለቤት የሆነ ክለብ ነው…የደጋፊው ስሜት በራሱ ወደ ክለቡ ይጎትትሃል፤ከዚህ ሌላ ደግሞ በሀገሪቱ እግር ኳስ የገዘፈ ስምና ታሪክ ያላቸው ተጨዋቾች ማልያውን ለብሰው ተጫውተዋል ከእነሱ ጋር ታሪክ ለመጋራትም ለክለቡ መጫወትን ትመኛለህ…ከላይ የጠቀስኩልህን ጨምሮ አጨዋወቱም ነው ወደ ክለቡን እንድመርጥ ያደረገኝ፡፡

ሀትሪክ፡- …ለመጀመሪያ ጊዜ የቡናን ማልያ ለብሰህ የመጫወት እድል ስታገኝ በውስጥህ የተፈጠረውን ስሜት ዛሬ ላይ ሆነህ ታስታውሰዋለህ…?

ወንድሜነህ፡- …በጣም የቅርብ ጊዜ ስለሆነ አዎን አስታውሰዋለሁ…ለመጀመሪያ ጊዜ የቡናን ማልያ ለብሼ በመጫወት ህልሜ እውን መሆኑን ያረጋገጥኩት በሲቲ ካፑ ከሰበታ ጋር በተጫወትንበት ጨዋታ ነው…በጨዋታው ድል ባይቀናንም በእኔ የእግር ኳስ ህይወት ሌላ አዲስ ታሪክ የተፃፈበት ቀን ስለነበር በጣም የተለየ ስሜት ነበር የተሰማኝ፤ያ ሁሉ ደጋፊ ማልያውን ለብሶ ሲዘምር ስታይ ልክ ኤሌክትሪክ የነካህ ያህል ይነዝርሃል…የሆነ የማታውቀው አይነት ስሜት ሁሉ ይሰማሀል…በድንገት ልትንቀጠቀጥ ሁሉ ትችላለህ…በጣም ደስተኛ ከመሆንህ የተነሣ…፤…እናም በወቅቱ የተዘበራረቀ…ግን ደስ የሚል ስሜት ውስጥ ነበርኩ…፡፡

ሀትሪክ፡- …ኢት.ቡና አንደኛውን ዙር 11ኛ ሆኖ አጠናቋል፤ የቡድኑን ስብስብ ግለፅልኝ ብልህ እንዴት ትገልፀዋለህ…?

ወንድሜነህ፡- …ስብስባችን በጣም ምርጥ የሚባል ስብስብ ነው…በአብዛኛው ወጣቶች… ሲኒየር የሚባሉ የሌሉበት…ሁሉም በተመሳሳይ እድሜ…የጨዋታ ታሪክ ውስጥ የሚገኙ ወጣት ተጨዋች ያሉበት ስብስብ ነው ብዬ ነው የማስበው፤ይሄ የተደረገበት ደግሞ የራሱ ምክንያት አለው…ብዬም አስባለሁ…ምክንያቱም ፍልስፍናው አዕምሮን የሚጠይቅና አዕምሮ ላይ ትኩረት ያደረገ ነገር ስለምንሰራ ይበልጥ ወጣቶችን ይፈልጋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ስብስባችን በወጣቶች የተገነባ…ብዙም በትልቅ ክለብ ደረጃ ተጫውተው የማያውቁ…ግን በክለቡ ታሪክ የመሰራት ረሃብ ያላቸው ወጣቶች የተሰበሰቡበት ምርጥ ስብስብ ነው ለእኔ፡፡

ሀትሪክ፡- …በሱሉልታም ይሁን በባህር ዳር ከዚያም በፊት ይሁን በተለያዩ አሰልጣኞች ሰልጥነህ አልፈሃል…አሁን ደግሞ የተለየ ፍልስፍና አለው በሚባለው ካሳዬ አራጌ እየሰለጠንክ ነው፤ ካሳዬን እንደ አሰልጣኝ እንዴት አገኘኸው?

ወንድሜነህ፡- …ኡ…ካሳዬ በጣም የተለየ አሰልጣኝ ነው…እንዳልከው በተለያዩ አሰልጣኞች በክለብም፣በብ/ቡድን ደረጃም ሰልጥኜ አይቻለሁ…እውነት ለመናገር ግን ካሳዬ በጣም ይለያል…ካሳዬን ለመግለፅ የእኔ ሰው መሆን ብቻውን የሚበቃ አይነት ነው ብዬ አላስብም፤በጣም የተለየው ኳሊቲው ደግሞ ችግሮችን ወደ ተጨዋቾች የሚገፋ ጥሩ ነገር ሲኖር ከፊት ለመሰለፍ የሚጣደፍ ሰው ሆኖ አለማግኘቴ ነው፡፡ ብዙ አሰልጣኞች ካመኑበት ነገር ሲንሸራተቱ ታያለህ…ካሳዬ ግን ሁሌም ከዚህ በተቃራኒው ነው… ባመነበት ነገር እስከመጨረሻው የመሄድ ብንሳሳትና ችግር ቢፈጠር እንኳን “እኔ ያልኳቸውን ነገር ለማድረግ ሲሞክሩ ነው የተሳሳቱት” ብሎ ራሱን አሣልፎ ሰጥቶ ተጫዋቾቹን ነፃ የሚያወጣ አሰልጣኝ ነው፡፡ የግል ስብዕናውንም ብታይ በጣም ጥግ ድረስ የሄደ ነው…ቤንችም፣አውት ኦፍ ቤንችም፣ ተሰላፊ የሆነ ተጨዋችም እኩል የሚወደው አሰልጣኝ ነው፤የተሰለፈውም ያልተሰለፈውም ለእሱ ተመሳሳይ ስሜት ነው ያላቸው…ይሄንን በሁላችንም ልብ ውስጥ የፈጠረው ልዩ በሆነው ስብዕናው ነው…ሌላ ያየሁበት ትልቅ ነገር ደግሞ…

ሀትሪክ፡- …ሌላ ምን አየህበት…?

ወንድሜነህ፡- …ካሳዬ ያለው በራስ የመተማመን ስሜት በጣም ይገርማል…በጣም የሚገርመው ኳሊቲው ተሸንፈን ወይም አቻ ወጥተን እኛ ጭንቀት ውስጥ ስንገባ ራሱን በእኛ ስሜት ውስጥ የማይከት በትንሽ ነገር የሚረበሽ አይነት አሰልጣኝ አለመሆኑ ነው፡፡ ተቃውሞ ይምጣ ቅሬታ ካሳዬ እንደ መልካም ነገር ከማየት በስተቀር አይረበሽም…በዚህም ያለውን ከፍተኛ በራስ የመተማመን ስሜት አይቻለሁ፤ካሳዬ የትኛውንም አይነት ነገር መቋቋም የሚችል ስብዕና ያለው አሰልጣኝ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …ከዚህ አባባልህ በመነሣት ኢት.ቡና ከህልሙ የሚያገናኘውን ትክክለኛውን ሰው አግኝቷል ብሎ መናገር ይቻላል…?

 ክፍል ሁለትን ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ 👇

https://www.hatricksport.net/የኢትዮጵያ-ቡናን-ማልያ-ለብሼ-እንድጫወ-2/

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.