“የኢትዮጵያ ቡናን ማልያ ለብሼ እንድጫወት ትልቁ ምክንያት የሆነኝ በቃላት የማይገለፀው ደጋፊው ነው”ወንድሜነህ ደረጀ (ኢት.ቡና)

ክፍል ሁለት 

በይስሐቅ በላይ

ወንድሜነህ፡- …እኔ እንደዛ ነው የሚሰማኝ…በነገሮች ሃሣቡን የማይቀይር የራስ መማተመኑ ጣሪያ የነካ ሰው ስለሆነ እኔ እንደዛ ነው የሚሰማኝ፤የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ የሚታወቅበት ጨዋታ እንዲመለስለት አጥብቆ ይፈልጋል…ለዚያ የሚሆን የታመነ አሰልጣኝ ነው የተሾመው…፤…የክለቡን ባህል፣ታሪክ፣ደጋፊው የሚፈልገውን፣ ማልያውን በትክክል የሚያውቅ ሰው ነው የተሾመው የሚል የግል አመለካከት አለኝ። በጣም የሚገርምህ ሌሎች ያልታዘቡትና እኔን በጣም የገረመኝ ነገር ሁሌም ከጨዋታ በኋላ መልበሻ ቤት ውስጥ ስንዘምር ካሳዬ አብሮን በስሜት ነው የሚዘምረው…ይሄ ራሱ የሚነግርህ ነገር አለ…ቡና ማለት ውስጡ እንደሆነ ከውስጡ እንደሚሰራም ይነግረሃል፤ለዚህ ክለብ ማድረግ የሚችለው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ ብዬ ነው የማስበው… ምክንያቱም ከውስጡ ከልቡ ስለሆነ፡፡

ሀትሪክ፡- …አሁን እሱ ይዞት የመጣው ፍልስፍና ኢትዮጵያ ቡናን የት ድረስ ይወስደዋል ብለህ ታስባለህ…?

ወንድሜነህ፡- …እንግዲህ ካሳዬ ገና የመጀመሪያ አመቱ ነው…እንደ አጀማመር ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው፤ጥሩ ቡድን ነው የገነባው የሚልም የግል እምነት አለኝ፡፡ ይሄ የመጀመሪያ አመቱ ከመሆኑ የተነሣ በቀጣይ በሂደት የተሟላ ነገር ሊያሳየን ይችላል ነው የምለው፤ምክንያቱም ይሄንን ቡድን የገነባው የሊጉን ውድድር ተጫዋቾን አይቶ መርጦ አይደለም…ለእሱ አጨዋወት ይሆናሉ የተባሉ ተጨዋቾች ተመርጠውለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በመጀመሪያ አመት እስከ አንደኛው ዙር የሆነ ትንሽዬ ብልጭታ አሳይቷል…የደጋፊውን ልብም በአብዛኛው መያዝ ችሏል…በቀጣይ አመት ሊጉን ሲላመድ ተጨዋቾቹንም በደንብ እያወቀ ሲመጣ የተሻለ ነገር ስለመፍጠሩ ጥርጣሬው የለኝም…የተሻለ ነገርም ይፈጥራል ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን ራሱ ኢት.ቡናን የሆነ መልክ አስይዞታል ብዬ ነው የማስበው…ክለቦች እኛን ለመግጠም ሲመጡ ኢት.ቡና ከበረኛ መስርቶ ነው የሚጫወተው ብለው ስትራቴጂ ነድፈው እንዲመጡ አስገድዷቸዋል…ይሄ ራሱ አንድ ነገር ለመሰራቱ ጠቋሚ ነው፤ቡና ካሳዬን ካገኘ በኋላ የሆነ መልክ እንዳስያዘው ይሰማኛል፡፡

ሀትሪክ፡- …ግን አንተ በዚህ ደረጃ ብትገልፀውም ኢትዮጵያ ቡና አንደኛውን ዙር 11ኛ ሆኖ ነው የጨረሰው…ወላይታ ድቻን ከማሸነፋችሁ በፊት በወራጅ ቀጠና ውስጥ ሆናችሁ ነው ያሳለፋችሁት…ይሄ አንተ ከምትለው ነገር ጋር አይጋጭም…የመውረድ ነገርስ እንደ ተጨዋች አላሳሰብህም… ?
ወንድሜነህ፡- …ስለመውረድ…ወራጅ ቀጠና…እየተባለ ሲወራ እሰማለሁ…እኔም ጋ ሆነ የቡድኑ ተጨዋቾች ስለመውረድ ያሰብንበት አጋጣሚ የለም፤ገና አንደኛ ዙር ላይ ሆነን በጣም ብዙ ቀሪ ጨዋታ እያለን…በአንድ ጨዋታ ውጤት በአንዴ ከፍ እንደሚባል እያወቀን…እንዴት ስለመውረድ እናስባለን፡፡ ብንሸነፍም በአንድም ጨዋታ ተበልጠን አልተሸነፍንም…ምናልባት ተበልጠን ተሸንፈናል ብዬ የማምነው አንድ የአዳማን ጨዋታን ነው…ልክ ያልነበርንበት ጨዋታ እሱ ነው…ከዚያ ውጪ በልጠን ነው የተሸነፍነው…በሌሎች ውጤት ሲገባን ነው ያጣነው…አንዳንድ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ ከተባለ…አዎን ማስተካከል ያለብን ነገር አለ…ስህተትም መቀነስ አለበት… አዎን አለበት…አንደኛውን ዙር በድል ነው የዘጋነው…ያንን ስሜት በሁለተኛው ዙር ለማስቀጠል…ባየናቸው ችግሮች ላይ ጠንክረን የምንሰራ ይሆናል፡፡

ሀትሪክ፡- …በቁጭት የምታነሣው ጨዋታ አለ…?

ወንድሜነህ፡- …አዎን በጣም ብዙ ናቸው…የአዳማውን ሽንፈት እንኳን ተወው…ምንም መደበቅ አያስፈልግም…ተበልጠን ነው የተሸነፍነው፤ከዚህ ውጪ ግን በመሸነፋችን በቁጭት የማነሣቸው ብዙ ጨዋታ አሉ…ከነዚህ ውስጥ 3ቱን እንኳን ነቅሼ አውጥቼ ብጠቅስልህ በባህር ዳር 3ለ2 የተሸነፍንበት ጨዋታ…መሸነፍ አይገባንም…መሸነፉን ተወው…ነጥብ ተጋርተን መውጣት እንኳን አይገባንም…ማሸነፍ ነበረብን፤ከፋሲል፣ ከጅማ ጋርም እዚሁ በሜዳችን ማጣት የማይገባንን ውጤት ያጣንባቸው ጨዋታዎች ናቸው…በእነዚህ ጨዋታዎች ውጤት ብንይዝ የምንገኘው ከላይ ይሆን ነበር፤እነዚህ በጣም ይቆጩኛል፡፡

ሀትሪክ፡- …ካሳዬ ይዞት የመጣው የጨዋታ ፍልስፍና ዋናው ብልቱ የሚባለው ቦታ የግብ ጠባቂው፣የአንተና የፊቱዲን ቦታ ነው፤ከዚህ አንፃር በፍልስፍናው ዙሪያ ትነጋገራላችሁ…የተለየ ነገርስ ትሰራላችሁ…?

ወንድሜነህ፡- …እንዳልከው የእንቅስቃሴው መነሻ እኛ ጋ ስለሆነ በደንብ እንነጋገራለን… እንመካከራለን…፤…ጎል ለማግባት፣ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ለማሳየት፣ኳስ በደንብ ተመስርቶ፣ተደራጅቶ መሄድ ያለበት ከእኛ ጋር ነው…ከእኛ የሚጠበቀውን ማድረግ ካልቻልን ፍልስፍናው የሆነ ቦታ ይሰበራል…ተክለማርያም ይሰለፍ በረከትም የተሻለ ነገር ለመስራት በደንብ እንነጋገራለን፡፡

ሀትሪክ፡- …ከፊቱዲን ጋር ከኋላ ያላችሁን ጥምረት እንዴት ትገልፀዋለህ…?
ወንድሜነህ፡- …ከፊቱዲን ጋር ያለን ጥምረት በጣም ጥሩ ነው…በጣም ተናበን፣በጣም ተግባብተን፣ተሸፋፍነን፣አንዳችን የአንዳችንን ፍላጎትና አቅም ተረድተን ነው የምንጫወተው…፤…ከሁሉም በላይ በግልፅ መነጋገራችንና፣መመካከራችን ጥሩ ጥምረት እንዲኖረን ረድቶናል፡፡ከዚህ በፊት ከ23 አመት በታች ብ/ቡድን ተመርጠን ስለነበር አብሮ የመጫወቱና መተዋወቁ ነገር ከዛ ይጀምራል…ከዚህ አንፃር ጥሩ መግባባቱ ስላለን አልተቸገርንም…ከሁሉም በላይ ተክለሰውነታችን፣የኳስ ችሎታችን፣ስታይላችን ተቀራራቢ መሆኑ…እንዳንቸገር አድርጎናል ብዬ አስባለሁ…፡፡

ሀትሪክ፡- …የአንተንና የፈቱዲንን ጥምረት የሚያደንቁ እንዳሉ ሁሉ…አንዳንዴ ከመጠን ያለፈ በራስ የመተመን ስሜት…ራሣቸውንም ቡድኑንም ችግር ውስጥ ሲከቱ ይታያሉ ብለው የሚወቅሷችሁ አሉ…ወቀሳውን ትቀበለዋለህ…?

ወንድሜነህ፡- …አዎን በጣም እቀበለዋለሁ…ከጨዋታ በኋላ ቪዲዮውን ስንመለከት እንዲሁም ከሰው ከሚደርሰኝ አስተያየት ስነሣ…ተገቢ አስተያየት እንደሆነ ነው የማምነው፤የበዛ ነገር ሲደረግ ለሪስክ(ለአደጋ) አሣልፎ ይሰጣል፤የደጋፊው ስጋትም ይገባኛል…ቡድኑ ለሸንፈት እንዳይጋለጥ ስለሆነ አስተያየቱን እቀበላለሁ።ግን ገና ለገና ለሪስክ(ለአደጋ) አጋልጣለሁ ብለህ ፈርተህ ማድረግ ያለብህን ሳታደርግ መቅረት አለብህ ብዬ አላምንም…አንዳንዴም ሪስክ ደፍረህ መውሰድ ያስፈልጋል…ይሄንን በተመለከተ አሰልጣኛችን ምን ይለናል መሰለህ “ካለ ሪስክ ጨዋታ የለም” ይለናል…አንዳንዴም ቢሆን ሪስክ ደፍረህ መውሰድ አለብህ…ትልቁ ነገር መቼና እንዴት…?…የሚለው ነው መታወቅ ያለበት…በእርግጥ እንደ ተባለው አንዳንዴ ሪስክ አለው…ግን ያንን ሪስክ አሰልጣኞችን ወስዶልናል፤እኛ ሪስክ ወስደን ካልጀመርን ፍልስፍና የሚባል ነገር አይኖርም፤በረኛው በእግሩ መጫወት ካልቻለ…እኛ ኳሱን ይዘን መጫወት ካልቻልን ፍልስፍናው ተሰበረ ማለት ነው…ከዚህ ውጪ ከሆነ ልክ ሌሎች እንደሚያደርጉት ረዥም ኳስ ልንጫወት ነው ማለት ነው…፤…ይሄን አደረግን ማለት ፍልስፍናው ቆመ ማለት ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …ግን እኮ የበዛ ሪስክ ከመውሰዳችሁ የመጣ በተለይ አንተ ከወልቂጤ ጋር በነበራችሁ ጨዋታ በሰራኸው ስህተት ቡድኑ ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ ዋጋ አስከፍለሀዋል? ይሄ ለአደጋው አንዱ ማሳያ አይሆንም….?

ወንድሜነህ፡- …ይሄንን ያነሳኸውን ጥያቄ እንድትጠይቀኝ በውስጤ እፈልግ ነበርና እንኳንም አነሳኸው(…ሳቅ…)…ሰው ሲሰራ ይሳሳታል…ስህተቱን ለማስተካከል ደግሞ መጀመሪያ መሳሳቱን ማመን ያስፈልጋል…እኔም በእለቱ ጨዋታ አዎን ተሳስቼያለሁ… ብቻ ሣይሆን በጨዋታ ዘመኔ በጣም ከተከፋሁባቸውና በጣም ከተቆጨሁባቸው አንዱ ይሄ የወልቂጤ ጨዋታ ነው፤ወልቂጤን፣ሰበታንና ወላይታ ድቻን አሸንፈን በውጤትም በደረጃም ከፍ እንላለን የተሻለ ደረጃ እንደርሳለን ብለን አቅደን ስለነበር…እኔ በሠራሁት ስህተት ነጥብ ተጋርተን መውጣታችን በጣም ቁጭት ውስጥ ከቶኛል፡፡ ከጨዋታው በኋላ በጣም ከባድ ተቃውሞ ነው የነበረው…በተፈጠረው ነገር ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቱን እኔ መውሰድ ነው ያለብኝ፡፡ ግን ካሳዬ ጋ ያለው እምነት ደግሞ የበለጠ ጠንካራ ያደርግሃል…እሱ የሚረዳበት መንገድ ችግር የለውም ብለህ ኃለፊነት እንድትወስድ ያደርግሃል…ገና ለገና ስህተት ይፈጠራል ብሎ መፍራት የለብህም…እየተሳሳትክም ቢሆን እዛው ውስጥ መቆየታችንን ነው የሚወደው አሰልጣኛችን…እኛም እሱ ያለንን ነው የምናደርገው…፡፡

ሀትሪክ፡- …አሁን አሁን…አንዳንድ አሰልጣኞች የቡናን አጨዋወት ነቅተበታል…ከበረኛ ጀምረው ኳሱን ወደ ተከላካይ ሲያንሸራሽሩ እዛው አፍነን ግብ በማስቆጠር እናሸንፋቸዋለን እያሉ ሲናገሩ ይሰማል…ይሄ ነገር አያሰጋችሁም…?

ወንድሜነህ፡- …እኔ ሁሉም ግርም የሚለኝ ነገር አለ…ክለቦች እኛ የምንጫወትበትን መንገድ ለማበላሸት ለምን እንቅልፍ አጥተው እንደሚመጡ አይገባኝም፤የሰው ጨዋታ አበላሽተው ለማሸነፍ ወይም ለመጫወት ከመምጣት ለምን እንደ ካሳዬ የራሣቸው የጨዋታ ፍልስፍና አይኖራቸውም…ሁሌም ስታያቸው እኛ ጨዋታ ውስጥ ሆነው ነው የሚያስቡት…ከዚህ ይቅር የራሣቸው የሆነ መታወቂያ ወይም አጨዋወት ቢኖራቸው ነው ተጠቃሚ የሚሆኑት የሚል እምነት አለኝ።የጨዋታ ሲስተማቸውን ነቅተንባቸዋል ብለው የሚመጡ ክለቦች እንዳሉ እናውቃለን…ራሱ ካሳዬም የሚለን ነገር አለ…“ቡና ሁሌም የሚገመት…ተገማች ቡድን ነው” ይለናል…ከየት ጀምረን የት እንደምንደርስ ይታወቃል…አንዳንዴ እንደውም ረዥም ኳስ ባይባልም…ረዥም ኳስ ለመጠቀም ስንሞክር ይታያል፤ ይሄንን የምናደርገው ከፍልስፍናው ወጥተን ሣይሆን የታሰረውን ለማስፈታት ነው፡፡ ይሄንን በተመለከተ እሱ የሚነግረን ነገር አለ…ከጨዋታ በኋላም እንደ ቡድን የጨዋታ ፊልሞችን መልሰን እናያለን…ፊቱዲንና ወንድሜነህን የማፈንን ነገር ሊመጣ ይችላል…እንደዛ ከሆነ ሌላ አማራጭ እንዴት መጠቀም እንዳለብን ይነግረናል…ያስረዳናል፡፡ ክለቦችም የቡና ጨዋታ ለማበላሸት ሳይሆን በራሣቸው መንገድ ለማሸነፍ ቢመጡ ነው ለእግር ኳሱም የሚጠቅመው፡፡

ሀትሪክ፡- …ፕሮፌሽናል ተጨዋች ስለመሆን ታስባለህ…?

ወንድሜነህ፡- …አዎን በጣም አስባለሁ…አሁንም የጀመርኳቸው ነገሮች አሉ…ከሀገር ወጥቼ የመጫወት አቅም እንዳለኝ ራሴን መፈተሽ እፈልጋሁና…አዎን ትልቅ ህልም አለኝ፡፡

ሀትሪክ፡- …አንድ ማልያ ለብሼ አብሬው ብጫወት ብለህ የምትመኘው…?

ወንድሜነህ፡- …ከጌታነህ ከበደ ጋር አብሬ በአንድ ቡድን ውስጥ ስጫወት ራሴን ባገኘው በጣም ደስ ይልኛል…፡፡

ሀትሪክ፡- …የምታደንቀው ተጨዋች…?
ወንድሜነህ፡- …ሙሉአለም ረጋሣ…ሙሌ በጣም የተለየ ኳስ የሚችል ተጨዋች ነው… ሀትሪክ፡-.. አብሬው ሳልጫወት ያመለጠኝ ግን ደግሞ እንደገና የመጫወት እድል ባገኝና አብሬ ብጫወት ብለህ የምትመኘው ተጨዋች…?
ወንድሜነህ፡- …አበዛኸው እንዳትለኝ እንጂ…አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን…ካሳዬን ሲጫወት አላየሁትም…ስለ እሱ ግን ብዙ ሲባል…ሲደነቅ እሰማለሁ፤አሁን ከእኛ ጋር ትሬይኒንግ ሲሰራ…ሲጫወት ስታየው…አሁንም አቅሙ አብሮት እንዳለ ነው…በዚህ የተነሳ በዘመኔ ስጫወት ባየው ወይም እንደገና እድል ተሰጥቶት አብሬው ብጫወት የምለው ካሳዬን ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …ከሀገር ውጪ የምታደንቀው ክለብና አሰልጣኝ…?

ወንድሜነህ፡- …አርሴናልንና የቀድሞ የክለቡ አሰልጣኝ የነበሩትን አርሴን ቬንገርን

ሀትሪክ፡- …የምታደንቀው…አንድ ቀን የማግኘት እድል ባገኝ የምትለው…?
ወንድሜነህ፡- …ሊዮኔል ሜሲን…አንድ ቀን እሱን የማግኘት እደል ባገኝ በጣም ነበር የምደሰተው፡፡

ሀትሪክ፡- …አሁን ኢትዮጵያ ቡናን በቋሚነት በጥሩ ብቃት እያገለገልክ ነው ስምህ ግን ከብ/ቡድን ጋር ተያይዞ ሲነሣ ብዙም አይደመጥም፤100 ሚሊዮን ህዝብ የመወከል ህልምህ ምን ድረስ ነው?

ወንድሜነህ፡- …ትልቁ ህልሜ ይሄ ነው…ለአንድ ተጨዋች ከዚህ በላይ የሚያስደስት ህልም የለም፤ከዚህ በፊት ከ23 አመት በታችና ለቻን ብ/ቡድን ተመርጬ በመጫወቴ ጉጉቴን በመጠኑም ለማስታገስ ሞክሬያሁ…በወቅቱ በጣም ትልቅ የደስታ ስሜት ነው የተሰማኝ…፤…በእርግጥ ከዚህ በኋላ ነገሮች እንደፍላጎቴ አልሄዱልኝም…ጥሪውም አልደረሰኝም…የዚህ ነገር ውሳኔው የአሰልጣኙ ነው…ኢት.ቡና ውስጥ በቋሚነት ጥሩ እየተጫወትኩ እንደሆነ…ለብ/ቡድኑ መመረጥ እንዳለብኝ የሚነግሩኝ ብዙዎች ናቸው… ይሄን የመወሰን ስልጣኑ የአሰልጣኙ ነው…የእኔ እምነት ጊዜውን እግዚአብሔር ያመቻቻል የሚል ነው፤ግን ጊዜው መቼ ነው ብትለኝ ይሄንንም እሱ ነው የሚያውቀው…ከእኔ የሚጠበቀው የበለጠ ራሴን በየጨዋታው ብቁ አድርጎ መቅረብ ነው፤አንድ ቀን አምላክ አሳክቶት ሀገሬን በቋሚነት እንደማገለግል ግን የጠነከረ እምነት በውስጤ አለ፡፡

ሀትሪክ፡- ከአንተ ጋር በነበረኝ ቆይታ በጣም ተደስቻለሁ፤በተለይ የትናንት ማንነትህን አለመደበቅህ…በኩራት መናገርህ…ይበልጥ እንዳከብርህ እንዳደረገኝ ሳልገልፅልህ አላልፍም፤ለነበረኝ ቆይታ ከልብ የመነጨ ምስጋና አቅርቤ ከመለያየታችን በፊት ቀረ የምትለው ካለ…?

ወንድሜነህ፡- …የማመሰግናቸው አሉ…በቅድሚያ ከፊት ከፊቴ እየቀደመች የምታግዘኝ ልቤ ውሰጥ ያለችውን ኪዳነ ምህርህረትን በጣም አመሰግናለሁ…፤…በመቀጠል የሁሉ ነገር መሠረቴ የሆነችው እናቴን አንቺን ለማመስገን ቃላቶች አይበቁኝም…ለዚህ ስላበቃሽኝ ከልቤ አመሰግንሻለሁ በልልኝ፡፡ ከዚህ ውጪ ብዙ አሰልጣኞች ህይወቴ ውስጥ አሉ የፕሮጀክት አሰልጣኜ ተሻለ ምንዳዬ፣ሀብተወልድ፣ሙሉጌታ የመጀመሪያ ክለቤ አሰልጣኝ፣እዮብ ማለ (አሞካቺ)፣ ማቲያስ ከበደንና ጳውሎስ ጌታቸው /ማንጎ/ን በጣም አመሰግናለሁ፤አንድ የመጨረሻ እድል ከሰጠኸኝ የሀገሬን ማልያ የመልበስ ህልሜን እንዳሳካ እድሉን የሰጠኝን አንስትራክተር አብርሃም መብራቱን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

 ክፍል አንድን ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ 👇

https://www.hatricksport.net/የኢትዮጵያ-ቡናን-ማልያ-ለብሼ-እንድጫወ/

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.