የአሠልጣኞችና የእግር ኳሱ ጠበቃ አሳዛኝ ህልፈት ከ1956-2013 ዓ.ም

የአሠልጣኞችና የእግር ኳሱ ጠበቃና ተሟጋች በመሆን ተለይቶ የሚታወቀው የቀድሞ ተጫዋች፣አሠልጣኝ፣የአ.አ አሠልጣኞች ማህበር ፕሬዘዳንት የነበረው አቶ አስናቀ ደምሴ ህይወቱ አለፈ፤የቀብር ሥነ-ስርዓቱም በዛሬው ዕለት ተፈፅሟል።
በተጫዋችነት ለእርሻ ሰብል፣ለኪራይ ቤቶች በመጫወት አሳልፏል፤ኪራይ ቤቶች ደግሞ ከመጫወት ባሻገር የእሱን የሰልጠና በረከት የቀመሠ የእግር ኳስ ክለብ ነው።
ከተጫዋችነቱና አሠልጣኝነቱ ባሻገር ለአሠልጣኞች፣ለሙያተኞችና ለእግር ኳሱ ህግ መከበር በመታገልና በመሟገት ተለይቶ የሚታወቀው የቀድሞ ተጫዋች፣አሠልጣኝና የአ.አ አሠልጣኞች ማህበርን በፕሬዝዳንትነት ሲያገለግል የነበረው አቶ አስናቀ ደምሴ በአጋጠመው ድንገተኛ ህመም ታህሳስ 10 ቀን 2013 ዓ.ም በተወለደ በ57 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ ሲሆን የቀብር ስነ-ስርዓቱም ዛሬ(ሠኞ)ታህሳስ 12 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 9:00 ሠዓት ቤተሰቦቹ፣ጓደኞቹ፣የሥራ ባልደረቦቹ፣የሙያ ጓደኞቹና የስፖርት ቤተሰቦች በተገኙበት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን በክብር ተፈፅሟል።
ብዙውን ዘመኑን ለአሠልጣኞች መብት መከበር፣ከልዩነት ይልቅ ወደ አንድነት እንዲመጡ፣ለማህበራቸው መመስረት ብቻ ሳይሆን ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ እንዲሁም በእግር ኳሱ ላይ የሚካሄዱ ሸፍጦችን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ጭምር ተለይቶ የሚታወቀው አቶ አስናቀ ደምሴ በአጋጠመው ድንገተኛ ህመም ምክንያት ይህቺን ዓለም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተሰናብቶ ሄዷል።
ህይወቱ እስከለፈችበት ዕለት ድረስ በህግ ሙያው ለብዙዎች ተከራካሪና ጠበቃ በመሆን ሲያገለግል የነበረው አቶ አስናቀ ደምሴ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን(ኢ.ሠ.ማ.ኮ)
ዋና ፀሐፊ የሆቴል፣የቱሪዝም ጠቅላላ አገልግሎት ፕሬዘዳንት እንዲሁም የኢ.ሠ.ማ.ኮ ፅ/ቤት የህግ ክፍል ኃላፊ በመሆንም አገልግሏል።
አቶ አስናቀ ደምሴ በህይወት ዘመኑ አሁሉም ተግባቢ፣ለፍትህና ለዕውነት የቆመ፣የሠዎች ጥቃት የሚያንገበግበው ደግና ሩህሩህ ሠው ነበር።
የሀትሪክ ድረ-ገፅ፣የሀትሪክ ጋዜጣና መፅሔት ዝግጅት ክፍል በአስናቀ ደምሴ ህልፈተ ህይወት የተሠማቸውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፁ ለቤተሰቦቹ፣ለጓደኛቹ፣ለሙያ ባልደረቦቹና ለስፖርት ቤተሰቡ መፅናናትን እየተመኘን አምላክ ነፍሱን ከደጋጎች ጎን እንዲያሳርፍ አብዝተን እንለምናለን።

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.