የጨዋታ ዘገባ | ወልቂጤ ከተማ ከጅማ አባ ጅፋር ነጥብ ተጋርተዋል!

 

በመጀመሪያው ሳምንት የ ቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ ነጥብ የጣሉት ሁለቱ ቡድኖች በዚህ ሳምንት ሲገናኙ ጨዋታቸውን ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ለማጠናቀቅ ችለዋል ።

በወጣት ተጫዋቾች እና ልምድ ባካበቱ ተጫዋቾች እየተገነባ የሚገኘው የደግ አረገ ይግዛው ስብስብ በዛሬው ጨዋታ በአመዛኙ ጥሩ እንቅስቃሴን ቡድኑ ሲያሳይ ለተመልካች አሰልቺ የሆነ ጨዋታ ሆኖ አልፏል ። የፓውሎስ ጌታቸው ስብስብ ጅማ አባ ጅፋር በመጀመሪያው ሳምንት ገጥሟቸው ከነበረው የግብ ጠባቂ ችግር የተላቀቁ በሚመስል ሆኔታ ወደ አሰላለፉ ጃኮ ፔንዞን አስገብተዋል ።

 

በጨዋታው ላይ ወልቂጤ ከተማዎች በግራ መስመር በረመዳን የሱፍ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ሲሞክሩ በተደጋጋሚ ሲታይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃ ላይም ረመዳን የሱፍ ሞክሮት የግብ አግዳሚው የመለሰችባቸውን ሙከራ የምታስቆጭ ነበር ።

ከዚህ ሙከራ በኋላ እምብዛም በሙከራዎች ያልታጀበ እና በተቆራረጠ የኳስ ፍሰት ጨዋታው ሲቀጥል ጅማ አባ ጅፋር በመልሶ ማጥቃት እና በረጃጃም ኳሶች ወደ ግብ ለመቅረብ ሲሞክሩ ተስተውለዋል ።

በሁለተኛው አጋማሽ ወጣቱን ተስፈኛ ያሬድ ታደሰን ቀይረው ማስገባት የቻሉት ወልቂጤዎች የተሻለ እንቅስቃሴን ማሳየት ሲችሉ በተደጋጋሚ ወደ ግብ መቅረብ ችለውም ነበር ።

በሁለተኛው አጋማሽ ወልቂጤዎች የሚያስቆጩ አጋጣሚዎችን ሲያባክኑ በተለይም የፊት መስመር አጥቂው አህመድ ሁሴን ሞክሯት የግቡ አግዳሚ የመለሰችበት የግብ ዕድል የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች ። ወልቂጤዎች ከዚህ በተጨማሪም በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ በገባው አብድራህማን ሙባረክ ከርቀት አክርሮ የሞከራት እና የግቡ የላይኛው አግዳሚ የመለሰበት ሙከራ ሌላኛው የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር ።

ውጤቱን ተከትሎ ጅማ አባጅፋር በደረጃ ሰንጠረዡ በአንድ ነጥብ አስረኛ ሲቀመጡ በተቃራኒው ወልቂጤ ከተማ በሁለት ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዘው በጊዜያዊነት መቀመጥ ችለዋል ።

Hatricksport website Editor

Twitter

kidus Yoftahe

Hatricksport website Editor