የጨዋታ ዘገባ | ኢትዮጵያ ቡና የውድድር አመቱን የመጀመሪያ ድል አስመዝግቧል

በቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የሁለተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ 4፡00 ላይ ኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከተማን ያገናኘ ሲሆን በጨዋታውም ኢትዮጵያ ቡና 3-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

በመጀመሪያው ሳምንት ፋሲል ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስን በማሸነፍ ኢትዮጵያ ቡና ደሞ ከወልቂጤ ከተማ ጋር አቻ ተለያይተው በመምጣታቸው ፋሲል ከነማ ሁለተኛ ድሉን ለማስመዝገብ ኢትዮጵያ ቡናም ወደ ድል ለመመለስ ከባድ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ሲጠበቅ  ኢትዮጵያ ቡና በጨዋታው የበላይነቱን ይዘው አጠናቀዋል።

በጨዋታው የመጀመሪያውን ሙከራ በማድረግ ኢትዮጵያ ቡና ቀዳሚው የነበረ ሲሆን 12ኛው ደቂቃ ላይ አለምአንተ ካሳ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ተመስገን ካስትሮ በግንባሩ ሲገጨው አቤል ከበደ ወደ ግብ ቢሞክረውም በግቡ ቋሚ ወደ ውጭ ወጥቶበታል። ከዚህች ሙከራ 3 ደቂቃዎች በኋላ 15ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከተማው ሱራፌል ዳኛቸው የኢትዮጵያ ቡና ግብ ክልል አካባቢ ያገኝውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሲሞክረው በተከላካይ ተጨራርፎ በዛብህ መለዮ ጋር የደረስ ቢሆንም ወደ ግብ ሞክሮት ወደ ውጭ ወጥቶበታል።

ፋሲል ከተማዎች በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋሉ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ 22ኛቅ ደቂቃ ላይ በኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል አካባቢ የተገኘውን ቅጣት ምት ሱራፌል ዳኛቸው በቀጥታ መቶት የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ተ/ማርያም ሻንቆ በድንቅ ሁኔታ አውጥቶበታል።

በጨዋታው 34ኛ ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ተከላካይ አበበ ጥላሁን በረጅም ያሻገረውን ኳስ ታፈሰ ሰለሞን ኳሷን በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ወደ ግብነት ቀይሯት ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ሆኖም ግን ይህ መሪነት መዝለክ የቻለው ለ4 ደቂቃዎች ብቻ ሲሆን ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በዛብህ መለዮ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይሮ ፋሲል ከተማን አቻ በማድረግ የመጀመሪያው አጋማሽ በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።


ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በመጀመሪያው ደቂቃ (46ኛው ደቂቃ) የጨዋታውን መልክ ሊቀይር የሚችል ሁነት የተፈጠረ ሲሆን የኢትዮጵያ ቡናው ተመስገን ካስትሮ የፋሲል ከተማው አጥቂ ሙጂብ ቃሲም ላይ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል። ሆኖም ግን ፋሲል ከተማዎች የተጫዋች ብልጫ መጠቀም ተስኗቸው ተስተውሏል።

55ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር የፋሲል ከተማ ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ ያገኘውን ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር 1-1 ተገናኝቶ የነበረ ቢሆንም የፋሲል ከተማው ግብ ጠባቂ ሚካኤል ሳማኪ በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሚካኤል ሳማኪ አቡበከር ናስር ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍጹም ቅጣት እራሱ መቶት ወደ ግብነት ቀይሮት ቡድኑን በድጋሚ ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

65ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ሰለሞን እና አቡበከር ናስር በግሩም ቅብብል የፋሲል ከተማ ግብ ክልል ውስጥ ከተገኙ በኋላ አቡበከር ናስር ያሻገረውን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ አስቆጥሮት የኢትዮጵያ ቡናን መሪነት ወደ 3 ከፍ ማድረግ ችሏል።

ከዚህች ግብ መቆጠር በኋላ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳይደረግበት ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 3-1 አሸናፊነት መጠናቀቅ ችሏል። ይህንን ተከትሎም ድል የቀናው ኢትዮጵያ ቡና 4ነጥቦችን በመሰብሰብ የሊጉ አናት ላይ መቀመጥ ሲችል የተሸነፈው ፋሲል ከተማ ደግሞ 3ነጥቦችን ይዞ 7ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website

Facebook

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website