“ፋሲል ከነማን የሚመጥነው ሻምፒዮናነት ብቻ ነው” አምሳሉ ጥላሁን /ሳኛ/ /ፋሲል ከነማ/

የፋሲል ከነማ እና የኢትዮጵያ ቡና ተጠባቂው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ዛሬ ከ4 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታድየም ይካሄዳል፤ ፋሲል ከነማ የመጀመሪያ ሳምንት የሊግ ጨዋታውን ቅ/ጊዮርጊስን በሙጂብ ቃሲም ብቸኛ ግብ በማሸነፍ ከመሪዎቹ ክለቦች ተርታ ለመሰለፍ የቻለ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያደረገውን ጨዋታ በአቡበከር ናስር ሁለት ግቦች ሲመራ ከቆየ በኋላ ግጥሚያውን በአቻ ውጤት ሊያጠናቅቅ ችሏል፡፡

የፋሲል ከነማ እና የኢትዮጵያ ቡናን ጨዋታ አስመልክተን እንደዚሁም ደግሞ ባሳለፍነው ሳምንት ፋሲል ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስን ድል ስላደረገብ ጨዋታ እንደዚሁም ደግሞ ከቡድናቸው ጋር በተያያዘ የክለቡን የግራ መስመር የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች አምሳሉ ጥላሁንን /ሳኛ/ የሀትሪክ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አጠር ባለ መልኩ አናግሮታል፤ ቃለ-ምልልሱም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡

ሀትሪክ፡- የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታችሁን በድል ጀምራችኋል፤ ያሸነፋችሁትም ቅ/ጊዮርጊስን ነው፤ ስለ ጨዋታው ምን ትላለህ?

አምሳሉ፡- ባሳለፍነው ሳምንት ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ያደረግነው ጨዋታ እንደ መጀመሪያ እና እንደ መክፈቻ ግጥሚያችን ውጤቱን በጣም ፈልገነው ስለነበር ከመደበኛ አጨዋወታችን ወጣ ባለ መልኩ እና የጨዋታ ቅርፃችንንም በለቀቅንበት ሁኔታ ነበር ስንንቀሳቀስ የነበርነው፤ በምንፈልገው መልኩም ጥሩ ለመጫወት አልቻልንም፤ ይሄ ሁሉ ሊሆን የቻለውም የድል ውጤቱን ከመፈለግ አኳያ ጭንቀት ውስጥ ስለገባንም ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ጥሩ ያልተጫወታችሁት እናንተ ብቻ ናችሁ ወይንስ ቅ/ጊዮርጊሶችም ጭምር?

አምሳሉ፡- ሁለታችንም ነን ጥሩ ያልተጫወትነው፤ የመጀመሪያ የሊግ ግጥሚያችን ስለሆነም መሰለኝ በምንፈልገው መልኩ ልንንቀሳቀስ ያልቻልነው፡፡

ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስን ለማሸነፍ የቻላችሁበት ጠንካራው ጎናችሁ ምን ነበር? የድል ውጤቱስ ለእናንተ ይገባ ነበር?

አምሳሉ፡- አዎን፤ ከእንቅስቃሴ አንፃር በምንፈልገው መልኩ ለመጫወት ባንችልም ከእነሱ ግን እኛ እንሻል ስለነበርን ነው ልናሸንፋቸው የቻልነው፤ እነሱን ለማሸነፍ እንድንችልም እኛ የነበረን ጠንካራ ጎን ሜዳ ላይ ያለንን ሰጥተን ስለተጫወትን፤ ተከላካዮቻችን ጠንካራ እና አይበገሬ ሆነው የቅ/ጊዮርጊስ ስመ ጥር አጥቂዎችን አላፈናፍን ስላሉ ያ ነው ለድል ያበቃን ፡፡

ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስን በማሸነፋችሁ በጣም ተደሰታችሁ?

አምሳሉ፡- ከሚገባው በላይ ነዋ! ምክንያቱም ቅ/ጊዮርጊስ በጣም ትልቅ ቡድን ነው፤ በዛ ላይ ጨዋታውን ያሸነፍነው በመክፈቻው ቀን ግጥሚያም ነው፤ ይሄ ሆኖ ሳለ ደግሞ ከእዚህ ጊዜ ጀምሮ የሚያዝ ነጥብ በጣሙን የሚጠቅመን ስለሆነም ነው ልደሰት የቻልኩት፤ ከዛ ውጪም ደስታዬን ለየት ያደረገው ይሄን የሊግ ጨዋታ ያደረግነው በኮቪድ የተነሳ ላለፉት 7 እና 8 ወራቶች ከሜዳ ርቀን በመጣንበት ወቅትም ስለሆነ ሊጉን በአሸናፊነት መጀመራችን ለእኛ ትልቅ ነገር ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡናን በወሳኙ እና በተጠባቂው ጨዋታ ዛሬ ትፋለሙታላችሁ፤ ምን ውጤት ይጠበቅ? ስለ ጨዋታውስ ምን ትላለህ?

አምሳሉ፡- ቅ/ጊዮርጊስን በመክፈቻው ግጥሚያ አሸንፈን ከመምጣታችን አንፃር ከቡና ጋር የምናደርገው የዛሬ ጨዋታ ፈፅሞ አይከብደንም፤ ፋሲል በመጀመሪያው ጨዋታ ማሸነፉ በጥሩ ሞራል ወደ ሜዳ እንዲገባ ያደርገዋል፤ የራስ መተማመኑንም ይጨምርለታልና በሁለታችንም መካከል የሚደረገው የዛሬ ጨዋታ ሁለታችንም አንድ አይነት እንቅስቃሴን ከመከተላችን አኳያ ጥሩ ፉክክር የሚታይበት ይሆናል፤ እንደዛም ሆኖ ግን የእኛ ቡድን በፕላን ቢ ደረጃ የሚጠቀምበት አጨዋወት ስላለው በመጨረሻም የግጥሚያው አሸናፊ ፋሲል ከነማ ይሆናል፡፡

ሀትሪክ፡- ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የምታደርጉት የከዚህ ቀደም ጨዋታ በጣም የሚጠበቅ እና የተለየ ግምት የሚሰጠው ነበር፤ የዛሬውስ?

አምሳሉ፡- ከበፊት አኳያ ይሄን ዛሬ ላይ አልጠብቀውም፤ ኢትዮጵያ ቡና ከፋሲል ከነማ፤ ፋሲል ከነማም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያደርጉት የነበረው የከዚህ ቀደም ጨዋታ በሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን በተጨዋቾቻቸውም መካከል በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቅ ነበር፤ ይባስ ብሎም ጎንደር እና አዲስ አበባ ላይ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ላይም አንዱ ለአንዱ ጥሩ እና ደማቅ አቀባበልን ያደርጉ እና አካባቢያቸውን በዓል ሁሉ ያስመስሉት ነበር፤ ከዛ ውጪ ሁለቱ ቡድኖች በፍቅር የተሳሰሩም ነበር፤ ያ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከኮቪድ አንፃር ብዙ ተመልካች ወደ ሜዳ ስለማይገባ አሁን ላይ ከ90 ደቂቃ ጨዋታ ውጪ የተጠባቂነት ድባቡን ያጣ ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- በእዚህ ዓመት ምን ውጤትን ታመጣላችሁ ብለን እንጠብቃቸሁ?

አምሳሉ፡- የሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታችንን ቅ/ጊዮርጊስን በማሸነፍ በድል ከፍተናል፤ ዛሬ ደግሞ ቡናን በመርታት አሸናፊነታችን ይቀጥላል፤ ፋሲል ከነማ ትልቅ ቡድን ከመሆኑ የተነሳም የዓመቱ የሊግ ውድድር ሲጠናቀቅ እኛን የምትጠብቁን ዋንጫውን ጨብጠን ስንጨፍር ነው፤ ከዛ የሚያንስ ውጤት ደግሞ ቡድናችንን እንደማይመጥነው ልናገር እፈልጋለው፡፡

ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ ምርጥ የተጨዋቾች ስብስብ ነው ያለው?

አምሳሉ፡- ከሞላ ጎደል አዎን፤ እንደዛም ሆኖ ግን ቡድናችን በአጥቂው መስመር ላይ የሙጂብ ቃሲም ጥገኛ ስለሆነ እሱን የሚያግዙ ሁለት ተጨዋቾች እንደሚያስፈልጉን እርግጠኛ ሆኜ ልናገር እፈልጋለው፡፡

ሀትሪክ፡- ለፋሲል ከነማ ዘንድሮ ምን ልታበረክትለት ዝግጁ ነህ?

አምሳሉ፡- ፋሲል ከነማ ለእኔ ብዙ ነገርን ያደረገልኝ የምወደው ክለቤ ነው፤ ያ ስለሆነም በእዚህ ዓመት በሚኖረኝ የቡድኑ ቆይታ ክለቡን ውጤታማ በሚያደርግ መልኩ ያለኝን ሁሉ ልሰጥ ተዘጋጅቻለው፡፡

ሀትሪክ፡- ኮቪድ ወደ አገራችን መግባቱን ተከትሎ ላለፉት 7 እና 8 ወራቶች ከሜዳ ለመራቅ ችለህ ነበር፤ እነዛን ጊዜያቶች እንዴት አሳለፍክ?

አምሳሉ፡- ያለ ኳስ ከሜዳ መራቅ ያልጠበቅኩት ሁኔታ ስለነበር በወቅቱ ከባድ ጊዜያቶችን ነበር ሳሳልፍ የነበረው፤ እንደዛም ሆኖ ግን ከባዱን ወቅት ራሴን ለዘንድሮ የውድድር ዘመን ብቁ አድርጌ ለማቅረብ በግሌ ስዘጋጅበት የነበረበት ሁኔታ ስላለ ያ ለአሁን ቡድን ግልጋሎቴ የሚሰጠኝ ጥቅም አለ፡፡

ሀትሪክ፡- እስካሁን ያለ አንድም የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ሳታሳካ አለህ፤ አይቆጭህም?

አምሳሉ፡- በጣም ነው እንጂ የሚያስቆጨኝ፤ ዓምና ይሄን ድል ለማሳካት እድሉ ይኖረን ነበር፤ ግን ኮቪድ ውድድሩን አቋረጠው፤ ካቻምና ደግሞ ዋንጫውን ለማንሳት ከጫፍ ደርሰንና በደል ተሰርቶብንም መቐለ 70 እንደርታ ሻምፒዮና እንዲሆን ተደረገ፤ ስለዚህም ይህን የዋንጫ ቁጭቴን በእዚህ ዓመት ከፋሲል ከነማ ጋር ድል በመቀዳጀት አህምሮቴን የምወጣው ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የፋሲል ጠንካራ ጎኑ ምንድን ነው?

አምሳሉ፡- ህብረቱ ነዋ! ሁሉም ተጨዋች ወደ ሜዳ ሲገባ አቅሙን አውጥቶ ነው የሚጫወተው፤ የሚሳሳው ምንም ነገርም የለም፤ ከዓመት ዓመት የአሸናፊነት መንፈስንም ይዞ ነው የሚመጣው፤ አሸናፊነቱንም በዓል እያደረገው ስለመጣ ይሄ ሊነገርለት የሚገባ ጥሩ ጎኑ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን በቱኒዚያው ክለብ ተሸንፋችሁ ከውድድር ወጣችሁ? ምክንያቱ ምን ነበር?

አምሳሉ፡- ወደ ፍፁም ቅጣት ምት /መለያ ምት/ ልናመራ በተቃረብንበት አጋጣሚ ነው ድንገት በሜዳችን ላይ በተቆጠረብን ግብ በአጠቃላይ ውጤት በአሳዛኝ መልኩ ተሸንፈን ከውድድሩ ልንወጣ የቻልነው፤ ፋሲል ወደ ተከታዩ ዙር የሚያልፍበት እድሉ ነበረው፤ ግን ኳስ ሆነና ከውድድሩ ወጣ፤ እነ ሊቨርፑልን ባርሴሎናን የመሳሰሉ የዓለም ሀያላን ክለቦች ከእዚህ በፊት እንዲህ ባለ መልኩ ከውድድር የተሰናበቱበት አጋጣሚም ነበርና ያን ጭምር ነው ያስታወሰኝ፤ ለፋሲል ከውድድሩ መሰናበት ሌላው በምክንያትነት ልጠቅሰው የምፈልገው ራሳችን ጥሩ ሆነን ሳለን እነሱን አግዝፈን ስለምንመለከትም ጭምር ነው፤ ከዛ በተጨማሪም ለግቡ መቆጠር ምክንያት የነበረውም የእኛ በረኛ እና የእነሱ አጥቂ በተጋጩበት ጊዜ በእነሱ ተጨዋች ላይ ጆሮው አካባቢ ተጎድቶ ነበርና ብዙ ደም ሊፈሰው በመቻሉ ያ ጥሩ ያልሆነ ስሜትን በቡድናችን ተጨዋቾች ላይ አለመረጋጋትን ሊፈጥርም በመቻሉ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በዲ.ኤስ.ቲቪ ስለመተላለፉ ምን አልክ?

አምሳሉ፡- ለኢትዮጵያ ትልቅ ነገር ነው፤ እንደ እነ ሱራፌል ዳኛቸው እና በአሁን ሰዓት ላይ ደግሞ ምርጥ ብቃቱን እያስመለከተን ላለው ሀብታሙ ተከስተ /ጎላን/ ለመሳሰሉ ተጨዋቾች እንደዚሁም እኔን ጨምሮ ለሌሎችም የአገራችን እግር ኳስ ተጨዋቾች ወደ ባህር ማዶ በመሄድ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት የምንጫወትበትን እድል ስለሚፈጥርልን ከዛ በተጨማሪ ደግሞ የግጥሚያው መተላለፍ አቋማችን በምን ደረጃ ላይም እንዳለ ስለሚያስመለከትተንም አጋጣሚውን ጠንክረን በመስራት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…?

አምሳሉ፡- ኢትዮጵያ ቡናን ዛሬ እናሸንፋለን፤ የዓመቱ መጨረሻ ላይ ደግሞ የቤትኪንግ ዋንጫን ከፍ አድርገን ስለምናነሳ ታሪካዊ ቡድን እንባላለን፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website