የቀድሞው ግብ ጠባቂ ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ የሚውል ማቴሪያል ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ረዳ

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ በወጣትነት ዕድሜው ከ1980ዎቹ የመጨረሻ ዓመታቶች አንስቶ እስከ 1990ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታቶች ላይ በክለብ ደረጃ ለኪቤአድ፣ ለኒያላ፣ ለሳቢያን ብረታ ብረት፣ ለአየር መንገድ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈውና በአሰልጣኝ ስዩም አባተ /ነፍስ ይማር/ ለሚመራው የወጣት ቡድን ከተመረጠ በኋላ በእዛው ዓመት ላይ ከሀገር በመውጣት ኑሮውን በጣሊያን ሀገር ያደረገው የቀድሞው የኪቤአድ፣ የኒያላ፣ የሳቢያን ብረታ ብረት፣ የአየር መንገድ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ የቀድሞ ግብ ጠባቂ አንድነት በቀለ /ቀዬ / በእዚህ ሳምንት ውስጥ ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ የሚሆን ግምቱ ወደ 200 ሺህ ብር የሚያወጣ የማቴሪያል ድጋፍ ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አድርጓል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታውን የተለያዩ ክለቦች ውስጥ በግብ ጠባቂነት በመጫወት ያሳለፈው አንድነት በቀለ ለሆስፒታሉ ያደረገው የማቴሪያል ድጋፍና እርዳታ የአሁን ሰዓት ላይ ለዓለምም ሆነ ለሀገራችን ከፍተኛ ስጋት ሆኖ የበርካታዎችን ህይወት እየቀጠፈ ላለው እና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችንም ለህመም እየዳረገ የመጣውን የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እንዲቻል በማሰብ ቫይረሱ ወደ አገራችን መግባቱን ተከትሎ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሀገር ወዳድ ሁሉ እሱም ኮሮና ቫይረስን በጋራ ለመከላከል እንዲቻል ያደረገው የማቴሪያል ድጋፍ ዶክተሮች በሽተኛውን በሚያክሙበት ጊዜ ህመምተኞቹ አፋቸውን በሀይል ስለሚከፍቱ ባክቴሪያው ወደ ዶክተሩ እንዳይሄድ የሚያደርግ እና ቫይረሱም ከአንዱ ወደ አንዱ እንዳይተላለፍም የማድረግ እና ብሎም ደግሞ የአሁን ሰዓት ላይ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኙ ምክንያትም ህክምናን እየሰጡ ያሉ በርካታ የዓለም ዶክተሮችም ሙያዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ባለበት ሁኔታም የቫይረሱ ተጠቂ ሆነው ህይወታቸውን እያጡ ያለበት ደረጃ ላይም በመደረሱ ከወዲሁ በእኛ ሀገር ከቫይረሱ ለመከላከል የሚቻልበትን እርዳታ ተጨዋቹ ማድረጉ ነው የተገለፀው።

በግብ ጠባቂነት ሙያው በተለያዩ ክለቦች ውስጥ ገብቶ ሲጫወት የሚታወቀው አንድነት በቀለ ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ የማቴሪያል ድጋፍን በማድረጉ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከፍተኛ ምስጋና የቀረበለት ሲሆን ያበረከተው ማቴሪያልም ጥቅሙ ከፍተኛ እና ጥሩ ሆኖ በመገኘቱም ኮተቤ ለሚገኘው ቅርንጫፍ መስሪያ ቤትም ሌላ አቅርቦት እንዲያደርግም ጥሪው እንደቀረበለትም ተገልጿል። የቀድሞው ተጨዋች በእስካሁን የህይወት ዘመን ጉዞው ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን ለቡ መብራት ሀይል እና ሀና ማሪያም አካባቢ በከፈተው የመስታወት ፋብሪካም ቀደም ባሉት ጊዜያት ለሀገር ትልቅ ውለታ ሰርተው ያለፉና እንደልፋታቸውም የተረሱ እና የተቸገሩ ቁጥራቸው እስከ 10 እና 12 የሚደርሱ ተጨዋቾችንም በድርጅቱ ውስጥ በመቅጠር እና በመርዳት ሙያዊ ስራ እያሰራቸው እና ህይወታቸውንም እንዲለውጡም እያደረጋቸው መሆኑም ታውቋል።

በጣሊያን ሀገር ኑሮውን ካደረገ በኋላ የአሁን ሰዓት ላይ እዚሁ እየኖረ እና ለስራ ጉዳይም ወደ ጣሊያን በመመላለስ ላይ የሚገኘው አንድነት በቀለ የራሱን ድርጅት ከከፈተ በኋላ ስለሚያደርጋቸው የበጎ አድራጎት ተግባራት ብዙም እንዲነገርለት የማይፈልግ ተጨዋች ቢሆንም እኛ ሰሞኑን ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ ያደረገውን ድጋፍ በመስማታችንና እና በማረጋገጣችን እንደዚሁም ደግሞ የቀድሞ ስፖርተኞችንም በማገዙ በኩል ለሚሰራቸው ስራዎች በሀትሪክ ስፖርት ድረ ገፅ ስም ምስጋናን ልናቀርብለት እንፈልጋለን።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website