መነሻ ገጽ Oldies but Goodies  “ኢትዮጵያ ቡና ክብርም ፍቅርም ያገኘሁበት ክለብ ነው”ገ/ኪዳን ነጋሽ /ጋምብሬ/
Oldies but Goodies ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣብቸኛዋ ባለቀለም የስፖርት ጋዜጣ

“ኢትዮጵያ ቡና ክብርም ፍቅርም ያገኘሁበት ክለብ ነው”ገ/ኪዳን ነጋሽ /ጋምብሬ/

አጋራ
አጋራ

በመሸሻ ወልዴ
በኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ ለረጅም ዓመታት ተጫውቶ አሳልፏል፤ በክንፍ ስፍራም ላይ በመጫወት 
የእኛ ሀገር ምርጥ የኮሪደር ስፍራ ተጨዋች የሚል ስያሜንም አግኝቷል፤ አዎን፤ ገ/ኪዳን ነጋሽ /ጋምብሬ/ን ብዙዎች አሁንም ድረስ ነው የቀድሞ ብቃቱን በማድነቅም ሲያወድሱት የምናደምጠው፤ ጋምብሬ በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኑ ከቡና ውጪ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ለአየር መንገድ፣ ለኢትዮጵያ መድንና ለትራንስ ኢትዮጵያም ተጫውቶ አሳልፏል፤ በብቃቱ የብዙዎችንም ቀልብ ገዝቷል፤ የኢትዮጵያ ቡናው 
የቀድሞ የኮሪደር ስፍራ ተጫዋች ጋምብሬ ኳሱን ካቆመ አሁን ረጅም ጊዜያትን እያስቆጠረ ሲሆን ከቡና 
ክለብ ባለቅ ኖሮ ኳሱን ሳላቆም ለረጅም ዓመታት የምጫወትበትም ዕድሉ ይኖረኛል ሲልም አስተያየቱን 
ይሰጣል፤ ጋምብሬ ኳሱን ካቆመ በኋላ በአሁን ሰአት ታዳጊ ወጣቶችን በኃላፊነት በመምራት በማሰልጠን 
ላይ ሲሆን ይህንን የቀድሞ ዝነኛ ተጨዋች ስላሳለፈው አስገራሚ የኳስ ህይወቱና ሌሎችንም የኳስ 
ገጠመኞቹን አንስተን አውግተነዋል፤ እሱም የሚከተለውን ምላሹን ሰጥቶናል፡፡​

በእግር ኳስ በጣም የተደሰተበት 
ቀን፦በኢትዮጵያ እግር ኳስ በተጫዋችነት 
በቆየሁባቸው ጊዜያቶች በጣም የተደሰትኩበትና 
ዛሬም ድረስ ከውስጤ ፈፅሞ ያልጠፋ የደስታ 
ስሜት የፈጠረብኝ የኢትዮጵያ ሻምፒዮናን በ1990 
ዓ.ም ያነሳንበት ወቅት ነው፤ ጨዋታው ከመብራት 
ኃይል ጋር ሲሆን የክረምት ወራት በመግባቱ 
ምክንያት ከ1989 ዓ.ም የውድድር ዘመን የዞረ 
ነበር፤ በጨዋታው ቡድናችን መብራት ኃይልን 
1-0 በማሸነፍ ነበር ዋንጫውን ያነሳውና በሜዳ 
ላይ ከነበረን ምርጥ ቡድንና እንደዚሁም ደግሞ 
ከያዝናቸው ኳስን በአስገራሚ ክህሎት ከሚጫወቱ 
ተጫዋቾች አኳያ ስመለከተው የተሰማኝ ስሜት ከፍ 
ያለ ነበርና እንደዚያ አይነት ጥሩና አስገራሚ የሆነ 
ቡድን በኳስ ህይወቴም አጋጥሞኝም አያውቅም፡፡ 

በእግር ኳስ በጣም ያዘነበትና ልቡ የተሰበረበት 
ቀን፦
የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች እያለሁ የቡድናችን 
ምርጥ ተጫዋች በነበረው አባይ ሰለሞን /ሪኒ/ ላይ 
የእግር መሰበር አደጋ ደርሶበት የተመለከትኩበት 
መጥፎ አጋጠሚ ነው፤ ያኔ /ሪኒ/ የተሰበረው 
ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስንጫወት በሁለተኛው 
አጋማሽ ነበር ጉዳቱን ያስተናገደው፤አጋጣሚውን 
ለእኔ በጣም መጥፎ ያደረገው ደግሞ ጉዳቱ ሲደርስ 
እኔ አጠገቡ መሆኔ ነው፡፡ ከአባይ ሰለሞን /ሪኒ/ 
የከፋ ጉዳት በተጨማሪ ሚልዮን በጋሻውም በዚህ 
ጨዋታ ላይ እንዲሁ ተፈንክቶም ነበርና ያ አስከፊና 
የሚደብር አጋጣሚ ስለነበር ያንን ግጥሚያ ሁሌም 
በሃዘን የማስታውሰው ነው፡፡ 

እግር ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮ በምን ሙያ 
እናገኝህ ነበር፦
አላውቅም ፤ከህፃንነቴ አንስቶ ኳስ 
ተጫዋች ስለመሆን ብቻ ነበር አስብ የነበረው፤ ሌላ 
ነገር ፈፅሞም አዕምሮዬ ውስጥ የለም። በአንድ 
ወቅት ላይ ግን ልጅ ሆኜ የእናቴ ወንድም የሆነው 
አጎቴ ጨርቆስ አካባቢ ጋራዥ ነበረውና እናቴ እዚያ 
እንድውልና ሙያ እንድማር ትፈልግ ነበር፤ ወደ 
ጋራዡ በጠዋት ሄድኩ ነገር ግን ወቅቱ ክረምት 
ነበርና ዝናብ ማካፋት ጀመረ በመሃል ይሄንን 
እቃ አምጣ ሲሉኝ እኔ ውስጥ የነበረው ሃሳብ 
ኳስና ኳስ ስለነበር 10 ደቂቃ ሳልቆይ ጠፍቼ ወደ 
ሰፈሬ ሄድኩና ኳስ መጫወቴን ቀጠልኩ፤እነዚህን 
ነገሮችን ስታዩ ለኳስ የተፈጠርኩ ሰው ብቻ 
መሆኔን እወቁልኝ፡፡ 

የጫዋታ ዘመኑ ምርጥ ግብ፦ማራኪ በነበረው 
የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ ስጫወት የጉና 
ንግድን 4-0 ስናሸንፍ ያስቆጠርኳቸው ሁለቱም 
ግቦች ለእኔ ምርጦች ነበሩ፤ አሁንም ድረስ እነዚያን 
ግቦች ያሰቆጠርኩበትን ሁኔታ ወደኋላ ተመልሼ 
ሳስታውሰው የተለየ የደስታ ስሜትም ይሰማኛል፡፡ 

የእስካዛሬው የተጫዋችነት ዘመኑ ምርጥ 
ጨዋታ፦
የኢትዮጵያ ቡናና የኢትዮጵያ ብሄራዊ 
ቡድን ተጫዋች ለነበረውና ያን ወቅት ላይ በሞት 
ለተለየው ዮናስ ተፈራ የተዘጋጀው የመታሰቢያ 
ግጥሚያ ላይ በማታ በፓውዛ ተጫውተን ቅዱስ 
ጊዮርጊስን 4-0 ያሸነፍንበት ግጥሚያና የግብፁን 
አል-አህሊ ካይሮ ላይ በአፍሪካ ሻምፒንስ ሊግ 
1990 ላይ ገጥመን 2-2 በመለያየት ወደተከታዩ 
ዙር ያለፍንበት ጨዋታ ለእኔ ከእስከዛሬው 
የኳስ ህይወቴ ምርጥ የምለው ግጥሚያ ነው፡
፡ የእግር ኳስን ጥበብ በእነዚያ ጨዋታዎች ላይ 
አሳይተንበታል፡፡ በወቅቱ ባገኘናቸው የሁለቱም 
ጨዋታዎች ውጤታማነትም በጣሙን ልደሰትበት 
ችያለሁ፡፡ 

የጫዋታ ዘመኑ ምርጥ አሰልጣኝ፦ምንም 
ጥያቄ የለውም ለኳስ ውበትና ማማር የሚጨነቀው 
ስዩም አባተ የእኔ የምንጊዜውም ምርጡ አሰልጣኝ 
ነው፤ እድሜ ልኬን ሳደንቀውም እኖራለሁ፡፡ ከእሱ 
ቀጥሎ የሚል ጥያቄ ካለ ደግሞ ወርቁ ደርገባና 
ገ/መድን ኃይሌን ሌላ የማደንቃቸው አሰልጣኞች 
ናቸው፡፡ 

የጫዋታ ዘመኑ ምርጥ ተጨዋች፦የኢትዮጵያ 
ቡና ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ ስጫወት የቡድኔ አጋር 
የነበረውና በምርጥ ተጨዋችነትም የማደንቀው 
ተጨዋች ቢኖር ካሳዬ አራጌ /ኢኒጂነር/ ነው እሱ 
በችሎታው የተለየና ኳስንም አስቦ የሚጫወት ነው፤ 
ኳስ ሲያቀብል መሳሳትን ብዙ አትመለከትም፡፡ ኳስ 
ሸፍኖ ሲጫወት ይገርምሃል ከእዚያ በላይ ለቡድኑ 
ሟችም ነውና ለእኔ ከተመለከትኳቸው ውስጥ 
ምርጡ ተጨዋች ነው፡፡ 

በጫወታ ዘመኑ ያስቸገረው ተጨዋች፦ማንም 
የለም፤ ለእኔ ሁሉም ነገር ቀሎኝ ነበር ስጫወት 
የነበረው፡፡ 

በጫዋታ ዘመኑ አብሮት ባለመጫወቱ 
የሚቆጨው፦
በእኛ አገር አለ ብዬ 
አላስብም፤ከአብዛኛዎቹ ጋር ተጫውቼ 
አሳልፌያለሁ፤ምክንያቱም በክለብ ደረጃም ሆነ 
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ደረጃ ከተጫወትኳቸው 
ውስጥ ለምሳሌ እንኳን ብጠቅስ ከካሳዬ አራጌ፣ 
ከጥላሁን መንገሻ፣ ከአብዱራዛቅ አብዱራህማን፣ 
ከአሸናፊ በጋሻው፣ ከሙሉጌታ ከበደ፣ ከኤልያስ 
ጁሃር፣ ከአሰግድ ተስፋዬና ከአንዋር ያሲንና 
ከመሳሰሉት ጋር አብሬ ተጫውቼ አሳልፌያለሁና 
የሚቆጨኝ ነገር ምንም የለም፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ማየትና መስማት 
የማይፈልገው፦
በስቴድየም ውስጥ የሚታየው 
የከፋ ፀብ ድብድብና አስፀያፊ ስድቦችን መስማትም 
ማየትም አልፈልግም፡፡

-ገ/ኪዳን ራሱን በ3 በተመረጡ ቃላቶች ሲገልፅ፦ 
ለሰዎች ጥሩ አስባለው፤ መጨቃጨቅ አልወድም፤ 
ፍራቻ ውስጤ የለም፡፡

-ከእግር ኳስ ህግ አጥብቆ የሚጠላው፦የእግር 
ኳስ ጫወታ ላይ የምጠላው ነገር ቢኖር የእጅ 
ውርወራን ነው፤ ኳስ እንዴት በእጅ ትያዛለችም ብዬ 
አስባለው፤ የእኛ አገር ላይ ከእዚህ በፊት ለጨዋታ 
ልንገባ ስንልም ሆነ የልምምድ ላይ ስናማሙቅ 
አየሩ ብርድ ሆኖ ሁሉ ጓንትና ጃኬት ነገር እንኳን 
እንድናደርግ ሳይፈቀድልን ኳስን በእጅ ተቀባበሉ 
ሲባል ሁሉ ይደብረኝ ነበርና ኳስ ከእዚህ በኋላ ወደ 
እጅ ፎሪ ሲወጣ ኳሱን በእግር መተነው ብንጀምረው 
ጥሩ ነው፡፡

እግር ኳስ ተጫዋች ሆኖ በማለፉ ምን ትርፍ 
አግኝተሃል፦
በጣም ብዙ ነገር አግኝቼበታለሁ፤ 
የሰው ፍቅር ከሁሉም ነገር ይበልጣልና ምርጥ 
ምርጥ ጓደኞችን አግኝቼቤታለው፤ ብዙ ሰውም 
አሁን ያገባዋትን ባለቤቴን ጨምሮ አውቄበታለሁ፤ 
ከእዚህ በላይ ለኳስ ተጨዋች ምን የተለየ ደስታ 
አለ ብለህ ነው፡፡

-በእግር ኳሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከፈለው 
ትልቅ ደሞዝ፦
የኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ለሲ ቡድን 
ስጫወት ለመጀመሪያ ጊዜ የተከፈለኝ ክፍያ 2 
ኪሎ ቡና ነበር ወደ ዋናው ቡድን ሳድግ የ1983 
ዓ.ም ላይ ሳድግ ደግሞ 90 ብር ተሰጠኝ ያንን 
ብር በጊዜው ያደረግኩት ከጓደኞቼ ጋር ፏ ብለን 
የተዝናናንበት ነበር፤ ብሩም የማያልቅና ትልቅ 
ዋጋም ስለነበረው የደምወዝ ክፍያው ከ2 ኪሎ ቡና 
ወደ 90 ብር ሲያድግልኝ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ 
-ደሞዙን አሁን ከሚከፈለው በወር 166 ሺህ 
ብር ጋር ሲነፃፀር ዛሬ ተጨዋች ብሆን ኖሮ ብሎ 
ያስባል?፦
በፍፁም…! በአሁን ሰአት ተጫዋቾች 
ያንን ያህል ክፍያ አገኙ ብዬ ዛሬ ላይ ተጫዋች 
ልሁንም አልልም፤ ስለዚህም የእግር ኳስ ተጫዋቾች 
አሁን የሚያገኙት ክፍያ ይገባቸዋል ነው የምለው፡፡ 
ክፍያውን ማግኘታቸው ተገቢ ነው ብልም በሜዳ ላይ 
እንቅስቃሴ ግን ብዙ ነገርን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል 
ነው የምለው፤ ተጫዋቾ ብቻ ሳይሆን ክለቦችም 
ለእግር ኳሱ መለወጥ ብዙ ነገር ሊሰሩም ይገባል፤ 
ከሚያገኙት ክፍያ አኳያ ይህ ጨዋታ መታየትም 
የለበትምና በእግር ኳሱ ላይ ሁሉም አባላት 
ተረባርበው በመስራት በጋራ እግር ኳሱን 
ልናሳድገው ይገባል፡፡ 

ኢትዮጵያ ቡና እያለ በጣም ካዝናኑህ 
ነገሮች የምትጠቅሰው ፦
በኢትዮጵያ ቡና 
ውስጥ በነበርኩበት የበርካታ አመታት ላይ ብዙ 
የሚያዝናኑና የሚያስቁ ነገሮች ነበሩ፤ ከእነዚያ 
ውስጥም በአንድ ወቅት 8 የምንደርስ ተጨዋቾች 
ወደ ዋናው ቡድን አድገን ለልምምድ እየሄድን 
ሳለ እኛ የተቀመጥንበት ሰርቪስ አካባቢ ያለው 
መስተዋት ቀደም ሲል የቡና ክለብ ከም/ጦር 
ጋር ሲጫወት የመስተዋት ሰርቪሱ ተሰብሮ 
ነበርና በምንሄድበት ቦታ ሁሉ ማማ ወደ 
ዋናው ቡድን አደገ ብለው የሚጠይቁ ልጅች 
ያጋጥሙናል ከእነዚያም መካከል የአሸናፊ 
በጋሻው ጓደኛ የሆነና የቢ ጨዋታን ብዙ 
ጊዜ የሚከታተል ሄካል የሚባል ልጅ ይህንን 
ጥያቄ ሲጠይቅ ጳውሎስ ጌታቸው ማንጎ 8 
ጥቋቁር ልጆች አድገዋል ሲል እኛ ቀደም ሲል 
ካደግነው ተጨዋቾች መካከል ኳስን ለረጅም 
ጊዜ ለተጫወተው ጳውሎስ አንተ ማብቂያ ጊዜ 
ደርሷል ዝም ብትል ይሻላል ያልንበትን ወቅት 
አልረሳውም፡፡ 

-የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ 
ስትጫወት የደስታ ምንጫቸው ስለነበረው 
ተጨዋች፦
የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋት እያለን 
የእኛን ቡድን የካምፕ መንፈስ ሁልጊዜም ቢሆን 
ደስታን የሚፈጥረለት ተጨዋች አያጣውም 
በተለይ ደግሞ ዋናው ሰው ሳምሶን ሽፈራው /
ጆሮ/ ነው፤ ጆሮ ካለ ሳቅ አለ፤ ደስታም ሁሌም 
አለን፤ እሱ መብራት ጠፍቶ ሁሉ የሚያስቀንና 
የሚያዝናናን ተጨዋች ነው የወሬ ፋብሪካም 
ነው የምንለውና እሱ ያስቀን ነበር፡፡

ስለባለውለተኛ ስፖርተኞች ምን 

የምትለው ነገር አለ፦
የኢትዮጵያ ቡና ክለብ 
ውስጥ በምጫወተበትም ሆነ ከእዚያ በኋላም 
ኳስ ሳቆም የባለውለተኛ ስፖርተኞች 
በሚታሰቡትም ሆነ በሚረዱበት ፕሮግራም 
ላይ ያልተሳተፍኩበት አጋጣሚ ኖሮ አያውቅም 
እኛ ሀገር ባለውለተኛ ስፖርተኞች ላይ ብዙ 
ስራ አልተሰራም እነሱን ሁሌ ልናስብ ይገባል፤ 
በስፖርቱ ውስጥ ብዙ ሰርተው ያለፉትንም 
ስናበረታታም መልካምነትም ነውና በእንደዚህ 
ያሉ በጎ ተግባራት ላይ መሰማራት ጥሩ ነው፡፡ 

በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኑ ዛሬም 
ድረስ የሚቆጭበት፡-
የእግር ኳስ ተጨዋችነት 
ዘመኔ በደስታ የተሞላ ነው፤ ኳሱን አፍቅሬውና 
በጣም ወድጄውም ነው የተጫወትኩት፤ 
በበርካታ የቡና ደጋፊዎችና የስፖርት 
ቤተሰቦችም ፊት ታጅቤ የተጫወትኩበት 
አጋጣሚም ስለነበርና በኳሱም ስለረካውም 
የምቆጭበት ነገር ፈፅሞ የለኝም፡፡

በምድር ላይ ካጣቸው መኖር አልችልም 
ስለሚላቸው ነገሮች፡-
ባለቤቴንና ልጆቼን ያለ 
እነሱ መኖር አልችልም

ስለቤተሰብህና ስለስራህ ምን የምትለው 
አለ፦
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ኳስን 
ስጫወት ካስገኙልኝ ነገሮች መካከል ቤተሰቤን 
የመሰረትኩበት አጋጣሚ የሚጠቀስ ነው የቡና 
ተጨዋች ሆኜ ከባለቤቴ ወይንሸት ንጉሴ ጋር 
ትዳርን መስርቻለሁ የ1990 ላይ የረጅም ጊዜ 
ጓደኛዬ ነበረችና እሷ ጥሩ ባለቤትም ነች ከእሷ 
ሁለት ሴት ልጆችንም ለማፍራት በቅቻለሁ፡፡ 
እድላዊትና መሃላ ገ/ኪዳን ይባላሉ፤ ፡፡ 

የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ ለረጅም 
ጊዜያት ተጫውቶ ስለማሳለፍና ስለደጋፊዎቹ፦

የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ገና የህፃንነት እድሜዬ 
ላይ ሆኖ ጀምሮ የወደድኩትና የተጫወትኩበት 
ምርጥ ክለቤ ነበር ለእኔ ቡድኑ ቤቴም 
ማለት ነው ረጅምን ወቅትም ከወጣት ቡድኑ 
አንስቼም በፍቅር ሆኜም ተጫውቼበታለሁ፡፡ 
ይህም ሆኖ ግን እኔ ቡናን መልቀቅ ሳልፈልግ 
ነው በአንዳንድ ለክለቡ ጥሩ ባልሆኑ ሰዎች 
አማካይነት ልለቅ የቻልኩት፡፡ ይሄኔ እኔ በቡና 
ቀጥዬ ቢሆን ኖሮ የእዚያን ወቅት ላይ የእግር 
ኳሱን ላላቆም ሁሉ እችል ነበር፡፡ 

ጋምብሬ ማለት ትርጓሜ አለው ምንስ 
ማለት ነው ማንስ አወጣልህ፦
ጋምብሬ 
የሚለውን ስም ያወጣልኝን ሰው እያፈላለግኩት 
ነው እስካሁን ማግኘትም አልቻልኩምና 
ትርጓሜውን አላወቅኩትም፡፡

የእግር ኳስን ካቆመ በኋላ ስለተሰማራበት 
ሙያ፦
የእግር ኳሱን ካቆምኩ በኋላ የራሴ 
ስራ ላይ ተሰማርቼ ስንቀሳቀስ ነበር በእዚያም 
ቤተሰቦቼን ስላተዳዳር ቆይቻለሁ አሁን አሁን 
ደግሞ የስልጠና ህይወት ውስጥ ገብቼ አቤል 
ያቋቋመው ፕሮጀክት ላይ የታዳጊ ወጣቶችን 
ፕሮጀክት በማሰልጠን እየሰራው ነው፡፡ አሁንም 
እነዚያን ህፃናት እያሰለጠንኩ ነው የቀጣይ 
ጊዜም ላይ የስልጠና ህይወት ላይ በጣም መጓዝ 
ስለምፈልግ ለአገሬ የሚቻለኝን ሁሉ ግልጋሎት 
መስጠት እፈልጋለሁ፡፡

በመጨረሻ፦ የኢትዮጵያ እግር ኳስ 
ውስጥ ስጫወት ብዙ ከጎኔ የነበሩ ሰዎች አሉ 
የእነሱ ድጋፍም ለእዚያ ደረጃ አብቅቶኛል 
ተፈሪ ዘውዴ ብሩክ አየለ ደረጄ ባቢ ተወልደ 
ገብረየሱስ ሁለቱ ወንድሞቼ ቴዎድሮስና 
ንርአዬና በጣም የምወዳቸውን ቤተሰቦቼን 
ሌሎችንም ስማቸውን ያልጠቀስኳቸውን ሰዎች 
ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣዜና እረፍትዜናዎች

የጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አጭር የህይወት ታሪክ

ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ከእናቱ ከወ/ሮ ጌጤ ገ/ስላሴ እና ከአባቱ ሀምሳ አለቃ ወልዴ...

ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣ

ሀትሪክ አሁንም ቀጠሮ ማክበር ስልጣኔ ነው በሚለው አቋሟ ጸንታለች

ቅዳሜ ጠዋት በቀጠሮ  ቀናችን  እርስዎ ጋዜጣዋን በእጅዎ ያስገቡ እንጂ አዳዲስና ያልተሰሙ መረጃዎችን...

ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣዜናዎች

ሀትሪክ አሁንም ቀጠሮ ማክበር ስልጣኔ ነው በሚለው አቋሟ ጸንታለች

ቅዳሜ ጠዋት በቀጠሮ  ቀናችን  እርስዎ ጋዜጣዋን በእጅዎ ያስገቡ እንጂ አዳዲስና ያልተሰሙ መረጃዎችን...