መነሻ ገጽ ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣ “ኢትዮጵያ ቡና ከእግር ኳስ በላይ ፍቅር የሆነ ክለብ ነው” ሀብታሙ ታደሰ
ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣቃለመጠይቅኢትዮጵያ ቡናዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

“ኢትዮጵያ ቡና ከእግር ኳስ በላይ ፍቅር የሆነ ክለብ ነው” ሀብታሙ ታደሰ

አጋራ
አጋራ

ኢትዮጵያ ቡና በቅርቡ ከሲዳማ ቡና ጋር ባደረገው ጨዋታ 2-1 ማሸነፉ ይታወሳል፤ የክለቡን የድል ጎልም ሀብታሙ ታደሰ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል፤ ተጨዋቹ ለቡድኑ ወሳኟን የድል ጎል ካገባ በኋላም ደስታውን በከፍተኛ ስሜት ውስጥ ሆኖም ሲገልፅ ታይቷል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ቡና በክረምቱ ወራት የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት በመምጣት የተቀላቀለው ይኸው ተጨዋች ለክለቡ በአሁን ሰዓት ጎል ከማስቆጠሩም ባሻገር የቡድኑ አባል በመሆኑ ብቻም የተለየ የደስታ ስሜት እንደሚሰማውም ይናገራል፤ ሀብታሙ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ከመጣ በኋላም ክለቡን ከገለጸባቸው ንግግሮቹ መካከልም “ኢትዮጵያ ቡና ከእግር ኳስ በላይም የሆነ ፍቅር የሆነ ክለብ ነው” የሚል ምላሽም ይገኝበታል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ያለውን ይህን ተጨዋች ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በጥምቀት ዋዜማ በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ አናግሮት ነበርና ተጨዋቹ ምላሾቹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፤ ለንባቡም መልካም ቆይታ ብለናል፡፡
ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡናን ዘንድሮ ተቀላቅለህ እየተጫወትክ ይገኛል፤ ለቡድኑ መጫወት መቻል የተለየ ስሜትን ይሰጣል?
ሀብታሙ፡- አዎን፤ በመጀመሪያ ኢትዮጵያ ቡና ከእግር ኳስ በላይም አልፎ ፍቅር የሆነም ቡድን ነው፤ ቡድኑ ውስጥ ስትመጣም ቤተሰባዊነትን የምታይበትም ነው፤ ሁሉም ደጋፊ ቤተሰብህና ወዳጅህም ነው፡፡ ስለዚህም እኔ ወደዚህ ቡድን ውስጥ መጥቼ በመጫወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ የተሳካና ምርጥ ጊዜን የምታሳልፍ ይመስልሃል? ክለቡስ ጥሩ ውጤትን ያመጣል?ሀብታሙ፡- አዎን፤ እንግዲህ እኔ እንደዛ ብዬ ነው የማስበው፤ በሊጉም ጥሩ ተፎካካሪም ነው የምንሆነው፤ እኔን በሚመለከት ደግሞ ለሊጉ አዲስ ተጨዋች ብሆንም አሁን ላይ ከጅማሪዬ ለክለቡ ከእግዚአብሄር እርዳታ ጋር ጎሎችን እያስቆጠርኩለት ነውና እዚህ ጋር ደርሻለው፤ ልምዱን በደንብ ሳገኝ ደግሞ ለቡድኑ ከዚህ የበለጠ ግልጋሎትን ሰጥቼ ቡድኔን ለስኬታማነት ማብቃት እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- ሲዳማ ቡናን በቅርቡ መርታት ችላችኋል፤ ጨዋታው በምን መልኩ ይገለጻል?
ሀብታሙ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ያለፈው ሳምንት ቅዳሜ ዕለት የነበረው ጨዋታው የሚገለጸው ከሽንፈት መጥቶ ያደረገው ነበርና ግጥሚያውን በድል መወጣቱ ደስ ይላል፤ ድሉ ማገገሚያችን እና ቁስላችንንም የምናክምበት ነበርና ደማችንን ሰጥተን በመጫዋት ነው ውጤቱን ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ልናሳከው የቻልነውና በጨዋታውና በተገኘው ድል ተደስተናል፡፡
ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ቡና በመጫወት ጥሩ እንቅስቃሴን እያሳየህ ይገኛል፤ ለክለቡ የድል ጎልን ማስቆጠር መቻል የተለየ ስሜትን ይሰጣል?
ሀብታሙ፡- አዎን፤ አንተ የምትፈልገውን ነገር ስታገኝ ሁሌም ደስ ይላል፤ በዛ ላይ ይሄ ሁሉ ደጋፊ ጎል አግብተህ ሲጨፍርልህ ስታይ በጣም ደስ ብሎኛልና ከዚህ በኋላም ሌሎችን ጎሎች ለማስቆጠርና ለመደሰት ከፍተኛ ጥረትን አደርጋለው፤ ከሲዳማ ቡና ጋር በነበረን ጨዋታ የመጀመሪያውንም ፔናሊቲ ያስገኘሁት እኔ ነበርኩ፤ በዕለቱ በጣም ደስ ብሎኝም ነበር የተጫወትኩት፡፡
ሀትሪክ፡- ከሲዳማ ጋር ስትጫወቱ የዳኝነቱን ችግር በመግለፅ የፍጹም ቅጣት ምቱ አያሰጥም የሚሉ አሉ፤ ለአንተስ….?
ሀብታሙ፡- ያው እንግዲህ የፍጹም ቅጣት ምቱን በተመለከተ እኔ በክልሉ ውስጥ ተነክቼ ወድቄያለው፤ ከመነካትም አልፎ ኳሱን ይዤም ገብቻለው፤ ኳሱ ስለቀደመኝና ስለነካኝ ነው የወደቅኩት እንጂ ከውጪ ላለ ሰው የሚያሰጥ አይደለም፤ ይሄን እኛ ሀገር ስለሌለ ነው እንጂ ቫር በሚለው ውሳኔ አይተው ሊያስተካክሉት ይገባ ነበር፤ የዳኝነት ውሳኔ ግን ያለ እና የሚኖር ነው፤ ይፈጠራልም፤ በእኔ በኩል ሳልነካ አልወድቅም፤ ልጁ ስለነካኝና ጫናም ስለነበር ነው የወደቅኩት ተሳስቶ በቀይ ካርድ ሊያስወታ ይችላል እንዲህ ያሉ ነገሮች በእኔ በኩል ሳልነካ አልወድቅም

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና በሰሞኑ ጨዋታው ማሸነፍም ነጥብ መጋራትም ችሏል። በእዚህ ስኬት ይቀጥላል?
ሀብታሙ፡- ከሲቲ ካፑ እና ከፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታችን ጀምሮ እያሻሻልን እያሻሻልን በመሄድ ነው አሁን ላይ የመጣነው፤ ብዙም ነገርን አስተካክለን መጥተናል፤ ደጋፊውም ከእኛ ጋር ሆኖም ሊታገሰን ይገባልና ከእነሱ ጋር በመሆን ቡድናችን በቀጣዮቹም ጨዋታዎች በድሉ ይጓዛል፡፡
ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና ሽንፈትን ባስተናገደባቸው የዘንድሮ ጨዋታዎቹ ውጤት ያጣው ተበልጦ ነው…?
ሀብታሙ፡- አይደለም፤ በእዛን ጊዜ አንድአንድ ክፍተቶች እንደነበረብን ግን እናምናለን፤ ያም ሆኖ ግን በኳስ ቁጥጥር በማንም ቡድን አልተበለጥንም፤ ቡድናችን ሲጀመር ኳስን የሚጫወተው ጥሩ ተጫውቶና ኳሱንም ተቆጣጥሮ ነው፤ የጥለዛ እና የልጊያ ጨዋታ እኛ ጋር አይሰራም፤ ኳስን ደግሞ በጥሩ ሁኔታ ካልተጫወትከው አይለወጥምና የእኛ ቡድን አቋም ጥሩ ተጫውተን ስኬታማ ውጤት ማምጣት መቻል ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ በምን መልኩ ይገለጻል?
ሀብታሙ፡- አሰልጣኙ…ማለት ስለእሱ ምን ብዬ እንደምገልጽልህ አላውቅም፤ ሁሌም ማድረግ ያለብህን እና ማስተካከል ያለብህን ነገር ይነግርሃል፤ ማንንም ከማንም ጋር አያበላልጥም፤ አያሳንስምም፤ ወደ ቡና ለመጀመሪያ ጊዜ ስመጣ በመስመር ላይ ሆኜ ነው እየተጫወትኩኝ የምገኘው፤ ከዛ በፊት አጥቂም ነበርኩ ግን አሰልጣኝ ተጫወት በሚለኝ ስፍራ እየተጫወትኩ ነውና በእዚህ መልኩ ነው በመጓዝ ላይ ያለሁት፤ እኛ ቡድን ውስጥ ለአሰልጣኙ ሁላችንም እኩል ነን፤ ከዛም አልፎ ሁሉም ተጨዋች ለቡድኑ ውጤት ማማር አሰልጣኙ ከሚሰጠን ነፃነት በመነሳት ኃላፊነቱን ወስዶ ይጫወታል፤ እኛ ቡድኑ ውስጥ ሁሉም የየራሱ ድርሻ አለው፤ ይሄ የእከሌ ነው ይሄ የእከሌ ነው የሚል ነገርም የለምና ቤት ሲገነባ ከላይ አንደማይጀመረው ሁሉ ተጋግዘን በመጫወትም ነው ክለቡን ለታላቅ ውጤት ለማብቃት እየተጋን የምንገኘው፡፡
ሀትሪክ፡- እግር ኳስን ለማን ለማን ቡድኖች ተጫወትክ? የትስ ተወልደህ አደግክ?
ሀብታሙ፡- የተወለድኩት በምህራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ ከተማ ነው፤ እዛም ነው ኳስን መጫወት የጀመርኩት፤ በ2010 ላይ ደግሞ ወደ ወልቂጤ ከተማ በማምራት ለሁለት ዓመታት በመጫወት አሳልፍኩና የአሁን ሰዓት ላይ ቡናን ተቀላቀልኩ፡፡
ሀትሪክ፡- በወልቂጤ ከተማ የተሳካ የኳስ ጊዜን ነው ያሳለፍከው?

ሀብታሙ፡- ወደ ቡድኑ በመጣሁበት የመጀመሪያ ዓመት ላይ ከተጨዋቾቹ ጋር በደንብ አልተላመድኩም ነበርና ስኬቴ ያንን ያህል አልነበረም፤ በኋላ ላይ ግን ጥሩ የቡድን ቆይታው ኖረኝና እስከ 13 የሚደርሱ ጎሎችንም በማስቆጠር የኮከብ ግብ አግቢም ልሆን ችያለው፡፡ ያኔ የተጫወትኩበት ደቂቃም በአቬሬጅ ሲሰራም ከሁሉም ተጨዋቾች የተወሰነ ጨዋታ የተጫወተውና ብዙ ጎል ያለኝ ተጨዋች እኔ ሆኛለው አሁንም ወደ ቡና ስመጣ ሶስት ጨዋታ ተጫውቼ ሶስት ግብ አስቆጥሬያለውና በእዚሁ ነው የምቀጥለው፡፡
ሀትሪክ፡- በአንድ ጨዋታ በርካታ ግብ አስቆጥረህ ታውቃለህ?
ሀብታሙ፡- አዎን፤ ለወልቂጤ ከተማ ስጫወት እና ናሽናል ሲሚንትን 7-1 ስናሸንፍ ስድስት ጎል አግብቻለው፤ ከዛ በፊት ደግሞ ሶስት እንደዚሁም ደግሞ ሁለትም ያስቆጠርኩባቸውም ጊዜያቶች አሉ፡፡
ሀትሪክ፡- ቤተሰቦችህን ግለጽ? ከአንተ ውጪ ኳስ ተጨዋችስ አለ?
ሀብታሙ፡- ስለ እነሱ ምን ልበልህ፤ የኳስ ተጨዋችነት ፍላጎቴን በደንብ ነው የሚያሟሉልኝ፤ የሚያከብሩልኝም፤ ታላቅ ወንድሜም ለሙገር ሲሚንቶ ይጫወት ነበረ፤ ዳግም ታደሰ ይባላል፤ በአጠቃላይ የእኛ ቤተሰቦች ፍላጎቴን ይወዱልኝም ስለነበር ከፈጣሪ እርዳታ ጋር በአባት እና በእናቴ ጸሎት እዚህ ጋር ደርሻለው፤ በእዚሁም እቀጥላለው፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን ልጅ ሆነህ ስትጫወት ማንን አድንቀህ አደግክ?
ሀብታሙ፡- ብራዚላዊውን ሮናልዲኒሆ ጎቾን ነዋ! ከሀገር ውስጥ ተጨዋቾች መካከል ደግሞ የሽመልስ በቀለም አጨዋወት ከእሱ ጋር የሚመሳሰልብኝም ነገር አለና እሱን አደንቃለው፡፡
ሀትሪክ፡- በግንባር ገጭቶ ጎል ማስቆጠር ልምድህ ነው?
ሀብታሙ፡- አዎን፤ የጭንቅላት ኳስ እገጫለው፤ ሙሉ ተጨዋች ስትሆንም ያን ማድረግ አለብህ፤ በእዚህ መልኩም ከዚህ በፊት ሌሎችን ግቦችን አስቆጥሬያለው፡፡
ሀትሪክ፡- ወደ ኢትዮጵያ ቡና እገባለው ብለህ አስበህ ወይንም ደግሞ ጠብቀህ ታውቃለህ?
ሀብታሙ፡- ወደ ቡና እኔ እገባለው ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ በዛ ሰዓት ወልቂጤ ላይ ባሳየሁት ነገር ለእኔ የሰጡኝ ግምት ትንሽ ነበርና አቅሜን ቡና መጥቼ በማሳየቴ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ በእዚህም ወደ ቡና በመምጣቴ ፈጣሪ እዚህ ጋር ትደርሳለህ ብሎ ነው ያመጣኝና እሱን ላመሰግን እፈልጋለው፡፡


ሀትሪክ፡- የተለየ ልምድ አለህ?
ሀብታሙ፡- አዎን፤ የተለየ ልምዴ ከሰዎች ጋር እግባባለው፤ ቀለል አድርጌም ነው የምግባባው፡፡
ሀትሪክ፡- የፀጉር ቁርጥህ ለየት ይላል?
ሀብታሙ፡- ያምራል አይደል፤ ጸጉሬ በአጋጣሚ ነው ያደገው፤ ብዙ ሰው ሲወድልኝም በዛ መልኩ አሳድጌው ተጓዝኩ፡፡
ሀትሪክ፡- ወደ ትዳር አምርተሃል?
ሀብታሙ፡- አላገባውም፤ ያገባ ጓደኛም የለኝም፡፡
ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ተጠባባቂ ተጨዋች ነበርክ፤ አሁን ግን ቋሚ ሆነህ ክለቡን እያገለገልክ ይገኛል?
ሀብታሙ፡- የእግር ኳስ ተጨዋች ስትሆን በእዚሀ መልኩ ትጀምራለህ፤ ትላልቆቹም ተጨዋቾች የጀመሩት በእዚሁ መልኩ ነውና ይሄ ሊያስገርም አይችልም፤ ጥሩ ስትሆን ትገባለህ፤ ጥሩ ሳትሆን ደግሞ ትወጣለህ፤ ያም ሆኖ ግን ጥሩ ሆንኩ ብለህ መስነፍ የለብህም፤ አንድ አንዴ እኛ ተጨዋቾች ሰነፎች ነን አቅም እያለን አልባሌ ቦታ እንውልለን፤ ከትልልቆች ከሞዴሎች መማር ያለብን ነገር አለ፤ እነሱ ስራቸው ላይ ብቻ ነው ትኩረት የሚያደርጉት እና አልባሌ ቦታ ላይ የመዋሉ ነገር ሲጠፋ ሀገራችንም በኳስ ትልቅ ደረጃ ላይ የምትደርስ ይሆናል፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ….?
ሀብታሙ፡- ልዑል እግዚአብሄርን አመሰግናለው፤ ከዛ በመቀጠል ቤተሰቦቼን፤ እናትና አባቶቼን፤ ከልጅነቴ ጀምሮ ድሮ ያሰለጠነኝን ተከተል መሰለን እኛ አካባቢ ፕሮጀክት የለም ነበርና በራሱ ፍላጎት ምንም ነገር ሳይሰጠው ጠዋት በፊሽካ እያስነሳን ያሰራን ነበርና ስለ እሱ ሰፊ ጊዜ ወስጄ ባወራ በጣም ደስ ይለኛልና ለእሱ ልለው የምፈልገው እኔ እዚህ ጋር ደርሼልሃለው፤ እዚህ ጋርም አላቆምም፤ብቃቴን አስቀጥዬም እጓዛለው በማለት እሱን ማመስገን እፈልጋለው፤ ከዛ ውጪም ወደ ቡድኑ ያመጡኝን ሄጀንቶቼንም ለማመስገን እፈልጋለው፡፡

📷 Fekadu

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየዲሲፕሊን ውሳኔዎችዲሲፕሊን ውሳኔ

የ32ኛ ሳምንት የዲሲፕሊን ውሳኔዎች

የዲሲፕሊን ውሳኔዎች አህመድ ረሺድ (ድሬደዋ ከተማ) : በኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር 1 እንዲሁም...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ሀምራዊ ለባሾቹ እና የጣና ሞገዶቹ ጣፋጭ ሦስት ነጥብን ወደ ቋታቸው ከተዋል

በሊጉ የሳምንቱ የሁለተኛ ቀን ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ባህርዳር ከተማ ወሳኝ...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ሲዳማ ቡና ሲሸነፍ በተጠባቂው ጨዋታ መቻል በጎል ፌሽታ ነገሌን ረቷል

በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ጨዋታ የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በሀድያ ሆሳዕና ሽንፈት ሲያስተናግድ...

ዜናዎችየኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

ውጤት ለውጧል የተባለው ዳኛ ተባረረ

በዮሴፍ ከፈለኝ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውጤት ለውጠዋል የተባሉ አርቢትሮችን ወደመጡበት መመለሱን አሁንም ቀጥሏል። ከቀናት...