አዲሱ አሰልጣኝ ኮስታዲን ፓፒች መደበኛ ስራቸውን ዛሬ ጥቅምት 27/2010 ዓ.ም ጀመሩ
የቀድሞ የቡድናችን ዋና አሰልጣኝ ሰርቪያዊው ድራጋን ፖፓዲች በህመም ምክንያት በአሰልጣኝነት የሚያስቀጥል ጤንነት ላይ ባለመሆናቸው ክለባችን ኢትዮጵያ ቡና አዲስ ሰርቪያዊ አሰልጣኝ ማምጣቱ ይታወቃል፡፡ ከክለባችን የስራ አመመራር ቦርድ ጋር የተለያዩ ድርድሮች ካደረጉ በኋላ ለ2 ዓመት ከኢትዮጵያ ቡና የሚያቆያቸውን ውል ዓርብ ጥቅምት 24/2010 ዓ.ም የፈረሙት አሰልጣኝ ፓፒች ዛሬ ጥቅምት 27/2010 ዓ.ም መደበኛ ስራቸውን ጀምረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ቡናን በአፍሪካ መድረክ ውጤታማ ለማድረግ የረዥም ጊዜ እንዲሁም በአጭር ጊዜ ቡድኑን እራሳቸው በሚፈልጉት ማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወት በመቅረፅ ውጤታማ ቡድን መገንባት የአጭር ጊዜ ግባቸው እንደሆነ የተናገሩት አሰልጣኝ ፓፒች በሌሎች የአፍሪካ ክለቦች ያሳኩትን ድል ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በመድገም ተወዳጁ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊን ማርካት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
አሰልጣኝ ፓፒች የደቡብ አፍሪካ ክለቦች ኦርላንዶ ፓይሬትስ እና ካይዘር ቺፍ፣ የጋናው ሄርት ሶፎክ፣ የታንዛንያው ያንግ አፍሪካ፣ እንዲሁም የተለያዩ የናይጀሪያ ክለቦች በማሰልጠን በአፍሪካ እግር ኳስ ልምድ ያላቸው አሰልጣኝ ናቸው፡፡
አሰልጣኝ ፓፒች ቡድኑን የተረከቡት የ2010 ፕሪሚየር ሊግ ሊጀምር በተቃረበበት ሰአት ቢሆንም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለቻን ዋንጫ ለማለፍ ከሩዋንዳ አቻው ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና 3 ተጫዋቾች በማስመረጡ ቡድኑ የፕሪሚር ሊግ ጨዋታው ስለማይጀምር ያላቸውን ጊዜ በአግባቡ ተጠቅመው ውጤታማ እና ስኬታማ ቡድን ገንብተው ፕሪሚየር ሊጉን እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል፡፡
Source-ethiopia coffee offical page

አስተያየት ይስጡ