መስከረም 26 ጅማሬውን ያደረገው ትግራይ ዋንጫ ትላንት በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች የምድብ ጨዋታዎችን በማጠናቀቅ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ያለፋትን አራት ክለቦች አሳውቋል።በዚህም መስረት ከምድብ ‘ሀ’ ሽረ እንዳስላሴ ና ደደቢት ከምድብ ‘ለ’ መቐለ 70 እንደርታ ና ድሬዳዋ ከተማ ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ አክሱም ከተማ ወልዋሎ ዓ/ዩኒቨርሲቲ ከውድድሩ ተሰናብተዋል።
ሽረ እንዳስላሴ 2-1 ደደቢት
8 ሰዓት ላይ የተጀመረው የደደቢት ና የሽረ እንዳስላሴ ጨዋታ በሽሬ እንዳስላሴ አሸናፊነት ተጠናቋል።መሃል ሜዳ ላይ በሚቀባበሉ ኳሶች ትኩረት ያደረገው የመጀመርያ 45 ደደቢቶች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢያሳዩም ወደ ሜዳው የመጨረሻ ክፍል በሚሄዱበት ጊዜ የመናበብ ችግር ታይቶባቸዋል።ሽሬዎች በ3-5-2 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ቢወርዱም መሃል ላይ የተሰለፋት ሳሙኤል ተስፋይ፣ሄኖክ ካሳሁን እና ሰለሞን ገ/ማርያም የቡድኑን ማረጋጋት ተስኗቸው ኳስ ቁጥጥር በደደቢት ብልጫ ተወስዶባቸዋል።በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድን የተጫዋች ለውጥ በማድረግ የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል።

ግብ የማግባቱን ቅድሚያ የወሰዱት ደደቢቶች ውድድሩ ላይ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ በሚገኘው አለምአንተ ካሳ ኣማካኝነት ነበር።ከግቡ መቆጠር በኃላ ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ሽሬዎች በኣራት ደቂቃ ውስጥ በንስሃ ታፈሰና በሰይድ ሃሰን ኣማካኝነት ባስቆጠሩት ግቦች ታግዘው ጨዋታውን አሸንፈው መውጣት ችለዋል።
ድሬዳዋ ከተማ 1-1 ኣክሱም ከተማ
10 ሰዓት ላይ የተካሄደው የድሬዳዋና የአክሱም ጨዋታ ጥሩ ፋክክር የታየበት ነበር።ሁለቱም ቡድኖች በ4-2-3-1 ኣሰላለፍ የገቡ ሲሆን በመጀመርያው አጋማሽ ውድድሩ ላይ ጥሩ ብቃት እያሳዩ ሚገኙት በጌታቸው ዳዊት እሚመሩት አክሱሞች ጥሩ መንቀሳቀስ ችለዋል።በተለይ መሃል ሜዳ ላይ የተሰላፋት ስለሺ ዘሪሁን እና ትእዛዙ ፍቃዱ ቡድኑን ሚዛኑን ጠበቆ እንዲጫወት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል።ድሬዎችም የቆሙ ኳሶችን በመጠቀም የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት አክሱሞች በ56 ደቂቅ ላይ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ልዑልሰገድ ኣስፋው አስቆጥሮ አክሱምን መሪ ማድረግ ችሏል።ከግቡ መቆጠር በኃላ ድሬዎች በሙሉ ሃይላቸው ጫና መፍጠር ሲጀምሩ አክሱሞችም በመልሶ ማጥቃት እድሎችን መፍጠር ችለዋል።በ85 ደቂቃ ሲላ ኣብዱላሂ ባስቆጠረው ግብ ድሬዎች ውድድሩ ላይ መቆየታቸውን አረጋግጠዋል።
የትግራይ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች
አርብ ጥቅምት 2 ቀን 2011
8:00 ሽሬ እንዳስላሴ ከ ድሬዳዋ ከተማ
10:00 መቐለ 70 እንደርታ ከ ደደቢት
አስተያየት ይስጡ