“በኢትዮጵያ ቡና በነበረኝ ቆይታዬ የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ታሪክ ባፅፍና ደጋፊው ሲደሰት ባይ ልዩ ታሪክ ይኖረኝ ነበር”ጋቶች ፓኖም

በኢትዮጵያ እግር ኳስ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው ለአሳዳጊ ክለቡ ኢትዮጵያ ቡና እና መቐለ 70 እንደርታ ተጫውቶ አሳልፏል፤ በቡና ክለብ ቆይታውም በሜዳ ላይ በሚያሳየው እንቅስቃሴ በርካታ አድናቂዎችንም ለማትረፍ ችሏል፤ ከዛም ባሻገር ለክለቡ ተጫውቶ በማሳለፉም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን መለያ ለመልበስም በቅቷል፤ የጋምቤላው ተወላጅ ጋቶች ፓኖም በእዚህ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው ከሀገር ውጪም ወደ ባህር ማዶም በመጓዝ ለግብፆቹ ክለቦች ኤል- ጉናሃ እና አራስ ኤል ሁዳድ ቡድኖች የተጫወተ ሲሆን ከዛም የአራስ ኤል ሁዳድ ክለብ ለሳውዲው ቡድን አል አንዋር በውሰት ሰጥቶት በኮቪድ 19 ኳሱ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ሲጫወት ቆይቷል፤ አሁን ደግሞ ይሄ ተጨዋች የሀገሪቱ የሊግ ውድድሮች ከቆሙበት ሊጀመሩ ስለሆነ ቀሪዎቹን ሶስት ጨዋታዎች ለማድረግ ሐሙስ ዕለት ወደ ሳውዲ አረቢያ ሊጓዝ ችሏል፤ ከጋቶች ፓኖም ጋር ሀገር ቤት በነበረበት ሰዓት ስልክ ደውለን የአሁን ሰዓት ላይ ስለሚገኝበት ሁኔታ እና ስላሳለፋቸው የኳስ ህይወቶቹ እንደዚሁም ደግሞ ስለ ኮቪድ እና ስለ አባይ ግድብ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጠይቆት ምላሾቹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል ተከታተሉት፡፡

ሀትሪክ፡- በቅድሚያ ከስም መጠሪያህ እንጀምርና ጋቶች ማለት ምን ማለት ነው?

ጋቶች፡- በአማርኛ እንኳን ትርጉሙን አላውቀውም፤ እንግዲህ የሚያውቁትን መጠየቅ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ቤተሰቦችህም አልነገሩክም?

ጋቶች፡- አዎን፤ እኔም የስሙ ትርጓሜ ምን ማለት እንደሆነ አንድም ቀን ጠይቄያቸው አላውቅም፡፡

ሀትሪክ፡- በቤተሰባችሁ ውስጥ ስንት ወንድም እና እህት አለ? አንተስ ለቤተሰቡ ስንተኛ ልጅ ነህ?

ጋቶች፡- እኔ የቤቱ ሁለተኛ ልጅ ነኝ፤ ሶስት ወንድሞች ሲኖሩኝ፤ የእህቶቼ ብዛት ደግሞ አምስት ናቸው፡፡

ሀትሪክ፡- ከቤተሰባችሁ አባላት ውስጥ ስፖርተኛው ወይንም ደግሞ የእግር ኳስ ተጨዋቹ አንተ ብቻ ነህ?

ጋቶች፡- አዎን፤ እኔ ብቻ ነኝ፤ ሌሎቹ ትናንሽ ልጆች ስለሆኑ በአሁን ሰዓት ትምህርታቸውን እየተማሩ ነው፤ አልፎ አልፎ ደግሞ ኳስን በሰፈር ደረጃ ይጫወታሉ፡፡

ሀትሪክ፡- በልጅነትህ ኳስ ተጨዋች እሆናለሁ የሚል ህልሙ ነበረህ?

ጋቶች፡- በፍፁም፤ ያኔ ኳሱን እጫወት የነበረው ለስሜት እና ፍላጎቴን ለማሟላት ከዛ ባሻገር ደግሞ ጤንነቴን ለመጠበቅ ብቻ ነበር፤ እያደግኩ እና ብዙ ነገሮችን እያወቅኩ ስመጣ ግን ኳስ ተጨዋች መሆንን አለምኩ፡፡

ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ባትጓዝና በዛ ቦታ ላይ ባናገኝህ ኖሮ የአንተ መድረሻ የት ይሆን ነበር?

ጋቶች፡- ትምህርቴን ተምሬ እና ተመርቄ በአንድ ትልቅ የመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ነበር ሰራተኛ ሆኜ የምታገኙኝ፡፡

ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ልጅ ሆነህ ኳስን ስትጫወት አንድ አንድ ቤተሰብ ጨርሶ አይፈቅዱልህም፤ በትምህርትህ ብቻም እንድታተኩር ይፈልጋሉ፤ የተወሰኑት ደግሞ መጫወትህን ሊፈቅዱልህ ይችላሉ፤ የአንተስ?

ጋቶች፡- የእኔ ቤተሰቦች ኳስን እንድጫወት ከማይፈልጉት ውስጥ የሚመደቡ ነበሩ፤ ያም ሆኖ ግን በድብቅ ደረጃ እኔ በትምህርት ቤት ውስጥ ኳስን እጫወት ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- በጋምቤላ ክልል ተወልደህ እንደማደግህ ለአንተ የእግር ኳስ ተጨዋችነት ህይወት አርአያ ወይንም ደግሞ ሞዴልህ የሆነህ ተጨዋች ነበር?

ጋቶች፡- ማንም የለም፤ ምክን ያቱም አንድን ተጨዋች የአንተ ተምሳሌት አልያም ሞዴልህ ለማድረግ እሱን ሲጫወት በቅርብ ማየትና መከታተል ይኖርብሃል፤ እንደዚሁም ደግሞ ስለ ችሎታውም በቂ ግንዛቤው ሊኖርህም ያስፈልጋል፤ የእግር ኳሱን ያኔ እኛ በክልላችን ስንጫወት ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ በቴሌቪዥን መስኮት የሚተላለፍበት ሁኔታ ፈፅሞ ስላልነበር ማንንም ተጨዋች ሞዴሌ አላደረግኩም፤ እንደውም ሞዴል ወይንም ደግሞ ተምሳሌት የሚለውን ነገርም ተግባራዊ ማድረግ የጀመርኩት የአውሮፓ ኳስን መከታተል ከጀመርኩ በኋላ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የአውሮፓ ኳስን ስትከታተልስ የትኛውን ተጨዋች ተምሳሌትህ አደረግክ?

ጋቶች፡- የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ ሆኜ ነበር ያደግኩትና ሁሌም የፖል ስኮልስ አጨዋወት ይስበኝ ነበር፤ ከዛም እሱን መመልከት ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ ምርጡን እንግሊዛዊ ተጨዋች አርአያዬ አደረግኩት፡፡

 

ሀትሪክ፡- ማንቸስተር ዩናይትድ አሁን አሁን የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግን ዋንጫ እያነሳ አይደለም፤ ሊቨርፑል ደግሞ ከ30 ዓመታት በኋላ ይሄን ክብር ተቀዳጅቷል፤ እንደ ማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊነትህ የሊቨርፑልን ዋንጫ ማንሳት በምን መልኩ ነው የምትመልሰው?

ጋቶች፡- በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ምንም እንኳን የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ ሆኜ ባድግም የሊቨርፑልን ዋንጫ ማንሳት አሁን ላይ ሆኜ የምመልሰው እንደ ፅንፈኛ ደጋፊ ሆኜ ሳይሆን እንደ አንድ እግር ኳስ ተጨዋችና እንደ አንድ ባለሙያ ሆኜ ነው፤ በፊት ልጅ በነበርክበት ሰዓት ይሄ ቡድን ዋንጫ ባይበላ ብለህ ትመኝ ነበር፤ አሁን ግን የኳስ እውቀትህ እየጨመረ ሲመጣ እና ሊቨርፑልን የመሳሰሉ ጠንካራ ክለቦች ደግሞ የሊጉን ዋንጫ ሲያገኙ ለእነሱም ክሬዲቱን መስጠት ይኖርብሃልና የሊቨርፑል የእዚህ ዓመት ድል የተጠናቀቀው ገና ሰባት ጨዋታዎች በቀሩበት ጊዜ ስለነበር ድሉ በጣሙን የሚገባቸው ሆኖም ነው ያገኘሁት፡፡

ሀትሪክ፡- ኮቪድ 19 በባህር ማዶ የምትጫወተውን አንተን ጨምሮ በርካታ የእግር ኳስ ተጨዋቾችን ከሜዳ አርቋል፤ ለአራት ወራት ከእግር ኳስ የመራቅ ስሜቱን እንዴት አገኘኸው?

ጋቶች፡- የእግር ኳስ ጨዋታ በጣም የሚወደድ፣ ሙያችንና መተዳደሪያችንም ከመሆኑ አንፃር ለወራቶች ያህል በጉዳት ሳይሆን በእዚህ ክፉ ወረርሽኝ ምክንያት ኳሱን ሳንጫወት ከሜዳ መራቃችን ስሜቱ በጣም ከባድ እና አስከፊ ነው፤ ከኳስ መራቁ በብዙ ነገሮችም እንድትቆጭ ያደርግሃል፤ ያም ሆኖ ግን ፈጣሪ ያመጣውን ነገር የግድ መቀበል ስለሚያስፈልግና ምንም ነገርንም ማድረግ ስለማትችል አሁንም ፈጣሪ ይሄን በሽታ እስኪያጠፋልን ድረስ የእሱን ትህዛዝ መጠበቅ የግድ ነው የሚለን፤ እስከዛው ግን ወደ ኳሱ ባንመለስም እንደ ስፖርተኝነታችን የራሳችንን ሰውነት መጠበቅ ስለሚያስፈልገን ከስፖርት እንቅስቃሴው ፈፅሞ መራቅ አይኖርብንም፡፡

ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ ለእዚህን ያህል ጊዜ ከሜዳ የራቅክበት ጊዜ የአሁኑ የመጀመሪያው ይመስለኛል?

ጋቶች፡- አዎን፤ ምን ለእኔ ብቻ ይሄ ለሁሉም የእግር ኳስ ተጨዋቾችም የመጀመሪያቸው ይመስለኛል፤ ከእዚህ በፊት ከሜዳ የምትርቀው በጣም ጠንካራ የሚባል ጉዳትን ካላስተናገድክ በስተቀር ቢያንስ ለጥቂት ጊዜ ነው፤ ኮቪድ ግን በጣም ክፉ ወረርሽኝ በመሆኑ ይኸው ለወራቶች ከቤታችን አስቀምጦናል፡፡

ሀትሪክ፡- ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ በጋምቤላ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል? አንተስ ወቅቶቹን በምን መልኩ እያሳለፍካቸው ነው የምትገኘው?

ጋቶች፡- በእኛ ክልል እስካሁን ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የታማሚ ቁጥር ብዙም የለም ማለት ትችላለህ፤ ለዛም ነው ወደ ውጪ በመውጣት አስፈላጊ የሆኑትን የአካል ብቃት ልምምዶችን የምንሰራው እና የመሀል ባልገባ ጨዋታዎችንም በተደጋጋሚ ጊዜ እየተጫወትን የምንገኘው፡፡ ከዛ ውጪም ፊልም አያለው፤ አዲስ አበባ በነበርኩበት ሰዓት ደግሞ ወደ እንጦጦ በመሄድ በሳምንት ሁለት ቀናት የአካል ብቃት ልምምድ እሰራ ነበር፤ በጓደኛዬ ኤልያስ ማሞ እና አንድ አንድ የንግድ ቤትም በመሄድና ሻይ በመጠጣትም እናሳልፍ ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- ቤተሰቦችህን በኮቪድ 19 ምክንያት አሁን ላይ በሰፊው ጊዜ አግኝተሃል፤ ናፍቆትህንና ፍቅርህን በሚገባ እያጣጣምክ ነው ማለት ይቻላል?

ጋቶች፡- አዎን፤ ምክንያቱም ይሄ ሊሆን የቻለው ለዛ የሚሆን በቂ ጊዜን ስላገኘው ነው፤ እንደ ፕሮፌሽናል ተጨዋችነቴ ከዚህ በፊት ቤተሰቦቼን ላገኝ እና ላይ እችል የነበረው በጣም አጭር እና ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነበር፤ አሁን ግን ምንም እንኳን ከኳሱ መራቁ ቢያስከፋኝም በአንድ በኩል ስታየው ለወራቶች ያህል ከእነሱ ጋር ጊዜዬን እያሳለፍኩ መሆኑ በጣሙን እያስደሰተኝ ነው ያለው፡፡

ሀትሪክ፡- በፍጥነት መልስ…አሁን ላይ በዋናነት ምንድን ነው የናፈቀህ?

ጋቶች፡- ወደምንወደው የእግር ኳስ ጨዋታ መመለስ ነዋ!፡፡

ሀትሪክ፡- ጋቶች ፓኖም ትዳርን መስርቶ እየኖረ ይገኛል፤ እስኪ ስለ ባለቤትህ እና ስለ ፍቅር ህይወትህ አንድ አንድ ነገር ብትለን?

ጋቶች፡- ባለቤቴ ናሮድ ትባላለች፤ትዳርን ከመመስረታችን በፊት ለዘጠኝ ዓመት ያህል አብረን በፍቅር አሳልፈናል፤ በእዚህ ብዙ ውጣ ውረድ በነበረው የፍቅር ህይወታችንም ሁሉን ነገር በመመካከር እና እንደዚሁም ደግሞ በመግባባት ነገሮችን አልጋ በአልጋ ሆኖልን እንዲሄድ ያደረግንበት ሁኔታ ስለነበር አሁን ላይ ለእዚህ ጣፋጭ የትዳር ህይወት ልንበቃ ችለናል፡፡

ሀትሪክ፡- ባለቤትህ በኳሱ ለደረስክበት ደረጃ የነበራት አስተዋፅኦዎ የጎላ ነው ማለት ይቻላል?

ጋቶች፡- በሚገባ! እሷ ሁሌም ቢሆን አብራኝ ነው ያለችው፡፡
ሀትሪክ፡- አሁን ልጅም መጣ አይደል?

ጋቶች፡- አዎን፤ እሷ /ልጃችን/ በመምጣቷ ከአሁን በኋላ እኔም ሆንን ባለቤቴ የምንኖረው ለልጃችን ነው፤ ልጅ ሲመጣ ሁሌም የቤተሰብህን ደስታ ይጨምረዋልና በዛም በጣም ደስተኛ ሆነናል፡፡

ሀትሪክ፡- በአገራችን ብዙ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ትዳርን ሲፈሩና ሲሸሹ ይታያሉ፤ አንተ ጠልቀህ ስለገባክበት ልትላቸው የምትፈልገው ነገር አለ?

ጋቶች፡- አዎን፤ ትዳር ጥሩ ነገር ነው፤ እኔም ገብቼበት ስላየሁት ይሄን የሰጠኝ አምላኬን በጣሙን አድርጌ አመሰግነዋለሁ፤ ስለዚህም ለሌሎች ተጨዋቾች ማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር ትዳር ዝም ብለህ በአጋጣሚህ የምትገባበት ሳይሆን ወስነህ መግባትም ይኖርብሃልና ያን እንዲያደርጉ ነው ምክሬን የምለግሳቸው፤ ያን ካደረጉም ህይወታቸውን በሚገባም ነው የሚቀይሩት፡፡

ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ ህይወትህ ደስተኛ ነህ?

ጋቶች፡- በጣም፤ ምክንያቱም እግር ኳስን ተጫውተህ እንዴት ነው ደስተኛ የማትሆነው፡፡

ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን ተጫውተህ መከፋትም እኮ አለ?

ጋቶች፡- እሱማ መቼ ይቀራል ብለህ ነው፤አንዴ ወደ ሩሲያው ክለብ አንዚ ማካቻካላ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ለመጫ ወት ተጉዤ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ሳልጫወት ተመልሼ መጣሁ፤ያ ለጊዜው ሊቆጨኝ ቢችልም በራሴ የወሰንኩት ስለነበር ቁጭቴን ወዲያው ረስቼዋለሁ፤እንደውም በኳስ ህይወቴ የምደሰትባቸው ጊዜያቶች በጣሙን ስለሚያመዝኑም ለተከፋሁባቸው ወቅቶች ብዙም ትኩረትም አልሰጣቸውም፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ ሩሲያ በተጓዝክበት ሰዓት ለምን ነበር ለመመለስ የቻልከው?

ጋቶች፡- ወደ ሀገር ቤት የተመለስኩት ልጫወትበት ከተስማማሁበት አንዚ ማካቻካላ ክለብ ጋር በክፍያ አፈፃፀም ዙሪያ ልንስማማ ስላልቻልን ነው፤ ያኔ የሩሲያው ክለብ ክፍያን ቶሎ ቶሎ ይፈፅም የነበረው ለሀገሩ ልጆች ብቻ ነበር፤ ለእኛ እና ለሌሎች የሀገሩ ነዋሪ ላልሆንን ልጆች ግን ያኔ ክፍያውን በፍጥነት አይፈፀምልንም ነበር፤ እኔ ደግሞ ቤተሰቦቼን ከመርዳት ጋር ተያይዞ ቶሎ ካልተከፈለኝ የምጎዳበት ሁኔታ ስለነበር ያ ሳይስማማኝ ቀርቶ ነው ወደ ሀገር ቤት እንድመለስ ያደረገኝ፤ ያ ባይሆን ግን በሩሲያ ጥሩ ቆይታ ይኖረኝ እንደነበር ይሰማኛል፡፡

 

ሀትሪክ፡- በግብፅ ሊግ ተጫውተህ አሳለፍክ፤ በኋላ ላይ ደግሞ በውሰት በሳውዲ ዐረቢያ ሊግ ለመጫወት ቻልክ፤ በአጠቃላይ ስለነበረህ የተጨዋችነት ጊዜ ቆይታህ አንድ ነገር ብትለን? በቆይታህ ያጋጠመክ የተለየ ነገር አለ?

ጋቶች፡- ወደ ግብፅ ሊግ በተ ጓዝኩበት የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ለጉናህ ስጫወት ጥሩ ቆይታና ወቅትን አሳልፌ ነበር፤ ከዛም ሰርቢያዊ አሰልጣኝ ወደ ቡድኑ ሲመጣ እና እኔም ከክለቤ ጋር ያለኝን የውል ጊዜ ላጣናቅቅ ስል ከኤጀንቴ ጋር ባደረግኩት ንግግር ወደ ሌላው የሀገሪቱ ክለብ ወደ አራስ ኢል ሁዳድ ቡድን ለማምራት ችዬ ነበር፤ ከዛም በእዚህ የአዲሱ ቡድን የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ከአሰልጣኙ ጋር ለመግባባት ባለመቻላችን በውሰት ለሳውዲው ክለብ አል አንዋር ልሰጥ ቻልኩኝ፡፡ እዛ ስሄድ ቡድኑ ከላይኛው ሊግ ቀጥሎ ባለ የሊግ ደረጃ የሚጫወት መስሎኝ ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ ሳውዲ አረቢያ ስታመራ በላይኛው ሊግ እጫወታለው ብለህ አስበህ ነበር?

ጋቶች፡- የእኔ ፍላጎትማ ከተሳካ በዛ ደረጃ ካልሆነ ደግሞ በአንድ ደረጃ በሚያንስ ሊግ ውስጥ መጫወት ነበር፤ ያም ሆኖ ግን እዛ ከደረስኩ በኋላ ነው ከሁለቱም በታች በሆነ ሊግ ላይ መጫወቴን የተረዳሁት እና ያንን አስቀድሜ ባውቅ ኖሮ ፈፅሞ ወደዛ አልሄድም ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- የውል ጊዜህን ካለማጠናቀቅህ ጋር ተያይዞ አሁንም የግብፁ ክለብ ንብረት ነህ፤ ቀጣዩ ጉዞ እንዴት ነው የሚሆነው?

ጋቶች፡- በግብፁ ክለብ የአንድ ዓመት ውል ስላለኝ ወደ ቡድኑ ተመልሼ መሄዴ አይቀሬ ነው፤ እነሱ መመለስ አለብህ እያሉኝም ነው፤ ለዛም ጉዳይ ከኤጀንቴ ጋር የማወራቸው አንድአንድ ነገሮችም ይኖራሉ፡፡

ሀትሪክ፡- በግብፅ በነበረህ ቆይታህ ከአሰልጣኝህ ጋር ያለ አግባቡህ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ጋቶች፡- ያልተግባባነው ተሰልፎ ከመጫወት እና ካለመጫወት ጋር ነው፤ መጀመሪያ ላይ አምኖብኝ ያሰልፈኝ ነበር፤ ከዛም ሲቆይ ቀይሮ ያስወጣኝ ጀመር፤ በኋላ ላይ ደግሞ ምክንያቱን ባላወቅኩበት ሁኔታ ጭራሽ ከ18ቱ ውጪ ሲያደርገኝና እኔ ደግሞ መጫወትን ስለምፈልግ በእዚህ ነው ለመግባባት ያልቻልነው፡፡ ከዛ ውጪም አንዴ ደግሞ ምን ሆነህ መሰለህ ለብሔራዊ ቡድን የተመረጥኩበት ሰዓት ላይ ክለቡን አስፈቅጄ እያለው ለምን አንድ ቀን አሳለፍክ በሚልም እንድቀጣም በማድረጉ በዛ በዛ ነገር ነው ልንግባባ ያልቻልነው፡፡

ሀትሪክ፡- በግብፅ ሊግ አንተን ጨምሮ ሽመልስ በቀለ፣ ዑመድ ኡኩሪ፣ ጋቶች ፓኖም ከዛ በፊት ደግሞ ሳላህዲን ሰይድን የመሳሰሉ ተጨዋቾች ለመጫወት ችለዋል፤ ከእነዚህ ውስጥ አሁንም የሚጫወቱ አሉ፤ እዛ ሄዶ መጫወት ቀላል ነው ማለት ይቻላል?

ጋቶች፡- ቀላልማ አይደለም፤ ጠንካራ ሰራተኛ ከሆንክ እና ለመጫወት ደግሞ ሁሉን ነገር የምትደፍር አይነት ተጨዋች ከሆንክ ግን እልምህን የማታሳካበት ምንም አይነት ምክንያት የለም፤ ለዛ ደግሞ እኛን የመሳሰሉ ኢትዮጵያዊ ተጨዋቾች እየተጫወትንም ስለሆነ ሌሎችም ጥሩ ችሎታው ያላቸው ተጨዋቾች በራሳቸው የሚተማመኑና ጠንክረው የሚሰሩ ከሆነ ወደዚህ መጥተው መጫወት ይችላሉ፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች ወደ ግብፅ ሊግ መጥተው እንዲጫወቱ የምትነግራቸው ተጨማሪ ነገሮች ይኖራሉ?

ጋቶች፡- አዎን፤ በቅድሚያ ሁሌም ሄጄ እጫወታለው በሚል አህምሮአቸውን ማሳመን ይኖርባቸዋል፤ ከእነሱ ተጨዋቾችም በችሎታ እበልጣለው ብለውም ራሳቸውን ሊያዘጋጁ እና ጠንክረውም ሊሰሩ ይገባል፤ ያን ማድረግ ከቻሉ እና ወጥተውም እንዲጫወቱ አንድ አንድ መንገዶች ከተመቻቸላቸው በእኛ ተጨዋቾች ላይ ያለኝ እምነት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- አብዛኛዎቹ የእኛ ሀገር ተጨዋቾች በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ ወደ ባህር ማዶ ወጥቶ ለመጫወት ጥረትን ሲያደርጉ አይታይም፤ ከዚህ በመነሳት ምን የምትለው ነገር አለ?

ጋቶች፡- በቅድሚያ ከሀገር ወጥቶ ለመጫወት መጀመሪያ ራስህን በብሔራዊ ቡድን ደረጃ አስመርጠህ ችሎታህን ልታሳይ ይገባል፤ ምክንያቱም እነሱ አንተን ለመውሰድ ሲፈልጉ ብዙ ጊዜ ለብሔራዊ ቡድን መጫወትህን ነው የሚጠይቁህ፤ ይህ እንዳለ ሆኖ ደግሞ ለብሔራዊ ቡድን የተጫወቱ የእኛ ሀገር ተጨዋቾች ወጥቶ ለመጫወት እድሉ ካልመጣላቸው በስተቀር
በራሳቸው ጥረት ሙከራን ለማድረግ የመፍራት ነገር አለና ይሄን ችግር ሊያስወግዱት ይገባል፤ ተመልክተህ ከሆነ አሁን ላይ ብዙ ኳስ የማይችሉና ከእኛ ሀገር ተጨዋቾች የማይሻሉ ተጨዋቾች እኛ ሀገር ደፋር ስለሆኑ ብቻ መጥተው ይሞክራሉ፤ ስለዚህም የእኛም ተጨዋቾች ወጥተው መሞከርን ሊደፍሩ ይገባቸዋል፤ ከደፈሩ መንገዱ ይከፈትላቸዋል፤ ያላየከውን ነገር መፍራት አይኖርብህም፤ ሙከራን ስታደርግ ስለመመለስ ብቻ ማሰብ የለብህም፤ ሊሳካልህ ይችላል፤ ባይሳካ እንኳን ከዛ የጎደለክን ነገር እንዴት ማሟላት እንዳለብህ ስለምታውቅ በቀጣይነት ወጥተህ መጫወትን ትችላለህ፡፡

ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ሊግ ስትጫወት እና ወደ ግብፅ ሊግ አምርተህ በነበርክበት ሰዓት በሚሰጠው ስልጠና ዙሪያ የተመለከትከው ለውጥ እና ልዩነት አለ?

ጋቶች፡- በጣም፤ በሁለቱ ሀገራት በነበረኝ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ እነሱ ስራቸው ሁሉ ፕሮፌሽናል ስለሆነ በተጠና መንገድ ነው አንተን ሊለውጥህ እና የተሻለም ደረጃ ላይ ሊያደርስህ በሚችል መልኩ ስልጠናን የሚሰጡ ወደ እኛ ሀገር ስትመጣ ግን ያን ነገር ብዙም አትመለከትም፤ ስለዚህም እዚህ ሀገር ላይ ስትጫወት የራስህን ጥረት ጭምር ካላከልክበት በኳሱ ትልቅ ደረጃ ላይ ስለመድረስ ፈፅሞ ማሰብም የለብህም፡፡

ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ቡና እና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ብሎም ደግሞ ወደ ባህር ማዶም ሄደህ ከመጫወትህ አንፃር ስለ ቀጣይ ጊዜ የኳስ ህይወትህ ምንድን ነው ከወዲሁ እያሰብክ የምትገኘው?

ጋቶች፡- በእግር ኳስ ህይወቴ አሁን ላይ ኳስን ገና ጠግቤ አልተጫወትኩም፤ ስለዚህም በእዚህ ሰዓት እያሰብኩ የምገኘው ለብሄራዊ ቡድናችን ብዙ ነገሮችን ሰርቼ የሀገሬን ስም ማስጠራትን ነው የምፈልገው፡፡

ሀትሪክ፡- ለብሔራዊ ቡድን የመጫወት ስሜቱን በተደጋጋሚ ጊዜ ተመልከተኸዋል፤ ጣዕሙ ምንድን ነው የሚመስለው?

ጋቶች፡- በአሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ለብሔራዊ ቡድን ከተመረጥኩበትና መጫወትም ከቻልኩበት የሌሴቶው ጨዋታ አንስቶ አሁን እስከምገኝበት የብሄራዊ ቡድን ደረጃ ድረስ ሀገርህን ወክለህ ስትጫወት በውስጥህ የሚኖረው የደስታ ስሜት በጣም ከፍ ያለ ነው፤ ጣዕሙም እንደ ወይን በጣም ጣፋጭ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በኳሱ ከዚህ ቀደም ብዙም ከማትታወቀው የጋምቤላ ክልል እኔን ጨምሮ እስከ አራት የምንደርስ ተጨዋቾች ለብሔራዊ ቡድን ተጨዋችነት በተለያዩ ወቅቶች እየወጣን ለመጫወት እና ጥሩም ነገርን ለህዝቡ ለማሳየት የቻልንበት ሁኔታ በመፈጠሩ በዛም ደስተኛ ነኝ፤ እኔንም ብቸኝነት እንዳይሰማኝም አድርጎኛል፡፡

ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ቡና ተጫውተህ አሳልፈሃል፤ ክለቡ ከፍተኛ እውቅናን እንድታገኝም አድርጎሃል፤ “ጋቶቼ ናና” ተብሎም ተዘምሮልሃል፤ ቡና ለአንተ ምን ማለት ነው? ስለነበረክስ ቆይታ ምን ትላለህ?

ጋቶች፡- ኢትዮጵያ ቡና ማለት ለእኔ ከተተኪው ቡድን አንስቶ የተጫወትኩበት፣ የቤቴን ያህል የምቆጥረው እና በጣም አድርጌም የምወደው ቡድኔ ነው፤ በእግር ኳሱ አሁን ለደረስኩበት ደረጃም ቀዳሚውን ክሬዲት የሚወስደውም እሱ ነው፤ በክለቡ ስለነበረኝ ቆይታ ደግሞ ማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር በጣም ጥሩ የሚባሉ ጊዜያቶችን ለማሳለፍ ችያለው፤ ከዛ ውጪም ለቡና ተጫውቼ በማለፌም ደስታዬ አሁንም ድረስ በውስጤ አብሮኝም ነው ያለው፡፡

ሀትሪክ፡- “ጋቶቼ ናና” ተብሎ ተዘምሮልህ…ኢትዮጵያ ቡናን ግን ለቀቅ፤ በምን ምክንያት ነበር ከክለቡ ጋር የተለያየኸው?

ጋቶች፡- ወደ ባህር ማዶዋ ሀገር ሩሲያ ተጉዤ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ ለመጫወት እድሉን በማግኘቴ ነበር ከክለቡ ጋር የተለያየሁት፤ በዚህ ዙሪያም ከክለቡ ሀላፊዎች ጋር ከተነጋገርንም በኋላ ነው እዛ ሄጄ ስመለስ ቡና ቤቴ ስለሆነ ለክለቡ ነው ቅድሚያ ፈርሜ የምጫወተውም ብያቸው ነው ወደዛ የሄድኩት፡፡

ሀትሪክ፡- ከሩሲያ ስትመለስ ግን አንተ ቡናን ጥለህ ወደ መቐለ 70 እንደርታ አመራህ፤ ቃልህን አጠፍክ ማለት ነው?

ጋቶች፡- በፍፁም፤ የመጫወት ቅድሚያውን የሰጠሁት ከዚህም ስሄድ ተናግሬያለው ለቡና ነው፤ ያኔ ወደ ሀገር ቤት እንደተመለስኩም ቡና ነው መጀመሪያ ያናገረኝ፤ ወደዛ ስታመራም አንድ ሰውን ብቻም አይደለም የምታዋረው፤ ብዙ ሰውን ነው፤ ከዛ እነሱን ሳናግር ሀሳባቸው የተለያየ ሆነብኝ በሚሰጡኝ ክፍያ ዙሪያም መስማማት አልቻልኩም፤ በእዚህ ጊዜም በተለያዩ ድረ ገፆች እና ፌስ ቡክ ላይ በተጋነነ መልኩ የቀረበውን የፊርማ ክፍያ ሳልጠይቅ ጋቶች ቡናን ይሄን ያህል ከፍተኛ በመጠየቁ ከክለቡ ጋር ሳይስማማ ቀረ፤ ወደሌላ ክለብም ሊያመራ ነው የሚል ብዥታ ነገር በመፈጠሩ እኔን በጣም አናደደኝ፤ ማውራት ያለብህ እኮ ከክለቡ ባለቤት ወይንም ደግሞ ከክለቡ ሀላፊዎች ነው፤ ስታወራም እኮ ነገሮች ሚስጥሮች ናቸው፤ ሚስጥር ምንም ነገር ሳይፈጠር ከፈረምክ በኋላ ቢወጣ ሚስጥሩ እኮ ችግር የለውም፤ ሚስጥሩ ሳይወጣ ግን እንትና ይሄን ያህል ጠየቀ አይሆንም ከክለቡ ጋር የሚያጋጭህም ሁኔታ ይሄ ነው፤ እግር ኳስ እኮ በአንተና በክለብህ መካከል መተማመን ሊኖርህ ያስፈልጋል፤ አሁን ያወራከው ነገር መንገድ ጀምሮ አሁን የሚወጣ ከሆነ ነገሮችን አስቸጋሪዎችም ነው የሚያደርጋቸው፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡናን በጊዜው እንደተባለው ከፍተኛ ክፍያ አልጠየቅክም ማለት ነው?

ጋቶች፡- አዎን፤ እኔ የጠየቅኩት ለሌሎች የቡድኑ ተጨዋቾች የሚከፈለውን ከፍተኛ ክፍያ ነው ለእኔም ይሰጥ ያልኩት፤ እኛ ሀገር ግን ይሄን ስትል ነገሮች ይጋነናሉ፤ ለምሳሌ እኛ ሀገር ላይ ለዜጎች የሚከፈለው ክፍያ ከእኛ ተጨዋቾች የበለጠ ነው፤ እኛ ክፍያውን ስንጠይቅ ደግሞ ለምን እንደሆነ አላውቅም አይስማማቸውም፤ ሌላ ሀገር ብትሄድ ለሀገራቸው ተጨዋቾች ነው ከፍተኛ ክፍያን የሚሰጡት፤ ከውጪ ለሚመጣ ያን ክፍያ አይሰጡም፤ ያለንን እምቅ ችሎታን ካወጣን በኋላ ነው እንጂ እዛ በቡድኑ ውስጥ እያለን ስለ እኛ ብዙ ነገር አያውቁም፤ ለእዚህም ነው ብዙ ተጨዋቾች እኛ ሀገር ላይ የተጎዳው፤ ችሎታና አቅም ካለ የምትጠይቀው ክፍያ አግባብ በሆነ መልኩ ሊፈፀምልህ ይገባል፤ አቅም ሳይኖርህ ከውጪ ስለመጣህ ብቻ ሊከፈልህ አይገባም፡፡

ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ቡና ተጫውተህ ስታሳልፍ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለአንድም ጊዜ ለማንሳት አልቻልክም፤ በዚህ ዙሪያ ምን ማለት ይቻልሃል?

ጋቶች፡- በኢትዮጵያ ቡና በነበረኝ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ የሊጉን ዋንጫ ባነሳ በጣም ደስ ይለኝ ነበር፤ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳትም የሚችሉ የተጨዋቾች ስብስብም ነበረን፤ ያም ሆኖ ግን እኔ ካደግኩበት ጊዜ ጀምሮ በየጊዜው አሰልጣኞች ስለሚቀያየሩ፣ በክለቡ ጥሩ የተላመድን ልጆችም ለሁለት እና ለሶስት ዓመትም አብረን በጋራ ባለመ ቆየታችን እና ክለቡም እየፈረሰ እንደ አዲስ ይገነባ ስለነበር ያ ስኬታማ እንዳንሆን አድርጎናልና ክለቡን የጎዳውም ይሄ አሰራሩ ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በድጋፍ ድባባቸው ይለያሉ ወይንስ…..?

ጋቶች፡- ምርጥ ደጋፊዎች ናቸው፤ የሚሰጡህ ድጋፍ ለየት ስለሚል ሁሌ አቅምህን አውጥተህ እንድትጫወት ያደርጉሃል፤ ከዛም ውጪ በከፍተኛ ስሜት ላይ ሆነህ ተነሳስተህ እንድትጫወትም ያደርጉሃል፡፡

ሀትሪክ፡- አዲስ አበባን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት እና በምን መልኩ ነበር ያየሃት?

ጋቶች፡- ከጋምቤላ ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት ልጅ ሆኜ ነው፤ እስከ ሶስተኛ ክፍልም እዚ ነው ለመማር የቻልኩት፤ በኋላም ተመልሼ ወደዛ ካመራሁ በኋላ ነው እግር ኳስን በፕሮጀክት ደረጃ ተጫውቼ በመምጣት ኢትዮጵያ ቡናን ክለብ በተተኪው ቡድን ደረጃ የተቀላቀልኩት፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና የ2003ቱን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ባነሳበት ዓመት ላይ አንተ የት ነበርክ?

ጋቶች፡- ያኔ ክለቡን በተስፋ ቡድን ደረጃ የተቀላቀልኩበት ጊዜ ስለነበር ከዋናው ቡድን ተጨዋቾች ጋር በመሆን ሜዳ እገባ ነበር፤ ብዙ ጨዋታዎችንም ተመልክቻለው፤ በፍፃሜው ቀን ደግሞ ከፍተኛ የሰው ቁጥር ስለነበር ጨዋታውን በቴሌቪዥን መስኮት ለመከታተል ችያለው፡፡

ሀትሪክ፡- ክለቡ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን ከፍ አድርጎ ሲያነሳ የተፈጠረብህ ስሜት ምን ይመስል ነበር? ድባቡንስ እንዴት አገኘኸው?

ጋቶች፡- ያን ዕለት በጣም ነበር የተደሰትኩት፤ እንዲህ ያለ የሰው ጎርፍንም ተመልክቼ አላውቅም፤ ቡና ምን ያህል ተወዳጅ ክለብ መሆኑንም በሚገባ ተረድቻለሁ፤ በስታድየም የነበረውን ድባብ ስመለከትም ምናለ የዚህ ቡድን አባል አድርጎኝ ቢሆን ኖሮም ብዬ ተመኝቻለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ አብሮ ተጣምሮ ሲጫወት ምቾት የሚሰጥህ ተጨዋች ማን ነው?

ጋቶች፡- ብዙ ናቸው፤ ያም ሆኖ ግን በቡና ክለብ ውስጥ በብዛት ስለቆየሁ ከመስዑድ መሐመድ እና ከኤልያስ ማሞ ጋር የነበረኝን ጥምረት ነው በጣም ምርጥ የምለው፡፡

ሀትሪክ፡- ምርጧ ጎልህ የቷ ነች?

ጋቶች፡- ለብሔራዊ ቡድን በተጫወ ትኩበት ሰዓት ሌሴቶን ስናሸንፍ ከርቀት መትቼ ያስቆጠርኳትን ነው ቀዳሚ የማደርጋት፡፡

ሀትሪክ፡- ምርጡ ጨዋታዬ የምትለውስ?

ጋቶች፡- አሁንም ከብሔራዊ ቡድን አልወጣም፤ ከአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ጋር 3-3 የወጣንበት ጨዋታ እንደ ግልም እንደ ቡድንም ጥሩ ስለነበርን እሷን ጨዋታ አስቀድማታለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ከባህር ማዶ አሰልጣኞች የምታደንቀው?

ጋቶች፡- አሌክስ ፈርጉሰንን፤ እሳቸውን ያደነቅኩትም ጥሩ ተጫውቶ ዋንጫ የሚያነሳ ቡድንን ስለሰሩም ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- የዓባይ ግድብን ተንተርሰህ አንድ ነገር በል? በግብፅ እያለህ በዚህ ጉዳይ ላይ ከእነሱ ሀገር ተጨዋቾች ጋር ትነጋገር ነበር?

ጋቶች፡- የአባይ ግድብ ጥቅሙ ለሀገራችን እና ለህብረተሰባችን እስከሆነ ድረስ ሁላችንንም ይመለከተናል፤ ስለዚህም ግድቡ በፍጥነት ሙሉ ለሙሉ ቢገደብልን በጣም ጥሩ እና አሪፍም ነው የሚሆንልን፤ ከግብፅ ጋር በተያያዘ በቆይታዬ በግድቡ ዙሪያ ማለት የምፈልገው እነሱ ነዳጅ እና ብዙ ነገር አላቸው፤ ያ ስለሆነም እኛም በራሳችን ሀብት ማለትም በአባይ ግድባችን በጣም መጠቀም ስላለብን በዛ ዙሪያ ብዙ ጊዜ ከእነሱ ተጨዋቾች ጋር እንነጋገራለን፤ እንደ ፖለቲከኞች ሳይሆን እንደ እግር ኳስ ተጨዋቾች ሆነንም በቀልድ መልክ ስንነጋገርም እነሱ ልገድቡብን ነው አይደል ሲሉኝ እኔም አዎን እኛም በሀብታችን መጠቀም አለብን በሚልም ነው የምመልስላቸውና ስለ አባይ ጉዳይ የማያውቅ ማንም እንደሌለም ልረዳም ችያለው፡፡

ሀትሪክ፡- ሳቂታ ነህ ልበል?

ጋቶች፡- አዎን፤ መሳቅ በጣም ደስ ይለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- በጣም የሚያዝናና ተጨዋች ማን ነበር?

ጋቶች፡- ሙሉዓለም ጥላሁን፣ ቢኒያም ታዬ /ግስላ/ እና ታፈሰ ተስፋዬ በእዚህ በኩል ለየት ስለሚሉ እነሱ ነበር የሚያስቁኝ፤ ከእነሱ ጋር ከዋልክም ፈፅሞ አይደብርክም፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…..?

ጋቶች፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከፈለግን ብዙ ነገሮችን ማሻሻል ይኖርብናል፤ መጀመሪያ ኳሳችንን ፕሮፌሽናል ሊግ ማድረግ ይኖርብናል፤ የሜዳ ብዛት እና የሜዳ ጥራት ሊኖረን ይገባል፤ ኳሱ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ ልናሟላም ይገባናል፤ ያን ማድረግ ከቻልን ወደ ተጨዋቾቻችን እና አሰልጣኞቻችን የጥራት ደረጃ እናመራለንና በዚሁ ነው ልንጓዝ የሚገባን፡፡ ከዛ ውጪ ልናገር የምፈልገው ነገር አሁን ላይ በኳሱ ለደረስኩበት ደረጃ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱልኝ ቤተሰቦቼ ባለቤቴ እና እኔን ከስር ጀምሮ ላሰለጠኑኝ እና ለመከሩኝ ሁሉ ምስጋናዬ ከፍ ያለ መሆኑን ነው፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website