በ24ኛው ሳምንት ከባለሜዳው መከላከያ ጋር እዚሁ አዲስ አበባ ስታዲዬም በደጋፊዎቹ ፊት የተጫዎተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ተጋርቶ የሊጉ መሪ የሚሆንበትን ዕድል አባክኗል፡፡
ባለፈው ሳምንት እዚሁ ስታዲዮም ወልዋሎን 1-0 የረታው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዛሬው ጨዋታ ለአዳነ ግርማና በሀይሉ አሰፋ ቅድሚያ በመስጠት አቡበከር ሳኒና አሜ መሀመድን በማሳረፍ ገብተዋል፡፡ባለሜዳዎቹ መከላከያዎች በድሬድዋ ከተማ ሽንፈት ሲያስተናግዱ በመጀመሪያ ቋሚ 11 አሰላለፍ ከተካተቱት ተጨዋቾች በሀይሉ ግርማን በማሳረፍ ማራኪ ወርቁን ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡
በበርካታ ተመልካች ታጅቦ በተጀመረው ይሄው ጨዋታ ግብ የተስተናገደበት ገና በጊዜ ነበር፡፡ግቧ ምናልባትም የኘሪሚዮር ሊጉ ፈጣኗ ግብ ልትሆን ትችላለች፡፡ማራኪ ወርቁ ከመሀል ሜዳ በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ በአግባቡ ተቆጣጥሮ በግቡ ትይዩ 2 ጊዜ ወደ ፊት ኳሷን ከገፋ በሇላ ሳጥኑ ውስጥ እንደገባ አክሮ የመታው ኳስ ሮበርት ኦዶንካራ ለማውጣት ቢሞክርም ሳይሳካለት ኳስና መረብ ተገናኝተው ጦሮቹ በጊዜ መሪ መሆን ቻሉ፡፡ከግቧ መቆጠር በሇላ ፈረሰኞቹ የአቻነቷን ግብ ፍለጋ መከላከያን አስጨንቀው ለመጫዎት ባደረጉት ሂደት በ4ኛው ደቂቃ ናትናኤል ዘለቀ ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔ ሲመልሰው ተጨርፎ የደረሰውን ኳስ አዳነ ግርማ በድጋሚ ሞክሮት አገባው ሲባል ኳስ በግቡ አግዳሚ ወደ ላይ ስትወጣ በድጋሚ በ9:10:እና 11ኛው ደቂቃ ላይ ፈረሰኞቹ በአዳነ ግርማ፡ናትናኤል ዘለቀ እና ኦልቫልዶ ታቫሬዝ አማካኝነት ያለቀላቸው ኳሶችን ቢያገኙም ሳይጠቀሙባቸው ባክነዋል፡፡በተለይም በ17ኛው ደቂቃ የመከላከያ የተከላካይ ክፍል የሰሩትን ጥፋት ጠቅሞ ከርቀት የተሻገረለትን ኳስ አዳነ ግርማ በደረቱ አብርዶ ወደ ግብ አክሮ የመታው ኳስ መባከኑ እንጁ ፈረሰኞቹን ወደ አቻነት በጊዜ ሊመልስ ይችል ነበር፡፡
ከዚህ በሇላ በጣለው ዝናብ ምክንያት ለመጫዎት ፈታኝ በነበረው ሜዳ ጨዋታው ሚዛኑ ሀይል ወደ ተቀላቀለበትና የሚቆራረጥ፡ኳሶች ሲላኩ በታሰበላቸው ተጨዋቾ እና የሜዳ ክፍል ሳይደርሱ መሃል ላይ የሚቀሩበት ሁኖ አምሽቷል፡፡በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ የመከላከያው ፍፁም ገብረማርያም ብቻውን ከግብ ጠባቂው ኦዶንካራ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ልዩነቱን ማስፋት የሚችልበትን ዕድል ሲያባክን ውጥረት በነገሰበት የምሽቱ ጨዋታ ሳላዲን ባርጌች ከማዕዘን በሀይሉ ያሻገረውን ኳስ በጭንቅላቱ ገጭቶ ሞክሮት የግቡ ቋሚ ኳስን ጨርፎ አውጥቷል፡፡ሀይል ያመዘነበት አጨዋወት በነገሰበት በዚሁ ጨዋታ ውጥረቱም እየጋለ መጥቶ በመጀመሪያው አጋማሽ ማገባደጃ 45ኛው ደቂቃ ፈረሰኞቹ በቀኝ መስመር ወደ መከላከያ የግብ ክልል ያሻገሩትን ኳስ ለማግኘት በነበረው እንቅስቃሴ ኳስን ይድነቃቸው ኪዳኔ ቀድሞ ሲይዝ አዳነ ግርማና አዲሱ ተስፋዬ ኳስን ለማግኘት በወደቁበት የመከላከያ የግብ ክልል ውስጥ ባደረጉት መጎሻሸም /መሰናዘር/ የመሃል ዳኛው የነበረውን ሁኔታ በቀኝ መስመር ከነበረው ረዳት ዳኛ ጋር በመነጋገር ሁለቱም ተጨዋቾች በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወጡ የጨዋታው አጋማሽ በዚሁ ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በጎደሎ ተጨዋቾች መጫዎታቸው በእንቅስቃሴ ላይም ተፅኖ አሳድሯል፡፡በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ ስንመለከት ፈረሰኞቹ በአንፃሩ እንደመጀመሪያው አጋማሽ በርካታ የግብ ሙከራዎችን ባያደርጉም የተሻሉ ሁነው ሲያመሹ መከላከያ ወደ ሇላ አፈግፍገው ሲከላከሉ አምሽተዋል፡፡በ61ኛው ደቂቃ በሀይሉ አሰፋ ከማዕን ያሻማውን ኳስ ኦዝቫልዶ ታቫሬዝ በጭንቅላቱ ገጭቶ ኳስን ከመረብ በመሳረፍ ቡድኑን ወደ አቻነት መልሷል፡፡ከግቧ መቆጠር በሇላ ፈረሰኞቹ ጫና ፈጥረው ግብ ለማግኘት ሲቀሳቀሱ፡መከላከያዎች አልፎ አልፎ በግራ መስመር በኩል የሚሰነዝሩት ጥቃት ጥሩ ቢሆንም በዚህኛው ጨዋታ ቡድኑ የበለጠ ጫና ውስጥ የገባበት ክስተት ተፈጥሯል፡፡
በ69ኛው ደቂቃ በጨዋታውና በዳኛው ውሳኔ ሲበሳጭ ያመሸው ዳዊት እስጢፋኖስ በፈረሰኞቹ የሜዳ ክፍል በክርኑ አስቻለው ታመነን በመማታቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣ የዕለቱ የጨዋታው 3ኛ ተጨዋቾች ሁኗል፡፡ከዚህ በሇላ በ9 ተጨዋቾች ጨዋታውን ለመጨረስ መከላከያ ጫና ውስጥ በመግባቱ ውጤቱን ለማስጠበቅ የመከላከል ባህሪ ያላቸው ተጨዋቾችን በቁጥር አብዝተው በመጠቀም ውጤቱን ለማስጠበቅ ተጫውተዋል፡፡የተጨዋቾች የቁጥር ብልጫ የነበራቸው ፈረሰኞቹ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ አስቻለው ታመነ በጭንቅላቱ ገጭቶ ለግብ የቀረበ ሙከራ ከማድረጉ በተጨማሪ ከርቀት አብዱልከሪም ኒኪማ ባደረገው ሙከራ ሌላ ግብ ሳይቆጠር 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ጨዋታው ሲጠናቀቅ ፈረሰኞቹ ወደ ሊጉ መሪነት የሚመለሱበትን መልካም አጋጣሚ ሳይጠቀሙበት ባክኗል፡፡በዚህም ፈረሰኞቹ በ41 ነጥብ በጅማ አባጅፋር በግብ ክፍያ ተበልጠው 3ኛ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡ መከላከያም አሁንም ከወራጂ ስጋት ሳይላቀቅ በ29 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
☞መከላከያ- አሰልጣኝ ስዩም ከበደ
ከመውረድ ስጋት ነፃ ለመሆን እያንዳንዱ ጨዋታ ወሳኝ ነው፡፡በጨዋታው ለማሸነፍ ያደረግነው ጥረት ጥሩ ነበር፡፡በተጋጣሚያችን የጨዋታ ብልጫ ተወስዶብን ነበር ፡፡ወደ ሇላ አፈግፍገን ተጫውተናል ግን የኔ ትዕዛዝ አልነበረም፡፡ድሬድዋ ላይ ነጥብ በመጣላችን ውጤቱን ዛሬ ማስጠበቅ ነበረብን 1ነጥብ ተጋርተናል፡፡
☞ቅ/ጊዮርስ- ቫስ ፒንቶ
በጨዋታው እየተመራን ነበር ጨዋታውን የጀመርነው፡፡ነገር ግን የቡድናችን እንቅሰስቃሴ ጥሩ ነበር ፡፡የጨዋውን የበላይነት መውሰድ ችለናል፡፡በርካታ የግብ ዕድሎችን ፈጥረን 1ግብ ብቻ አስቆጥረን ነጥብ ለመጋራት ተገደናል፡፡ዕድለኛም አልነበርንም፡፡
አስተያየት ይስጡ