መከላከያ በከፍተኛ ሊግ እየተጫወተ በፕሪምየር ሊጉ ውል ሊያስገድደኝ አይችልም” አናጋው ባደግ (መከላከያ /ወላይታ ድቻ)

 

የመከላከያው አናጋው ባደግ የ1 አመት ውል እያለው መልቀቂያ ሳይሰጠውና ከክለቡ ፍቃድ ሳያገኝ ለወላይታ ድቻ መፈረሙ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

የወላይታ ዲቻው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኢያሱ ነጋ “የተጨዋቹ ቤተሰቦች እዚሁ እኛ አካባቢ ስላሉና እሱንም በየቀኑ ከማግኘታችን ውጭ ምንም አይነት ድርድር አላደረግንም” በማለት ቢያስተባብሉም የክለቡ ፔጅ ግን በፎቶ አስደግፎ ይፋ ባደረገው መረጃ አናጋው ባደግ ለክለቡ መፈረሙን ዘግቧል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከሀትሪክ ጥያቄ የቀረበለት አናጋው ባደግ በበኩሉ “ፕሪሚየር ሊጉ ላይ ይቆያሉ በሚለው የፌዴሬሽኑ ውሣኔ መሠረት 2 አመት ፈርሜ ነበር፤ ነገር ግን ውሣኔው ተገልብጦ በከፍተኛ ሊግ እንዲጫወቱ በመደረጉ ክለቡን ለመልቀቅ ብፈልግም ወኪሌ ውሉን ለማስጨረስ በመዘግየቷ መከላከያ ልቀጥል ተገድጃለሁ፡፡ እሱም የተደረገው በአንድ አመት ውል ተስማምተን ነው፤ እነሱ ግን ያፀደቅነው የፕሪሚየር ሊጉን ውል በመሆኑ ቀሪ አንድ አመት አለብህ በማለታቸው ቅር ብሎኛል” ብሏል፡፡

© photo official wolita dicha page

አናጋው እንደሚለው “ሌላ ክለብ አግኝቼ ከፈረምኩ በኋላ ደውለው ውል እንዳለኝ ነገሩኝ፡፡ ለአንድ አመት እንድጫወት ግን አሰልጣኞቹ እና ቡድን መሪው ባሉበት ተነጋግረን ነው የተስማማነው፡፡ ይህ ስምምነታችን ግን ጥሰውታል፡፡ አሰልጣኝ ዮሀንስ ማንንም አስገድጄ ማስቀረት አልሻም ተጨዋቹ ከፈለገ ልትለቁት ይገባል ብሏል፡፡የክለቡ አመራሮች ግን ሊለቁኝ አልፈለጉም” ሲል ተናግሯል፡፡

“ለዚህ ሁሉ ክፍተት የዳረገችኝ ወኪሌ ናት የተለያየ ምክንያት አብዛታ ሳትፈርምልኝ በመቅረቷ አንድ አመት ልቆይ ተገድጃለሁ፡፡ ክለቡ ቃል የገባልኝን ቦነስ ሳይፈፅም ትጥቅ መልስ ብለውኝ ከመለስኩ በኋላ ይሄን ችግር መፍጠራቸው አስከፍቶኛል” ያለው ተጨዋቹ “ውል ያላቸውንና የማይፈልጓቸውን አሰናብተዋል፤ ባለኝ ስምምነት መሠረት አንድ አመት በመጨረሴ ሊለቁኝ ሲገባ ቀሪ አንድ አመት አለህ እያሉኝ ነው ፤ ጉዳዩን እንድታስተካክልልኝ ወደ ወኪሌ ብደውልም ከአገር ውጭ መሆኗን ነገሩኝ ያለኝ እድል በወቅቱ እማኝ ወደ ነበሩት መደወል ቢሆንም ስልካቸውን አንስተው ሊያናግሩኝ አልፈቀዱም” ሲል ቅሬታውን ለሀትሪክ ገልጿል፡፡
አናጋው ባደግ “ለወላይታ ድቻ ከመፈረሜ በፊት አናግሬያቸዋለሁ አመቱ ሙሉ አልተጫወትኩም፤ ቁጭ ብዬ ነው አመቱ ያለቀው ሌሎች መልካም አጋጣሚዎችን እንዳልጠቀም አድርገው ሌሎችን በፈቃደኝነት ለቀው እኔን ነው ያጉላሉኝ፤ ቃል የገቡትን ሁሉ ሳይፈፅሙ ቀርተው መልቀቂያየን ለመስጠት አለመፍቀዳቸው አሳዝኖኛል፡፡ መከላከያ በከፍተኛ ሊግ እየተጫወተ በፕሪሚየር ሊጉ ውል ሊያስገድደኝ አይችልም” ሲል ቅሬታውን ለሀትሪክ ገልጿል፡፡
የመከላከያ ቡድን መሪ ኮ/ል ደሱ ግን በፍፁም ውሸት ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ “ሲጀመር ቦነስ ይሰጣል ብለን ቃል አልገባንም ከቡድኑ ላደጉት ተጨዋቾች ብቻ ነው ቦነስ የሰጠነው፤ አናጋው ትልቅ ውሸት እየዋሸ ነው ልውጣ ብሎ ጠይቆንም አያውቅም፤ ክለባችን ፕሪሚየር ሊግ እንደማይወዳደር ሲነገረን ለከፍተኛ ሊግ ጥቅማ ጥቅም የለንም በማለታችን በርካታ ተጨዋቾች ለቀዋል፡፡ ያኔ አይለቅም ነበር?” በማለት ጠይቀዋል፡፡ ኮ/ል ደሱ እንደሚሉት “ስም ማጥፋቱን አቁሞ ውሉን ማክበር አለበት ይሄ ግዴታው ነው ለእሱ የቅርብ ሰው ማሳሰቢያችንን ልከናል፡፡ የፈረመው ካለ ቶሎ ያስተካክል ወይንም ስህተቱን ቶሎ ያስተባብል አለበለዚያ ከባድ ርምጃ እንወስዳለን ይሄ የመጨረሻ አቋማችን ነው” በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡

 

በሌላ በኩል የፋሲሉ የመስመር አጥቂ ሽመክት ጉግሳ ከፋሲል ከነማ አመራሮች ጋር ተስማምቶ በጎን ለወላይታ ዲቻ የመፈረሙ ነገር ጥያቄ አስነስቷል፡፡ በዝውወር ሕጉ የዝውውር መስኮቱ ተከፍቶ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት በመገኘት ክለቦችና ተጫዋቾች ውላቸው እንዲፈፅሙ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ውሉ ተፈፃሚነት የለውም በሚል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ቢያዝም ሰሚ ጆሮ አላገኘም፡፡

የባህር ዳር ከተማው ግርማ ዲሳሳ ለፋሲል ከነማ ከፈረመ ከወር በኋላ ወደ ቀድሞ ክለቡ የመመለሱ ዜና የወላይታ ድቻ አመራሮችን ሳያሳስብ ባለፈው ረቡዕ የቀድሞ አጥቂያቸውን ሽመክት ጉግሳን አስፈርመውታል፡፡ ተጨዋቹ ለፋሲል ትልቅ ክብር እንዳለው ገልጾ ከ15 ቀን በፊት ጀምሮ የሚፈልገውን እንዲሰጡት ለአመራሮቹ ቢነግራቸውም ምላሽ ባለማግኘቱ የራሱን ውሣኔ እንደወሰነ ተናግሯል፡፡

በርካቶችን ጥያቄ እንዲጠይቁ ያደረገው ተጨዋቹ ለፋሲል ከነማ አመራሮች ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ አጥቶ ለወላይታ ዲቻ የፈረመው ምን ቢያገኝ ነው የሚለው ምላሽ የሚያስፈልገው ሆኗል፡፡ የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በሁኔታው መደንገጡን ለሀትሪክ ገልጿል፡፡ አሰልጣኙ እንደሚለው “ሽመክት ጉግሳ አንደኛ ደረጃ ፈራሚ መሆኑን ነው የማውቀው፡፡ በሚፈልገው መልክ ተደራድሮና ተስማምቶ ነው የወጣው የማውቀው ከክለቡ ጋር ሙሉ በሙሉ መስማማቱን ነው፡፡ ክፍያው የሚፈፀመው መስከረም 21/2012 ውል ከተዋዋልክና ሕጋዊ የክለቡ ተጨዋች መሆንህ ከተረጋገጠ በኋላ ነው ክፍያው የሚፈፀመው… በፋይናንስ ስርዓቱም አሁን ገንዘብ ማውጣት ይቸግራል ከፈረሙ በኋላ ይወስዳሉ ይሄ ነው እውነቱ… ሕጋዊ ባልሆነ መንገድም ወላይታ ድቻ ካስፈረመው ትክክል አይደለም፡፡ በፋሲል ከነማ አሰራር የዝውውር መስኮቱ ሲከፈትና ውል ሲፅድቅ ከነማው በጀቱን ይለቅልናል ሁሉም ተጨዋች ይህን ያውቃል” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ “መስከረም ወር ላይ የዝውውር መስኮቱ ከተከፈተና ተጨዋቾኝ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ሄደው ከፈረሙ በኋላ ውሉ ይፀድቃል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ስለ ክፍያ ማውራት የሚቻለው….ፌዴሬሽን የፀደቀ ውል ካላገኘ የፋይንስ ኃላፊው መቼም ቢሆን ክፍያውን አይፈፅምም፡፡ ይሄ ነው ሕጋዊ ስርዓቱ.. ከዚያ ውጪ ከከፈለ የመንግስት የፋይናንስ ስርዓት ተጥሷል ማለት ነው” ሲሉ ይናገራሉ፡፡ አሁን ባለው የዝውውር መንገድ ይሄ የመንግሥትን የፋይናንስ ስርዓት ያከበሩ ክለቦች ጥቂት ናቸው አብዛኞቹ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ነው ያስፈረሙት.. ሕግ ባለማክበር ራሳቸውን እያጠናከሩ ነው በሚል የክለብ አመራሮችና ተጨዋቾቹ ይታማሉ፡፡ በጎን በተፈረሙ ከፍተኛ የፊርማ ዋጋ ይጫወቱ የነበሩ ተጨዋቾች በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ውድድር ሲቋረጥ ግን ክለቦቹ የ50 ሺ ብሩን ሕግ ጠብቀው የተጣራ 34 ሺ ብር ብቻ እየከፈሏቸው መሆኑን በምሣሌነት የሚያነሱ አሉ፡፡ አሁንም 50 ሺ ብር የሚለው ሕግ ለሌብነትና ለማጭበርበር በር የከፈተ እንጂ መንግሥትን ገቢ እያሳጣ መሆኑን በርካቶች ይናገራሉ፡፡

ለ2 አመታት ሽመክት ጉግሳን ያስፈረሙት የወላይታ ድቻ የእግር ኳስ ክለብ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኢያሱ ነጋ ግን ምንም የተጣሰ የፋይናንስ ስርዓት የለም ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ “ሽመክት ከኛ ጋር ተደራድሮ በመስማማት ፊርማውን አኑሯል፡፡ ገና መስከረም 2 የዝውውር መስኮቱ ሲከፈት ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ሄደን ማፅደቅ ቢጠበቅብንም በስምምነታችን ደስተኞች ነን፡፡ በስምምነቱ መሰረት የከፈልነው ክፍያ የለም የተደራደርነው በደመወዝ ነው… ያሳደግነው ልጅ በመሆኑ ለቡድኑ ቅድሚያ ሰጥቶ ፊርማውን አኑሯል ያለው እውነታ ይሄ ነው” ሲሉ ለሀትሪክ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport