መቐለ 70 እንደርታ በናይጀርያዊው አጥቂ ኦኪኪ ኦፎላቢ ሁለት ግቦች ሰበታ ከተማን አሸነፈ።በትግራይ ስታድየም ሰበታ ከተማን ያስተናገዱት ምዓም አናብስቶች ኦኪኪ በመጀመርያውና በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ግቦች ታግዘው ማሸነፍ ችለዋል።መቐለ ባሳለፍነው ሳምንት ወልቂጤን ካሸነፋት የመጀመርያ ተሰላፊዎች ምንም ለውጥ ያላደረጉ ሲሆን በአንፃሩ ሰበታዎች 2 ቅያሬዎችን አድርገዋል።ሳሙኤል ታዬ እና ዳዊት እስጢፋኖስ ወጥተው ሲላ አሊባድራ እና ጌቱ ሀይለማርያም ገብተዋል።
ቀዝቀዝ ባለ የጨዋታ እንቅስቃሴ የጀመረው የመጀመርያው አጋማሽ በመጀመርያዎቹ 10 ደቂቃዎች ላይ መሀል ሜዳ አካባቢ ከሚደርጉ ቅብብሎች ውጪ ይህ ሚባል የግብ እድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር።ሆኖም መቐለዎች በተለመደው ቀጥተኛ አጨዋወታቸው በአማኑኤል ገብረሚካኤል እና ዮናስ ገረመው አማካኝነት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ዳንኤል አጃይ በቀላሉ ሊይዛቸው ችሏል።
ቀስ በቀስ በተሻለ መልኩ ፍጥነቱን እየጨመረ የመጣው ጨዋታ መቐለዎችን ቀኝ መስመር ላይ ትኩረት ያደረገ አጨዋወትን በመጠቀም እድሎችን ፈጥረዋል።የዚህ እንቅስቃሴ ውጤትም ቀኝ መስመር የተገኘውን ቅጣት ምት ዮናስ ገረመው አሻምቶት ግዙፋ አጥቂ ኦኪኪ ኦፎላቢ በግምባሩ ገጭቶ አስቆጥሮታል።በዚህም ናይጀርያዊው አጥቂ በመቐለ 70 እንደርታ ማልያ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ግቡን ማስቆጠር ችሏል።ኳስ ተቆጣጥሮ መጫወት ላይ ጥሩ የነበሩት ሰበታዎች አብዛኛው ቅብብላቸው መሀል ላይ ከመሆኑ በተጨማሪ ከመስመር ሚያሻግርዋቸው ኳሶች የጠሩ አለመሆናቸው የግብ እድሎችን እንዳይፈጥሩ አድርግዋቸዋል።በመጀመርያው አጋማሽም ባኑ ዲያዋራ ከቅጣት ምት ከሞከረው ሙከራ ውጪ ለግብ የቀረበ ሙከራን ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በመቐለዎች ፈጣን የመስመር ማጥቃት የተጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ ግብ ለማስተናገድ ከአንድ ደቂቃ በላይ አልፈጀበትም።ቀኝ መስመር ላይ ስዩም ተስፋዬ ከዮናስ ገረመው የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ያሻማው ኳስ ኦኪኪ ኦፎላቢ በግምባሩ አስቆጥሮ ለራሱም ለክለቡም የጨዋታው ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።ሳይታሰብ በሁለተኛው አጋማሽ መጀመርያ ላይ ግብ ያስተናገዱት ሰበታዎች አሁንም በተመሳሳይ ተከላካይ ክፍላቸውን ወደ መሀል አስጠግተው በአጫጭር ቅብብሎች ወደ መስመር በመውጣት ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ እድሎችን ፈጥረዋል።ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን በቅርበት የተገኘችውን ቅጣት ምት ባኑ ዲያዋራ መትቷት ለትንሽ ከግቡ አናት የወጣው እና ተቀይሮ የገባው ኤፍሬም ሲሳይ ከግራ መስመር አሻምቶት ፍፁም ገብረማርያም ተንሸራቶ በእግሩ ገጭቶት ለትንሽ ከግቡ ጎን የወጣው ተጠቃሽ ሙከራዎች ናቸው።በአንፃሩ መቐለዎች የሰበታ ተከላካይ ክፍል ወደ መሀል ሜዳ መጠጋትን ተመልክተው በፈጣን መልሶ ማጥቃት በአማኑኤል ገብረሚካኤል እና ኦኪኪ ኦፎላቢ አማካኝነት እድሎችን ቢፈጥሩም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።
ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች እድሎች መፍጠራቸውን የቀጠሉት ሰበታዎች በ79ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ጌቱ ሀይለማርያም ያሻማው ኳስ ሲይላ አሊባድራ በደረቱ ሲያበርደው ተቀይሮ የገባው እንዳለ ዘውጉ በሚገባ ተጠቅሞ ሰበታዎችን ማነቃቃት ችሏል።ከግቧ መቆጠር በኃላ ሰበታዎች ሙሉ ሀይላቸውን ማጥቃት ላይ አድርገው በሚጫወቱበት ሰዓት መቐለዎች በመልሶ ማጥቃት በአማኑኤል በኩል ሄደው ፈጣኑ አጥቂ ፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ በአዲስ ተስፋዬ መጎተቱን ተከትሎ ፍፁም ቅጣት ምት ማግኘት ችለዋል።ሆኖም አማኑኤል የመታው ፍፁም ቅጣት ምት ዳንኤል አጃይ ሊያድንበት ችሏል።መደበኛው ጨዋታ ተጠናቆ የዕለቱ ዳኛ በጨመሩት የባከኑ 5 ደቂቃዎች ላይ ሰበታዎች አቻ ሚያደርጋቸው ግብ ለማግኘት ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርትዋል፣መቐለዎችም በመልሶ ማጥቃት በኦኪኪ ኦፎላቢ ሁለት ለግብ የቀረቡ መከራዎችን አድርገው አግዳሚ ብረትና፣ዳንኤል አጀይ መልሶባቸዋል።
ውጤቱን ተከትሎ መቐለ 70 እንደርታዎች ነጥባቸውን 19 በማድረስ መሪነታቸውን አስቀጥለዋል።
አስተያየት ይስጡ