“መቐለ 70 እንደርታን ጠንካራ ያደረጉት ኳስን በእውቀት የሚደግፉት ደጋፊዎቻችን ናቸው”ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ /መቐለ 70 እንደርታ/ (ክፍል-1)

“ክለቦቻችን ውስጥ የሚታየው ኢትዮጵያዊነት ሰፍቶ
ዘረኝነት ከምድሪቱ ተወግዶ ማየት እመኛለው”

“መቐለ 70 እንደርታን ጠንካራ ያደረጉት ኳስን በእውቀት

የሚደግፉት ደጋፊዎቻችን ናቸው”

“2ኛ ዙር ላይ ማየት የማልፈልገው
የዳኞችን የስህተት ውሳኔ ነው….”

 

መቐለ ቀበሌ 06 በተለምዶ ዶምቦስኮ የሚሰኝ ስፍራ አለ…..እንግዳችን በልጅነቱ እዚህ አካባቢ ኳስ እየጫወተ አድጓል፡፡ ከስሁል ሽረው አምበል ዮናስ
ሀኪምም ከእንግዳችን ጋር እየጫወተ አድጓል፡፡ በቀበሌ 05 ፋዘርቲኖ የተሰኘ ሜዳ አለ፡፡ በአንድ በኳስ ፍቅር ባበዱ የውጪ ሀገር ዜጋ በተሰየመው በዚህ
ሜዳ ላይ የመቀለ ምልክት ከሆኑ ተጨዋቾች መሀል አንዱ የሆነው እንግዳችን ብቅ ብሎ በፕሪሚየር ሊጉ በመቀለ 70 እንደርታ የመሀል ሜዳ ላይ ሲጫወት
መታየቱ ለአብሮ አደጎቹና ለአካባቢው ሰዎች ደስታን ፈጥሯል፡፡ ዶምቦስኮ በሚባል ስያሜ በተሰየመውና በነጮች በተያዘው ሜዳ ላይ ከእግር ኳስ ውጪ
የቅርጫትና የእጅ ኳስ ጨዋታዎች ይካሄድበታል፡፡ ለመማር እያሰበ ባልታሰበ ገጠመኝ ለትራንስ ኢትዮጵያ 4 ጨዋታ አድርጎ አስገራሚ በሆነ ሁኔታ ለመቐለ
ከነማ የፈረመው እንግዳችን ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ ባለፉት 8 አመታት ለመከላከያ ለወልዲያ ለአውስኮድ ከተጫወተ በኋላ አሁን የመቀለ 70 እንደርታ
የትላንቱ መቐለ ከነማ ግልጋሎት እየሰጠ ነው…… በሻምፒዮኑ መቐለ ቤት ውስጥ የቡድኑ አባል በመሆን ብዙዎች የሚመኙት ጥቂቶች ብቻ የሚያገኙትን
የሊጉን ድል ተቀዳጅቷል፡፡ በ2012 የ1ኛ ዙር 15 ጨዋታዎች መሀል በአስራ አንዱ የተጫወተው ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ ከዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ
ለበርካታ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ተጨዋቹ ስለ አስገራሚው የእግር ኳስ አጀማመሩ፣ ስለ ሚወደውና የሚያደንቀው አሰልጣኝ፣ ስለ 1ኛ ዙር ምርጥ
ቡድንና ምርጥ ተጨዋች፣ ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት፣ ስለ አምና ድል፣ ስለ ክለቡ ደጋፊዎች፣ ስለ ደመወዛቸው፣ በቦታው ምርጥ ስለሆነው ተጨዋች፣ በሀገር
ደረጃ ጠፍቶ ማየት ስለሚፈልገውና ሌሎች ጉዳዮች የሰጠው ቃለ ምልልስ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

ሀትሪክ፡- መቐለ ከነማ ጀምረህ አሁን ያለኸው መቀለ 70 እንደርታ ነው አጀማመርህ ምን ይመስላል?
ሙሉጌታ፡- እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሰፈር ውስጥ ኳስ ስጫወት ነው ያደኩት… ነገር ግን ተምሣሌት የሆነ ተጨዋች ባይኖረኝም የኳስ ፍቅር ነበረኝ በልጅነቴ ቤተሰቤ እንድማር እንጂ
ኳስ እንድጫወት ስለማይፈልጉ ትምህርቴን እየተማርኩ አንዳንዴ ብቅ እያልኩ ኳስ እጫወት ነበር በአንድ አጋጣሚ ክረምት ላይ ከ15 አመት በታች ውድድር ሲካሄድና ስጫወት ተስፋ እንዳለኝ
ይነግሩኝ ነበር ዮሀንስ የሚባል አሰልጣኝ ትራንስ ሊወርድ በነበረበት አመት ቀሪ 4 ጨዋታ ስለነበር የልደት ካርድ አውጣ አለኝና ካርዱን ይዤ ከዋናው ቡድን ጋር 4ቱን ጨዋታ ተጫወትኩ የኔ
ታሪክ የጀመረው እዚህ ጋር ነው….. ከ4ቱ ግጥሚያ በኋላ ትራንስ ኢትዮጵያ ተበተነ ወዲያውኑ መቐለ ከነማ ተቀላቀልኩ አብረውኝ ከነበሩ 6 ተጨዋቾች ጋር መቐለ ገባን፡፡

ሀትሪክ፡- አራቱ ጨዋታዎች ለመቐለ ከነማ እንድትፈርም አድርጎሃል ማለት ይቻላል?
ሙሉጌታ፡- አዎ በደንብ ጠቅሞኛል፡፡

ሀትሪክ፡-እውቀት ጨመረልኝ በኔ ላይ ትልቅ ለውጥ አመጣ የምትለው አሰልጣኝ ማነው?
ሙሉጌታ፡- ገ/መድህን ኃይሌ ነዋ……መከላከያ ትንሽ ጊዜ አብሬው ሰርቻለው እያደክ ስትሄድ ስታውቅ ነው እየተሻሻልክ የምትመጣውና የተሻለ ነገር ሰጠኝ የምለው ገ/መድህን ኃይሌን
ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የመቀለ ከነማ የወቅቱ አሰልጣኝ ማን ነበር?

ሙሉጌታ፡- አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ነበር….. እርሱ የሙሉ ጊዜ አሰልጣኜ ነበር፡፡

ሀትሪክ፡-ወደ 4 ክለቦች ተጫውተሃልና ቆይታህን እስቲ አውጋን?

ሙሉጌታ፡- አጠር ባለ ጊዜ ውስጥ ነው ወደዚህ ደረጃ የደረስኩትና በጉዞዬ ደስተኛ ነኝ….. ተስፋ ቡድን አለመስራቴ ወዲያውኑ ዋና ቡድን መቀላቀሌ ጠቅሞኛል…..መቐለ ከነማ 1
አመት መከላከያ 2 አመት፣ ወልዲያ ከተማ 2 አመት፣ አውስኮድ 1 አመት አሁን መቐለ 70 እንደርታ 2ኛ አመቴን ይዣለሁ፡፡ በመቐለ ሻምየን ቡድን ውስጥ ነበርኩ በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡
አሁን 3ኛ አመቴን ይዣለው በቆይታዬ ደስተኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡-አምና ከነበራችሁ ውጤት አንፃር የዘንድሮውን እንዴት አየኸው?

ሙሉጌታ፡- የአምና 1ኛ ዙርን ለየት የሚያደርገው ወደ 11 ግጥሚያ ሳንሸነፍ መዝለቃችንና 1ኛ ዙርን በመሪነት መጨረ ሳችን ነው….ዘንድሮ ግን 3ኛ ሆነን ነው 1ኛ ዙርን የፈፀምነው፡፡
ይሄኛው አመት ላይ ቡድኖች ጠንክረው መጥተዋል፡፡ እነጊዮ ርጊስም ወደ ተፎካካሪነት ተመልሰዋል ፋሲ ልም በጥንካሬው ቀጥሏል ፈተናው እየጠነከረ መጥቷል ያም ሆኖ የዘንድሮ 1ኛ ዙርም
ከባድ አይደለም፡፡

ሀትሪክ፡-ዘንድሮ የመቐለ 70 እንደርታ ቀንደኛ የዋንጫ ተፋላሚ ማነው?
ሙሉጌታ፡- ጠንካራ ተፎካካሪ ናቸው የምለው ፋሲል ከነማንና ቅዱስ ጊዮርጊስን ነው፡፡ ሁለቱም ጥሩ አቋም ላይ ይገኛሉ እኛ ያለን ርቀት የ1 ጨዋታ ውጤት ነው ገና ያልተጫወትነው 15
ጨዋታ አለን (ቃለ ምልልሱን የሰራነው ሀሙስ እለት ነው) በነዚህ ግጥሚያዎች ጠንክረን ተፋልመን አሸናፊ ለመሆን እንጥራለን ለዚህም ተዘጋጅተናል የተሻለ ነገር እንሰራለን ብዬም
አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡- ለሙሉጌታ የ1ኛ ዙር ምርጥ ቡድንና ምርጥ ተጨዋች ማነው?

ሙሉጌታ፡- እንደ ቡድን ምርጡ መቐለ 70 እንደርታ ምርጥ ተጨዋች ደግሞ ስዩም ተስፋዬ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-በቃ.. ሌላ የለም…?

ሙሉጌታ፡- በጨዋታ ውስጥ ማየት የምችለው አጠገቤ ያለውን ነው፡፡ በውድድር ውስጥ በመሆኔ ሁሉንም ማየትና መገምገም አልችልም ስለዚህም ነው ብዙ መናገር ያልቻልኩት፡፡

ሀትሪክ፡-በ15 ጨዋታ 14 ግብ ያስቆጠረውን ሙጂብ ቃሲምንስ እንዴት ረሳኸው?

ሙሉጌታ፡- አዎ አዎ ልዩ ጊዜ እያሳለፈ ነው ምርጥ አቅሙንም አሣይቷል ስዩምና ሙጂቢን በጥሩነት ያዝልኝ እንደ ቡድን ሁሉም ጥንካሬ ብቻ አይደለም ያለው…. በኔ እምነት መቐለ 70
ከነድክመቱም ጥሩ ቡድን እንደሆነ ይሰማኛል፡፡

ሀትሪክ፡-አንተ ባለህበት ጨዋታ ቡድንህ ድል ይቀናዋል ወይስ?

ሙሉጌታ፡- ሁሉም ነገር ገጥሞታል ተረናል አቻ ወጥተናል ተሸንፈናል…

ሀትሪክ፡-በ1ኛ ዙር 15 ጨዋታ አይተኸው ያልተመቸህ በ2ኛው ዙር ማየት የማትፈልገው ጉዳይ ምንድነው?

ሙሉጌታ፡- በሁለት መንገድ እንመለከ ተው.. በእግር ኳሱ ደረጃችን ኳሱ ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለው… በተለይ ከአምና አንፃር ስናየው 2ኛ ዙር ላይ ማየት የማልፈልገው የዳኞችን
የስህተት ውሳኔ ነው…. በተለይ 2ኛ ዙር ላይ ለዋንጫና ላለመውረድ የሚደረጉ ግጥሚያዎች ስለሆኑ ሚዛናዊና ምክንያታዊ ዳኝነት ብናይ ደስ ይለኛል….. እንደ ክለብ ደግሞ በጥቃቅን ስህተት
የሚከሰት ሽንፈት ባላይ እመርጣለው፡፡ በተለይ በዳኝነት የሚታጣ ነጥብ ቅር ያሰኛል፡፡

ሀትሪክ፡-በአንደኛው ዙር 15 ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታ በዳኛ ነጥብ ያጣበት ጨዋታ አለ?

ሙሉጌታ፡- አይ ያን ያህል የተጋነነ ስህተት አላየሁም ነገር ግን ማግኘት እየቻልን የተከለከልንበት ጨዋታ አለ… እንደ ትልቅ ችግር አይቼው አይደለም ቢስተካከሉ ይሻላል የምለው ስለሆነ
ነው፡፡
ሀትሪክ፡-በ2ኛ ዙር ግን ተመሳሳይ ውሳኔዎች አደጋ ሊፈጥሩ ይችላሉኮ?

ሙሉጌታ፡- አዎ አንደኛ ዙር ላይ የተከሰተው 2ኛ ዙር ላይ ቢከሰትና ውጤት በጠፋ ቁጥር ክለቡ እየወረደ ስለሚመጣ 90 ደቂቃ እየለፋን እንደሆነ ታውቆ ከእግዚአብሔር ጋር ጥሩ ዳኝነት
ቢኖረን ደስ ይላል ከሞላ ጎደል 1ኛ ዙር አሪፍ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-መቐለ 70 እንደርታ በተከታታይ ዋንጫ የመውሰድ አቅም አለው?

ሙሉጌታ፡- በሚገባ ዋንጫ የመውሰድ አቅም አለን…. 1ኛ ዙር በጥቃቅን በሆኑ የራሣችን ስህተቶችም ያጣናቸው ነጥቦች አሉ፡፡ ያንን አርመን የተሻለ ነጥብ አምጥተን ባለድል የመሆን
አቅም አለን፡፡ መቐለ 70 እንደርታ በርግጠኝነት ወደ ዋንጫ የመሄድ አቅሙ አለው፡፡

ሀትሪክ፡-የአማኑእል ገ/ሚካኤል ግቦች መቀነሳቸው ክለባችሁን አልጎዳም?

ሙሉጌታ፡- አዎ በእርግጥ አማኑኤል የክለቡ ግብ አስቆጣሪ ነው፡፡ በርሱ ግቦች አምና ብዙ ነጥቦችን አግኝተናል…. ከቡድኑ ጋር በነበረ ቅንጅት ጥሩ ውጤት መጥቷል፡፡ እግር ኳስ
እንደመሆኑ በ1ኛ ዙር ብዙም ባይሳካለትም በ2ኛ ዙር የተሻለ አቅሙንና ግቦቹን እንደምናገኝ ተስፋ አደርጋለው፡፡

ሀትሪክ፡-አሰልጣኝ ገ/መድህን ጨመረልኝ ያልከውን አቅም ግለፅልኝ?

ሙሉጌታ፡- ገብረ መድህን ልጅ ሆኜ ነው የሚያውቀኝ….. በየጊዜው ኮመንት ይሰጠኝ ነበር በባህሪው ኳስ እስከቻልክ ድረስ በነፃነት እንድትጫወት ያደረግሃል በዚህ ቅርፅ ተሞርጄ ነው
የመጣሁት ስህተት ላይ የማያተኩር ስህተትን ለማስወገድ ደጋግሞ ሲሰራ ወደ ተሻለ ደረጃ ማደግ እንደሚቻል ያስባልና ከርሱ ጋር መስራቴ ለተሻለ ደረጃ አብቅቶኛል….. በዚህ አጋጣሚ
አመሰግነዋለው፡፡

ሀትሪክ፡- የ2012 መርሀ ግብር 1ኛ ዙር ላይ ቢያልቅ ኮከቡ ላንተ ማነው?

ሙሉጌታ፡- የኛ ተከላካይ ስዩም ተስፋዬ ይመስለኛል ምርጥ አቋሙን አይቼበታለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-በቦታህ ተቃራኒ ተፋላሚ ሆኖ የሚያስቸግርህ ተጨዋች ማነው?

ሙሉጌታ፡- ይህን መናገር አልችልም በዘንድሮ የ1ኛ ዙር ያን ያህል ያስቸገረኝ የለም፡፡

ሀትሪክ፡-ወቅታዊ አቋምህን ከመነሻህ አንፃር ስታየው ወርዷል አድጓል… ወይስ ቆሟል?

ሙሉጌታ፡- በአሁኑ ሰዓት ጥሩ ነኝ አምና ተቀይሬ እየገባሁ ጥሩ ለማድረግ እጥር ነበር…. ዘንድሮ ደግሞ ቋሚ የመሆን እድል አግኝቻለሁና እድሌን ላለማጣት ጠንክሬ እየሰራሁ ስለሆነ ጥሩ
ደረጃ ላይ እገኛለሁ ማለት እችላለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-ለመቐለ ከባዱ አምና ወይስ ዘንድሮ?
ሙሉጌታ፡- አይ የአምናው ይከብዳል፡፡ የአምናው መልካም ውድድር አልነበረም ይሄኮ ይታወቃል….. ኳሱ ወደ ፖለቲካ ዞር ብሎ ስጋት ስለነበር በነፃነት መጫወቱ ከበድ ብሎ የነበረበት
አመት ነው፡፡

ሀትሪክ፡-አብሬው ብጫወት ደስ ይለኛል የምትለው ተጨዋች አለ?

ሙሉጌታ፡- ሚካኤል (ጣሊያኑ) ከርሱ ጋር መጫወት እፈልግ ነበር በመከላከያ አብረን ሰርተናል ግን 1 ጌም ብቻ ነው አብሬው የተጫወትኩት ዘንድሮ 1ኛ ዙር ላይ ጉዳት ገጥሞት
አልተጫወተም 2ኛ ዙር ላይ ስለማገኘው አብሬው እንደምጫወት ተስፋ አደርጋለው፡፡

ሀትሪክ፡-የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎችን እንደት አገኘሃቸው?

ሙሉጌታ፡- ምርጥ ደጋፊ ነው፡፡ እንደ 12ኛ የክለባችን ኃይል ሆነው ያልተለዩን ታማኝ ደጋፊዎችን ናቸው በነርሱ ደስተኛ ነኝ ከዲሲፕሊን አንፃር ኳስ ከማወቁም አንፃር ምርጥ ናቸው
ለቡድናችን አብረው እየሄዱ ብርታት የሆኑን ደጋፊዎች አሉን… ለነርሱ ትልቅ ፍቅርና ክብር አለኝ…. የነርሱ ጥንካሬ የኛ ጥንካሬ ሆኗል፡፡ መቐለ 70 እንደርታን ጠንካራ ያደረጉት ኳስን በእውቀት
የሚደግፉት ደጋፊዎቻችን ናቸው፡፡

ሀትሪክ፡-ደጋፊው በስፖርታዊ ጨዋነት ጥሩ ነበር ማለት ይቻላል?

ሙሉጌታ፡- እግር ኳስ የፍቅርና የደስታ መገለጫ መዝናኛ ኢንዱስትሪ ነው… ከዚያ ሲያልፍ ቢዝነስ ይሆናል… በቃ ይሄ ነው ትክክለኛው መንገድ…. እኛ አገር ግን እንዲህ አልነበረም፤ ገና
እያደገ ባለ እግር ኳሳችን እግር ኳሳዊ ያልሆኑ ጉዳዮች ሲከሰቱ ያስጨንቃሉ አሁን ግን አሪፍ ላይ ነው ያለው ለውጥም አለ፡፡ ደጋፊው ውጤት ሲያጣ መጮሁ አይቀርም ያኔ ደግሞ ለቀጣዩ
በርትተህ እንድትገባ ያደርግሃልና መኖራቸው ትልቅ ጥቅም አለው……ሁሉም ነገር ግን በዲሲፕሊን ቢሆን ደስ ይላል፡፡

ሀትሪክ፡-የተጨዋቾች ደመወዝ ከ50 ሺህ ብር አይብለጥ መባሉ ኳሱን ያሳድጋል.. ትክክለኛስ ውሳኔ ነው ማለት ይቻላል?

ሙሉጌታ፡- ለኳሱ እድገት ከታሰበ ከታች መጀመር አለበት… ከትምህርት ቤት ከማሰልጠኛ ተቋማት በመጡ ተጨዋቾች ኳሱ ሲጠቀም አይታይም…ይሄ ላይ ማተኮር ያለብን…ለዕድገቱ
የሚበጀውም ይህ ነው… ከዚያ ውጪ በኔ ህይወት ማንም ጣልቃ ባይገባ ደስ ይለኛል… እኔ ውጤታማ ስሆን ከታች ያሉ እኔን እያዩ ሲያድጉ ኳሱ ሊያድግና ተተኪ ሊያገኝ ይችላል…. ያ ነው
ትክክለኛ መንገድ፡፡ ከዚያ ውጭ የደመወዝ ቅነሳ ተገቢ አይደለም፡፡ አንተ እየለፋህ ሌላው ሲወስን ቅር ያሰኛል ከስር መስራት እንጅ ደመወዝ ቅነሣ መፍትሔ አይሆንም ይሄን ፌዴሬሽኑ ፌዴሬሽኑ
ሊያስብበት ይገባል፡፡ ከስር ታደጊ ላይ ሰርተው ለውጡን አያዩም ብዬ አላምንም፡፡ ችግሩ ሌላ መፍትሔው ሌላ መሆኑ ተገቢ አይደለም፡፡ ሲስተሙ ላይ እንጂ የደመወዝ ማደግና ማነስ ለአገራችን
እግር ኳስ አይጠቅምም፡፡

ሀትሪክ፡-የ2012 1ኛ ዙር ሲገመገም በስፖርታዊ ጨዋነት ጥሩ ነው ማለት ይቻላል?

ሙሉጌታ፡- የዘንድሮው አሪፍ ነው መቀጠል ካለበትም በሁሉም ዘርፍ ጥንቃቄ ይጠይቃል…. ደጋፊው፣ተጨዋቹ፣ሚዲያውና ሁሉም የየራሣቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ አለባቸው… 2ኛው
ዙር የዋንጫ አሸናፊ ወራጅ ክለብ የሚለይበት በመሆኑ ጥንቃቄ ያሻዋል፡፡

ሀትሪክ፡-የውጪ ኳስ ትመለከታለህ? የማን ደጋፊ ነህ?

ሙሉጌታ፡- ኳስ ተጨዋች እንደመሆኔ እግር ኳስን በማየትም መዝናናት ይጠበቅብ ኛልና በደንብ አያለው…. ውስጤ ለማን.ዩናይትድ ያመዝናል፡፡ ነገር ግን ጥሩ ጥሩ ጨዋታዎችን
አያለው.. በኳስ ያለኝ ደስታ ሰፊ ነው… መማር መፈለጌ ደግሞ ኳስ እንዳያመልጠኝ አድርጎኛል… በሙያዬ የተሻለ ለመሆን ኳስ ማየት የተሻለ መንገድ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-በአንተ ቦታ በአለም ላይ ምርጡ ተጨዋች ማን ነው?

ሙሉጌታ፡- ዋው…ያለጥርጥር የማን.ሲቲው ኬቨን ደብሩይነ ነው… በጣም የሚገርም ብቃት እያሳየ ነው፡፡ በጣም በማጥቃቱ ላይ እያመዘነ የሚጫወት የምርጥ ክህሎቱ ባለቤት ነው….
ለጎል ቅርብ ነው ግብ ያስቆጥራል አሲስት ያደርጋል… ለኔ ልዩ ሆኖብኛል ወደፊት ወደ አጥቂ ቦታ እየተጠጋ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴ ያስደስታል፡፡ በሻምፒዮንስ ሊጉ ከሪያል ማድሪድ ጋር
ሲጫወቱ ካየኸው ከጎል እስከ ጎል የመጫወት አቅሙን አሳይቷል…. በጣም ነው የማደንቀው፡፡

ሀትሪክ፡-ከሀገር ውስጥስ?

ሙሉጌታ፡- /ሳቅ/.. ይሄ ጥያቄ ይለፈኝ

ሀትሪክ፡-ለምን.. ? የለም…?

ሙሉጌታ፡- /ሳቅ/

ሀትሪክ፡-ቦታዬን ለማስከበር ጠንክሬ እየሰራሁ ነው ማለት ትችላለህ?

ክፍል ሁለትን ለማንበብ ምስሉን ይጫኑ 👇

“መቐለ 70 እንደርታን ጠንካራ ያደረጉት ኳስን በእውቀት የሚደግፉት ደጋፊዎቻችን ናቸው”ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ /መቐለ 70 እንደርታ/ (ክፍል-2)

 

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport