“ለምን እንደማልመረጥ ባላውቅም ብ/ቡድኑን በብቃት ማገልገል የምችልበት መቶ ፐርሰንት ብቃቱ ግን አለኝ” ፍሬው ሰለሞን (ጣቁሩ)

በእስር፣ በኮሮና ቫይረስ ወሬ የተፈተነውና ግን በጥንካሬው የዘለቀው የፍሬው ሰለሞን (ጣቁሩ) የእግር ኳስ ህይወት

“ለምን እንደማልመረጥ ባላውቅም ብ/ቡድኑን በብቃት ማገልገል የምችልበት መቶ ፐርሰንት ብቃቱ ግን አለኝ”
ፍሬው ሰለሞን (ጣቁሩ)


 

በይስሐቅ በላይ

ወደ ታሪክነት ለመቀየር ጥቂት ቀናቶች የቀሩት 2012 ዓ.ም ለእሱ የቁጥሩ ሙሉነትን ያህል ሙሉ አልሆነለትም፤በብዙ መልኩ ፈትኖታል፤በሰው መግጨት ክስ ተፈርዶበት በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ማረሚያ ቤት ወርዷል…በዚህ ሳያበቃም በአካባቢው ሰዎች ጥቆማ የኮሮና ቫይረስ ካለበት ሰው ጋር ንኪክ አለብህ ተብሎ ተጠርጥሮም ከባለቤቱ ጋር ኳራንታይን ለ15 ቀናት ገብቷል፡፡ እነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ቢደራረቡበትም የእግር ኳሱ ኮከብ የሆነውን፣የማይደክመውን፣ የማይቆመውን ፍሬው ሰለሞን (ጣቁሩን) አላንበረከኩትም፤ ይልቁንም ከብረት የጠነከረ አደረጉት እንጂ፡፡

“በእርግጥ ሕይወት በፈተና የተሞላች ነች፤ ለፈተና መንበርከክ ሳይሆን ፈተናን በፅናት ተቋቁሞ ማለፉ ነው ትልቁ ቁም ነገሩ̋ የሚለው ፍሬው ሰለሞን (ጣቁሩ) ̋በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረን ከባለቤቴ ጋር በኳራንታይን ያሳለፍነው ጊዜ እጅግ አስጨናቂ ነው፤በማረሚያ ቤት ያሳለፍኩት ጊዜም በሕይወት ዘመኔ የማላውቀው አስፈሪና ከባድ ቢሆንም የሁለቱም መጥፎ አጋጣሚዎች በትምህርት ቤት የማላገኘውን ትልቅ ቁም ነገር ገብይቼበታለሁ” የሚለው ሙሉ ሜዳ በማካለል የሚታወቀውና የሁለት ሰው ትንፋሽ ያለው ተጨዋች ነው የሚባለው አዲሱ የወልቂጤ ከነማው ፈራሚ ፍሬው ሰለሞን (ጣቁሩ) ከሀትሪክ ኤክስኪዮቲቭ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ጋር ፌዴራል ፖሊስ ስለመግጨቱና ስለመታሰሩ፣ በኮሮና ቫይረስ ተይዟል ተብሎ ኳራንታይን ስለመግባቱና ስለተወራበት ወሬ፣ ስለትዳር ሕይወቱና እንዲሁም ብሄራዊ ቡድን አለመመረጤ ለእኔም ዕንቆቅልሽ ሆኖብኛል፤ያለኝ ብቃት መቶ ፐርሰን ለብሄራዊ ቡድን ያስመርጠኛል በማለት በድፍረት የተናገረውንና ጊዜ ወስዶ ያወሩትን ለእናንተ ለተከበሩ አንባቢዎቻችን በሚመች መልኩ አቅርበነዋል፡፡ እንደተለመደው ጊዜያችሁን አውሱን፡፡


በኮሮና ቫይረስ ተይዟል ተብሎ እሱም ቤተሰቦቹም ስለመጠርጠራቸው…

“ይሄ በጣም አስገራሚ ታሪክ አለው፤ነገሩን አሳጥሬ ስነግርህ ከአዲስ አበባ ጠቅልዬ ስወጣ የእኔ መኖሪያ ቤት እስኪደርስ በሚል ለጊዜው ሙሉ ግቢ እከራያለሁ፤የቤቱ አከራዬ አዲስ አበባም ሌላ ቤት ስላለው፣የተከራየሁትን ቤትም ለመቆጣጠር ይረዳኛል…ሆቴል አልጋ ከመያዝ ከሰርቪስ ቤቶች ውስጥ አንዱን ክፍል ለጊዜው ልጠቀምበት ስጠኝ ይለኛል፤እኔም ምንቸገረኝ… የራሱ ቤት ነው…ይጠቀምበት ብዬ እፈቅድለታለሁ፤ይሄ ሰውዬ ታዲያ ሳምባ ምች በሽተኛ ነው…በጣም ያስላል…ሳሉም የማያቋርጥ ነው፤ይሄንን የተመለከቱ ሰዎች “ይሄማ የጤና አይደለም ኮሮና ቫይረስ ነው…ከዚያ ውጪ ሊሆን አይችልም፤) ብለው ይደመድሙና ለጤና ሚኒስቴር ስልክ ደውለው ይጠቁማሉ…የጤና ባለሙያዎችም አንቡላንሳቸውን እያስጮሁ እየበረሩ በራችን ላይ ከተፍ ይላሉ…እዚህ ቤት ውስጥ የታመመ…ከኮረና ምልክቶች አንዱ የሆነው ከፍተኛ የሳል ምልክት ያለበት…ተጠርጣሪ ሰው አለና ለምርመራ ይዘን እንሄዳለን…አሉ…አረ የሚያስለው ሰውዬ የሳምባ ምች በሽተኛ ነው እንጂ በኮረና የተያዘ አይደለም…ብሏ ባለቤቴም ሰውዬው ራሱም ለማስረዳት ቢሞክሩም ለመስማት ፍቃደኛ አልሆኑም…ይዘነው ሄደን በምርመራ ነው የምናረጋግጠው አሉ…በመጨረሻም ነገሮች ከአቅም በላይ በመሆናቸው ወሰዱት፤በሰውዬው ተገርመን ሳንጨርስ በነጋታው ደግሞ ሌላ ያላስብነው ዱብ እዳ መጣ…እኔ በሌለሁበት ቤታችን መጥተው ባለቤቴን እናንተም ከሠውዬው ጋር ንክኪ ስላላችሁና ተጠርጣሪ ስለሆናችሁ ለደህንነታችሁ ሲባል መሄድ አለባችሁ አሏት፤ እሷም በጣም ደነገጠች…ፈራች…ወዲያው ወደ እኔ ጋር ደውላ ታሪኩን ስትነግረኝ…አይዞሽ አትደንግጪ… ታዲያ ምን ችግር አለው…?እኔ አሁኑኑ መጣሁ…አንቺ ግን አምቡላንስ ውስጥ እንዳትገቢ መሄድ አለባችሁ ከተልባንም በእኔ መኪና ነው የምንሄደው…ምንም እንዳትፈሪ አልኳት… በፍጥነት ወደ ቤት ስመጣ…በሩ ላይ ትንሽ ግርግር አለ…አምፑላንሱም ቆሟል…ምንድነው ብዬ ስጠይቃቸው…ባለቤቴ የነገረችኝን ደገሙልኝ…በኮሮና ተጠርጥራችኋል ለምርመራ መሄድ አለባችሁ ሲሉኝ…ምን ችግር አለው ብለን ለምርመራ ሄድን”

በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው 15 ቀናት በኳራንታይን ስለማሳለፉ…

“በኮሮና ተጠርጥራችኋል ብለው አንድ የተዘጋጀ ሆቴል ነገር ነበር እዛ ወስደው ከተቱን…ሁለቴ የምርመራ ናሙና ወሰዱ…ኮሮና እንደሌለብን ብንገምትም…የሚያደርጉት ነገር በጣም ያስጨንቃል…15 አስጨናቂ ጊዜያትን በሆቴሉ (በኳራንቲ) ለማሳለፍ ተገድድን፤በመጨረሻ በተደረገ ምርመራ እኛም ቤቱን ያከራየንም ሰውዬ ነፃ ናችሁ ተብለን እንድንወጣ ተደረገ፤እኛ ለ15 ቀን ኳራንቲ በመግባታችን ሰው በኮሮናና ኳረንቲ በመግባት መካከል ያለው ልዩነት ባለማወቁ ብዙ ነገር ተባለ፤ በተለይ እኔ ላይማ ያልተባለ ነገር የለም…ፍሬውና ቤተሰቡ በኮሮና ቫይረስ ተያዙ… ከአዲስ አበባ ይዞ ነው የመጣው ኳራንቲ ገብቶ በፀና ታሞ ተኝቷል…ብቻ ምን ያልተባለ አለ…ብዙ ተባለ…እውነታው ግን…እኔንም ቤተሰቤንም የኮሮና ቫይረስ አልያዘንም…ገና ለገና…ቤቱን ያከራየን ሰውዬ በጣም ያስላል ብለው…ጠቁመውብን በጥርጣሬ ለደህንነታችሁ ሲባል ብለው ነው ለምርመራ ወስደው ኳራንቲ ያስገቡን፤ሰው በኮሮና ቫይረስና በኳራንታይን መካከል ያለውን ልዩነት ባለማወቁ ነው ወሬው አዲስ አበባ ድረስ የተሰራጨው እንጂ…ከመነሻውም እኔም ቤተሰቤም አልተያዝንም…ተመርምረንም ነፃ ነው የተባልነው፤ደግሞም አንድ ሰውበኮሮና ቫይረስ ተያዘ ማለት በቃ አለቀለት ይሞታል ማለት አይደለም…ያገግማል፤ይድናልም ”

የፌዴራል ፖሊስ አባል በመኪና ስለመግጨቱና ስለመከሰሱ….

“ነገሩ የሆነው እንዴት መሰለህ ትሬይኒንግ ሰርቼ በጣም ደክሞኛል፤ፍልውሃ አካባቢ አንድ እርጎ በማር የሚሸጥባት ሱፐር ማርኬት አለች…እዛ ሄጄ ተመልሼ መኪናዬን አስነስቼ ጎንበስ ብዬ ቀና ስል ለካ ገፍተር አድርጌዋለሁ…በዚህን ጊዜ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ኧረ ገጨኸው፣ገደልከው ብለው ሲጮሁ…አውነት ሰው የገደልኩ መሰሎኝ በጣም እደነግጥና ፍሬን የያዝኩ መስሎኝ ነዳጁን እረግጠዋለሁ…በዚህን ጊዜ የፌዴራል ፖሊሱን አሸቅንጥሬ…ገፍትሬ መሬት ላይ ጣልኩት…ጥርሱ ተሸረፈ…ግንባሩ…እጁ ሁሉ ሳይቀር ተላጠ ቆሰለ ደማ…ወዲያው አፋፍሰን ሀኪም ቤት ወሰድነው…በጣም ደንግጬያለሁ…ግን እግዚአብሔር እኔንም እሱንም አትርፎናል…አሳከምኩትም…በኋላ ላይ ሁለታችሁም አስባችሁት አይደለም…አጋጣሚ ነው… ጉዳዩ ወደ ክስ ወደ ፍ/ቤት ከሚሄድ…ለምን በሽምግልና አይያዝም ተባለ…እሺ አልኩ…እሱም ተስማማ…ጉዳዩን በስምምነት ፈታነው…በወቅቱ እኔ ትኩረቴ ጨዋታ ላይ ስለነበር ጉዳዩን የቴክኒክ ኮሚቴያችን የነበረው ዋሲሁን (ነፍሱን ይማረውና) አንተ ጨረስልኝ ብዬ ሰጠሁት… የተፈራረምንበት…የተስማማንበት ወረቀት እጃችን ላይ ሲገባ እኔም እሱም ተዘናጋን ትኩረቱን ወደ ስራዬ አደረኩት”

ያለሰበው የፖሊስ ጥሪና የሁለት ወር የእስር ፍርድ…

“በጣም የሚገርምህ ስለ ሕግ ግንዛቤ አለመኖር እንዴት እንደሚጎዳ ያወኩት በዚህን ጊዜ ነው፤ ከገጨሁት የፌዴራል ፖሊስ ጋር በሽማግሌ ታርቀን…ተስማምተን የእርቅ ስምምነቱን ደብዳቤ በእጄ ሳስገባ ነገሩ ያለቀ የሞተ ያህል ተሰምቶኝ ነገረ አለሙን ረሳሁት…ጭራሹንም ምንም እንዳልተፈጠረ ቆጥሬ ትኩረቴን ወደ ትሬይኒንጌና ወደ ጨወታዬ አዞርኩት፡፡ በዚህ መሀል እያለሁ አንድ ቀን የእጅ ስልኬ ጮኸ…አቤት ስል ከፖሊስ እንደተደወለና በሰው መግጨት ክስ የተከፈተው ፋይል ባለመዘጋቱ እንደምፈለግ…መጥሪያ መጥቼ እንድወሰድ ወዲያው ገለፀልኝ እንደ አዲስ ደነገጥኩኝ፤ስሄድ ጉዳዩ እንዳልተዘጋና ክሱ ተጠናቆ ለአቃቤ ሕግ መሰጠቱና ክስ እንደተመሠረተብኝ ገልፀልኝ…እኔ በፊትም የፍ/ቤትና የቀበሌ ጣጣ አይመቸኝም…ልክ መጥሪያውን እንደተቀበልኩ የገጨሁት ፌደራል ፖሊስ ጋር በመደወል ክሱን ባለማዘጋታችንና የእርቅ ደብዳቤውን ባለማስገባታችን መጥሪያ ተሰጠኝ…ክስም ሊመሰረትብኝ ነውና እባክህ ቶሎ ድረስልኝ ስለው “አሁን እኔ ግዳጅ ላይ ነኝ መምጣት አልችልም” ሲለኝ ሰማይና ምድሩ ዞረብኝ… አረ ባክህ እንደምንም ድረስልኝ ስለው “ከሶስት ቀን በኋላ እመጣለሁ” አለኝ…እኔ ደግሞ ፍ/ቤት የቀጠሮ ቀኔ ከዚያ በፊት ነው…በጣም ተረበሽኩ…የፍርድ ቤቱ ቀን ከብርሃን ፍጥነት በሮ ደረሰ…ችሎት ስቀርብ ዳኛዋ ሴት ነበረች…ጉዳዩን ከመረመረች በኋላ ለሁለት ወራት ወደ ማረሚያ ቤት እንድወርድ ተፈረደብኝ…በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ማረሚያ ቤት ወረድኩ…ለሁለት ወራትም ታሰርኩ…”

የሁለት ወራት የማረሚያ ቤት ቆይታው …

“ወደ ማረሚያ ቤት ከመውረዴ በፊት ለተወሰኑ ቀናቶች በእስር ቤት ነው ያሳለፍኩት…4 እና 5 ቀን በእስር ቤት አሳልፌያሁ…እውነት ለመናገር በእስር ቤት ደስ የማይል ጊዜን በማሳለፌ ሁለት ወራትን በማሳልፍበት ማረሚያ ቤት…ከዚህ የባሰ ነገር ይገጥመኛል በሚል ትልቅ ፍርሀት በውስጤ ነገሰ…እንዴትስ ነው በዚህ መልኩ ሁለት ወራትን የማሰልፈው? ብዬ በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ወደኩ…በጣም ተረበሽኩ…ኧረ እንደውም አልፎ ተርፎ አምላኬን ምነው ምን በደልኩህ…?ብዬ ሁሉ እስከማማረር ደረስኩ፤ቀኔ ደርሶ ወደ ማረሚያ ቤት ስወርድ ግን የገጠመኝ ነገር እንደፈራሁት ሣይሆን በጣም በተቃራኒ ሆኖ አገኘሁት፡፡ እንደውም እንዴ እስር ቤት ማለት እንደዚህ ነው እንዴ? ብዬ ራሴን እስከመጠየቅ ሁሉ ደርሻለሁ…እስር ቤት ስገባ ልክ እንደ ዩኒቨርሲቲ ተደራራቢ አልጋ ላይ ነው የምንተኛው…ለአንድ ሰው አንድ አልጋ ነው…የራሱ ሻወር ሽንት ቤት አለው… ቴሌቪዥን በየቦታው አለ…ፀጉር ቤት፣ሻይ ቤት፣ላይብረሪ ብቻ ሁሉም ነገር ተሟልቶ ሣይ እስር ቤት እንደዚህ ነው ብዬ ተገረምኩ…ጠዋት ተቆጥረን እንወጣለን ማት ደግሞ ተቆጥረን እንገባለን፤የጠበኩትን ሣይሆን ያልጠበኩትን በማግኘቴ ሁለት የጨለማ ወራት ይሆናሉ ብዬ ያሰብኩት እስር ቤት በፍጥነት ሁለት የብርሃን ወራት ሆና ለመቀየር ብዙም ጊዜ አልወሰደብኝም”

“እግር ኳስ ተጨዋችነቱና ታዋቂነቱ በእስር ቤት ስላስገኘለት ጥቅም…

“ብዙዎች ከተክለ ሰውነቴም እንደውም ሜዳ ውስጥ በማልያና በልብስ ካለኝ ሰፊ ልዩነት ቶሎ አልለዩኝም እኔም ተጨዋች መሆኔን ለማንም አላውራሁም፤መጀመሪያ ላይ ብዙውን ጊዜ በእስር ቤት ጠያቂ ሲመጣ የምትጠራው በማይክሮፎን ነው…ፍሬው ሰለሞን ስባል መጀመሪያ ልብ ያለ አልነበረም፤እየተደጋገመ ሲጠራ ግን የጠረጠሩ ነበሩ፤ በኋላ ላይ ስሰማ የታሰርኩበት ክፍል ውስጥ የኢት.ቡናና የቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ነበሩ፤ እነሱ ስሜ ተደጋግሞ ሲጠራ ሲሰሙ ይሄ መከላከያ የሚጫወተው ጣቁሩ የሚባለው ልጅ ይሆን እንዴ? በማለት ስሜን አንስተው ሲነጋገሩ እንደነበርና በመጨረሻም አይ እሱ እዚህ ምን ያደርጋል የስም መመሳሰል ነው ብለው መደምደማቸውን ሰማሁ፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ራሴን ሳላስተዋውቅ ከቆየሁ በኋላ የእኛ ክፍል አስተዳደር የራሱ ፀጉር ቤት አለው…ታዲያ አንድ ቀን ፀጉሬን ለመስተካከል ስሄድ ያበጠ ይፈንዳ ብዬ ነገርኩት…ስነግረው “እንዴ አንቺ ነሽ እንዴ ፍሬው (ጣቁሩ)…”ብሎ ወዲያው…”የት ነው የምትተኛው?”…አለኝ ተደራራቢ አልጋ ላይ ከላይ እንደምተኛ አሳየሁት…ለመተኛት የሚመረጠውና ምቹው ከታች ስለነበር ወዲያውኑ “እታች ነው መተኛት ያለብህ”ብሎ ቀየረኝ…ከዚያን ቀን በኋላ እስከወጣ ድረስ የነበረውን እንክብካቤ ልነግርህ አልችልም ልዩ ነበር…እኛ ክፍል ውስጥ ለነበሩት የቅ/ጊዮርጊስና የኢት.ቡና ደጋፊዎች “ፍሬው (ጣቁሩ) የምትባል ተጨዋች እዚህ መጥታላችኋለች” ሲላቸው “እኛም እኮ ጠርጥረን ነበር ብለው እኔጋ መጡ”ተንከባከቡኝ…ያሳዩኝ ክብርና ፍቅር በጣም ልዩ ነበር…አብሬያቸውም አሣልፍ ነበር፤ውድድር ውሰጥም አስገብተውኝ ክፍሌን ወክዬ ኳስ ሁሉ ተጫውቻለሁ…በቃ ፍቅራችን ልዩ ሆነ…የጨለማ ያህል ያየሁት እስር ቤት ወደ ብርሃንነት ተለወጠ…በጣም ተደስትኩ…እኔም ቤተሰብ…ተጫዋቾች ሊጠይቁኝ ሲመጡ የሚሰጡኝን ገንዘብ ምንም ስለማላደርገው…ጠያቂ ለሌላቸው ልጆች መመገቢያ በማዋል ከሁሉምም ጋር እየተግባባሁ እየተላመድኩ መጣሁ፤የሚገርምህ ሁለት ወሩ ሁለት አመት ይሆንብኛል ብዬ የሰጋሁት ሰው…ቀኑ ሳላስበው እያለቀብኝ መጣሁ፤ እውነት ነው የምልህ ሁለት ወር ታሰርኩ ሣይሆን ጥሩ ተማርኩ…የተለየ የህይወት ክፍልንም አየሁበት ነው የምለው”
በእስር ቤት ቆይታው የተለየ አጋጣሚ ካለው…
“ያን ያህል እንኳን የተለየ የምለው አጋጣሚ የለም ግን አንዳንድ የታዘብኳቸውና ከእኔ አዕምሮ በላይ የሆኑ ነገሮችን አይቻለሁ…ሠምቻለሁም…፤…ለምሣሌ እስረኞች…አንዳንድ ጥጋበኛ የሆኑ…ሠላማዊ ሰዎችን የሚያውኩ ሰዎችን አደብ የሚያስዙበት መንገድ ፍርሃትን የሚያጭር ነው፤ጥጋቡ ያልበረደለት ሠላማዊ እሠረኞችን የሚረብሽ ሰው ተመክሮ አልሰማ ብሎ ሲያስቸግር የሆነ ቆሻሻ ውሃ ያለበት ታንከር አለ እዛ ውስጥ ከተው ልክ ያስገቡታል ድርጊቱ ልክ ነው ብዬ ባልደግፍም…ለቤቱ ግን ሠላምን ሲያመጣ አይቻለሁ፡፡
ከዚህ ውጪ በእስር ቤት በተለይ በሕግ ዙሪያ ብዙ ትማራለህ…ታውቃለህ…የተለያዩ ትላልቅ ሰዎችን እውቀቱ ያላቸውን ሁሉ ታገኝበታለህ…እኔ ከእስር ቤት ከወጣሁ በሃላ በህግ ላይ ያለኝ እውቀት በጣም ጨምሯል…የቱ…ምን አይነት የሕግ ጥያቄ እንደሚያመጣ…ምን ስታደርግ…ምን ልትሆን እንደምትችል ጥሩ ትምህርት ቀስሜ ነው የመጣሁት…እኔ አሁን አንድ ነገር ከማድረጌ በፊት በህግ በኩል ምን ተጠያቂነት ያመጣል? የሚለውን ቀድሜ ነው የማየው…በዚህ በኩል ተምሬ ወጥቻለሁ፡፡ ግን ሳልደብቅህ መናገር የምፈልገው በእስር ቤት የምትሰማቸው አንዳንድ ወንጀሎች ለመስማት በጣም የሚያሳቅቁና የሚረብሹ ናቸው…የዘጠኝ አመት ለጋ ሕፃን ልጅ ደፍረው…አባት ልጁን ደፍሮ ወንድ ለወንድ ግብረ ሰዶም አድርገው ሰውን በመጥረቢያ ቀጥቅጠው ገድሎ ነው የመጣው የሚለውን ስትሰማና ሰውዬውን ስታየው በጣም ይረብሸሃል…የሰው ፍጡር ነው…?…ምንድነው…?…ብለህ እስክትጠራጠር ድረስ…ደግነቱ እንደዚህ አይነት ወንጀል የሚሰሩ በቤቱ ስለሚገለሉ እንጂ በጣም ያማል…እንደመጥፎ አጋጣሚ የማነሳው ይሄንን ነው”

እስር ቤት እያለ በክለቡ“አይከፈልህም” ስለተባለው ደሞዝ…

“እንደ አጋጣሚ ሆኖ እኔ እስር ቤት እያለሁ የሁለት ወር ደሞዝ አልገባልኝም፤ለምን አልገባልኝም…?…አኔ የታሰርኩት በድንገተኛ ገጠመኝ ነው ሊከፈለኝ ይገባል ብዬ ጠይቄ ነበር…ነገር ግን በእኛ የመግሥት አሠራር ሁለት ወር በስራ ገበታው ላይ ያልተገኘ ሰው ደሞዝ ይከፈለው…የሚል ሕግ የለም…ብለው ሞገቱኝ እኔም የተቀጠርኩት በመንግሥት ሕግ ሳይሆን በፌዴሬሽኑ የመተዳደሪያ ደንብና ውል መሠረት ነው ብዬ ሞገትኳቸው… በዚህን ጊዜ እነሱም ለሁለት ተከፈሉ…”ይከፈለው፤አይከፈለው” በሚል…በመጨረሻ “ይከፈለው” ወደሚል ውሳኔ መጥተው ሊከፍሉኝ ሲል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአለምም ወደ ሀገራችንም መጥቶ…ውድድሩም ተቋረጠ…ሳይከፈለኝም ተንጠልጥሎ ቀረ…ይሄው እስከ አሁንም አልተከፈለኝም፤እኔም በቃ አልተፈቀደልኝም…ብዬ ትቼው ተቀምጫለሁ…”

ስለ ቡሄ በዓልና አከባበሩ በልጅነቱ ገንዘብ ያዢ ስለመሆኑ…

“ቡሄን በልጅነቴ ጨፍሬ ተደስቼ አሣልፌያሁ…በወቅቱም የሙልሙል ዳቦ ሣይሆን የገንዘብ ያዢነትን ኃላፊነት የተሰጠኝ ለእኔ ነበር፤በእኛ ጊዜ ገንዘብ ይዞ መጥፋት የሚባል ነገር ስለሌለ ጨፍረን ያገኘነውን በጨዋነት አናስረክብ ነበር፡፡ የተገኘውን ገንዘብ ስንካፈል የተረፈ ካለ ለሚያስጨፍረው ልጅ እንዲጨመርለት ነበር የምናደርገው…አሁን ደግሞ ቡሄን እያከበርኩ ያለሁት ቤተሰብ መስርቼ የልጅ አባት ሆኜ ነው…ልጆቼ ስለ በዓሉ በደንብ እንዲያውቁ አድርጌ…ከባለቤቴ ጋር ደስ በሚል ሁኔታ ባህሉን ጠብቀን ነው ያከበርነው”

ስለ ቤተሰቡና ከባለቤቱ ጋር ስለተዋወቀበት አጋጣሚ…

“ከቀድሞ ፍቅረኛዬ ከአሁኗ ባለቤቴ ጋር ከተዋወቅን ከተገናኘን ወደ አምስት አመት አካባቢ ይሆነናል፤ ባለቤቴ የአምሮት አስረስ ትባላለች…ማራኪ ፍሬው የሚባል የ4 አመት ከስድስት ወር ወንድ ልጅና ከሁለት ወር በኋላ ሶስት አመት የምትደፍን ዳግማዊት ፍሬው የምትባል ሴት ልጅ አባትም አድርጋኛለች፤በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ፤ከባለቤቴና ከልጆቼ ጋር የማይደገሙ የሚመስሉ በጣም አስደሳች ጊዜያትን እያሳለፍን ነው፤ከባለቤቴ ጋር የተገናኘንበት አጋጣሚ ከመነሻው የቤተሰባዊ ቅርርብ ነበረን…በተለይ ወንድሟ አብሮ አደጌ ነው…አብረንም ኳስ እንጫወት ነበር፤ወንደሟ ዘነበወርቅ አካባቢ የባጃጅ ስራን ይሠራ ነበር፤እንደ አጋጣሚ ትንሽ ታመመ ለቤተሰቡ ሣይነግር እኔጋ መኖር ጀመረ፣በዚህን ጊዜ እናትዋ ሄደሽ ጠይቂው ስትላት እኔ ጋ መምጣት ጀመረች፤ወንድሟን ለማግኘት ስትመጣ እግረ መንገድ እኔጋ ማረፉን ቀጠለችበት…ይሄ አጋጣሚ ይበልጥ እያቀራረበን በፍቅር መታያየት…መፈላለግ ጀመርን…ግንኙነታችን በዚህ መልኩ ተጀምሮ ፍቅር ውስጥ ገባን…እያለ እያለ ሄዶ… አድጎ ለጋብቻና ሁለት ልጆችን አፍርተን በደስታ በአንድ ጣሪያ ስር ለመኖር በቃን”

የትዳር ህይወትና ተጨዋችነትን በተመለከተ…

“ለአኔ ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ በጣም ይበዛብኛል…ትዳር ለተጨዋችነቴ ትልቅ ጥቅም ሰጥቶኛል…ባለቤቴ እንድትንከባከበኝ…በፕሮግራም እንድመራ…ኃላፊነትም እንዲሰማኝ ቀለል የማይባል ጥቅምን ሰጥቶኛል…፤…አንድ የማልዋሸው ነገር ግን መጀመሪያ አካባቢ በጣም ተቸግሬ ነበር…ከባለቤቴ ከልጆቼ ጋር ተራርቆ መኖሩ ትንሽ ፈትኖኛል፤ከቤተሰቤ ርቄ ላለለመኖር ስል አዲስ አበባ ባሉ ትላልቅ ክለቦች ሣይቀር እየተፈለኩ ለቤተሰቤ ስል ብዙ ዋጋ ከፍያለሁ፤ወደ ሀዋሳ የመመለሴ ምስጢርም ከቤተሰቤ ላለመራቅ ነው…ከዚህ ውጪ ትዳሬ ለተጨዋችነቴ ትልቅ ጥቅም ሰጥቶኛል”

የትውልድ ቦታው ስለሆነው የአረብ ሰፈር…

“የአረብ ሰፈር በጣም የምወደው የተለየ ታሪክ ያለው ሰፈሬ ነው፤በርካታ ተጨዋቾችንም በማፍራት ይታወቃል፤ተጫውተን ቦርቀን ያደግነበት ሠፈሬ ነው…በተለይ አርብ አርብ የጁመዓ ቀን ስለሆነ የተለየ የትዝታ ስሜት አለኝ፤አርብ ቀን ሰፈሩ በጣም ይደምቃል… ይጨናነቃል…በብዛት አረቦችና ሙስሊሞች ስለሚበዙበት አረብ ሠፈር የሚል ስም ወጠቶለታል…ከዚህች ወርቃማ ሠፈር ወጥቼ ለዚህ በመድረሴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

እያደነቀው ስላደገው ተጨዋች…

“ብዙ ተጨዋቾች አሉ…ለሀዋሳ ከነማ ሲጫወቱ የነበሩትን…እነ ሙሉጌታ ምህረትን… በኃይሉ ደመቀን…እነ አዳነ ግርማን እያየሁ እያደነኩ ነው ያደኩት…እነሱ ናቸው…ለእኔ የእግር ኳስ ህይወት መነሳሳትን የፈጠሩልኝ፡፡”

በተለይ ተፅዕኖ አሳርፎአል አድንቀዋለሁ ስለሚለው ተጨዋች…

“ከበኃይሉ ደመቀ ውጪ ሌላ ተጨዋች ለመጥራት ይቸግረኛል…በኃይሉ ደመቀ ተፅዕኖ ከፈጠሩብኝ…እንደ ሮል ሞዴል አይቼ ካደኳቸው…ተጨዋች ቅድሚያውን ይወስዳል…”

ከአሰልጣኞች በጣም የሚያደንቀው…

“ውበቱ አባተ ለእኔ በጣም የተለየና በጣም የማደንቀው አሰልጣኝ ነው…”

ከማን ጋር ተጣምሮ ሲጫወት ጨዋታ ይቀለዋል…

“ከታፈሰ ሰለሞን ጋር አብሬ ስጫወት በጣም ይመቸኛል…በሀዋሳ ሁለት አመት አብረን ስንጫወት ያረጋገጥኩትም ይሄንም ነው”

በተቃራኒው የሚያስቸግረው አላንቀሳቅስ ስለሚለው ተጨዋች…

“በዚህ በኩል እንኳን አለ ብዬ የምጠራው ተጨዋች የለም፤ያስቸገረኝም የፈተነኝም ተጨዋች የለም፡፡ ምክንያቱም እኔ አንድ ቦታ አልቆምም፤ሜዳውን ከጫፍ ጫፍ ነው የማካልለው፡፡ ፍሬውን ያዙት ተብሎ ተጨዋች ተመድቦ ይገባል፤ግን እኔ ሙሉ 90 ደቂቃ ስለማልቆም ወዲያው ነው ከአጠገቤ የሚጠፉት፤ስለዚህ በዚህ በኩል አስቸገረኝ ብዬ የምጠራው ተጨዋች የለም”

አብሮት በአንድ ማልያ ሣይጫወት ጫማ በመስቀሉ የሚቆጭበት ተጨዋች

“ከሙሉጌታ ምህረት ጋር አብሬው በአንድ ማልያ ብጫወት በጣም ደስ ይለኝ ነበር ነገር ግን እኔ ወደ ሀዋሳ ስመጣ እሱ ከጨዋታ አለም ራሱን በማግለሉ ምኞቴ አልተሳካም”

የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ ግብ…

“መከላከያ እያለሁ በ2011 ዓ.ም ላለመውረድ እየተጫወትን ባለበት ጊዜ ከሲዳማ ቡና ጋር አዲስ አበባ ስታዲየም ስንጫወት 4ለ1 ስናሸንፍ የበረኛውን መውጣት አይቼ በቺፓ ያስቆጠርኳት ግብ የእኔ የምጊዜውም ምርጧ ግብ ናት”

ከማን ጋር ሲጫወት ጨዋታ ይቀለዋል…

“ምን እንደሆነ ምክንያቱን አላውቀውም…ግን ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ስንጫወት ጨወታው ይቀለኛል ፤የሚገርምህ ከጊዮርጊስ ጋር ስንጫወት ሁሌም የጨዋታው ኮከብ (Man of the match) እየሆንኩ ነው የምወጣው”

ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ቪዲዮውን ስልኩ ላይ አድርጎ አሁንም ድረስ ደጋግሞ ስለማየቱ…

“የጨዋታ ዘመንህ ምርጥ ጨዋታ የቱ ነው?ብለህ ብትጠይቀኝ አሁንም መልሴ ከቅ/ጊዮርጊስ አይወጣም፤ሀዋሳ እያለሁ ሀዋሳ ላይ ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ተጫውተን በሚያስገርም ጨወታ 4ለ1 ያሸፍንበት ጨዋታ የእኔ የጨዋታ ዘመኔ ምርጡ ጨዋታ ነው፤ የሚገርምህ የመጀመሪያውን ጎል ከማስቆጠሬ ውጪ ለሶስቱም ጎሎች መገኘት ወይም አመቻችቼ የሰጠሁት እኔ ነኝ፤በቀላሉ ጨዋታውም ቀኑም የእኔ ነበር ማለት ትችላለህ…የዚህን ጨዋታ ቪደዮ ስልኬ ላይ ጭኜው ዛሬም ድረስ ቪዲዮውን እየደጋገምኩ አየዋለሁ”

በእስከአሁኑ የእግር ኳስ ህይወቱ በጣም የተደሰትኩት አጋጣሚ…

“በጣም የተደሰትኩት ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር አንድ ልጅ በቀይ ወጥቶብን ያሸነፍንበትን የጥሎ ማለፉ ጨዋታ ነው…የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ደደቢት እንስቶታል…ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ መድረክ ለመሳተፍ ብቸኛ ተስፋው የጥሎ ማለፉን ዋንጫ ማንሣት ብቻ ነው…የሊጉን ቁጭትም ለመዘጋጀት ይሄ ዋንጫ ያስፈልጋቸው ስለነበር…ምን ያህል ተዘጋጅተው እንደሚመጡ እኛም ገመተን ስለነር…ጠንክረን ተጫውተን አንድ ልጅ በቀይ ወጥቶብን አሸንፈናቸው ዋንጫውን ያሸነፍንበት አጋጣሚ በጨዋታ ዘመኔ በጣም የተደሰትኩበት ነው፡፡”

በእስከአሁኑ የእግር ኳስ ህይወቱ በጣም የሚቆጭበት አጋጣሚ…

“ዋናውና ትልቁ የእግር ኳስ ህይወቴ አስቆጪው ጊዜ መከላከያ የወረደበት ጊዜ ነወ በእስከዛሬው የእግር ኳስ ህይወቴ በመጥፎ ታሪክነትም የሚነሣው ይሄንን አጋጣሚ ነው ምክንያቱም መከላከያ ትልቅ ታሪክ ያለው ክለብ ነው በስብሰብም በአሰልጣኝም በፋሲሊቲም በጣም የተሟላ ትልቅ ክለብ ነበር፤ በዚህ ደረጃ የተገነባው መከላከያ መውረድ ሣይሆን የዋንጫ ተሻሚ መሆን ሲገባው መውረድ የጨዋታ ዘመኔ መጥፎው ታሪክ ወይም አጋጣሚም ነው ማለቱ ነው የውስጤን የሚገልፀው፤ የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ሁለቴ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ያነሳ ትልቅ ታሪክ ያለው መከላከያ በእኔ የተጫዋችነት ዘመን ሲወርድ ማየት በጣም ያማል፡፡

በእግር ኳስ ህይወቴ ሳላሳካው የሚለው…

“የሀገሪቱ ትልቂ ዋንጫ የሆነውን የኢት.ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ከፍ አድርጎ ማንሣት የመጀመሪያው ትልቁ ህልሜ ወይም ግቤ፤አሁን ከተቀላቀልኩት ወልቂጤ ጋርም ይሁን ከማንኛውም ክለብ ጋር ላሳካው የምመኘው ነው”

ትልቅ አቅም ያለው ተጨዋች ሆኖ…ለብ/ቡድን እየተጠራ ስለመመለሱ…

“በተጫዋችነቴ በጣም ከሚያሙኘ ነገሮች አንዱ የሀገሬን ብ/ቡድን በቋሚነት አለማገልገሌ ነው፤አቅም ባይኖረኝም ለብ/ቡድኑ ብቁ ባልሆን እሺ እቀበላለሁ፤በጣም እንደሚያመኝም እንደሚያበሳጨኝ የሚያደርገው ሀገሬን በብቃት ማገልገል የምችልበት መቶ ፐርሰንት አቅሙ እያለኝ እድሉን ማጣቴ ነው፡፡ የሚገርምህ ከ31 አመት በኋላ ዋንጫ ከበላው የሰውነት ቢሻው ቡድን ጀምሮ እስከ አሁን ለብ/ቡድን ለይስሙላ እጠራለሁ ግን ደግሞ ይመልሱኛል…፤…ትንሽም ቢሆን እድል የተሰጠኝ በዮሀንስ ሣህሌ ጊዜ ወጣ ገባ ስል የነበረው…፤…አሰልጣኞቹ እኮ አቅሙ እንዳለኝ ያምናሉ፣ግን ደፍረው አያቆዩኝም፡፡ መጨረሻ ላይ የተረዳሁትና ራሴን ያሳመንኩት ምንድነው እምነት በእኔ ላይ እንደማያሳድሩ ነው፤ከፈረጠሙ የአፍሪካ ተጨዋች ጋር መሀል ላይ ገብቶ እንዴት ነው የሚታገላቸው ብለው ለመቀነስ ይሮጣሉ…በጣም የሚገርምህ በክለብ ደረጃ ስጫወት በጣም እገዝፋባቸዋለሁ፤ወደ ብ/ቡድን መጥቼ አጠገባቸው ስቆም አንስባቸዋለሁ መሰለኝ፡፡ ብቃቴ ከፍ ባለበት ሰዓት ሀገሬን ባለማገልገሌ በጣም እቆጫለሁ፤ እነሱ እየጠሩ ቢመልሱኝም አሁንም አስረግጬ በድፍረት የምናገረው ለብ/ቡድን መጫወት የሚያስችል መቶ ፐርሰንት አቅሙ አለኝ…ግን ምን ታደርገዋለህ ከችሎታ ይልቅ አካል ብቃት ላይ ትኩረት የሚያደርጉ አሰልጣኞች ሀገሬን በቁሚነት እንዳላገለግል ህልሜን እውን እንዳላደርግ እንቅፋት ሆነውብኛል፡፡”

 

ተክለ ሰውነቱ ደቃቃ መሆኑ ሠላባ አድርጎት ይሆን? ስለመባሉ…

“በተክለ ሰውነት ደረጃ እምነት የሚታጣብኝ በብ/ቡድን ደረጃ ነው፤እውነትም እንዳልከው በብ/ቡድን ደረጃ ጎድቶኛል ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል…በክለብ ደረጃ ግን የመጀመሪያ ተመራጭና ተጠቃሚው ተጨዋች አድርጎኛል”

የፍጥነትና የቅልጥፍናው ምስጢርስ ምን ይሆን?ስለመባሉ…

“ምስጢር ወይም ምክንያት ብዬ የማስበው…በዋናነት ከወደ ደቡብ የምንመጣ ተጨዋቾች አመጋገባችንና ሀዋሳ አካባቢ የፍቅር ኃይቅ ስላለ በኃይቁ ላይ እያዋኘን ማደጋችን ይመስለኛል፤ት/ቤት እየተማርን ከት/ቤት ስንወጣና ቅዳሜና እሁድ ሩጫችን ወደ ኳስ ነው…ኳስን በፍቅር እየተጫወትን ነው ያደግነው፤ ከጨዋታ በኋላ በአብዛኛው የምንመገበው ዓሳና የዓሳ ሾርባ የመሰሰሉት መሆናቸው ቤተሰቦቻችንም ወተትና አይብ እየተመገብን ማሳደጋቸው ያገዘን ይመስለኛል፤ሙሉ ሜዳ አካልዬ እንድጫወት ትንፋሽ እንዲኖረኝ በማድረጉ በኩል ዋና በየቀኑ እየዋኘሁ ማሳለፌ እንዲሁም የአንዱራንስ ሥራ ላይ ሠራተኛ መሆኔ ጠቅሞኛል ብዬ አስባለሁ”

ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመግባት ተቃርቦ ነበር ስለመባሉ…

“አዎን ትክክል ነው በጣም ተቃርቤ ነበር ብቻ ሣይሆን ለመፈረምም ጫፍ ላይ ደርሼ ነበር፤ድርድርም አድርገን ተስማምተን ነበር፤በተለይ አዳማ ላይ በነበረው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ወቅት በግልፅ አውርተን እኔም በጣም ደስተኛ ሆኜ ነበር፡፡ ግን በወቅቱ አቶ አብነት ገ/መስቀል በሀገር ቤት ስላልነበሩና እሳቸው እስኪመጡ ጠብቅ መባሌ ትንሽ አዘገየው…የቤተሰቤ ጉዳይም ትንሽ ስለረበሸኝና ዋጋ መክፈል ስነበረብኝ ፈረሰ እንጂ ተስማምተን ነበር፤ቤተሰቤ በተለይ ባለቤቴ ልጆች ይዤ እንዴት ተራርቀን እንኖራለን…ብላ በፍፁም ከሀዋሳ ውጪ እንዳልፈርም ጫና በመፍጠርዋ ከጊዮርጊስ ጋር የነበረው ድርድር ፍፃሜው እንዳያምር አድርጎታል፤ይሄን ክፍተትና አጋጣሚ የተከታተሉት የሀዋሳ አሰልጣኝ ውበቱ አባተና ሙሉጌታ ምህረት ለሀዋሳ እንድፈርም ባለቤቴን ማሳመንና መግፋት ጀመሩ…እኔም በመጨረሻ ለቅዱስ ጊዮርጊስ መጫወት ክብር ቢሆንም ቤተሰቦቼ ከሚጎዱ…ብዙ ነገሮችን ቢያሳጣኝም ሣልወድ በግድ ለሀዋሳ ለመፈረም ተገደድኩ እንጂ ጊዮርጊስ ለመግባት ተቃርቤ ነበር፡፡”

 

አያቱ የመጫወቻ ጫማውን በእሳት ስለማቃጠላቸው…

“እንደ አጋጣሚ ሆኖ ያደኩት በአያቴ እጅ ነው፤አያቴ ትምህርት እንድማርና ቤተክር ስቲያን እንድከታተል እንዳገለግል እንጂ ኳስ እንድተጫወት አትፈልግም ነበር፤እኔ ግን ትምህርት ቤት… ቤተክርስቲያን እሄዳለሁ እያልኩ እየተደበኩ ኳስ ስጫወት ነበር የምውለው…አቧራ በአቧራ ሆኜ መምጣቴን ተመልክታ ጥርጣሬ ውስጥ የገባችው አያቴ ትከታተለኝ ነበርና አንድ ቀን ነቃችብኝና በኋላ ላይ ፕሮጀክት ስሰራበት የነበረውን ጫማዬን እሳት ውስጥ ከታ አቃጥላብኛለች…ይሄንን አጋጣሚ መቼም አልረሣውም”

ሀዋሳን ለቆ ወደ ወልቂጤ ስላመራበት…

“የቤተሰቤ ጉዳይ ሁሌም ስለሚያሳስበኝ ሀዋሳ ላይ ቤዝ ላደረገ ክለብ የመጫወት ፍላጎት ነው በውስጤ የነበረው…ወይ ሀዋሳ አሊያ ሲዳማ ቡና፣ በዚህ ዙሪያ ከአሰልጣኞቹ ጋር ስናወራ የሲዳማው ዘርአይ ሙሉ ቆይ ነባሮቹን ላስፈርም…የሀዋሳው ሙሉጌታ ብዙ አውርተን ቆይ በጀት ላስፈቅድ እያለ አቆየኝ በመሀል ደግሞ ከአዲስ አበባና ከተለያዩ የክልል ክለቦች መቐለ 70 አንደርታን ጨምሮ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ግን እንዳልኩህ ለቤተሰቤ ዋጋ መክፈል ስላለብኝ ብዙ መራቅ አልፈልኩም…በመሀል ወልቄጤ ስመጣ ወሰንኩ…ወልቂጤ መፈረሜ ዜናው ሲወጣ እኛ ጋር ትፈርማለህ ብለን እየጠበቅንህ ብለው ተንጫጩ በተለይ ሙሉጌታ ሲያወራኝ ወልቂጤ እኮ ይሄን ያህል ሊሰጡኝ ተስማማን ስለው ውይ እኛ እንኳን ይሄን ያህል መክፈል አንችልም አለኝ፣ግን የተወሰነ ማሻሻያ አድርግና ወደ እኛ ጋር ና ያሉኝ ነበሩ፤ ለገንዘብ ብዬ ይሄን ለማድረግ ህልዬ አልፈቀደልኝም…ወልቂጤ አምኖ ተቀብሎኛል…እነሱን በገንዘብ መለወጥና መሸጥ አልፈለኩም፤ለበጎ ነው ብዬ ወስኛለሁ”

ከወልቂጤ ጋር ለማሳካት ስለሚያስበው…

“ከወልቂጤ ጋር አሪፉ ጊዜ የማሳልፍ ይመስለኛል…ለሊጉ እንግዳ ሆነው ጥሩ ተፎካካሪና…ጥሩ ኳስ የሚጫወት ቡድን ነበር ይዘው የቀረቡት፤ቡድኑን አሁንም እንዳለ ይዘውታል…ከአንድ ግብ ጠባቂ በስተቀር የለቀቀ የለም…ይሄም መልካም ጎኑ ነው…ከዚህ በመነሣት ከቡድኑ ጓደኞቼ ጋር በመሆን በሊጉ ጥሩ ተፎካካሪ ከመሆን ባለፈ ወደ ዋንጫ የሚጠጋ ቡድን ይኖረናል ብዬ አስባለሁ”

“አሻራቸውን ስላሳረፉበት ሰዎች…

“በመጀመሪያ የፈጠረኝን አምላኬን እና ድንግል ማርያምን ከምንም ነገር በላይ ማስቀደም እፈልጋለሁ፤ ካለነሱ እዚህ መድረስ አልችልም ነበርና አመሰግናለሁ፤በእግር ኳስ ህይወቴ አሻራችንን ያሳረፉት መዘርዘር ከባድ ነው አሰልጣኝ ገ/መድህን፣ውበቱ አባተ፣ስዩም፣ሞውሪንሆ እያልኩ ብዘረዝር ብዙ ናቸው…በደፈናው በእግር ኳስ ህይወቴ አሻራቸውን ያሳረፉትን በሙሉ…በፕሮጀክት ታመነ፣ካሳሁን ሎሪንጎን…ሚሊዮን አካሎን…በተለይ በተለይ ትልቅ ውለታ የዋሉልኝን ነፍሳቸውን ይማረውና አቶ አዳነን በጣም አመሰግናለሁ…የባለቤቴ ውለታም ትልቅ ስለሆን እሷንም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.