ከ 1.2 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች፣ከ14 በላይ ታላላቅ ሙዚየሞችን በውስጧ ሽሽጋ ያያዘችው፣ከሀገሪቱ አራተኛ ትልቋ ከተማ በሆነችው ኦቷዋ ያለው ድባብ ከወትሮው የተለየ ነው።ክረምቱን ሸኝቶ በእግሩ የተተካው የፀደይ ወራት ከልምላሜው ጋር ተዳምሮ ኦቷዋ ከተማን ይበልጥ እንድትደምቅ በውበት ላይ ውበት ጨምራ እንድታበራ አድርጓታል።
ሁሌም የፈረንጆቹ የሜይ ወር በገባ የመጨረሻው ሳምንት ቅዳሜና እሁድ የሚካሄደው የ10ኪ.ሜትርና የኦቷዎ ማራቶን ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት ሆኗት ይበልጥ አፍክቷታል።
በዚህም ኦቷዋ የመንግስቷ መቀመጫ፣የፖለቲካ ዋና ከተማ ብቻ ሣትሆን የሩጫ ዋና ከተማ መሆኗንም እንድታስመሰክር አድርጓታል። ትናንት ማምሻውን (ቅዳሜ) በተካሄደው 44ኛው የኦቷዋ የ10ኪ.ሜ ውድድር ላይ የታየው ክስተትም ይሄንኑ የሚያረጋግጠው በእርግጥም ኦቷዋ የመንግስት መቀመጫ የፖለቲካ ዋና ከተማ ብቻ ሳትሆን የሩጫ ዋና ከተማ ሰለመሆና የመሰከረ ነው፤44ኛው የኦቷዋ ማራቶን ከመጀመሩ በፈት በሚካሄደው የ10ከ.ሜ ውድድር ኢትዮጵያዊው በአምላኸ በልሁ በውድድሩ ላይ ኬንያዊውና ሞሮኮአዊው የአምና አሸናፊ ከዃላ አሰከትሎ አንደኛ በመውጣት ለራሱም ለሀገሩም ድል አስመዝግቧል።
27 ደቂቃ ከ48 ሰከንድ አንድአምላክ የ2018 የኦቷዋ የ10ኪ.ሜ ውድድር አሸናፊ መሆኑንና የ10,000 ዶላር ተሸላሚ መሆኑን ያወጀበት ሰዓት ሲሆን ለአሸናፊነት ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ኬንያዊው ቤናርድ ኪሚሊ በ28:22 ሁለተኛ ሞሮኮአዊው መሀመድ ረዳ በ28;23 ሶስተኛ በመሆን አጠናቀዋል።

በለንደኑ የዓለም ሻምፒዬና አገር የመወከል ዕድል አግኝቶ የ10ሺ ሜትሩን በ27:08:94 በሆነ ሰዓት በ10ኛ ደረጃ በማጠናቀቅ ለነገ የርቀቱ አልጋ ወራሽነቱ ፍንጭ የሰጠው አንድአምላክ “ሀይሌና ቀነኒሳ ሲሮጡ ወደ ከተማ መጥቼ ሲሮጡ ማየቴ ወደ ሩጫው እንድገባና ለውጤታማነት እንድነሳሳ ጉልበት ሆኖኛል” ሲል ሀትሪክ ድረገጽ እና ሀትሪክ ጋዜጣን ጨምሮ በኦቷዋ ለተገኙት ከመላው ዓለም ለመጡ የሚዲያ ሠዎች ተናግሯል።
በ2017 የደልሂ ማራቶንና በቅርቡ ተካሄዶ የነበረውን የኢትዮጵያ ሻምፒዮና በሁለተኝነት ያጠናቀቀው አንድአምላክ በልሁ ለመጀመርያ ጊዜ በተሳተፈበትና በኦቷዋ ማራቶን ታሪክ ስሙን ከአሸናፊዎች ተርታ ባሸነፈበት ምሽት ሁሌም በየዓመቱ ውድድሩን በአካል ተገኝቶ እንዲዘግብ ከኢትዮጵያ በብቸኝነት የተጋበዘው የሀትሪክ ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ባገኘው ድል በደስታ ባህር የሰመጠውን አንድአምላክ በልሁን ከድካም ስሜት ሳይላቀቅ ከዚህ በታች ባለው መልኩ አነጋግሮታል።
-የወርቅ ደረጃ ያለውን የኦቷዋ የ10ኪ.ሜ ውድድር ማሸነፉ ስለፈጠረበት ስሜት…
“በመጀመሪያ ለዚህ በመብቃቴ ፈጣሪን አመሰግናለሁ ፤በዚህ ደረጃ ያለን ውድድር ማሸነፍ ብዙ ትርጉም አለው።የ10ኪ.ሜትሩን የIAAF ዕውቅናና ትልቅ ደረጃ ያለውን ውድድር በማሸነፍ የራሴንም የአገሬንም ስም በማስጠራቴ በጣም ደስተኛ ነኝ”

-ውድድሩ ሲጀመር በፍጥነት ሰለመውጣታቸው በውስጥህ ስጋት አልፈጠረም…
“ሰጋት ከመፍጠር ይልቅ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ምክንያቱም እስከመጨረሻው በዚህ ፍጥነት እንደማይሄዱና ጥያቸው እንደምሄድ ውስጤ በጣም እርግጠኛ ነበር፤መውጣታቸው ከስጋት ይልቅ ለማሸነፌ የእርግጠኝነት ስሜት እንዲሰማኝ አድርጓል።”
-መጨረሻ ላይ ብቻቸውን መሮጡን በተመለከተ…
“ብቻዬን መሮጤ ትንሽ ከባድ ነበር ፤ አብሮ የሚፎካከር ቢኖር ይበልጥ ተጠቃሚ እሆን ነበር።ብቻዬን ከምሮጥ የሚፎካከር ሰው ቢኖር ከዚህ የተሻለ ሠዓት እንዳስመዘግብ ይረዳኝ ነበር። ”
-ሀይሌ ገ/ስላሴና ቀነኒሳ በቀለ ሰለፈጠሩበት ተፅእኖ…
“ሁለቱ ታላላቅ በእኔ የአትሌቲክስ ህይወት ትልቅ ተፅእኖ የፈጠሩ አትሌቶች ናቸው ፤ከገጠር ወደ ከተማ መጥቼ የእነሱን አሯሯጥና ውጤታማነት በቪዲዮና በቴሌቭዥን እያየሁ ነው ያደኩት ያ ደግሞ ለዛሬው ማንነቴ በጣም ጠቅሞኛል።”
-በለንደኑ ዓለም ሻምፕዮና 10ኛ ሰለመውጣቱ…
“ውጤቱ ለአንድ በዕድሜው ትንሽና ጀማሪ አትሌት በጣም ትልቅ ነው ፤በውድድሩ ትምህርትም ልምድም አግኝቼበታለሁ በቀጣይ አንደኛ ለመውጣት ጠንክሬ እሰራለሁ።”

-ቀጣይ ዕቅዱን በተመለከተ…
ሩጫን ገና መጀመሬ ነው፤ለአገሬ ብዙ መስራት እፈልጋለሁ ፤በተለይ በአለም ሻምፒዮናና በኦሎምፒክ ታሪክ መስራትን አስባለሁ ከእግዚአብሄር ጋር። ”
-ድል የተቀዳጀባት ኦቷዋን በተመለከተ…
“ኦቷዋ ምርጥ ከተማ ብቻ ሳትሆን ለመሮጥም የምትመች ከተማ ናት፤በዚህች ምርጥ ከተማ የመጀመሪያ ተሳትፎዬ ድል በማስመዝገቤ ሁሌም የስኬቴ አንዷ አካል አድርጌ አንድቆጥራት ያደርገኛል። ”
-በኦቷዋ ያገኘውን ድል መታሰቢያነት ለማን በሚል ለቀረበለት ጥያቄ…
“ከእኔ ጋር አብረው ለለፉ ቤተሰቦቼ ለወንድም እህቶቼ አብረውኝ ሲጨነቁ ሲያግዙኝ ለነበሩ ጓደኞቼ በሙሉ ድሉ ለእነሱ መታሰቢያ ይሁንልኝ።”በማለት የ2018 የኦቷዋ የ10ኪ.ሜ አሸናፊ በተለይ ለሀትሪክ ተናግሯል።

![]()

አስተያየት ይስጡ