የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት ጨዋታ በነገው ዕለትም ቀጥሎ ሲደረግ አመሻሽ 12:00 ጀምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚያገናኘው ጨዋታ ይጠበቃል።
በተለይም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ከታዳጊነቱ ጀምሮ ከ30 ዓመታት በላይ እጅግ ስኬታማ ጊዜያትን ያሳለፈው ፤ በ2014 እና በ2015 ቅዱስ ጊዮርጊስን በዋና አሰልጣኝነት እየመራ ሻምፒዮን የሆነው አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀድሞ ክለቡን መግጠሙ ጨዋታውን ተጠባቂ አድርጎታል።
በተጨማሪም ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሚመራው አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር በተጫዋችነትም ሆነ በአሰልጣኝነት በፈረሰኞቹ ቤት ታላላቅ ስኬቶችን በጋራ አስመዝግቧል።
አሰልጣኝ ዘሪሁን ከጨዋታው ጋር በተያያዘ ከሀትሪክ ስፖርት ድህረ ገፅ ጋር አጠር ያለ ቆይታን አድርጓል።
- ማሰታውቂያ -

የውድድር ዓመቱ ጅማሮ መልካም ነው የሚለው አሰልጣኝ ዘሪሁን በርከት ያሉ ወጣት ተጫዋቾች መያዙን በመጥቀስ የእስካሁኑ ጉዞ መጥፎ የሚባል አይደለም ጥሩ ነው ሲል ገልፆታል።
ከፕሪሚየር ሊጉ በጣት የሚቆጠሩ ተጫዋቾችን ብቻ ናቸው ያስፈረምኩት አብዛኞቹ ከከፍተኛ ሊግ የመጡ ናቸው ፤ ቢሆንም ግን እጅግ ጥሩ አቅም እና ተስፋ ያላቸውም ናቸው ብሏል።
“አቅም አላቸው ፤ መስራት የሚችሉ እና ወደ ፊት ትልቅ ተስፋ ያላቸው ናቸው። እነሱን ማቀናጀት እና ወደ ጥሩ ነገር ለመሄድ ጊዜ ይፈልጋል። አሁንም በዚህ ሂደት ላይ ነው የምንገኘው።ተዋህደው ከዚህ በላይ የማድረግ አቅም አላቸው።”
አሰልጣኝ ዘሪሁን በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከታዳጊ ቡድን ጀምሮ ሌላ ማልያን ሳይለብስ ለቢጫ እና ቀዩ ማልያ ታምኖ በተጫዋችነቱ በርካታ ዋንጫዎችን አሸንፏል።
ጫማውን ከሰቀለ በኋላም የፈረሰኛው እና የዘሪሁን ሸንገታ ቁርኝት በምክትል እና ዋና አሰልጣኝነት ታላላቅ ስኬቶቹን አስቀጥሎ ተጉዟል።
ሜዳ ላይ በሚያሳየው ብቃት የክለቡ ደጋፊዎች ደግመው ደጋግመው አዚመውለታል። በተጫዋችነት ያስፈነደቃቸውን የክለቡን ደጋፊዎች በምክትል አሰልጣኝነትም ዳግም ደስታቸውን ሲያስቀጥል በዋና አሰልጣኝነት ደግሞ ለአራት አመታት ከዋንጫ ርቆ የቆየውን ክለብ ባለ ድል አድርጓል። በተከታታይ ለሁለት ዓመታት ፤ ካደረጋቸው 60 ጨዋታዎች በሶስቱ ብቻ ተሸንፎ።
በአወዛጋቢ ሁኔታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ከተለያየ በኋላ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀድሞ ክለቡን በነገዋ ዕለት በተቃራኒ ሆኖ ይገጥማል።
አሰልጣኝ ዘሪሁን ስለዚህ ቀዳሚ ጨዋታ ሲናገርም ያሳደገኝን ክለብ መግጠም ከባድ ነው ሲል ተናግሯል።
“ከባድ ነው ፤ ካደክበት ብዙ ዓመት ካሰለጠንክበት እና ከተጫወትክበት ክለብ ጋር መጫወት ከባድ ነው ለኔ። ግን እንደማንኛውም ጨዋታ ያው እግር ኳስ ነው እንደ አሰልጣኝነቴ ከማንኛውም ቡድን ጋር እንደምጫወተው ጥሩ ዝግጅት እያደረኩ ነው ያለሁት።”
“ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ትልቁ ክለብ ነው። ይሄን ማንም የማይክደው ነው።ከእርሱ ጋር ነው የምጫወተው አዎ ፤ ትልቅ ቡድን ነው ጠንካራ ጨዋታ ይገጥመኛል።”
አሰልጣኝ ዘሪሁን ነገ የሚገጥመው 89ኛ ዓመቱን የደፈነውን የልጅነት ክለቡን ቅዱስ ጊዮርጊስን ብቻ ሳይሆን አብሮት በተጫዋችነት እና በአሰልጣኝነት ስኬትን ካጣጣመው አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር ነው።
“ይሄ ከባድ ጨዋታ ይሄ ቀላል ጨዋታ ነው የሚባል ነገር የለም ሁሉም ጨዋታ ትኩረት እና ትኩረት የሚፈልግ ነው። ወንድሜ ነው(አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ)ከወንድሜ ጋር ነው የምጫወተው በወንድምነት ሁለታችንም አብረን ያሳደገን እና ያደግንበት ክለብ ውስጥ ነው ያደግነው። ስንወለድ አንድ አካባቢ ያደግን ነን በወንድምነት። ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ አንድ ላይ ነው የተማርነው እና ስራችን እና ስራችን ላይ አተኩረን እሱም እኔም ጥሩ ነገር እንሰራለን ብዬ አስባለሁ።”
ከላይ እንደተጠቀሰው የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ቁርኝት እጅግ የተለየ ነው። እርሱ ሰለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች አንስቶ አይጠግብም። እነርሱም ለብዙ የደስታ ቀኖቻቸው ምክንያት ለሆነው ውድ ልጃቸው መውደዳቸውን ለመግለፅ ቃላት ለመምረጥ ይቸገራሉ።
እንግዲህ ነገም ያሳደገኝ ነው ከሚለው ክለብ ፣ ወንድሜ ከሚለው አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር ብቻ ሳይሆን ከነዚህ ደጋፊዎች ጋርም ነው በተቃራኒ ሆኖ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም የሚሰየመው።
ስለ እርሱ እና ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ትስስር አሰልጣኝ ዘሪሁን ሲያነሳ በነገው ጨዋታ ከባዱ እና ትልቁ ነገር ደጋፊዎች ናቸው ይላል።
“ለነሱ ትልቅ ክብር ነው ያለኝ መቼም የማልረሳው የማልጥለው ትልቅ ክብር አለኝ ለነሱ። በቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ደጋፊዎቼ ፤ 12ኛ ተጫዋቾቼ ነበሩ። ለቅዱስ ጊዮርጊስ የሚደክሙትን የሚለፉትን ነገር ስለማውቅ ከምንም በላይ እነሱን ነው ቀና ብዬ ማየት የማልችለው ለምን ? በጣም በጣም በጣም ትልቅ ነገር አድርገውልኛል። ውጤት እንዳመጣ አግዘውኛል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በሄደበት ሁላ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚደግፉ ተስፋ ሳይቆርጡ ለጥሩ ውጤት ያበቁ ትልቅ ደረጃ እንዲደርስ ትልቁን ሚና የተወጡ ናቸው። ከምነግርህ በላይ ትልቅ ክብር አለኝ ለነሱ።”
ከዚህ መልሱ በመቀጠል ያነሳንለት ጥያቄ ስለወቅቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሁኔታ ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከወትሮው ቡድኑ ቀዝቀዝ ብሎ ስለመቅረቡ ብዙዎች ይስማማሉ።
አሁን ላይ በውስጡ ስለሌለው ይህ ነው የምለው ነገር የለም የሚለው አሰልጣኝ ዘሪሁን ግን ዳግም ወደ ቀደመ ብቃቱ እንደሚመለስ ዕምነቱ መሆኑን ጠቁሞ አልፏል።
“ማንኛውም ቡድን ጠንክሮ መስራት እና የተሻለ ደረጃ መድረስ ይችላል። ጊዮርጊስ ደግሞ ትልቅ ቡድን ነው። ከየትኛውም ቡድን በላይ ትልቅ ቡድን ነው እና ወደ ጥሩ ነገር ይመለሳል ብዬ አስባለሁ ግን እዛ ውስጥ ስለሌለው ይሄ ይሄ ነው ብዬ መናገር ይከብደኛል።”
በዋና አሰልጣኝነት የሁለት ጊዜ ሻምፒዮን የሆነው አሰልጣኝ ዘሪሁን በውድድር ዓመቱ የሊጉን የሁለት ጊዜ ሻምፒዮን እየመራ ባደረጋቸው 10 የሊግ ጨዋታዎች በሶስት አሸንፎ ፣ በስድስት አቻ ሲለያይ በአንድ ብቻ ተሸንፏል።
በሊጉም ባለፉት ዘጠኝ ተከታታይ ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት ባለማስተናገድ ከሊጉ መሪ መቻል ጋር ተመሳሳይ ቁጥር ይዟል።
እግር ኳስ ሂደት ነው የሚለው አሰልጣኙ በዚህ ላይ የአብዛኞቹ ተጫዋቾቹ በፕሪሚየር ሊጉ ልምድ አልባ ስለመሆናቸው በማንሳት ካሉት ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ጋር በማጣመር የተሻለውን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለማሳየት ነው የምፈልገው ይላል።
አሰልጣኝ ዘሪሁን በቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሰልጣኝነት ኃላፊነት ላይ ሳለ በሰጠው አንድ ቃለ ምልልሱ ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ውጪ ከሌላ ክለብ ጋር ዋንጫ የማሳካት አቅሙ እንዳለው ተናግሮ ነበር።በኢትዮ ኤሌክትሪክ ክለብም ትልቁ ዓላማው ክለቡን ወደ ቀደመ ክብሩ መመለስ ስለመሆኑ ጠቅሷል።
“በዚህ ሰዓት ላይ ላይ ይሄ ይሄ ነው አልልህም ለምን ? አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው ፤ ቡድኑ እንደ እቅድ ሀ ብዬ የተቀበልኩት ነው እና ወጣቶች ናቸው ብዙዎቹ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች አይደለም ያሉኝ። ነገር ግን ይህን ስል የተሻለ ነገር የመስራት አቅም ያላቸው ተጫዋቾች አሉ። በሒደት ቡድኑን ከፍ ማድረግ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚታወቅበትን ወደ ጥሩ ቦታው ላይ ለመመለስ ነው ትልቁ ዓላማዬ።”
በቀድሞው ስሙ መብራት ኃይል በአሁኑ መጠሪያው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፕሪሚየር ሊጉ በአዲስ ቅርፅ ከ1990 ጀምር ሲደረግ ቀዳሚውን ዋንጫ የወሰደ ክለብ ነው።በ1993ም ሁለተኛውን ደግሟል።
ቀስ በቀስ ከነበረው የታላቅነት መድረክ ተንሸራቶ ከሊጉ እስከ መሰናበት ደርሶ ዳግም በዘንድሮው የውድድር ዘመን ቤተኛ እንግዳ ሆኖ ወደ ለመደው ሊግ ተመልሷል።
ክለቡ ከስም ለውጡ በኋላ ዳግም የቀደመ ስሙን ለመመለስ ስኬታማ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።
ይህ ይሳካ ዘንድም የአመራሩ ድጋፍ እንዳልተለየው አሰልጣኝ ዘሪሁን ገልጿል። “ይህ ክለብ ትልቅ ነው ከነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥሎ ታሪካዊ ክለብ ነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ። እነሱ ሲሰጡኝም ሆነ ስንወያይ የተሻለ ነገር ለመስራት ጥሩ ነገር ለማድረግ ነው እየሰራን ያለነው። ቀስ በቀስ የተሻለ ቡድን እንደምንሰራ ያውቁታል እነሱም ፤ ብዙ ድጋፍ እያደረጉልኝ ነው እና ጥሩ ነገር ለማድረግ እነሱንም አመሰግናቸዋለሁ።”
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሁን እየተካሄደ ባለበት ቅርፅ በተመረጡ ከተሞች መደረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ አዳማ ከተማ ተጉዞ አሸንፎ አያውቅም። ዘጠኝ ጨዋታዎች አድርጎ በሶስቱ አቻ ሲለያይ በስድስቱ ተሸንፏል።
የአሁኑ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን እየመራ ከመዲናዋ በ85 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ከተማ ካደረጋቸው 29 ጨዋታዎች በ18 አሸንፏል። ይህም ቀዳሚው አሰልጣኝ ያደርገዋል።
አሰልጣኝ ዘሪሁን ከዚህ ጋር በተያያዘም የኔ ትኩረት በአዳማ በሚኖረን ቆይታ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ስራዬን መስራት እና መስራት ብቻ ነው ብሏል።
በቡድን ዜና አኳያ ተከላካዩ አብዱላሂ አሊ በጉዳት ምክንያት ከጨዋታዉ ውጪ የሆነ ብቸኛው የቡድኑ ተጫዋቾች መሆኑን የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ገልጿል።
የ12ኛ ሳምንት መርሐግብሩን ዛሬ ማድረግ የጀመረው ፕሪሚየር ሊጉ ነገ ከአመሻሽ 12:00 ጀምሮ በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስን በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ከሚመራው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገናኛል።
ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም ተገናኝተው በሊጉ በ40 ጨዋታዎች ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ28 ሲያሸንፍ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ በ3 አሸንፎ ፤ በቀሪ 9 ነጥብ ተጋርተዋል።


